በኢኮኖሚ ዕድገታቸው እምርታ ካሳዩ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ኢትዮጵያ በተከታታይ አስራ አምስት ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ ካገዟት ዘርፎች ውስጥ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው የግብርና ምርቶችና የማዕድን ውጤቶችና ሌሎቹም ተጠቃሽ ናቸው።
ይሁንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው ኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ ንግድ ሀገራችን የተያያዘችውን እድገት እየተፈታተነ የመጣ ትልቅ አደጋ ሆኗል። ይህ ጥዩፍ ተግባር መንግሥት ከወጪና ገቢ ንግድ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም በእጅጉ ያሳጣና የንግድ ውድድርንም እየጎዳ ያለ ነው። ኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ ንግድ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በሚደረገው ጥረትም አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር እና ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል የምታደርገውን እንቅስቃሴ እየተፈታተነ ያለም ጭምር ነው።
በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል የተባለውን ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት ለመዋጋት መንግሥት አንድ ሀገራዊ የንቅናቄ ማዕከል በማድረግ ይፋ አድርጓል። በመሆኑም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮችንና ባለድርሻ አካላትን ያቀፈ አንድ አብይ ኮሚቴ በማቋቋም ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ለማድረግ ቁርጥ አቋም ይዞ ወደ ሥራ ገብቷል።
ኮሚቴው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የበላይ ሰብሳቢነት የሚመራ ሲሆን እስከታችኛው የቀበሌ መዋቅር ድረስ ትንፋሹ ሳይቆራረጥ በመስራት ይዞ የተነሳውን ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድን የማስቆም ተልዕኮ ከዳር ለማድረስ የሚሰራ ነው። ይህ ንቅናቄ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩትን እንቅፋቶች ሁሉ ለማስወገድ እያንዳንዱ ዜጋ ከአመራሩ ጎን በመቆም የድርሻውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ዕድል የፈጠረም ነው።
ኢንቨስትመንት ከገቢና ወጪ ንግድ ጋር ተመጋጋቢ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ይህን አጀንዳ የ2012 ዓ.ም የንቅናቄ ማዕከል በማድረግ የኢኮኖሚ አቅምን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የዕለቱ ፕሮግራምም የጸረ ኮንትሮባንድ ዘመቻና ሕገ ወጥ ንግድን የመከላከልና ሥርዓት የማስከበር ንቅናቄ የመጀመሪያው የትውውቅና የስምሪት መርሀ ግብር እንደሆነ ገ ልጸዋል።
ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም የአረንጓዴ ልማት አሻራ ለማስቀመጥ ከዳር እስከ ዳር የተካሄደው ሀገራዊ ንቅናቄ ስንተባበር እና ስንደማመጥ ምን ዓይነት ተዓምር መስራት እንደምንችል በእጅጉ ያመላከተ መሆኑን የገለጹት አቶ ደመቀ ተከታታይ ሆነው የመጡት የንቅናቄ አጀንዳዎችም ልክ እንደችግኝ ተከላው ከዳር እስከ ዳር በመነቃነቅ ልንረባረብባቸው እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ ለኢኮኖሚ ዕድገት ካንሰር መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕዝቡ ከዳር እስከ ዳር አንድ ሆኖ ሊጠየፈውና ሊቆጣጠረው እንደሚገባ አሳስበዋል። ኢኮኖሚውን በእጅጉ የሚጎዳና የውጭ ግንኙነትን የሚያሽመደምድ እኩይ ተግባር እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢኮኖሚያችን በተወዳዳሪነትና በነፃ ገበያ ቢደገፍ የት ሊያደርሰን እንደሚችል መገመት አያዳግትም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጨለማ ገበያው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እየጎዳ እንዳለ መታወቅ ይኖርበታል ብለዋል።
የሀገራችንን ምርቶች በኮንትሮባንድ የሚያገኙ ሀገሮች በዓለም ገበያ ከእኛው ጋር ተሰልፈው የላቀ ተወዳዳሪ ሆነው ሲገኙ ማየት የሚያስቆጭና የሚያሳፍር እንደሆነ በማስረዳትም በሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘኖች የኮንትሮባንድ መነሻና መድረሻዎችን በመለየት በዘመቻ ማሽመድመድ፣ ኔት ወርኩን መበጣጠስና መንገዶቹን መዝጋት እንደሚያስፈልግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ አሁን እየታየ ላለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች እንደ አንድ ምክንያት መሆኑን በመግለጽም ሕገ ወጦችን ሥርዓት በማስያዝ ሀገሪቱ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ማስወገድ ይገባል ብለዋል። ሀገራዊ ንቅናቄው ከፌዴራል ጀምሮ እስከታችኛው የቀበሌ መዋቅር ድረስ እርስ በእርስ እየተናበበ በመስራት የሕግ የበላይነትን በማስጠበቅ የሕዝቡንም ሆነ የሀገሪቱን ተጠቃሚነት የማረጋጋጥ ሀገራዊ አደራውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል። ኅብረተሰቡ ኢኮኖሚውን የመታደግ፣ ለውጡን ወደፊት የማራመድ፣ የሕዝብ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ፣ ያላግባብ የመበልጸግ አጀንዳን የመግራትና የሕግ የበላይነትን የማስፈን ኃላፊነት ወስዶ በአንድ ላይ መታገል እንደሚገባውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
መሪዎች የመምራት ኃላፊነታቸውን ተጠቅመው ኅብረተሰቡን በማነቃነቅ ዘመቻውን ውጤታማ በማድረግ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አደጋ የደቀነውን የኮንትባንድና ሕገወጥ ንግድ ለመቆጣጠር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚገባቸውና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ በበኩላቸው እንዳስረዱት በ2011 ዓ.ም ኮንትሮባንድን ለመከላከል እና ሕገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር እንዲሁም ለሕጋዊ ንግድ አመቺ ሁኔታ ለማመቻቸት ብዙ እንደተሠራና ውጤትም እንደተገኘበት በመግለጽ ያም ሆኖ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት እንዳልተቻለ ተናግረዋል። ለዚህም ዋናው ምክንያት በየደረጃው ያሉ አመራርና ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ እኩል ትኩረት በመስጠት ተቀናጅቶና ተናቦ የመስራት ክፍተት ስላለባቸው እንደነበር ገልጸዋል።
ኮንትሮባንዲስቶችና ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው ስልታቸውን እየቀያየሩ ለገቢ አሰባሰቡም ሆነ ለሕጋዊ ንግድ ሥርዓቱ እንቅፋት መሆናቸውንም ተናግረዋል። ከዚያም አልፎ ማህበራዊ መስተጋብርን በማናጋት በሀገሪቱ ሰላምና እድገት ላይ ተጽዕኖ መፍጠራቸውን አስታውሰዋል። ጉዳዩን ሀገራዊ አጀንዳ አድርጎ በጋራ ለመሥራት ብሔራዊ ግብረ ኃይል መቋቋሙ ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚረዳም አስረድተዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ ንግድ በሀገራችን እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖ ሲያስረዱ ከለውጡ ጉዞ በፊት በሕግ የተፈቀደ በሚመስል ደረጃ ኮንትሮባንድ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ስር ሰዶ እንደነበር አስታውሰዋል። በሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ኮንትሮባንድ የራሱ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደነበረውም ገልጸዋል። ይህንንም ችግር ለመቋቋም የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽንና የፌዴራል የጸጥታ አካላት ባደረጉት ጥረት ከፍተኛ አደጋዎችን ለመከላከል ቢቻልም ኮንትሮባንድ አሁንም አደጋነቱ አንደቀጠለ ያለና የሀገሪቱ ቁልፍ ችግር እንደሆነ ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ የጥናት ውጤቶችን ባቀረቡበት ወቅት ሲያስረዱም ኮንትሮባንድ ኔት ወርክ ያለውና በሕጋዊ አሠራሮች ሽፋን፣ በአቅርቦት እጥረት ሽፋን በግልጽና በስውር ዘዴዎች ጭምር በመታገዝ የሚፈጸም በመሆኑ ቁጥጥሩን አስቸጋሪ እንዳደረገው አስረድተዋል። ኢንቨስትመንትና የሀገር ውስጥ የንግድ ሥርዓትን ያዛባ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚትን ያሳጣና የኅብረተሰቡን ጤና ያወከ ትልቅ አደጋ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል።
እንደ አዲስ አበባ ኤርፖርት፣ ሀዋሳ፣ ሚሌ፣ ሞያሌ የመሳሰሉት የጉምሩክ ቅርንጫፎችም ከፍተኛ የገቢ ኮንትሮባንድ የተያዘባቸው መሆናቸውንና ከተያዙት ዕቃዎችም አዳዲስ አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ምግብና መጠጥ፣ ትንባሆን የመሳሰሉት ከፍ ያለውን ብዛት እንደያዙና አደንዛዥ ዕጽም ባልተለመደ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ቡና፣ ጫት፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች፣ የቁም ከብቶች፣ የማዕድን ውጤቶች ወዘተ ከሀገር ውስጥ ወደ ውጭ በስውር የሚወጡ እንደሆኑም ተጠቅሷል። በዚህም ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ከፍተኛ ገቢ እንዳጣች ተመላክቷል።
መንግሥት በ2011 ዓ.ም ከወጪ ንግድ ለማስገባት ያቀደው 4.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን የተገኘው ገቢ ግን 2.6 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑንና በተለይ ከ2007 ዓ.ም ወዲህ የመንግሥት የወጪ ንግድ ገቢ እያሽቆለቆለ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።
ኮሚሽነሩ የችግሮቹን መንስኤ ሲያስረዱም ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ እንዳይከሰት ተቋማት ይፈጽሙት ዘንድ በሕግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ አለመወጣት፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና አመራር በአስተሳሰብ፣ በአሠራር፣ በዕቅድ በተግባርና በውጤት ተቀናጅተው በከፍተኛ ቁርጠኝነት አለመመራት፣ መላውን ሕዝብና ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መንገድ በንቅናቄ አለመመራት፣ የተዋናዮቹን ማንነትና የግንኙነት ሰንሰለት በማጥናት የተደራጀና ተከታታይ ጠንካራ እርምጃ አለመውሰድ፣ በሕጋዊ ወጪና ገቢ ዕቃ ሽፋን እና በኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ሽፋን የሚፈጸም የንግድ ማጭበርበርን አጥንቶ ማስወገድ አለመቻል፣ ስር የሰደዱ የህቡዕ ኢኮኖሚ ተዋናዮች ላይ እርምጃ አለመወሰድ በዝርዝር የተብራሩ ችግሮች ናቸው።
በውይይቱ በርካታ ሃሳቦች የተሰነዘሩ ሲሆን በተለይም ለተጠቀሱት ችግሮች መፍትሄ ይሆናሉ የተባሉ ጉዳዮችን በመያዝ ሀገራዊ ንቅናቄውን በተቀናጀ መንገድ በመምራት ኢኮኖሚያችንን እየተፈታተነ ያለውን አደጋ ለማስወገድ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተመክሯል።
በዕለቱ ሀገራዊ ንቅናቄውን ለመምራት የተሰየመው ኮሚቴ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ምንጭ እና የጀርባ አጥንት የሆነውን የገቢና ወጪ ንግድ ለመታደግ ኅብረተሰቡን በማነቃነቅ ችግሮችን የማስወገድ ኃላፊነትና ስምሪት ተሰጥቷቸዋል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 9/2011
ኢያሱ መሰለ