
ጅግጅጋ፡- የ2012 የትምህርት ዘመን በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ብቻ ሳይሆን የሰላምን ምንነት ለማሳየት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገለጸ። በትምህርት ዘመኑ 3ሺ612 አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል መዘጋጀቱም ተጠቁሟል።
የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር አብዲ አህመድ ሀሰን እንደተናገሩት፤ የ2011 የትምህርት ዘመን የጎላ ችግር አይታይበት እንጂ ለዩኒቨርሲቲው አመራር፣ መምህራንና አጠቃላይ ሰራተኛው ፈተና ሆኖ አልፏል። ከዚህ ሂደት በመማርም የ2012 የትምህርት ዘመን ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን፤ ተግባሩም ዩኒቨርሲቲው የሰላምን ምንነት የሚያሳይበት፤ ህብረተሰቡም ሰላምን የሚያስተምርበት እንዲሆን ታስቦ እየተሰራ ነው።
እንደ ዶክተር አብዲ ገለጻ፤ 2010 ሐምሌ ወር ላይ ጅግጅጋ ከተማ የነበረው ችግር ባሳደረው ተጽዕኖ ምክንያት ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በ2011 በችግሩን ተቋቁሞ ማስተማር አይችልም የሚል ወሬ እንዲናፈስበት አድርጎም ነበር። ይሁን እንጂ የዩኒቨርሲቲው አመራር ከህዝቡም፣ ከሰራተኛውም፣ ከአገር ሽማግሌዎችም ጋር በመመካከርና በጋራ
በመስራትስጋቱን መቀነስና ወደስራ መግባት ተችሏል። እናም ዩኒቨርሲቲው በ2011 ዓ.ም ዋና ስራአድርጎ የያዘውም ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እንዴት በሰላማዊ ሁኔታ ቀጥሎ ተማሪዎችን ማስተማር ይችላል የሚለው ሲሆን፤ ይሄንንም እውን ለማድረግ በትኩረት ተሰርቷል። ዶክተር አብዲ እንዳሉት፤ ዓምና ከአንዴም ሁለት ጊዜ በተማሪዎች መካከል ግጭት ቢፈጠርም የከፋ ጉዳት አልደረሰም፤ የአንድም ሰው ህይወት አላለፈም።
ይልቁንም ጠዋት ተጣልተው ከሰዓት የክልሉ ፕሬዚዳንት በቦታው ተገኝተውችግሩን ፈትተዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ አይነት ድርጊቶች በ2012 በየትምህርት ዘመን መደገም ስለሌለባቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ለግጭት መንስኤ ይሆናሉ ያላቸውን ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ችግሮችን ለይቶና ኮሚቴ አቋቁሞ በመስራት
ላይ ይገኛል።በዚህ መልኩ የትምህርት ዘመኑ በጥሩ ሁኔታና በጥሩ መንፈስ እንዲጠናቀቅ ከከተማው፣ ከክልሉና ከፌዴራል የመንግስትና የዘርፉ አመራሮች ጋር ለመስራትም በእቅዱ ተቀምጦ ወደስራ በመገባቱ ዓመቱ በጥሩ ሁኔታ እንደሚጀመርም እርግጠኛ ናቸው።
በሶማሌና ኦሮሚያክልሎች መካከል በነበረው ግጭት የኦሮሞ ተማሪዎች በጊዜያዊነት ወደ ኦሮሚያ ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች፤ የሶማሌ ተማሪዎችምወደ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሄደው በጊዜያዊነት እንዲማሩ ተደርጎ እንደነበር የሚያስታውሱት ዶክተር አብዲ፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም በኋላ በተመደቡበት ይቀጥሉ የሚል ትዕዛዝ አሳልፎ እንደነበርም ይገልጻሉ። ሆኖም የተፈጠረውን ሰላም ተከትሎ ኦሮሚያ ክልል የሄዱ የኦሮሞ ተማሪዎች በራሳቸው ፍላጎት ጠይቀውና ዩኒቨርሲቲውም በደስታ ተቀብሎ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁና ተመርቀው የወጡም እንዳሉ ተናግረዋል።
ሰላሙ የመጣው ግን ዝም ብሎ ሳይሆን ለተማሪዎች ጥያቄ ተገቢውን መልስ በመስጠት እንደሆነ በመጠቆም፤ ዓምና ለተማሪዎች ግጭት እንደ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ በዩኒቨርሲቲው ያለው የውሃ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል።ይሄንና መሰል ለተማሪዎች ግጭት መነሻ ይሆናሉ የተባሉ ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረገ ስራ እየተሰራ መሆኑንና ቀሪ ስራዎች ቢኖሩ እንኳን የክረምት ተማሪዎች እንደወጡ የአንድና ሁለት ሳምንት እድሜ ተወስዶ የሚሰራ እንደሚሆንም አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም፣ ‹‹ማንም ሰው በሰላም ምክንያት ከዩኒቨርሲቲው እንዳይሄድ፤ ይልቁንም ከሌላ ቦታ ወደዩኒቨርሲቲው እንዲገቡ የሚያደርግ የሰላም ሁኔታ የምንፈጥርበት፣ ሰላም ምን እንደሆነ የምናሳይበት፤ ህዝቡም ሰላም ምን እንደሆነ በካበተ እሴቱ ተጠቅሞ ለሚመጡ ተማሪዎች የሚያስተምርበት የትምህርት ዓመት ይሆናል፤›› ብለዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2011
ወንድወሰን ሽመልስ