በመጪው ክረምት በቀጣናው ከባድ ዝናብ ስለሚኖር ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፡- ቀጣዩ ክረምት መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ስለሚጥል ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲደረግ የኢጋድ አየር ንብረት ለውጥ ምርምር እና ትንበያ ገለጸ፡፡

በኢጋድ የአየር ንብረት ተመራማሪ ትጥቄ ካሳ (ዶክተር)የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ሀገራት ጋር 70ኛ የአየር ንብረት ትንበያው ፎረም ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ ቀጣዩ የዝናብ ወቅት በተለይ በኢትዮጵያ በርካታ ምርት የሚመረትበት ነው፤በተለይ ከዓባይ ግድብ ጋር ተያይዞ የግድቡን ውሃ ለመሙላት ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፤ይህንን ትንበያ በመጠቀም በሁሉም የመንግሥት አካላት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ክረምት የምንለው ከሰኔ እስከ መስከረም ያለው ወቅት ነው፡፡ በእዚህ ወቅትም በርካታ የግብርና እንቅስቃሴዎች የሚካሄድበት ነው ያሉት ተመራማሪው፤በኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጁቡቲ እና ሶማሊያ የምርት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሰበሰብነው መረጃ መሠረት መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚጠበቅ ትንበያው ያሳያል ብለዋል፡፡

በቀጣይ የክረምት ወቅት መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚዘንብ ትንበያው እንደሚያመላክት ጠቁመው፤ በተለይ በአብዛኛው የደቡብ ሱዳን፣ ምዕራባዊ የኬንያ ክፍል፣ ምሥራቃዊ ኡጋንዳ እንዲሁም ሱዳን ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚገኝ ትንበያው ያመላክታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ይህ መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ የተተነበየው የክረምት ዝናብ ለግብርናው እጅግ አስፈላጊ ነው ያሉት ተመራማሪው፤ በግብርና እና በውሃ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች እንዲሁም የተለያዩ ዘርፎች በመመካከር አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ እና የግብርናውን እንቅስቃሴ እንዲደግፍ በማድረግ እንዲሁም ከግድቦች ጋር ተያያዥነት ስላለው ሁኔታ የበለጠ ምርታማነትን ለማሳደግ ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በተለይ በሐምሌ ወር መጨረሻ እና ነሐሴ መግቢያ ላይ የሙቀት መጠኑ ከመደበኛው በታች ስለሚሆን ይህ ደግሞ የዝናብ መጠን ከመደበኛው በላይ እንደሚሆን ተጨማሪ መረጃ ያመለክታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ትንበያው መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ በመሆኑ፤ በተለይ በኢትዮጵያ የዝናብ ወቅቱ በደቡብ ምዕራብ ጀምሮ ወደ ሰሜናዊ ምሥራቅ የሚቀጥል ነው፤ በመሃል ተከታታይነት ያለው ከመጠን በላይ የሆነ ዝናብ ሊከሰት ስለሚችል የጎርፍ ተጠቂ በሆኑ አካባቢዎች የቅድመ ጥንቃቄ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በደቡባዊ የሀገራችን ክፍል በሶስቱም የዝናብ ወቅቶች ከመደበኛ በላይ ዝናብ በመጣሉ ምክንያት የመሬት መንሸራተት ማጋጠሙን አስታውሰው፤አሁንም መሰል ችግሮች ሊከሰቱ ስለሚችሉ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ከባለሙያዎች ጋር በመወያየት የቅድመ ጥንቃቄ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You