በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት የመገናኛ ብዙኃንን ቁጥር ለማሳደግና የተሻለ አሰራር ለመፍጠር የተለያዩ አዋጆች ወጥተዋል፡፡
በተለይ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ እና የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ይጠቀሳሉ፡፡ የአዋጆቹ አተገባበር ግን በተዛባ መንገድ በጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ በመደገፍ ለፖለቲካ ጥቅም በመዋላቸው መገናኛ ብዙኃንን እንዳዳከሙ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰለሞን ጎሹ እንደሚሉት፤ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ የኢትዮጵያ ህግ የተቀበላቸው ገደቦች፣ የመገናኛ ብዙኃን ህጎች የተበታተኑ መሆን፣ ቅድመ ምርመራ፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለቤትነት፣ የመገናኛ ብዙኃን ወንጀሎች፣ ቅጣት፣ የተቆጣጣሪ ተቋማት ወይም የዘርፉ አስተዳዳሪ አካላት አወቃቀር ስልጣንና ተግባር፣ ራስን በራስ የመቆጣጠር ስርዓት እና ፍትሀዊ የማስታወቂያ ክፍፍል ላይ ችግሮች ነበሩባቸው፡፡
እንደ አቶ ሰለሞን አባባል፤ ለመገናኛ ብዙኃን መድከም የጋዜጣና የመፅሄት አሳታሚዎች በተመሳሳይ ስያሜ የሚታተሙ የጋዜጣና የመፅሄት ባለቤት እንዳይሆኑ መከልከላቸው፣ በተግባር የመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ መገናኛ ብዙኃን ገዥውን ፓርቲ ብቻ የማገልገል አዝማሚያ ማሳየታቸው፣ የጥላቻ ንግግር በአግባቡ ባለመተርጎሙ ገደቡ በውል አለመታወቁ፣ መገናኛ ብዙኃን የራስ ቁጥጥር ደካማ መሆን እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በ2008 ዓ.ም የተቋቋመ ቢሆንም እስካሁን ህጋዊ ሰውነት አለማግኘቱ ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው፡፡
የህግ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር መሰንበት አሰፋ እንደሚናገሩት፤ ህገ መንግሥቱ ማንኛውም የህትመት ስራ ይሁን በሌላ መንገድ የሚወጣ ሀሳብ መንግሥት ቅድመ ምርመራ እንደማያደርግበትና ምንም አይነት ክልከላ እንደማይኖረው ያስቀም ጣል፡፡ በመርህ ደረጃ ይዘትን መሰረት ያደረገ ክልከላ እንደማያስፈልግና ይዘትን መሰረት ያላደረገ ክልከላዎች መሆን እንዳለባቸውም ያመለክታል፡፡
በተግባር ግን የሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ለመገደብ አመፅ ማነሳሳት፤ ስም ማጥፋት፣ ዘርና ሀይማኖትን ተመርኩዞ የሚደረግ የጥላቻ ንግግር እና ሌሎች ጥፋቶች ከከፍተኛ ቅጣት ጋር በተለያዩ አዋጆች ውስጥ ተካተዋል፡፡
የወንጀለኛ ህግ አንቀፅ 244 ላይ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም የአገርን መልካም ስምና የተቋማት መልካም ስም ማጥፋት የሚል አንቀፅ እንዳለ የጠቆሙት ዶክተር መሰንበት፤ ማንኛውም ሰው የመንግሥትን ስም ያጠፋ፣ ያዋረደና የሰደበ በሦስት ወር እስራት እንደሚቀጣ መደንገጉን ይናገራሉ፡፡
የወንጀለኛ ህግ አንቀፅ 244 ግልፅነት የጎደለው፣ ትርጉም የሌለውና የሚያሻማ በመሆኑ መሰረታዊ ህግን እንደሚፃረር በመጥቀስም፤ መቼና እንዴት የአገር ስም ሲጠፋ ቅጣት እንደሚጣል አለመቀመጡን ያስረዳሉ፡፡
እንደ ዶክተር መሰንበት ገለፃ፤ አመፅ ማነሳሳት የሚለው ደግሞ ግልፅነት የጎደለው የጥፋት አይነት ነው፡፡ በወንጀል ህጉና በፀረ ሽብር አዋጁም ላይ ይህ የጥፋት አይነት ተቀምጧል፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ከተጋፉት ውስጥ አንደኛው አመፅ ማነሳሳት የሚለው የጥፋት አይነት ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጋዜጠኞች ላይ የተፈፀሙት የፖለቲካ አፈናዎች ይህንን ሽፋን በማድረግ የተፈፀሙ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
በፀረ ሽብር አዋጅ ውስጥ ሽብር ማነሳሳት የሚለው የጥፋት አይነት ሀሳብን በነፃነት ለመግለፅ አስቸጋሪና ውስብስብ ከሚያደርጉት ጉዳዮች ዋነኛው መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር መሰንበት፤ ሽብር ማነሳሳት የሚለው የጥፋት አይነት በባህሪው ንግግርን ብቻ መሰረት በማድረግ ወንጀለኛ የሚያደርግ ሲሆን ግለሰቡ በተግባር ወንጀል ሳይሰራ ተጠያቂ የሚደረግበት ስርዓት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በአዋጁ ላይ ሽብር በማነሳሳት የተያዘ ሰው ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ቅጣቱ እስከ 20 ዓመት እንዲሆን መደረጉ አዋጁ ለፖለቲካ ፍጆታ መዋሉን አንዱ አመላካች መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ የፀረ ሽብር አዋጅ ውስጥ አንድ የወንጀል ድርጊት በተግባር ሳይፈፀም ንግግር ብቻ በማየት ወንጀለኛ ማለት እንደሚቻል ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ንግግር አመፅ አነሳሳ የሚባለው መቼና እንዴት ነው የሚለው በግልፅ አልተቀመጠም፡፡ በዚህም ሀሳብ በነፃነት የመግለፅ መብት ከለላ እንዳይኖረው መደረጉን ያብራራሉ፡፡
ዶክተር መሰንበት እንደሚሉት፤ የሀሰት ወሬ ማሰራጨት በሚለው የጥፋት አይነት ብዙ ጋዜጠኞች ተከሰዋል፡፡ የሀሰት ወሬ ተሰራጨ የሚባለው እንዴት ነው? ግለሰቡም መጠየቅ ያለበት ባሰራጨው ወሬ ብቻ መሆኑን እና የሀሰት ወሬ አመፅን ለማነሳሳት ያለው ሀይል ምን ሲሆን ነው ወንጀል ሊሆን የሚችለው? የሚለው ጉዳይ በወንጀል ህጉ ላይ በዝርዝር አልተቀመጠም፡፡
ስም ማጥፋት አሁንም በአገሪቱ ወንጀለኛ ህግ ላይ የተቀመጠ ሲሆን በቅርቡ ዚምባቡዌ ስም ማጥፋትን ከወንጀለኛ ተጠያቂነት ውጭ በማድረግ በካሳ ጥያቄ ውስጥ እንዲካተት ማድረጋቸውን ዶክተር መሰንበት ይጠቅሳሉ፡፡ አንድ መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ጥረት አድርጎ የተሳሳተ መረጃ ቢያወጣ በህግ ላይጠየቅ እንደሚችል በመጥቀስ፤ የስም ማጥፋት በፍትሐብሄር ያለው ህግ ከዓለም አቀፍ ህግ ያነሰና ስም ማጥፋት መቼና እንዴት ነው ተፈጸመ? የሚለው በዝርዝር አለመቀመጡን ይናገራሉ፡፡
ከ1983 ዓ.ም በኋላ በመቶ የሚቆጠሩ መገናኛ ብዙኃን ወደ ሥራ ቢገቡም አብዛኛዎቹ በመንግሥት ጫናና በአቅም ማነስ ምክንያት ተዘግተዋል፣ ጋዜጠኞችም ታስረዋል፣ ተሰደዋል፣ ተሰቃይተዋል፡፡ የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ህግጋት በተለይ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000፣ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ 533/1999 እና የኮምፒውተር አዋጅ 958/2008 ዓለም አቀፍ ትችት በማስተናገድ በአገሪቱ ገፅታ ላይ ጥቁር ጥላ ካጠሉ ህግጋት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት በአሁን ወቅት የሚገኙ መገናኛ ብዙሀን አቅማቸው ደካማ ሲሆን በበቂ ጥናት ላይ የተመሰረተ የምርመራ ጋዜጠኝነት ፕሮግራም አለማቅረባቸው እንዲሁም እራሳቸውን ሳንሱር ወደ ማድረግ ማዘንበላቸው የነዚህ አዋጆች ውጤት ተደርጎ ይወ ሰዳል፡፡
እንደ አቶ ሰለሞን አባባል፤ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የሚያከብር ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰ ብን ለመፍጠር የሚያስችል የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ያስፈልጋሉ፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ በአገር ልማትና እድገት ውስጥ ያላቸውን ሚና ለማጎልበት የሚያስችል የህግ ማሻሻያ ካልተደረገ አሁን ያሉት ህግጋትና ተግባራት ቁጥጥርን መሰረት ያደረጉና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን አደጋ ላይ የጣሉ በመሆናቸው የመገናኛ ብዙኃኑን እድገት ይገቱታል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2011
በመርድ ክፍሉ