ኢትዮጵያ ወራሪውን የጣሊያን ጦር ድል አድርጋ ነጻነቷን እንድታስጠብቅና ጥቁር አፍሪካውያን ነጮችን በማሸነፍ አዲስ ታሪክ እንዲጽፉ ያደረጉት አንጸባራቂ ከዋክብቶቿ ዳግማዊ አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ የተወለዱት በተመሳሳይ ቀን በዚህ ሳምንት ነሐሴ 12 ነው።
ዳግማዊ አጼ ምኒልክ
አጼ ምኒልክ የንጉስ ሳህለ ሥላሴ ልጅ ከሆኑት አባታቸው ልዑል ሃይለ መለኮትና ከእናታቸው ከወይዘሮ እጅግአየሁ ለማ አዲያሞ አንጎለላ ልዩ ስሙ እንቁላል ኮሶ በተባለ ከደብረ ብርሃን ደቡብ ምዕራብ አምስት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም. ተወለዱ። ትልቁ የግብር አዳራሽ ሲመረቅ የአጼ ምኒልክ አዝማሪ ተከታዩን ተቃኝታ ነበር።
የመድኃኒት ጥቂት ይበቃል እያለች
የምኒልክ እናት አንድ ወልዳ መከነች
አዝማሪዋ እንዲህ ብላ መግጠሟ አጼ ምኒልክ ለእናታቸው አንድ መሆናቸውን፤ ያለተቀናቃኝ በቀላሉ ያባታቸውን ዙፋን መውረስ መቻላቸውም ለአባታቸው አንድ ሳይሆኑ እንደማይቀር ፍንጭ ይሰጣሉ።
ህዳር 1 ቀን 1848 ዓ.ም. የኃይለመለኮት ቀብር ከተፈጸመ በኋላ ምኒልክ የአባታቸውን አልጋ በይፋ ተረክበዋል። ይህ ሲሆን ዕድሜያቸው12 ነበር። መኳንንቱ ተማክረው አቶ ናደውን ሞግዚት አደረጉላቸው። ወዲውም አጼ ቴዎድሮስ ለ 150 ዓመታት ያህል የቆየውን የሸዋ መሳፍንት ራስን የማስተዳደር ታሪክ ለመቋጨት ወደ ሸዋ መጡ። አሸንፈው ሲመለሱም ምኒልክንና እናታቸውን ወይዘሮ እጅጋየሁን ጨምሮ ጥቂት ምርኮኞችን ይዘው ሄዱ።
ምኒልክ በአጼ ቴዎድሮስ ቤተመንግስት በነበራቸው ቆይታ ከንጉሱ ጋር የነበራቸው ግንኙነት የአባትና የልጅ ነበር። ልጃቸውን አልጣሽን ድረውላቸው የደጃዝማችነት ማዕረግም ሰጥተዋቸው ነበር። ሹመቱ የክብር እንጂ ግዛት ተሰጥቷቸው እንዲያስተዳድሩ የማድረግ ኃላፊነትን አይጨምርም።
ሰርገው ሐብሊ የተባሉ ጸሐፊ “ዳግማዊ ምኒልክ የአዲሱ ስልጣኔ መስራች” በተሰኘ መጽሐፋቸው ምኒልክ በመቅደላ ስለነበራቸው ቆይታ ተከታዩን ብለዋል።
“ምኒልክ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከቴዎድሮስ አጠገብ ማሳለፋቸው በሁለት መንገድ ጠቅሟቸዋል። በአንድ በኩል ለቴዎድሮስ ታማኝና የመክዳት ስሜት የሌላቸው መምሰል ችለዋል። በሌላ በኩል አጼ ቴዎድሮስ በኋላ በብስጭት መንፈሳቸው እስኪለወጥ ድረስ ቅን ፈራጅ ስለነበሩ ፍርድን በተመለከተ ምኒልክ ሰፊ እውቀት ቀስመዋል። ምናልባት ስለዚህ ይሆናል አባ ዳኘው የሚለውን የፈረስ ስም ያገኙት”
ደብተራ (በኋላ ሊቀ ጠበብት) ወልደማሪያም ባዘጋጁት የአጼ ቴዎድሮስ የህይወት ታሪክ የምኒልክን የመቅደላ ቆይታ ሲገልጹ “ንጉስ ምኒልክን የማይወድ አልነበረምና በመቅደላም ሲኖር በእንቁጣጣሽ፣ በመስቀል በፈረስ ጉግስ ጨዋታ ንጉስ ምኒልክን የሚመስል አይታይም ነበር።” ብለዋል።
የአጼ ቴዎድሮስ ባህሪ እየተለወጠ ሲመጣ ምኒልክ መራቅን ስለመረጡ ከሚያምኗቸው ሰዎቻቸው ጋር በመሆን ዕቅድ ማውጣት እንደጀመሩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ደጃዝማች ግርማሜ ወልደሐዋሪያት የተባሉ የአጼቴዎድሮስን ዘመድ አግብተው የንጉሱን አመኔታ ያገኙ ሰው ናቸው የምኒልክን ማምለጫ መረብ የዘረጉት። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደስላሴ የሕይወት ታሪካቸውን በያዘ መጽሐፋቸው ደጃዝማች ግርማሜ ከሸዋ ወደ ጎንደር፣ ከጎንደር ወደ ሸዋ እየተመላለሱ አጼ ምኒልክን ያገለግሉ ነበር ብለዋል።
ደጃዝማች ግርማሜ የአቡነ ተክለሀይማኖትን ክብረ በዓል አስታከው ትልቅ ድግስ አስደገሱ። ከዚያም ጠባቂዎቹን ሁሉ ጋብዘው በመጠጥ ኃይል ሲወድቁ ምኒልክንና እናታቸውን ወይዘሮ እጅጋየሁን ይዘው አመለጡ።
ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ “አጼ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት” በሚል መጽሐፋቸው
አጼ ቴዎድሮስ የምኒልክን ማምለጥ ሲሰሙ ምን እንዳሉ ሲገልጹ “የምኒልክን ማምለጥ አጼ ቴዎድሮስ እንደሰሙ ለምን አልጣሽን ጥሏት ሄደ አሉ ይባላል። ይኸውም ማለት ከምኒልክ ማምለጥ የልጃቸው አብሮ አለማምለጥ የቆጫቸው ይመስላል። ምናልባት ምኒልክ ወደፊት እንደሚነግስ ታይቷቸው ልጃቸው ከምኒልክ ጋር አብረው እንዲነግሱ በመመኘትም ይሆናል” ይላሉ።
ነሐሴ 24 በ1857 ዓ.ም. ምኒልክ ንጉሰ ሸዋ ተብለው በአባታቸው በንጉስ ኃይለመለኮት መንበር ነገሱ። ንጉስ ምኒልክ ሸዋን እያስተዳደሩ ከግራኝ መሀመድ በኋላ የኢትዮጵያ ግዛት ሳይሆኑ ለረዥም ጊዜ የቆዩ ክፍሎችን ከተከፋፈለው መሳፍንታዊ ስርዓት ፈንቅለው በመጠቅለል ለዮሐንስ አራተኛ እየገበሩ የሸዋ ንጉስ ሆነው ኖሩ።
አፄ ዮሐንስ መተማ ላይ በደርቡሽ ከተሰው በኋላ ጥቅምት 25 ቀን 1882 ዓ.ም. በእንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ምንልክ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ ተብለው ነገሱ። አጼ ምኒልክ ለሀያ አራት አመት ሸዋን ሲያስተዳድሩም ሆነ ከዚያ በኋላ መላው ኢትዮጵያን ሲገዙ የኢትዮጵያን ግዛት አስፋፍተዋል፤ ስልጣኔን ወደ አገራቸው እንዲገባ በማድረግ በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል።ይህን ጥረታቸውን በመመልከት ይመስላል ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እምዬ ምኒልክን “ዘመናዊት ኢትዮጵያን የፈጠረ ሰው” ይላቸዋል።
አጼ ምንሊክ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ካደረጓቸው አዳዲስ የአሰራር ስርዓቶችና ቴክኖሎጂዎች መካከል ትምህርት፣ ባቡር፣ ስልክ፣ ፖስታ፣ ኤሌክትሪክ፣ አውቶሞቢል፣ የቧንቧ ውሃ፣ ዘመናዊ ህክምና፣ ሆስፒታል፣ መድሃኒት ቤት፣ ባንክ፣ ገንዘብ፣ ማተሚያ ማሽን፣ ጋዜጣ፣ ሆቴል፣ የፅህፈት መኪና፣ ሲኒማ፣ ወፍጮ፣ ጫማ፣ ብስክሌት፣ የሚኒስትሮች ሹመት እና ባህር ዛፍ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።
አፄ ምንሊክ ውጫሌ ላይ ባደረጉት ውል የተነሳ ከጣልያን ጋር አለመግባባት ውስጥ ገቡ። ይህ ችግራቸው ወደ ጦርነት ስላመራ ከዘመናዊውና ስልጡኑ ጣልያን ጋር ጦርነት ገጠመው አድዋ ላይ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ድል አደረጉ። ከአድዋ ድል በኋላ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ዝና በአለም ናኝቷል። አጼ ምንሊክ ጣሊያንን ድል ቢያደርጉም ወራሪ ጠላት ቢሆኑም እንኳን በሞታቸው አለመደሰታቸውን “…በጥጋባቸው አድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ። እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረኳቸው ብዬ ደስ አይለኝም…” ሲሉ ገልጸዋል።
አጼ ምኒልክ በመታመማቸው ምክንያት እንደቀድሞው ለማስተዳደር ስለተቸገሩ ወራሻቸው ማን እንደሆነና አገሪቱ ወደፊት ችግር እንዳይገጥማት መደረግ ያለበትን ነገር የሚገልጽ ኑዛዜያቸውን በደብዳቤ አጽፈው ህዝቡና መኳንንቱ ጃንሜዳ ከተሰበሰቡ በኋላ ግንቦት 10 ቀን 1901 ዓ.ም. ተነበበ። በኋላም አፄ ምኒልክ በታላላቅ ስራዎችና በፍርድ ላይ በመግባት ይከታተሉ ነበር።
በመጨረሻም ታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም በ69 አመታቸው በእለተ አርብ ሞቱ። እንደሞቱ የግቢው ሰራተኞች የለቅሶ ድምጽ ሲያሰሙ የልጅ እያሱ ባለሟሎች አገር እንዳይሸበር በቶሎ ዝም አሰኟቸው። ከዚህም በኋላ አፄ ምኒልክ በህይወት አሉ እየተባለና እየተወራ እስከ ሰገሌ ዘመቻ ድረስ ሁለት አመት ከአስር ወር ተደበቁ። የመንግስቱም ስራ በስማቸው ይካሔድ ነበር። በሚስጥርም ቢሆን ህዝቡ እና መኳንንቱ
አርባ ስድስት አመት የገዛኸው ንጉስ
እንዳለህም ስጠኝ ከሌለህም ላልቅስ።
እያሉ በተለያየ መንገድ ሃዘናቸውን ይገልፁ ነበር።
እቴጌ ጣይቱ
እቴጌ ጣይቱ የተወለዱት ነሐሴ 12 ቀን 1832 ዓ.ም ጐንደር ውስጥ ደብረታቦር ከተማ ነው። ጣይቱ ገና ልጅ ሳሉ አባታቸው በጦርነት ውስጥ ሞቱባቸው። ከዚያም ጣይቱ ወደ ጐጃም መጥተው በደብረ መዊዕ ገዳም ገብተው በዘመኑ ይሰጥ የነበረውን ትምህርት በሚገባ ተከታትለው መማራቸው ይነገራል። ፅህፈትን፣ ንባብን፣ ግዕዝና አማርኛ ቅኔን፣ ታሪክንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በሚገባ ተምረው አጠናቀዋል።
እቴጌ ጣይቱ የዘር ሐረጋቸው የሚመዘዘው ከኢትዮጵያ ነገስታት ተዋዕረድ ውስጥ በመሆኑ በስርዓትና በእንክብካቤ ያደጉ ናቸው። ስለ እርሳቸው በየቦታው ይወራ ነበር። አጤ ቴዎድሮስ ወደ ሸዋ ዘምተው አጤ ምንሊክን ማርከው ወደ ጐንደር ወስደዋቸው በሚያሳድጓቸው ወቅት፣ ምንሊክ በተለያዩ ሰዎች አማካይነት ጣይቱ ስለምትባል ሴት ብልህነትና አርቆ አሳቢነት ወሬ በተደጋጋሚ ይሰሙ ነበር። ጣይቱ ማን ናት? ምን አይነት ሰው ናት እያሉ ልባቸው መንጠልጠል ጀመረች።
‹‹ጣይቱ የምትባል ብልህ ሴት ትወለዳለች›› እየተባለ በወቅቱ የሚነገር ንግርት እንደነበር ፀሐፊያን ይገልፃሉ። ጣይቱ ከብልህነቷ የተነሳ ኢትዮጵያን ትመራለች እየተባለ ለረጅም ጊዜ ሲነገር ቆይቷል። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደስላሴ “ጣይቱ በምትባል ሴት የኢትዮጵያ መንግስት ታላቅ ይሆናል እየተባለ ሲነገር ይኖር ነበርና ከአፄ ምኒልክ አስቀድሞ የነበሩ አንዳንድ ነገሥታት ስሟ ጣይቱ የምትባል ሴት እየፈለጉ ማግባት ጀምረው ነበር። ነገር ግን ጊዜው አልደረሰም ነበርና አልሆነላቸውም።
ዘመኑ በደረሰ ጊዜ ግን አፄ ምኒልክ እቴጌ ጣይቱን አገቡ። እቴጌ ጣይቱም የብሩህ አዕምሮ ባለቤት ስለነበሩ በመንግሥቱ ስራ ሁሉ አፄ ምኒልክን ይረዱ ነበር። እንደ ንግርቱም ቃል ኢትዮጵያ በእቴጌ ጣይቱ ዘመን ታላቅ ሆነች” ብለዋል ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ስላሴ በ1915 ዓ.ም ባሳተሙት የህይወት ታሪክ በተሰኘው መፅሐፋቸው።
ፋንታሁን እንግዳ ታሪካዊ መዝገበ ሰብ በተሰኘው መፅሐፋቸው “ይህን ሁሉ አጥንተው የሚያወቁት ንጉሥ ምኒልክ ሚያዝያ 25 ቀን 1875 ዓ.ም በአንኮበር መድኃኒያለም ቤተ ክርስቲያን ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል ጋር በቁርባን ጋብቻውን ፈፀሙ። አምስት ዓመታት ቆይቶም ጥቅምት 27 ቀን 1882 ዓ.ም ጣይቱ ብጡል እቴጌ ተብለው ተሰየሙ” በማለት ፅፈዋል።
አፈወርቅ ገብረእየሱስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በተሰኘው መፅሐፋቸው ስለ ጣይቱ ሲገልጹ “የሸዋ ቤተ-መንግሥት ዓለሙ የዚህን ቀን ተጀመረ። የሸዋ ቆሌ፣ የሸዋ ደስታ የዚህን ቀን ተጀመረ። የሸዋ መንግት ከጣይቱ በኋላ ውቃቢ ገባው፣ ግርማና ውበት ተጫነው፣ ጥላው ከበደ፣ የእውነተኛው አዱኛ፣ የእውነተኛው ደስታ ከጣይቱ ብጡል ጋር ገባ” ብለዋል።
ጣይቱ ያልተሳተፉበት ልማት አልነበረም። ስልኩ፣ ባቡሩ፣ ኤሌክትሪኩ፣ ፊልሙ፣ ውሃው፣ መኪናው፣ ት/ቤቱ፣ ሆስፒታሉ፣ ሆቴሉ፣ መንገዱ ወዘተ… መገንባትና መተዋወቅ ሲጀምር ጣይቱ የባልተቤታቸው የአፄ ምኒልክ ቀኝ እጅ ነበሩ።
እቴጌ ጣይቱ የጣሊያን አጭበርባሪዎች ኢትዮጵያን አሳስተው ውጫሌ ላይ የተደረገውን የሁለቱን ሀገሮች ውል ቅኝ ግዛት መያዣ ለማድረግ ማሴራቸውን ከተረዱ በኋላ በልበሙሉነት ከኢጣሊያ መንግስት ጋር ጦርነት ለመግጠም ተነሱ።
የኢጣሊያውን ዲፕሎማት አንቶኔሊን ጣይቱ እንዲህ አሉት፡- “ያንተ ፍላጐት ኢትዮጵያ በሌላ መንግስት ፊት የኢጣሊያ ጥገኛ መሆኗን ለማሳወቅ ነው። ነገር ግን ይህን የመሰለው የምኞት ሃሳብ አይሞከርም! እኔ ራሴ ሴት ነኝ። ጦርነት አልፈልግም። ነገር ግን ይህን ውል ብሎ ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ!” ሲሉ ተናግረዋል።
በሀገራቸው ሉዐላዊነት ላይ ምንም ዓይነት ድርድር እንደማያደርጉ በትንታግ ንግግራቸው አሳውቀዋል። ከዚያም ሦስት ሺ እግረኛ ወታደርና ስድስት ሺ ፈረሰኛ ጦር እየመሩ ከአጤ ምኒልክ ጐንና ከሌሎችም የአድዋ ጀግኖች ጋር ሆነው ዘምተዋል።
እቴጌ ጣይቱ በዘመናቸው እጅግ ገናና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴት ነበሩ። ዛሬ የአፍሪካ መዲና ተብላ የምትጠራውን አዲስ አበባን የመሠረቱ የግዙፍ ስብዕና ባለቤት ናቸው። በእስራኤል ውስጥ በተለይም በእየሩሳሌም ውስጥ ያለውን የዴር ሱልጣን ገዳምን በመርዳትና የኢትዮጵያ መሆኑን አስረግጠው ያስመሰከሩ ሃይማኖተኛ እና ፖለቲከኛ ነበሩ። ኢትዮጵያ በጦርነቱም፣ በስልጣኔውም፣ በፖለቲካውም፣ በመንፈሳዊውም ዓለም ጠንክራ እንድትወጣ ብዙ ጥረዋል። ተሳክቶላቸዋልም።
ታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም አጤ ምኒልክ ሲያርፉ የቤተ-መንግስት ሹማምንቶች እቴጌ ጣይቱን ስልጣን ከሸዋ እጅ ወጥቶ ወደ ጐንደር ሊሄድ ነው በሚል ፈሩዋቸው። ስለዚህ ጣይቱ እንጦጦ ማርያም ሄደው በግዞት እንዲቀመጡ ተደረጉ። በጣሙን አዘኑ። በዚያው የሐዘን ስሜታቸው አፍሪካዊቷ ጀግና እቴጌ ጣይቱ የካቲት 4 ቀን 1910 ዓ.ም ሌሊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 8 / 2011
የትናየት ፈሩ