አዲስ አበባ፡- ግጭቶች ባሉባቸው በምዕራብ ኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ያለውን ምርት በወቅቱ ለመሰብሰብ የአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፎ እንዲያደርግ የግብርና ሚኒስቴር ጠየቀ።
የግብርና ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሳኒ ረዲ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የአገሪቱ 40 በመቶ የበቆሎ ዘር የሚባዛበት ከመሆኑም አንጻር የአርሶ አደሩ ማሳ ብቻ ሳይሆን ለምርጥ ዘርነት ባለሀብቶች የዘሩት ሰሊጥና በቆሎ ችግር ላይ በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ለምርት አሰባሰቡ ሥራ የድርሻቸውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ አቶ ሳኒ ገለጻ ችግሩን ለመፍታት ከሁለቱም ክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከመከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ፣ ከአምራች ባለሀብቱና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋርም ውይይቶች ተደርገዋል። ሆኖም በአካባቢው ባለው የሰላም መደፍረስ ችግር ምክንያት በማሳ ላይ ያሉ ምርቶችን መሰብሰብ እንዳልተቻለ ጠቁመዋል።
መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አድርጎ ምርቱ እንዲሰበሰብ የማድረግ ሥራ ለመስራት የጋራ ኮሚቴ መቋቋሙን የተናገሩት አቶ ሳኒ ሠራዊቱም ሥራውን ለመስራት ተጨማሪ ምን ያህል ኃይል ያስፈልገኛል? የሚለውን እየለየ ነው ፤የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥትና የካማሼ ዞን አስተዳደርም የአካባቢው ነዋሪዎች ምርቱን ከሌብነትና ከቃጠሎ በመጠበቅ ላይ ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም ይህንን ኃላፊነት እየተወጣ ያለው አርሶ አደር ምርቱን የሚያነሳ የጉልበት ሠራተኛና ተሽከርካሪ ሲገባ ሰብሉ የአገር ሀብት መሆኑን ተገንዝቦ ድጋፍ እንዲያደርግና ከተቻለም በጉልበቱ እንዲሳተፍ አቶ ሳኒ ጥሪ አቀርበዋል ።
በአጠቃላይ የችግሩን ግዝፈት በመረዳት የመንግሥት አካላት፣ የወጣት አደረጃጀቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ምርቱ በወቅቱ እንዲነሳ ህዝቡን ወደ እርቀ ሰላም ለማምጣት የሚያስችሉ ትምህርቶችን መስጠት አለባቸው ያሉት አቶ ሳኒ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን ለቀጣይ ዓመት የምርት መቀነስና ብሎም የረሀብ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።
በደቡብ ክልል በተለይም የፀጥታ ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች ላይም አርሶ አደሩ በሙሉ ልቦና ጊዜው ምርቱን እንዳያሰባስብ የሚያስተጓጉሉ ችግሮች እየተስተዋሉ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2011
በእፀገነት አክሊሉ