
የታላቁ ረመዳን ወር ጾም አልቆ በየዓመቱ አዲስ ጨረቃ ሲታይ በዓሉ ይጀመራል። ለአራት ተከታታይ ቀናትም ዘመድ አዝማዱ ይጠያየቃል። ድሆችም ችግራቸውን ይረሳሉ። ሁሉንም በእኩል ደረጃ ለማየትና ለማስተናገድ ይሰራሉ። ይህንን ካላደረግን ጸሎታችን አይሰምርም።ስለዚህ በበዓሉ ዕለት ሁሉም የእምነቱ ተከታይ በአንድነት፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብ የሚጫወተው፤ የሚጠያየቀውም።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር ኢድሪስ ለ1ሺ440ኛው የአረፋ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል። ኢብራሂም የአምላኩን ፈቃድ ለመፈጸም የቀረበለትን ፈተና ተቋቁሞ በበግ መስዋዕትነት ችግሩ እንደተፈታለት ሁሉ ህዝበ ሙስሊሙም ሙክት አሊያም ከብት በማረድ የተቸገሩትን በማብላት፣ በማጠጣት ለችግራቸው መድረስ እንዳለባቸው መክረዋል።
ነብዩ ኢብራሂም ለፈጣሪ የነበራቸው እምነትና ፍቅር ፍፁም ነበር። በዚህም የሚወዱት ልጃቸውን እስማኤልን ይዘው ወደ መሰዊያው ሄደዋል። ስለዚህ የእምነቱ ተከታይም በፍጹም ፍቅርና አንድነት ችግረኞችን ለመርዳት መነሳት አለበት። በተለይ ይህንን በዓል ስናከብር እምነቱ የሚያዘውን ማድረግ ላይ ሊተኮር እንደሚገባና ድሃውን በፍቅር ተንከባክቦ ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
በዓሉን የተቸገሩትን በማሰብና በማካፈል በፍቅር ማሳለፍ ሲባል ምዕመኑ በዓሉን ሲያከብርም እምነቱ በሚያዘው መሰረት አቅመ ደካሞችን በማሰብ፣ ያለውን በማካፈልና በማስደሰት መሆን እንዳለበትም ይገልጻሉ። በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢው ጉዳይ አንድነትና ሠላምን ማስጠበቅ ነውና እጅ ለእጅ ለመያያዝ የእምነት መሰረት ጠቃሚ ነውና ለህጉ መገዛት እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ። «በሀገርም ሆነ በውጭ ያለን ሁሉ አንድነታችንንና ሠላማችንን ልንጠብቅ ይገባል» ሲሉም ጥሪያቸውን ያቀርባሉ።
ረዳት ፕሮፌሰር አዳም ካሚል እንደሚናገሩት፤ ይህ በዓል የዝምድናና የድሆች መብት የሚከበርበት ጊዜ ነው። እርስ በርስ የመረዳዳትና ከልብ የመዋደድም ዕለት ነው። ህዝበ ሙስሊሙ በአረፋ ሜዳ ላይ ዘር፣ ቋንቋ፣ አለባበስ፣ ሥልጣን ሳይገድበው በአንድ ልብ ለአምላክ ጸሎት የሚያቀርብበት፤ ምህረትና ይቅርታ የሚጠይቅበትም ልዩ ጊዜ ነው። ከጸሎት በኋላ በቤታቸው ሄደው እርድ ይፈጽሙና ዘመድ አዝማድ ጎረቤት ተጠርቶ በአንድነት ይቋደሱታል። እርዱ ምሳሌነቱ ቁርባን ነው። እናም ይህንን ቁርባን ለብቻ መመገብ በእምነቱ ዘንድ አይፈቀድም። ስለዚህ በተለይም ድሆችን በዚህ ላይ በስፋት በመሳተፍ በዓሉ እንዲከበር ይደረጋል። ምክንያቱም ድሆች በረከት አምጪዎች ናቸው።
የአረፋ በዓል ሁለት ነገሮች ልዩ ያደርጉታል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ለሀበሾች የተለየ አንድምታ እንዳለው ይናገራሉ። የነብዩ መሀመድ ተከታዮችን በመቀበል መልዕክቱን እንዲያስቀምጥና 124ሺ ተከታዮችን እንዲያፈራ ያደረጉት ሀበሾች ናቸው። ይህ ደግሞ ለእምነቱ መሰረት የመሆናቸውን ምሥጢር ይነግረናል።
በሌላ በኩል መሰረታቸው ሀበሻ የሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ክብር ያገኙበት እለት በመሆኑ ሀበሾች ከሌላው በልዩነት ያከብሩታል። ይህ ቀን ለሀበሾች ታሪካዊ ቦታውን ለማየትና በረከት ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ታሪካቸውንም ጭምር ለመረዳት የሚያስችላቸው ነው ።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ፤ ዕለቱ የደስታ ቀን ነው። ማንም እንዲከፋ አይፈቀድም። ስለዚህም
ድሆችም እንዲደሰቱ የማድረጉ ጉዳይ የሁሉም የእምነቱ ባለቤቶች ይሆናል። የተጣሉትም ተታርቀው በደስታ ማሳለፍና የእርቅም ጊዜ ይባላል።
የታላቁ አንዋር መስኪድ አሰጋጅ እና የኢድ በዓሉ የጸሎት መሪ ሼህ ጠሀ ሙሀመድ እንደተናገሩት ደግሞ፤ በእስልምና እምነት ከሚታወቁት ታላላቅ በዓላት አንዱ የሆነው ኢድ አል አድሃ፤ የረመዳን ወር ጾምን ተከትሎ የሚመጣ ሲሆን፤ ለአራት ቀናት የሚከበር ነው። ምክንያቱም ድሆችንም ሆነ ቤተዘመድን ለመጠየቅ በአንድ ቀን አይቻልም። እናም ጊዜውን በደስታና በፌሽታ ለማክበር የእምነቱ መሰረት ይህ ቀን ተቆርጦለታል ይላሉ።
ሼህ ጠሀ እንደሚሉት አረፋ የዕርድ በዓል ነው። አቅሙ ያለው ደካሞችን የሚደግፍበት፤ ድሃው ጠግቦ የሚያድርበት ልዩ በዓልም ነው ፤ አደባባይ ወጥቶ ጸሎትን በማድረግ ከእምነቱ አባቶች በረከት የሚያገኙበት ነው። በአገሪቱ እምነት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋልና ለአንድነትና ለሰላም እንዲሰራ ያበረታዋል። በበዓሉ ቡና ተጠራርቶ በሃይማኖት፣ በቋንቋና በዘር ሳይለያይ በአንድነት የመብላቱ ምሥጢርም ከእንደነዚህ አይነት ልዩ በዓላት የመነጩ ናቸውና ይህንን በማጠንከሩም ዙሪያ ሰፊ አማራጭን እንደሚሰጥ ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 5/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው