
አዲስ አበባ፡- ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የመውጫ ፈተና ውጤታማ ለማድረግና ተማሪዎች ቀድመው እንዲዘጋጁ ለማስቻል የተማሪዎች መመዘኛ ፈተናዎችን ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ መስጠት መጀመሩን አስታወቀ፡፡
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ሀብቴ ዱላ(ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚሰጠው የመውጫ ፈተና ቀድመው ራሳቸው እንዲያዘጋጁ ለማስቻል ብሎም የታቀደውን ውጤት ለማስመዝገብ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የሚሰጡ የኮርስ መመዘኛ ፈተናዎች ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡
ግቢው አብዛኛው የመማር ማስተማር ሂደት ከወረቀት ነጻ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ከአንደኛ ዓመት ተማሪዎች ጀምሮ ፈተና የሚወስዱት በበይነ መረብ ነው፡፡ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው የመውጫ ፈተናዎች ተማሪዎች እንዲዘጋጁበት ከማድረግ ጎን ለጎን የመልካም አስተዳደር ችግር ከመፍታት እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ለወረቀትና ለቀለም የሚያወጣውን ወጪ በመቀነስ ብዙ ሀብት ከብክነት ያዳነበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንደ ሀብቴ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ተማሪዎች ከመደበኛው መማር ማስተማር ጎን ለጎን በኢ- ለርኒግ የሚማሩበት እና የትምህርት ግብዓት የሚያገኙባቸው የተለያዩ መሠረተ ልማቶች ተሟልተዋል፡፡ እስከ እኤአ 2032 ድረስ ሙሉ በሙሉ ወደ አፕላይድ ሳይንስ ሊቀይሩ የሚችሉ ተግባራት ታቅደው በሂደት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚሰጠው የመውጫ ፈተና ከመስከረም ጀምሮ የተለያዩ ሞዴል ፈተናዎችና ቲቶሪያሎች ተዘጋጅተው ሲሰጡ ቆይቷል ያሉት ሀብቴ (ዶ/ር)፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዩኒቨርሲቲው የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል፡፡
በመጪው ሰኔ 2017 ዓ.ም ለሚሰጠው ሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና ከግንቦት ወር ጀምሮ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ለሚፈተኑ በ46 የትምህርት ክፍሎች አንድ ሺህ 400 ተማሪዎች በተለየ ሁኔታ እንዲዘጋጁ እየተደረገ እንደሚገኝም ነው ሀብቴ (ዶ/ር) የገለጹት፡፡
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን አሰልጥኖ ከማስመረቅ ባሻገር የሥራ እድል የሚያገኙበትን መንገድ ለመፍጠር ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ጋር የተለያዩ ወርክ ሾፖችና ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ የስምምነት ፊርማ መደረጉን አመላክተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ከሆነ ወዲህ አጠቃላይ በመማር ማስተማር ሂደት ላይና በግቢው የሚመረቁ ተማሪዎች ገበያው ምን ያህል ይፈልጋቸዋል የሚሉት ጉዳዮች ላይ ጥናት ተደርጓል ያሉት ሀብቴ (ዶ/ር)፤ እንደ ሀገር የተያዘውን ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ከማድረግ አኳያም አብዛኞቹ የግንኙነት መንገዶችና አገልግሎት አሰጣጡ በዲጂታል ዘዴ እየተሰጠ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሀብቴ (ዶ/ር)፤ የተለያዩ ሶፍትዌሮች በግቢው መምህራን በልጽገው ለአገልግሎት በቅተዋል ያሉ ሲሆን፤ ከእዚህ በተጨማሪም ሁሉም መማሪያ ክፍሎች ስማርት ተደርገዋል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ወደ ዲጂታላይዜሽን በሚያደርገው ጉዞ በተለይ የሚሰጣቸው የሚድና ፋይናል ፈተናዎች በሚሰጡበት ጊዜ የኃይል መቆራረጥ በመኖሩ አሠራሩ ላይ እክል እየፈጠረ እንደሚገኝ ሀብቴ (ዶ/ር) ጠቁመው፤ ይህም ተማሪዎች ላይ የሚፈጥረው ጫና እንዳለ ተናግረዋል፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም