በምግብ ራስን ለመቻል እየተሠራ ያለው ሥራ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል

አዲስ አበባ፦ ባለፉት ዓመታት ሀገር በቀል ሪፎርሞችን በመተግበር በምግብ ራስን ለመቻል እየተሠራ ያለው ሥራ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

አቶ አደም ፋራህ በምግብ ራስን ለመቻል የተካሄዱ ጥረቶች እና የተገኙ ልምዶች የሚገመግምበት መድረክ በጅማ ከተማ ትናንት ሲካሄድ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ያላትን መሬት እና የሰው ኃይል አጣምራ አለመጠቀሟ ለበርካታ ዓመታት ለተረጂነት ዳርጓት ቆይቷል፡፡ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት ሀገር በቀል ሪፎርሞችን እና ማሻሻያዎችን በመተግበር በምግብ ራስን ለመቻል እየተሠራ ያለው ሥራ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል ብለዋል፡፡

የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎትን በራስ አቅም ለመሸፈን በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት አቶ አደም፤ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ጉልህና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ሰውን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች መተግበር የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ማስቻሉን አንስተው፤በሌማት ትሩፋት እየተተገበረ ባለው ሥራ 26 ሚሊዮን የነበረውን የአንድ ቀን ጫጩት ሥርጭት ባለፉት 10 ወራት ወደ 100 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።

በተለይም የዶሮ፣ የአሳ፣ የወተት እና የማር ምርት ላይ በማተኮር በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ የመኖ አቅርቦት እና የገበያ ትስስር ላይም መሠራቱን አንስተዋል ።በተጨማሪም የወተት ልማትን የማጎልበት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ለምትተገብራቸው የምግብ ሥርዓት ሥራዎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ማግኘቷን ገልጸው፤ በእዚህም ሁለተኛውን የዓለም አቀፍ ዘላቂ የንብ ማነብና ዕፅዋት ተራክቦ ፎረም እንድታዘጋጅ መመረጧንም አንስተዋል።

ከእዚሁ ጎን ለጎን የግብርና ሥራን በማዘመን ረገድ ትልቅ ስኬት ማስመዝገብ መቻሉን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የግብርና ዘርፍን ለማሳደግ እና ለማዘመን የሚያስችሉ በርካታ እድሎች ያሉ መሆኑን አንስተው፤ የእንስሳት እርባታን በክላስተር ለማልማት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር የምግብ ሥርዓትን በማሻሻል ረገድ ትልቅ መነቃቃት የፈጠረ መሆኑን በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ አስታውቀዋል።

አቶ አዲሱ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር በቀላሉ የምግብ ግብአቶችን በማምረት የኅብረተሰቡን የአመጋገብ ባሕል ያሻሻለ እና የገቢ ምንጭን የፈጠረ እንቅስቃሴ ነው።

የሌማት ትሩፋትና የምግብ ሥርዓት መርሀ ግብሩን ለማጠናከር የተለያዩ ኢኒሼቲቮች ተቀርጸው ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

በክልሉ በበጋ ስንዴ ምርትና በክረምት ደግሞ በሩዝ ልማት እንዲሁም በማርና በወተት ልማትና በዶሮና በእንቁላል ምርት በከፍተኛ የአመራር ክትትልና ትኩረት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

አቶ አዲሱ አረጋ በክልሉ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ በ102 ወረዳዎች ውስጥ ሲተገበር እንደነበር ገልጸው፤ በ2018 ዓ.ም 57 ወረዳዎች እንደሚካተቱ አመልክተዋል። በተጨማሪም በራስ አቅም ራስን ለመቻል እየተሠራ ያለው ሥራ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ነው የተናገሩት፡፡

በመድረኩ የምግብ ሽግግር ሥርዓት ፕሮግራም አካል የሆነው የሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚሠሩ ሥራዎች አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑ ተገልጿል። የግብርናው ዘርፍ የራስን ፍላጎት በራስ ለማሟላት ያለው አቅም እየጨመረ እንደሚገኝ ተመላክቷል። በኢትዮጵያ የምግብ ሽግግር ሥርዓት ፕሮግራም ተጨባጭ ለውጦች እየታዩበት መሆኑም ተገልጿል። የሌማት ትሩፋት ከውጭ የሚገቡ የምግብ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል አቅም እየፈጠረ መምጣቱም ተነግሯል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You