የዲጂታል ሚዲያ ባለሙያዎች በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ የድርሻቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፡- የዲጂታል ሚዲያ ባለሙያዎች የሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ የድርሻቸውን ሙያዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጠይቋል፡፡

ኮሚሽኑ ትናንት ከዲጂታል ሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት እየተሠራ ነው፡፡ ዲጂታል ሚዲያው ላይ ያሉ ባለሙያዎች ሂደቱን በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል ብለዋል፡፡

በ11 ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ተሳታፊዎችን የመምረጥና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎችን ማከናወኑን አስታውሰው፤ የትግራይ ክልልን በሂደቱ ተሳታፊ ማድረግን ጨምሮ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ በሚኖረው ሂደት ዲጂታል ሚዲያው ሚናውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

የዲጂታል ሚዲያው በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ሊኖረው በሚገባው ሚና ላይ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዲጂታል ሚዲያ ባለሙያዎች የሀገራዊ ምክክሩ ባለቤት በመሆን ሙያቸውን ለእዚህ ታላቅ ሀገራዊ ግብ መሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሂደቱ በሚፈለገው መልኩ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻዎች የባለቤትነት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተው፤ የዲጂታል ሚዲያ ባለሙያዎች የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን የሚያግዙ የአብሮነት ትርክቶችን በማዘጋጀት ለምክክር ሂደቱ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ዲጅታል ሚዲያው እንደ ሀገር የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ወደ ምክክሩ ለማምጣት እና በሂደቱ ያልተሳተፉ አካላት ወደ ሂደቱ እንዲመጡ ለማድረግ ሙያቸውን መጠቀም ይገባቸዋል ብለዋል።

በማህበራዊ ሚዲያው ሀሰተኛ መረጃዎች ሲሰራጩ እንደሚስተዋል ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፤ ዲጅታል ሚዲያው የጋራ መግባባት መፍጠር የሚያስችሉ መልካም እሳቤዎችን በመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ወደ ውይይት እንዲመጣ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ያስፈልጋል፡፡ የሚያቀራርቡና ሀገርን ወደፊት የሚያራምዱ ሃሳቦች ላይ ማተኮር እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

በመድረኩ ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ጉዞው ያከናወናቸውን አበይት ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮች፣ የተወሰዱ የመፍትሔ ሃሳቦች እንዲሁም ቀሪ ተግባራት ለውይይቱ ተሳታፊዎች ቀርቧል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ኮሚሽኑ ዲጂታል ሚዲያው በኮሚሽኑ ሥራዎች ላይ የጎላ ተሳትፎ እንዲያደርግ እድል እንዳልፈጠረ አመልክተው፤ ሽፋን ለመስጠት ሙከራዎች ቢኖሩም በቂ እንዳልነበሩ አንስተዋል፡፡

ብዙዎቹ ዘገባዎችም ስሜታዊነት የሚንጸባረቅባቸው እና ከመግባባት ይልቅ ጥርጣሬ የሚፈጥሩ እንደነበሩ ጠቁመው፤ በቀጣይነት ኮሚሽኑ የሚፈጥርላቸውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ጥረት እንደሚያደርጉ አመላክተዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You