ሙዚቃ በቋንቋ፣በቀለምና በፖለቲካ አመለካከት ድንበር የታጠረውን የዓለምን ህዝብ አንድ የማድረግ አቅም አለው።ፍቅርን በመስበክ፣ በዘርና በጎሳ ጥላቻ የታመመ አንጎልን በመፈወስ። ታሪክን በመዘከር። ያስተሳሰብ አድማስን በማስፋት የማይተካ ሚና አለው።ለዚህ ደግሞ የሙያው ባለቤቶች ሚና ወደር የለውም። ጊዜ ገንዘብና ጉልበታቸውን አፍስሰው ጥረው ግረው ያወጡት ሙዚቃ የልፋታቸውን ያህል ወዛቸውን እንኳን ሳያብሱበት የዘራፊዎች ሲሳይ ለመሆን ተዳርገዋል። የድካማቸው ውጤት የሆኑት ሙዚቃዎቻቸው የዳኛ ያለህ በሚያስብል መልኩ ለሌሎች መጠቀሚያነት በመዋል ላይ ነው።
ሳይሰራ የሚበላው እየተበራከተ መጥቷል። እናም ድምጻውያኑ የለፉበትን ማቅረብ እየተው መጥተዋል። ለዚህ አብነት የሚሆነን ወደ ዝግጅት ክፍላችን ቅሬታውን ይዞ የመጣው ድምጻዊ ቢተው ዳዊት ነው።
ድምጻዊው «የት ተሄዶ አቤት ይባል። ደራሽም ተጠያቂም የለም።» ይላል እንግ ልቱን ሲያስታውስ። ባለቤትነቱ መነፈጉም አንገሽ ግሾታል። ንብረቱን የሸጠው ለኮከብ ሙዚቃ ቤት አሳታሚና አከፋፋይ ድርጅት ሲሆን፤ 56 ሺ ብር አውጥቶ በ26 ሺ ብር ነበር የተዋዋለው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የመጀመሪያው በመሆኑ በብዙ ሚዲያ እንዲተዋወቅለት በመፈለግ፣ ብዙ ገቢ አግኝቶ በቀጣይ የተሻለ ሥራ ይዞ ብቅ እንድል ያደርገኛል ብሎ በማመኑ ነበር።
ይሁንና ማተሚያ ቤቱ ትንሽ አሳትሞ ከሸጠ በኋላ ሙዚቃ ቤቱን ዘግቶ ጮራ ማተሚያ ቤት ስላደረገው ቪሲዲው መሸጡን አቆመ። ይህ በሆነበት ሁኔታ ከዓመታት ቆይታ በኋላ ግን «ጊዜው አድርጎኛል» የሚለው አልበሙ ፈቃድ ባላገኙ ድረ ገጾች ተጭኖ ሲደመጥ ተመለከተ።
እነዚህ ድረ ገጾች ጎጆ ሚዲያ፣ ሆርን ሚዲያ፣ አሻም አዲስ የሚባሉት ሲሆኑ፤ ቪሲዲውን ለቀው ብዙ ገቢ እየሰበሰቡበት መሆኑ ባሉት ተመልካቾች ብዛት መለካት ይቻላል የሚለው ድምጻዊው፤ ይህ ተግባራቸው ብሰራም ለሌላ ነው እንዲል እንዳደረገውና የሙዚቃ ሥራዎቹን በእጁ ይዞ ዓመታትን እንዲያሳልፍ እንዳስገደደው ይናገራል።
ሥራዎቹ ቢለቀቁ ኖሮ ብዙዎችን ያስተምሩ እንደነበር ያስረዳል። በተለይም ስፖርትና ፖለቲካው የተደበላለቀበትን ጉዳይ በሚገባ ያሳያልና ወጣቱን ያርማል ባይ ነበር። ነገር ግን «ለማን ብዬ በራሴ አሳትሜ እንዳለፈው በገንዘቤም በጉልበቴም ልክሰር» ብሎ እንደያዘው አጫውቶናል። ያለፈው ሥራውም ቢሆን መና መቅረት እንደሌለበት ያምናል።
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው በአዕምሯዊ ንብረት የቅጅ መብት ጥበቃ ልማት ዳይሬክተር አቶ ናስር ኑሩ ረሺድ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፣ ይህ ተግባር የእኛ አገር ችግር ብቻ አይደለም። ዓለምም እየታመሰበትና መፍትሄ አጥቶለት የቆየ ነው። ይሁንና በአገራችን የሚሰሩ ሥራዎች አሉ። በአዋጅ ድንጋጌዎችን ከማውጣት ጀምሮ ባለንብረቶች መብታቸውን እስከማስከበር ድረስ ሥራዎች ይሰራሉ። ሆኖም አዋጁን ተጠቅመው በራሳቸው ጥረት እስከመ ጨረሻ ካልታገሉ ማንም ሊከራከርላቸው አይችልም ይላሉ።
አዋጁ የሥነፅሁፍ፣ የኪነጥበብና ተመሳሳይ የፈጠራ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ ተዛማጅ መብቶችን በሕግ እውቅና ሰጥቶ ጥበቃ እንዲደረግ ያዛል። ለአብነትም በሙዚቃ ብቻ ቢነሳ ወጥ (ኦርጅናል) ሥራውን በተመለከተ የፈጠራው ባለቤት ሥራውን የማባዛት፣ ሥራን የመተርጎም፣ ሥራን የማመሳሰል፣ የማቀናበር ወይም ወደ ሌላ ዓይነት የመቀየር፣ በሽያጭ ወይም በኪራይ ኦርጅናል ሥራውን ወይም ቅጂውን የማከፋፈል ወይም ቅጂውን ከውጭ ሀገር የማስገባት መብት እንዳለው ይገልጻሉ።
የፈጠራ ባለቤቱ ኦርጅናል ሥራውን ወይም ቅጂውን ለህዝብ የማሳየት። በይፋ የመከወን። ብሮድካስት የማድረግ። በሌላ መንገድ የማሰራጨት ለመፈፀም ወይም ሌላ ሰው እንዲፈፅማቸው ለመፍቀድ ብቸኛ መብትም ተሰጥቶታል የሚሉት አቶ ናስር። በተለያየ ምክንያት ያለ ባለቤቱ ፈቃድ ተዘርፎ የሚገኝበት አጋጣሚ በመብዛቱና የድረገጾች አድራሻ አለመታወቅ ግን ክትትልና ጥበቃ ለማድረግ አስቸግሯል። የህግ ተፈጻሚነቱንም እየተፈታተነው እንደሆነ ያስረዳሉ።ስለዚህም በዋናነት ክትትልና ጥበቃ የማድረጉ ሥራው የራሱ የባለቤቱ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ።
እንደ አቶ ናስር ገለጻ፤የአንድ ወጥ የሥነ ጥበብ ሥራ ወይም የአንድ ደራሲ ወይም የዜማ ደራሲ ኦርጅናል ፅሁፍ በሥራው አመንጪ ከተላለፈ በኋላ ከሚደረገው ድጋሚ ሽያጭ ዋጋ ላይ የሥራ አመንጪው ወይም ወራሹየተወሰነ ድርሻ የማግኘት መብት እንዳለው አዋጁ ያስቀምጣል።ይሁን እንጂ ከሳሾች ወይም ተዘረፍን ባዮች ይህንን ቢያደርጉ የማያገኙበት አጋጣሚ ብዙ ነው።ምክንያቱም የቴክኖሎጂ መብዛት በግል የሚከፈቱ እውቅና የሌላቸውን ድረገጾች አበራክቷልና መፍትሄ ማግኘት ከባድ እንደሆነ ያነሳሉ። ሆኖም ተቋሙ ለማህበረሰብ ግልጋሎትና ለፈጠራ ባለሀብቶች መፍትሄ ማፈላለግ ኃላፊነት አለበትና ችግርን ለመቀነስ ከፍትህ አካላት ጋር መመካከር እንደጀመረ ይገልጻሉ።
እንደ ተቋም ባለንብረቶች የንብረቱ ባለቤት ለመሆናቸው መረጃ ይሰጣቸዋል። ከዚያም አልፎ ችግሩን በምን መልኩ መከላከል እንደሚቻል በማህበራት አማካኝነት ስልጠና ይሰጣል። የህግ ክለሳና መሰል ነገሮችም ቢሆኑ ይከናወናሉ። ይህ ደግሞ ሙዚቀኞች የራሳቸውን የፈጠራ ሥራ መስራት እንዲችሉ ያበረታታል። ሆኖም ችግር ሲያጋጥም የፈጠራ ባለሀብቱ ተሯሩጦ መፍትሄ ማግኘት አለበት የሚሉት አቶ ናስር፤አዕምሯዊ ንብረት ማድረግ የሚችለው ንብረቱ የሱ መሆኑን መንገር ነው።
ከዚያ በኋላ ንብረቱን የመንከባከብና ማስጠበቅ ሥራው የባለቤቱ ይሆናል። ችግር ደረሰብኝ ብሎ መረጃ ማግኘት ይችላል እንጂ ለእርሱ የምንከራከርበት ሁኔታ አይኖርም። ለፍትህ የሚያስፈልጉ ንብረትነቱ የሱ ለመሆኑ ማረጋገጫ ተቋሙ ከተጠየቀ ያቀርባል። ከዚያ አልፎ ግን የተሰጠው መብት ስለሌለ ምንም ማድረግ እንደማይችል ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት ድምጻዊዎች በለፉበት ልክ ገቢ እያገኙ እንዳልሆነ የሚናገረው ደግሞ የኢትዮጵያ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር ምክትል አስተዳዳሪ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ሞሲሳ ነው። እርሱ እንደሚያስረዳው፤ ችግሮቹን ለማቆም ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አሜሪካም ተስኗታል። በዚያ ላይ የአገር ውስጥ ህግ የውጪን ድረገጽ መቆጣጠርና መቅጣት አይችልም። በአገር ውስጥም ቢሆን እንኳን ድረገጾችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግ የለም። በዚህም ሙዚቀኞች ንብረታቸውን መዘረፋቸው አይቀሬ ነው።
ችግሮቹ ብዙ ሆነው እንደ ልምድ እየተቆጠሩ እንደሆነ የሚያነሳው ድምጻዊው፤ የአዕምሯዊ ንብረት ከባለቤትነት እውቅና ውጪ ሊሰራ የሚችለው ነገር የለም። ስለዚህ መደረግ ያለበት ባለንብረቱ በቀጥታ ተዋቂ ለሆኑ ድረገጾች በራሱ መንገድ ተዋውሎ እንዲያሰራጩለት ማድረግ ነው። ከዚያ ከሚገኘው ገቢ ይካፈላል። ይህ ካልሆነ ግን ሙዚቀኛው በመበዝበዝ ኑሮውን ይገፋል። በተለይም የማይታወቁ ድረገጾች መጫወቻ ነው የሚሆነው። እናም መፍትሄው ቅድሚያ ኮፒ አድርጎ ማስቀመጥና ህጋዊ ማድረግ ነው። ቀድሞ ከጫነው ተጠያቂነትን ስለሚያመጣበት አያደርገውምና በዚህ መከላከል እንደሚገባ ያሳስባል።
ማህበሩ «ሩያሊቲ» ሰብስቦ ለድረ ገጾችና ሙዚቃዎችን ለሚፈልግ ተጠቃሚዎች ማለትም እንደነቴሌ፣ አየር መንገድ የመሳሰሉት ያከፋፍላል የሚሉት ምክትል አስተዳደሩ፤ በዚህም የሙዚቃው ባለንብረቶች ገንዘብ እንዲያገኙ ያደርጋል። ይሁንና ሙዚቀኛው ራሱን የሚሸጥበት ምንም አይነት ነገር በመኖሩ እንዳልዘረፍ በማለት በራሱ ጥረት ለተለያዩ ድረገጾች ቴክኖሎጂውን ተከትሎ ሥራዎቹን ቀድሞ ይሸጣል። ሌሎች ድረገጾች ሊወስዱት ሲሞክሩ በዚያ ድረገጽ ተይዟል ስለሚባል አይሄድም። አልፈው ከወሰዱትም ለተዋዋለበት ነግሮ ማዘጋት ይቻላል። ይህ የሚሳካው ግን ብዙ ጊዜ ተዋቂነት ላለው ሙዚቀኛ ብቻ ነው። እናም ታዋቂ ላልሆኑ ይህንን እድል የማግኘቱ ሁኔታ አናሳ እንደሆነ ይናገራል።
በድረገጽ ጉዳይ ቋሚ መፍትሄ ለማግኘት እጅግ ይከብዳል። ስለዚህ ሰዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መስራት፣ የህግ ማዕቀፉን ጠንካራና ፈጣን ምላሽ ሰጪ ማድረግ፣ ህጉንም ማሻሻልና ድረገጽን የሚመለከት ህግ ማርቀቅ እንደሚገባ የሚያነሳው ድምጻዊ ቴዎድሮስ፤ ይህ ተጠያቂነት በተግባር መተርጎም ይኖርበታል። የት ሄደው መጠየቅ እንዳለባቸውም ማስተማር ያስፈልጋል። ካለዚያ ግን ተስፋ ቆራጭ ድምጻውያን ይበዙና ሙዚቃ እና ተጠቃሚ እንዳይገናኙ ይሆናል ብሏል። እኛም መፍትሄ መስጠት ያለበት መፍትሄ ይስጥ ብለን አበቃን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5 /2011
ጽጌረዳ ጫንያለው