የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ የአዲሱን ዓመት የከፍተኛ ትምህርት መጀመር አስመልክተው ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል። ይህንን መልዕክት በድጋሚ አቅርበነዋልና ያንብቡት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ተማሪዎችን እንዲህም ብለዋል፤
• ባልተግባባንባቸው ነገሮች ሁሉ አንጣላም፤
• የተማረ ሰው ማለት ተንትኖና አንጥሮ ማሰብ የሚችል ነው፤
• አንዲት ሀገር፣ የማያነብቡ ግን የተማሩ ሰዎች በብዛት የሚገኙባት ከሆነች ትጎዳለች፤
• መዝናኛዎቻችሁ አደንዛዥ ዕፆች፣ አስካሪ መጠጦች፣ ኢሞራላዊ ተግባራትና ሱስ አምጪ ነገሮች ፈፅሞ አይሁኑ፤
• ሁላችሁም ተማሪዎች ወገባችሁን አጥብቃችሁ ታጠቁ፤ ሀገራችሁና ወገናችሁ እየጠበቋችሁ ነው። ጊዜ የለንም፤ ፍጠኑ፤
ሙሉ መልዕክቱን ያንበቡ!
ይድረስ ለነገዎቹ
የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ ተማሪዎች ማለት የአንዲት ሀገር ‹ነገዎች› ናቸው። የአንዲት ሀገር መጻዒ እድል በዋነኝነት የሚወሰነው ያችን ሀገር ለመረከብ እየተዘጋጀ ባለው ትውልድ ማንነት ነው። ለእኛ፣ የነገውን የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ የምትወስኑት እናንተ የዛሬዎቹ ተማሪዎች የነገዎቹ አገር ገንቢዎች ናችሁ። አገር ስትገነቡ መዶሻችሁ የሚሆነው እውቀት፣ መጋዝና ሜትራችሁ የሚሆነው ክህሎት ነውና እነዚህን መሳሪያዎቻችሁን ከዩንቨርስቲዎችና ኮሌጆች ገብይታችሁ ስትወጡ ያን ጊዜ ኮርታችሁ ኢትዮጵያን የምታኮሩ የተማረ አገር ተረካቢዎች ትሆናላችሁ።
የተማረ ሰው ማለት ዕውቀት የሰበሰበ ሰው ማለት ብቻ አይደለም። የተማረ ሰው ማለት ተንትኖና አንጥሮ ማሰብ የሚችል ነው። እንዴትና ምን መማር እንዳለበት የሚያውቅ፤ ነጻ ሆኖ የሚስብ፤ ለነገሮች ትክክለኛ ብያኔ የሚሰጥ እና የሚጠበቅበትን ለመሥራት ራሱን በራሱ የሚቀሰቅስ ነው።
የተማረ ሰው ማለት ከሌሎች ጋር ሲኖር ልዩነቶችን በሠለጠነና ለሁሉም በሚጠቅም መልኩ ለመፍታት የሚችል፤ ችግሮችን በመጠናቸው ልክ የሚረዳና መፍትሔ የሚያፈልቅ፤ የራሱን ስሜትና ጠባይ እንዴት ማስተዳደር እንደሚችል የሚያውቅ፤ የሥራና የኑሮ ሥነ ምግባር ያለው ነው። ጾታ፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት፣ ቀለምና እድሜ ሳይለይ ለሰው ዘር ሁሉ እኩል አመለካከት ያለው፤ ከለውጥ ጋር እንዴት መሄድ እንዳለበት የሚረዳ ነው። ለኪነ ጥበብ፣ ለተፈጥሮ፣ ለእውቀት ልዩ ፍቅር ያለው፤ የማያውቃቸውን ባሕሎች፣ ቋንቋዎችና አካባቢዎች ለማወቅ የሚተጋ ነው።
በየትኛውም ማዕዘነ-ዓለም፣ የተማረን ሰው ለመበየን የሚቀርቡት መመዘኛዎች ከእነዚህ ብዙም የተለዩ አይሆኑም። እናንተ የኛ ‹ነገዎች› በእነዚህ መመዘኛዎች ራሳችሁን እንደምትለኩ እተማመናለሁ። እየተዘጋጃችሁ ያላችሁት ተምራችሁ ሥራ ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ከዚህ ከፍ ላለ አላማ ነው። የምትማሩት ሀገርን እንድትረከቡ ነው። የምትማሩት የዚህችን ሀገር ነገ እንድታሳምሩላትም ጭምር ነው። እናንተ የዚህች ሀገር ነገዎች ናችሁና።
ኮሌጅና ዩንቨርስቲዎቻችሁን ለነገው ኃላፊነት የመዘጋጃ ቦታዎች አድርጓቸው። አብያተ መጻሕፍቱ ዋና ማዕከሎቻችሁ ይሁኑ። በርትታችሁ አንብቡ። የምትማሩትን የትምህርት ዘርፍ ብቻ አይደለም። ሁለገብ ዕውቀት እንዲኖራችሁና ሁለገብ የሆኑ የሀገራችሁን ችግሮች መፍታት እንድትችሉ እንደ ንቧ ከየዓይነቱ ቅሰሙ። አንዲት ሀገር፣ የማያነብቡ ግን የተማሩ ሰዎች በብዛት የሚገኙባት ከሆነች ትጎዳለች።
ሌላው ቀርቶ ሕግና መመሪያ አንብቦና ዐውቆ የሚሠራ ሠራተኛ ልታጣ ትችላለች። ዩንቨርስቲዎች ዩንቨርሳል ሀሳቦች የሚስተናገዱባቸው መሆናቸውን ተረድታችሁ በትናንሽ ሳይሆን በትላልቅ ጉዳዮች፣ በመንደር ሳይሆን በአገር አጀንዳዎች ተጠምዳችሁ አመቱን እንደምታሳልፉ ተስፋ አደርጋለሁ። ከአካዳሚክ እውቀት በተጨማሪ ከሌሎች የእውቀት ዘርፎች አንብባችሁ የአስተሳሰባችሁን አድማስ አስፍታችሁ፤ ለነገ ህይወታችሁ ስንቅ የሚሆን ብዙ አይነት ክህሎት ይዛችሁ እንደምትወጡ አልጠራጠርም።
የምትገቡባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትንሿን ኢትዮጵያ አቅፈው የያዙ ናቸው። ከልዩ ልዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከመጡ ተማሪዎች መሃል መገኘት፤ አይነተ-ብዙ እምነት፣ ባሕልና ቋንቋ ካላቸው ሰዎች ጋር በአንድ ግቢ ውስጥ መመደብ ነገን ለሚረከብ ትውልድ በሚሊዮን ብር የማይገኝ እድል ነው። አገር መምራት የሚያስችል እውቀት ታገኙበታላችሁ፤ የኑሮ ዳገትንም ሆነ የህይወት ቁልቁለትን የምትሻገሩበት ዘዴና ብልሃት ትማሩበታላችሁ። የህይወት ጥሪያችሁ ወዴት እንደሚወስዳችሁ ብታውቁም መንገዱ ላይ ግን ምን አይነት ጋሬጣዎች እንደሚገጥማችሁ ፈፅሞ ልታውቁ አትችሉም።
ስለዚህ አሁን በእጃችሁ ያለውን እድል ተጠቀሙበት። የማታውቁትን ቋንቋ ለማወቅ፣ ሰምታችሁ የማታውቁትን ታሪክ ለመስማት፣ ያልለመዳችሁትን ምግብ ለመልመድ፣ የማትችሉትን ክህሎት ለመቻል፣ አዳዲስ አካባቢዎችን ለመጎብኘት፣ ከአዳዲስ ባሕሎች ጋር ለመተዋወቅ ይህንን እድል ተጠቀሙበት። የቡድን ሥራዎች ሲሰጧችሁ ከማትቀርቡት ሰው ጋር ለመቀራረብና አዲስ ነገር ለመማር ጥረት አድርጉ። ያለ ሰው ማደግ፣ ብቻችሁን ብዙ ምዕራፍ መጓዝ አትችሉምና ከአራቱም አቅጣጫ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውን ጋር ትስስር ፍጠሩ፤ ከምታውቁትና ከለመዳችሁት ማኅበረሰብ ውጭ ሌላ ወዳጅ አፍሩ።
የባሕል፣ የቋንቋ፣ የአመለካከትና የእምነት ልዩነቶች እንዴት ለአንዲት ሀገር እንደሚጠቅሙ እናንተ ካላሳያችሁ ከሌላ ከየትም አይመጣም። ክርክሮችና ወይይቶችን ልመዱ፤ ነገ የምረጡኝ ዘመቻ የምታደርጉ የዚህች ሀገር መሪዎች ናችሁና። የሠለጠነ የውይይትና የክርክር ሥርዓት መመንጨት ያለበት ከከፍተኛ የትምህር ተቋማት ነው።
በመረጃና በማስረጃ ማመን፣ በተጠየቅና በፍሬ ነገር መወያየትና መከራከር ለሕዝባችን ባሕሉ እንዲሆን እናንተ ካልሠራችሁ ሌላ ማን ይሠራል? ለዚህ ደግሞ ከሁሉም ማኅበረሰብ ባህል ውስጥ አዳዲስ ዕውቀት፣ ልምድና አሠራር መማርና መልመድ ያስፈልጋል።
በየትምህርት ተቋሞቻችሁ የሥነፅሁፍ፣ የሥነ-ሥዕል፣ የፍልስፍና፣ የሀገርህን ዕወቅ፣ የባሕልና የመሳሰሉት መድረኮች እንዲስፋፉ አድርጉ። የትምህርት ቤት ሕይወት አሰልቺ አይደለም። ከዕውቀት የበለጠ መዝናኛ የለም። የየባሕሉን ሙዚቃ፣ ሥነ-ቃል፣ ተረኮች፣ ወጎች፣ ቀልዶች፣ አለባበስ፣ የምግብ አሠራር፣ አሳሳል፣ የበዓላት አከባበሮች ወደ አንድ መድረክ አምጡትና እየተዝናናችሁ ተማማሩባቸው። ከዚህ ውጭ መዝናኛዎቻችሁ አደንዛዥ ዕፆች፣ አስካሪ መጠጦች፣ ኢሞራላዊ ተግባራትና ሱስ አምጪ ነገሮች ፈፅሞ አይሁኑ።
ይህንን ሁሉ የምታጣጥሙበትንና የነገዋ ኢትዮጵያ ገንቢዎች ሆናችሁ የምትወጡበትን የትምህርት ተቋም የግጭትና የጥላቻ መናኸሪያ ለማድረግ ተፍ ተፍ የሚሉ ካሉ በሰለጠነ መንገድ ገሥጹዋቸው። አርሟቸው። ተቃወሟቸው። ከልክ በላይ ከሄዱ ደግሞ ለተቋሙ አስተዳደር አባላትና ለጸጥታ አካላት አጋልጣችሁ ስጧቸው። እንደዚያ የሚያደርጉ ሰዎች የእናንተን ጣፋጭ የኮሌጅ ሕይወት ለማበላሸትና የሀገራችንን መጻኢ ዕድል ለማሰናከል የተሰለፉ ናቸውና ‹ልዩነታችን ውበታችን ነው› በሏቸው። ጥላቻን በፍቅር፣ ቂምን በይቅርታ አሸንፋችሁ አሳዩዋቸው።
ባልተግባባንባቸው ነገሮች ሁሉ አንጣላም። ነገ ወይ እንግባባባቸዋለን ያለበለዚያም ለየባለቤቱ ትተናቸው በተግባባንባቸው እንቀጥላለን። አንድ ሀገር የገነባነው በመሠረታዊ ነገሮች ተስማምተን እንጂ በሁሉም ነገር ተስማምተን አይደለም። ዋናው የመግባቢያ ሥርዓት ማደራጀት ነው። ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ የሚያስከድ ባሕል መገንባት ነው። ልዩነቶች የማያስደነግጡት ማኅበረሰብ ለመፍጠር ነው። ለዚህ ደግሞ በዕውቀት መስክ ላይ ከተሠማራችሁት ከእናንተ የተሻለ ለኢትዮጵያ ከወዴት ይመጣላታል? ሌላው፣ የዘንድሮ ተመራቂዎች የምታዘጋጇቸው የጥናት ወረቀቶችና ፕሮጀክቶች በጥረታችሁ አምጣችሁ የምትወልዱት እንጂ ሌሎች የለፉበትን የምትሰርቁበት አመት እንዳይሆን ከወዲሁ ራሳችሁን አዘጋጁ።
በተሰረቀ ምርምር ሲመረቁ የሚለብሱት ጥቁር ጋዋን ይኮሰኩሳል እንጂ አይለሰልስም፤ የምስክር ወረቀቱ የውርደት እንጂ የኩራት ሊሆን አይችልም። ይሄን አውቃችሁ በእውነት ተማሩ፣ ተመራመሩ:: ሁላችሁም ተማሪዎች ወገባችሁን አጥብቃችሁ ታጠቁ፤ ሀገራችሁና ወገናችሁ እየጠበቋችሁ ነው። ጊዜ የለንም ፍጠኑ። ከትናንቱ እጅግ ዘግይተናልና ለነገ መፍጠን አለብን። መሮጥ እንጂ መሄድ ብቻ አያዋጣንም። ለአልባሌ ነገር ጊዜ የለንም። ጊዜው የትምህርት፣ የሥራና የሀገር ግንባታ ነው።
መልካም የትምህርት ዘመን ይሁንላችሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረትና ሕብረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!
ጥቅምት 03, 2011 ዓ.ም