ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአዲሱ አመት መንግስታቸው በትኩረት ከሚያከናውናቸው ተግባራት ውስጥ የሥራ እድል ፈጠራ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል። የሥራ እድል ፈጠራው ዘላቂ እና አስተማማኝ እንዲሆን የግሉ ዘርፍ ያለውን አቅም አሟጠን እንጠቀማለን ብለዋል። ይህን እቅድ ስኬታማ ለማድረግ ባለሀብቶች እና ምሁራን እቅዱን ቢደግፉትም በዘርፉ የተደቀኑ ችግሮች ላይ ትኩረት አድርገው ይከራከራሉ።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ዳዊት ሀዬሶ እንደሚያስረዱት የግል ባለሀብቱ ሰፊ የሥራ እድል እንዲፈጥር ሲታሰብ መጀመሪያ ተቋማዊ ለውጦችን ማድረግና ሁኔታዎችን ማመቻቸት ግድ ይላል። ባለ ሀብቱ መዋዕለ ነዋዩን ለማፍሰስ አስተማማኝና ደህንነቱ የተረጋገጠ አካባቢና የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲኖር ይፈልጋል ብለዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ከባንክ የብድር አገልግሎት ማግኘትና ተመጣጣኝ ትርፍ ሊያገኝ የሚያስችለው የገበያ ሥርዓት እንዲኖረው ያልማል። የሀገሪቱ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ መሆን ለባለሀብቱ መተማመንን ይፈጥርለታል ሲሉ ይጠቅሳሉ። በቂ ክህሎት ያለው የሰው ሃይል መኖርና የመሰረተ ልማት መሟላትም እንዲሁ ባለሀብቱ ኢንቨስት ከማድረጉ በፊት ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ያስረዳሉ።
እንደ ዶክተር ዳዊት የግሉ ዘርፍ መረጃን የማግኘት ዕድል ሊመቻችለት ይገባል። የት ቦታ ኢንቨስት ማድረግ እንዳለበት፣ በየትኛው የሥራ ዓይነት ቢሰማራ ውጤታማ እንደሚሆን በቂ ዕውቀት አግኝቶ ወደ ሥራ ቢገባ እንደታቀደውም ባይሆን በተወሰነ መልኩ የተሻለ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል ይገልጻሉ።
በዓመት ሦስት ሚሊዮን ዜጎችን ወደ ሥራ ለማስገባት የተያዘው ዕቅድ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ስትራቴጂው ግን እምብዛም የሚያስኬድ አለመሆኑን የሚናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ክቡር ገና ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ይህን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ከግል ባለሀብቱ ይልቅ ከፍተኛ ተዋናይ መሆን የሚገባው መንግስት ነው ይላሉ። መንግስት ወጣቶችን ወደ ሥራ በማስገባት የሚከፍላቸው ገንዘብ በገበያ ውስጥ አገልግሎት ላይ ሲውል ኢኮኖሚውን ማንቀሳቀስና ማሳደግ የሚያስችል አቅም እንደሚፈጠር ይገልጻሉ።
ዛሬ ባለው ሁኔታ አብዛኛዎቹ የግል ኢንቨስትመንቶች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሰው ሃይል የሚቀንስ አሠራርን ለመከተል የሚፈልጉ ከመሆናቸው አንጻር መንግስት የግል ባለሀብቶችን ተጠቅሞ በዓመት ሦስት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እፈጥራለሁ ማለቱ ፈተና የበዛበት ነው ብለዋል። ምናልባት ከግል ባለሀብቱ ይልቅ ይህንን ያህል የስራ እድል ለመፍጠር አቅም የሚኖረው መንግስት እራሱ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ዶክተር ዳዊት በበኩላቸው መንግስትም ኢንቨስትመንቱ ይሸከመዋል ብሎ ባሰበው የሰው ሃይል ልክ የካፒታል አቅርቦት መኖሩን ማረጋገጥ ይኖርበታል ፤ ይህ ካፒታል የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ምንዛሬን የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። መንግስት ወደ ሥራ ለማስገባት ያስቀመጠውን የሥራ ዕድል ብዛት ስኬታማ የሚያደርገው የተጠቀሱትን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት ሲችል እንደሆነ ያሰምሩበታል።
መንግስት ትኩረት የሰጣቸው የሥራ ዘርፎችም አዋጭነታቸው በደንብ መጠናት እንዳለበት ዶክተር ዳዊት ይመክራሉ። እንደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የግብርናውን ዘርፍ ከአግሮ ኢንዱስትሪ ጋር ማስተሳሰር ጥቅም ሊኖረው የሚችለው ብዙ ካፒታል የማይጠይቅና አዋጭም በመሆኑ ነው ይላሉ።
የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ከምንም በላይ ሰላምና ደህንነትን የሚፈልግ በመሆኑ ከዚህ አንጻር መንግስት ትልቅ ሥራ ይጠበቅበታል ይላሉ። የቱሪዝም ዘርፍ በቂ ሆቴሎችና የተለያዩ ሀገሮችን የምግብ ሥርዓትም ወደ ሀገር ውስጥ ማምጣትን የሚጠይቅ ነው። ዘርፉ ከተሠራበት ከፍተኛ ገቢ ሊያመጣ የሚችልና ለብዙ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።
አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራ ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም እንዳለው ያስረዳል። አሁን ያለው የሀገሪቱ ሁኔታ ግን ይህን ለማድረግ የሚያስችል እንዳልሆነ በመጥቀስ መንግስት ከሁሉ አስቀድሞ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባሩ ሊሆንእንደሚገባ መክሯል ።
ይህ ባልሆነበት ግን ሶስት ሚሊዮን ሳይሆን ሶስት መቶ ሰዎችን የሥራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ እንደማይቻልም ተናግሯል። መንግስት ለሰላም ዋስትና በመስጠት የሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የውጭ ባለሀብቶችንም በመሳብ ከሚታሰበው በላይ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ይችላል ይላል ሻለቃ አትሌት ኃይሌ።
በሆቴል ቱሪዝም ልማት ኢንቨስት ያደረገው አትሌቱ እንደሚያስረዳው ለቱሪዝም ኢንቨስትመንቱ ከምንም በላይ ጸጥታና ሰላም ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ይናገራል። ቱሪስቱ የሚሄድበት አካባቢ ሰላሙ አስተማማኝ ካልሆነ መንቀሳቀስ አይፈልግም። ሰላም ሲኖር በኢንቨስትመንት ላይ የዋለው ኢኮኖሚ ተገቢውን ፍሰት ጠብቆ ይሄዳል። ሰዎች በሚፈለጉት ሥራ ላይ ተሰማርተው መኖር ይችላሉ። ቱሪስቶች በድንኳን ተቀምጠው ለሚበሉትና ለሚጠጡት ብቻ እንኳን ጥቂት ዶላር ቢከፍሉም ጥቅም አለው ። ስለዚህ ባለንበት ወቅት ቁጥር አንድ ተግዳሮት የሆነው የጸጥታና ሰላም ጉዳይ ነው።
ዶክተር ክቡር ገና እንደሚሉት ደግሞ ሰላምና ጸጥታ ይቅደም ወይስ ሥራ ይቅደም የሚሉትን አለያይቶ መመልከት አያስፈልግም ፤ ሁለቱም በአንድ ላይ አብረው የሚሄዱ ናቸው እንጂ ሰላም ከተረጋገጠ በኋላ የሥራ ዕድል ይፈጠር መባሉን አይስማሙበትም። በዚህ ሀገር ሰላም የጠፋው ወጣቱ የሥራ ዕድል ባለማግኘቱም እንደሆነ መታሰብ አለበት ይላሉ።
በሌላ በኩል አይ ሲ ቲ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ቢባልም ከቴክኖሎጂ ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ትልቅ ካፒታል የሚፈልግና ሥራ የመፍጠር አቅሙም እንደ ግብርናው ዘርፍ ላይሆን ስለሚችል ይህ ዘርፍ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ዶክተር ዳዊት ያስረዳሉ።
በማዕድን ፍለጋ ላይ ለመሰማራት ትልቅ ካፒታል ያስፈልጋል። የሥራ እድል የመፍጠር አቅሙም በወጣው ካፒታል ልክ ላይሆን ይችላል። ስለዚህ እንደ ግብርና እና ቱሪዝም ዘርፍ ሰፊ የሥራ ዕድልን የመፍጠር አቅሙ ውስን ነው። የማዕድኑ ዘርፍ ብዙ ወጪ በማይጠይቁና በርካታ የሰው ሃይል መሸከም በሚችሉ ቀለል ባሉ የሥራ አይነቶች ላይ ቢያተኩር ውጤታማ መሆን እንሚቻልም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቅ ሥራ ለመፍጠር በሚታሰብ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ኢኮኖሚው ውስጥ ገብቶ ግለት በመፍጠር የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነትንም እንዳያስከትል መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በአንድ በኩል የሥራ ዕድል ሲፈጠር በሌላ በኩል ደግሞ የኑሮ ውድነቱ እንዳይከፋ አመጣጥኖ መሄድ እንደሚያስፈልግ ዶክተር ዳዊት ይመክራሉ።
እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለፃ መንግስት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ ለሶስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያሰበውን እውን ማድረግ የሚቻለው በዘርፉ ላይ የተጋረጡትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣትና ማስተካከያ እርምጃ ሲወስድ ነው። መንግስት ትኩረት ያደረገባቸው የሥራ ዘርፎች የተጠቀሰውን አሀዝ መሸከም የሚችሉና ውጤታማነታቸውም መፈተሽ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 9/2011
ኢያሱ መሰለ