ሀዋሳ፦ አርሶአደሮች፣ የህብረት ስራ ማህበራት እና አቅራቢዎች ምርታቸውን ባሉበት ቦታ እንዲገበያዩ የሚያስችል ኤሌክትሮኒክስ የግብይት ማዕከል ትናንት ተመርቋል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ21 ሚሊዮን ብር ያስገነባው ማዕከሉ በደቡብ ክልል የመጀመሪያው ነው።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ የኤሌክትሮኒክስ የገበያ ማዕከሉ በተመረቀበት ወቅት እንደገለጹት፤ የሐዋሳ ኤሌክትሮኒክስ የገበያ ማዕከል ለደቡብ ክልል እና ለኦሮሚያ ጉጂ ዞኖች የሚገኙ አርሶአደሮች እና ገበያተኞች ምቹ አሰራር ይፈጥራል። በተለይም ለቡና አምራቾች ዘመናዊ የግብይት ማዕከሉ መገንባት የተሻለ የዋጋ ተጠቃሚነት ይፈጥርላቸዋል።
ቀደምባሉ ጊዜያት ተገበያዮች በአካል ተገናኝተው የዋጋ ድርድር የሚያደርጉበት አሰራር መኖሩን ያስታወሱት አቶ ወንድማገኘሁ፤ አሰራሩ ጊዜ የሚወስድ ከመሆኑ በላይ ለህግ ጥሰት የተጋለጠ ነበር። የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ስርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ መከናወን በመጀመሩ ግብይቱን ስኬታማ እና ዘመናዊ እያደረገው እንደሚገኝም አስታውሰዋል።
«እስከ አሁን ባለው የግብይት ስርዓት ተገበያዮች ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ይገደዳሉ። ይህን አድካሚ አሰራር ለመቀየር በሰባት የኢትዮጵያ ከተሞች የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማዕከላት ለመገንባት እየተሰራ ይገኛል። የሃዋሳ ማዕከልም የሙከራ ስራውን ጨርሶ ወደ አገልግሎት ገብቷል» ብለዋል።
የኢፌዴሪ ንግድ ሚኒስትር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው፤ ዘመናዊ ማዕከሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶች በማቅረብ መተማመን ያለበት ገበያ መፍጠር ያስችላል። አርሶአደሩ ዋጋ ተቀባይ ከመሆን የዋጋ ተደራዳሪ እንዲሆን የሚያስችል አሰራርን የያዘ ነው። አርሶአደሮችም በማዕከሉ አገልግሎት የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
ወጣት ፈትለወቅር ተመስገን፤ ቀደምባሉ ጊዜያት ለግብይት አዲስ አበባ ድረስ እንደምትሄድ አስታውሳ፤ ይህም የጊዜም ሆነ የሀብት ብክነት አስከትሎባታል። የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማዕከሉ መከፈቱ በአካባቢዋ የመረጠችውን ምርት በተሻለ ፍጥነት እንድታገኝ እንደሚያግዛት አስረድታለች።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአሁኑ ወቅት 22 የምርት መቀበያ ማዕከላት አሉት። ባለስልጣኑ ስራ ከጀመረበት ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ 203 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የግብርና ምርቶችን አገበያይቷል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2011
ሊዲያ ተስፋዬ