. በመረጃ እጥረት እንጂ የመከልከል ፍላጎት እንደሌለ ማህበሩ ገለጸ
አዲስ አበባ፡- የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አገልግሎት ጥሩ ቢሆንም ተገቢውን መረጃ በመስጠት በኩል ችግሮች እንዳሉበት አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ።የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር በበኩሉ ‘’የመረጃ እጥረት ስለሚገጥመን እንጂ ተሳፋሪዎቻችንን መረጃ ለመከልከል ብለን ያደረግነው ነገር የለም’’ ብሏል።
ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ የባቡር ጉዞ ላይ አግኝተናቸው አስተያየቱን የሰጡን አቶ መስፍን አበባው፣ አገልግሎቱ በጀመረበት ወቅት ጥሩ የነበረ ቢሆንም በጊዜ ሂደት ችግሮች እየተፈጠሩና መጉላላት እየደረሰ እንደሆነም ተናግረዋል።
የባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ መስፍን፣ ችግር ተፈጥሮ በሚቆሙበት፣ አንዳንዴም ወደመጡበት በሚመለሱበት ወቅት ስለተፈጠረው ሁኔታ መረጃ የሚሰጣቸው አካል አለመኖሩንና አስተናጋጆችም መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
የባቡር ትራንስፖርቱ ጥሩ ቢሆንም ጀማሪ ከመሆኑ አንፃር ክፍተቶች እንዳሉ የተናገሩት ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ወይዘሮ ሰብለ ድሪባ ፣በተለይም የባቡሩ የፍጥነት አቅም መገደቡን አንስተው ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ በአራት ሰዓት ይደርሳል የተባለው ባቡር እስከ አስር ሰዓት እየፈጀበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ በፊት ዘገየ ቢባል በስድስት ሰዓታት ይደርስ እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ሰብለ፣ አሁን እየደረሰ ያለውን የሥራ ሰዓት ብክነት ለመቀነስ የሌሊት ጉዞ ቢጀመር የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። ሻንጣዎችን የሚጭንና የሚያወርድ ሠራተኛ አለመኖርም ሌላው ችግር መሆኑን አስተያየት ሰጪዋ አንስተዋል።
የተነሱትን ችግሮችና አስተያየቶች ይዘን የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሳርካን አነጋግረናል። የተነሱት ችግሮች መኖራቸውን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለአብነት ከትናንት በስቲያ በኦሮሚያ ክልል ቦርደዴ በሚባል አካባቢ በፀጥታ ችግር ምክንያት የባቡር ሀዲዱ በድንጋይ በመዘጋቱ ባቡሩ ቆሞ እንደነበር ገልፀው፣ መሰል ችግሮች ሲፈጠሩ ጉዳዩ የሚመለከተው የጸጥታ መዋቅሩ ስለሆነ ጉዳዩን አጣርተው እስኪነግሯቸው ድረስ ምድር ባቡር መረጃ እንደማያገኝ ገልፀዋል።
‘’የመረጃ እጥረት ስለሚገጥመን እንጂ ተሳፋ ሪዎቻችንን መረጃ ለመከልከል ብለን ያደረግነው ነገር የለም’’ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ውስጣዊ ችግር ምክንያት አንድም ባቡር ቆሞ አያውቅም፤ ችግሮች የሚፈጠሩት በኃይል መቆራረጥ፣ ህብረተሰቡ ባቡሩን በማገት፣ በጸጥታ ችግሮች እና መሰል ጉዳዮች ነው ብለዋል።
‘’በየትኛውም ዓለም በባቡር አገልግሎት የሻንጣ ጫኝና አውራጅ ተቀጣሪ ሠራተኞች የሉም፤ እኛም ጋር መሰል አገልግሎት አንሰጥም’’ ያሉት ኢንጂነር ጥላሁን፣ ለእያንዳንዱ ተሳፋሪ በህግ የተፈቀደው ከ 10 ኪሎ ያልበለጡ ሁለት ሻንጣዎችን ብቻ ስለሆነና ይህ ደግሞ አጋዥ ያስፈልገዋል ተብሎ ስለማይታመን ተሳፋሪዎች በራሳቸው ይዘው እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
ትላልቅ ሻንጣዎችንና የኮንትሮባንድ እቃዎችን የሚይዙ ተሳፋሪዎች መኖራቸውን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህ አግባብ ባለመሆኑ እና ለእቃ መጫኛ የተዘጋጁ ባቡሮች ስላሉ ከኪሎ በላይ ለሆኑ እቃዎች ይህንን አማራጭ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።
ባቡሩ በሚፈጠሩ የተለያዩ ችግሮች ምክንያት የፍጥነት ገደቡ ውስን በመሆኑ ማታ መድረሱ ለአብዛኛው ተሳፋሪ ባለመመቸቱ የተነሳ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የሚደረገውን ጉዞ በሁለት ባቡሮች ማለትም ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ እና ከድሬዳዋ ጅቡቲ አገልግሎት በመስጠት ማታ ደርሶ የመጉላላቱን ችግር ለመቅረፍ እየሰሩ ሲሆን፣ የማታ ጉዞ ለመጀመር መስመሩ ከኮንትሮባንድ ጋር የተያያዘ መሆኑ አገልግሎቱን ለመስጠት አስቸጋሪ እንዳደረገውም ኃላፊው ገልፀዋል።
ችግሮችን ለመቅረፍ በጥናት ላይ የተመሰረቱ ሥራዎች እንደሚሰሩ የተናገሩት ኢንጂነር ጥላሁን፣ ተሳፋሪዎች የተመቸና አርኪ ጉዞ እንዲኖራቸው በርትተው እየሰሩ ሲሆን ከመነሻ እስከ መድረሻ ምንም አይነት ችግር የማይፈጠርበት የባቡር አገልግሎት ለመስጠት ውጥን እንዳላቸውም ገልፀዋል።
አገልግሎቱ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን ህብረተሰቡ በመረዳት ከአክሲዮን ማህበሩ ጎን እንዲቆምና ለሥራዎች መሻሻል ሁሉም የራሱን ድርሻ እንዲያበረክት ኃላፊው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
751.7 ኪ.ሜ የሚረዝመው የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር እአአ ጥር 1/2018 ሥራውን የጀመረ ሲሆን፣ቻይና ሬልዌይ ግሩፕ ሊሚትድ እና ቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በተባሉ ሁለት የቻይና ኩባንያዎች መገንባቱ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ፣ ነሀሴ 4/2011
ድልነሳ ምንውየለት