
አዲስ አበባ፡- ‹‹ግልጽ ተዓማኒና ትክክለኛ የኦዲት ሪፖርት በማቅረብ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ ፕሮፌሽናል የሂሳብ አያያዝን መከተል ያስፈልጋል›› ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ስለፕሮፌሽናል የሂሳብ አያያዝ ከአፍሪካ ሀገራት ልምድ ለመቅሰም ያዘጋጀው የሦስት ቀን ኮንፍረንስ በትናንትናው ዕለት በአያት ሪጀንሲ ሆቴል ሲከፈት እንደተናገሩት፤ ግልጽ፣ ተዓማኒና ትክክለኛ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ሪፖርት በማቅረብ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ ፕሮፌሽናል የሂሳብ አያያዝን መከተል ያስፈልጋል፡፡
የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ መቋቋም ከአፍሪካ ሀገራት እና ከሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመሥራት በእጅጉ የሚረዳ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የተቋሙ መመስረትና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አቅም መፍጠር ሀገሪቱ ዘላቂ ልማትን ለማስፈንና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡
በግልና በመንግሥት ተቋማት የገንዘብ አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ለማሻሻልና ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን በእጅጉ ይረዳል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ሀገራት በባቡር፣ በኔት ወርክ፣ በኢንዱስትሪ ፣በቴሌኮሙኒኬሽን፣ በንግድ፣ በኃይል አቅርቦትና በሌሎቹም ዘርፎች የሚያደርጓቸውን የኢኮኖሚ ትብብሮች እና ትስስሮችን ለማሳለጥ የፕሮፌሽናል አካውንታንቶች መኖር ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ አንስተው፤ ይህም ከአጀንዳ 2063 ጋር በቀጥታ የሚደጋገፍ እንደሆነ እዮብ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ መመስረቱ ባለሙያዎች በተለያዩ መንገዶች ሰልጥነው ዓለም አቀፍ የአካውንታንት ብቃት ማረጋገጫ እንዲያገኙ ከማስቻሉም ባሻገር በአካውንታንት መካከል ትብብር እንዲኖር፣ ግልጽና እና ተዓማኒ የኦዲት ሪፖርት እንዲቀርብ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል ድንበር ዘለል የንግድ ሥርዓትን ለማከናወን የሚጠቅም እንደሆነ ገልጸዋል።
በኢኮኖሚክ እድገት እና በሂሳብ አያያዝ ሥርዓት ውስጥ ግልጽነትና ተአማኒነት ዋናዎቹ ምሰሶዎች እንደሆኑ የተናገሩት እዮብ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
ፕሮፌሽናል የሂሳብ አያያዝ ሥርዓት በተለይም ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ እየተገበረች ላለችው፤ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የጎላ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው፤ እውነተኛ ብቃት ያላቸውን የሂሳብ አያያዝ ሙያተኞችን ማፍራት ሙስናን ለመዋጋትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል ነው ብለዋል። የሂሳብ አያያዝ ባለሙያዎች በውሳኔ አሰጣጥና በገንዘብ አስተዳደር ሥርዓት ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት መልካም አጋጣሚ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
ተቋሙ የልቀት ማዕከል በመሆን እንደሚያገለግል እና ችግሮችን መፍታት የሚችሉና ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉ ፕሮፌሽናል አካውንታትን ለማፍራት የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል፤ ይህም ሀገሪቱ የዘርፉን ሙያተኞች ለማብቃት እየወሰደች ያለችውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
የተቋሙ መመስረት ዓለም አቀፍ የአካውንታት ትስስር በመፍጠር እንዲተጋገዙ እንዲሁም መንግሥታዊ ተቋማትም ሆኑ ማህበራዊ ድርጅቶች ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል ነው ያሉት፡፡
ጠንካራ ሂሳብ አያያዝ ሙያተኞች መኖር ለኢንቨስተሮች መተማመን የሚሰጥ እንደሆነና ኢኮኖሚን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚጠቅም መሆኑን እዮብ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የ130 ሚሊዮን ሕዝብ ሀገር ናት፤ ፕሮፌሽናል የሂሳብ አያያዝ ሙያተኞች ከ540 የማይበልጡ ናቸው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ በውጭ ሀገር የተማሩና ልዩ ስልጠና የወሰዱ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
ኬንያ ከ65ሺህ በላይ ፣ ሩዋንዳ ከ6ሺህ በላይ ፕሮፌሽናል የሂሳብ አያያዝ ሙያተኞች እንዳሏቸው ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ የፕሮፌሽናል የሂሳብ አያያዝ ሙያተኞች ቁጥር አናሳ የሆነው ኢንስቲትዩቱ ባለመቋቋሙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ ውስጥ ፕሮፌሽናል የሂሳብ አያያዝ ኢንስቲትዩት ከሌላቸው ሦስትና አራት ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ እንደነበረች ጠቅሰው፤ ተቋሙ በኢትዮጵያ ከተመሠረተ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈለገው ደረጃ አለመጓዙን አስረድተዋል፡፡
አሁን በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ለመግባት የልምድ ልውውጥ እያደረገ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በሂሳብ አያያዝ ሙያ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ጀማሪ ሠራተኞች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አሠራርን ተረድተው ዓለም አቀፍ ሥራ የመሥራት እድል የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር አቶ ፍቃዱ አስረድተዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ በአፍሪካ የዓለም ባንክ ተወካዮች የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተጋባዦች ተገኝተዋል፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም