ተወልደው ያደጉት በትግራይ ክልላዊ መንግስት መዲና መቐለ ከተማ ሲሆን ያደጉትና ትምህርታቸውን የተከታተሉት ግን በአድዋ ከተማ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዛው በአድዋ ከተማ በሚገኘው ንግስተ ሳባ ትምህርት ቤት ተምረዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በሶሻል ወርክ ዘርፍ አግኝተዋል። በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ በውጭ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ሰርተዋል። ይሁን እንጂ በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ የህዝቡ የድህነት ኑሮ እየተባባሰ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የችግሮቹ ምንጭ ዘውዳዊው የፖለቲካ ስርዓት እንደሆነ በማመናቸው ስርዓቱን ለመጣል ከተደራጁ ወገኖች ጋር ህብረት ፈጠሩ።
በ1968 ዓ.ም አካባቢም ህወሓትን የተቀላቀሉ ሲሆን ድርጅቱ በተለይ የደርግ ስርዓትን ለመጣል ባደረገው ብርቱ ትግል ውስጥ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። በተለይም ሴትነታቸው ሳይበግራቸው የሚያምኑበትን ነገር ያለአንዳች ስጋት በመናገርና ያንኑ ሃሳብ በማራመድ ረገድ በርካቶች በአርዓያነት ያነሷቸዋል። ይህ ቆራጥና ፅኑ አስተሳሰባቸው ታዲያ ብዙ ዋጋ ከከፈሉበት የፖለቲካ ድርጅታቸው ሳይቀር እንዲሰናበቱ ምክንያት ሆኗቸዋል። እሳቸው ግን ዲሞክራሲና ፍትህ የሰፈነባትን ኢትዮጵያ ተገንብታ ማየት ስለነበር ህልማቸው ደማቸውን ካፈሰሰሉትና ህይወታቸውን ከከፈሉበት የፖለቲካ ድርጅታቸው መሰናበታቸው ተስፋ ሳያስቆርጣቸው ከሌሎች ተሰናባች ታጋዮች ጋር በመሆን የዓረናን ፓርቲ መሰረቱ። ስለዛሬዋ የዘመን እንግዳችን ታጋይ አረጋሽ አዳነ እኛ ይህን ያህል ካልን ዘንዳ ስለትግል ህይወታቸው፣ በህወሓት ውስጥ ተፈጥሮ ስለነበረው መከፋፈልና ስለወቅታዊ ፖለቲካ ያሉን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡– ወደ ፖለቲካ ትግል የገቡበትን አጋጣሚ እስቲ በጥቂቱ ያስታውሱን?
ታጋይ አረጋሽ፡– እኔ ወደ ትግል እንድገባ ምክንያት የሆነኝ በህዝቡ ላይ ይደርስ የነበረው የፖለቲካ ጭቆና እና ስር የሰደደው የህዝብ ድህነት ነው። በተለይም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ህዝቡ ላይ የደረሰው ስር የሰደደ ድህነትና ችግር የተፈጠረው ስርዓቱ ፀረ ህዝብ ስለሆነ ነው የሚል አስተሳሰብ በእኔም ሆነ በሌሎች ተማሪዎች ዘንድ እየተስፋፋ ሄደ። በኋላም የሚደረገውን የተማሪዎች እንቅስቃሴ መደገፍ ጀመርኩ። ትምህርቴን አጠናቅቄ ወደ ስራ ዓለም ከተሰማራሁ በኋላም ቢሆን ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ የሄደው የህዝብ ኑሮ ሊቀየር የሚችለው ስርዓቱ ሲቀየር መሆኑን ስለተገነዘብኩና የዚህ ትግል አካል መሆን እንዳለብኝ ስላመንኩኝ በ1968 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ህወሓትን ተቀላቀልኩ።
አዲስ ዘመን፡– ሴት በመሆንዎ ወደ ትግሉ እንዳይገቡ ከቤተሰብ ተቃውሞ አላጋጠምዎትም?
ታጋይ አረጋሽ፡– አስቀድሜ እንዳልኩሽ እኔ ወደ ትግል እንድገባ ምክንያት የሆነኝና ያነሳሳኝ የህዝቡ ሁኔታና ኑሮ ነው። በወቅቱ በተለይም የአደኩበት አካባቢ በርካታ ችግሮች ስለነበሩ ያ ሁኔታ በጣም ያሳዝነኝ ነበር። የሚገርመው ህዝቡ ግን የፈጣሪ ቁጣ አድርጎ ነበር የሚያስበው። እኔ ሃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ በገባሁበት ወቅት ግን የእግዜር ቁጣ ሳይሆን ስርዓቱ የወለደው ችግር መሆኑን ተገንዝቤያለሁ። የእኔ የመታገል ፍላጎት የተፀነሰውም እዚያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው ብዬ ነው የማምነው። በወቅቱ ነፃ የመውጣትና የእኩልነት ጥያቄ እያደገ መጥቶ ነበር። ህብረተሰቡ ለሴቶች የነበረው አመለካከት መልካም የሚባል ባይሆንም በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የነበርን ሴቶች ከወንዶች ባላነሰ መልኩ ለአገራችን ህዝብ ነፃ መውጣት አስተዋፅኦ ማድረግ እንችላለን የሚል ፅኑ እምነት ነበረን። እርስበርስ እንማማርና እንደጋገፍ ስለነበረ እዚያ እያለሁ ነው ፅናትና የመታገል መንፈሴ እየጎለበተ የሄደው።
ቤተሰቦቼ ሃይማኖተኞች ስለነበሩ ፈጣሪን እንድፈራና ማህበረሰቡን አክብሬ እንዳድግ ብርቱ ጥረት አድርገዋል። አስተዳደጌ ምንም እንኳ በመንፈሳዊ ትምህርት የታነፀ ቢሆንም በሴቶች አይሞከሩም የሚባሉ ነገሮች ሁሉ እደፍር ነበር። ብስክሌት እነዳለሁ፤ ዋና እዋኛለሁ፤ ከቀለም ትምህርት ውጭ እንደ ታይፕ የመሳሰሉትን ስልጠናዎችን ወስጃለሁ። ወላጆቼ ይህንን የተለየ ፍላጎቴን ያውቁ ስለነበር ብዙም ተፅእኖ አያደርጉብኝም ነበር። ይሁንና በምሰራበት ድርጅት ውስጥ ከአዲስ አበባ ወደ ሽሬ በመቀየሬ ግን ደስተኛ አልነበሩም። ምክንያታቸው ደግሞ በወቅቱ ሽሬ ወሮበሎች የሚበዙበት አካበቢ ነው ተብሎ ይታመን ስለነበር እንዳልጎዳ በመስጋት ነው። ከዚሁ ውጭ ግን አደርገው ስለነበረው ፖለቲካዊ ትግል እምብዛም እውቀቱ ስላልነበራቸው በይፋ አልተቃወሙኝም ነበር።
አዲስ ዘመን፡– በትግል ወቅት እንደ ሴት ያጋጠመዎት ፈታኝ ሁኔታዎችን እስቲ ይጥቀሱልን?
ታጋይ አረጋሽ፡– እንዳልሽው ጦርነት ለሴት ቀርቶ ለወንድም ቢሆን በጣም ፈታኝና አስቸጋሪ ነው። ሴት መሆን በራሱ ራሱን የቻለ ሌላ ችግር እንደሚኖረው ይታወቃል። ይሁንና እኔም ሆንኩ ሌሎች ሴት ታጋዮች ወደ ትግሉ ከመግባታችን በፊት ከሴትነት ጋር የተሳሰሩ ችግሮች እንደሚያጋጥሙን አውቀነው እና ራሳችንን አሳምነን ነው የገባነው። ለዚህም ነው ትግሉ ውስጥ ችግሮች ሲያጋጥሙንም እንደ ትልቅ ጉዳይ የማንወስደው የነበረው። ከዚያ ይልቅም ያንን ችግር በተለያየ መንገድ ለመፍታት ነበር ጥረት የምናደርገው። እንደገባንም የሴት ታጋዮች ኮሚቴ ነው የመሰረትነው። ይህ ኮሚቴ በአንድ በኩል የወንዶችን ትምክህት ለመታገል ሁለተኛ ከእኛ ተፈጥሮ ጋር የተሳሰሩ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንዳለብን ልምዶቻችንን ለመለዋወጥ እድል ፈጥሮልናል። በመካከላችን የመንፈስ መዳከም እንዳይፈጠር እየተወያየን እንደጋገፍ ነበር።
ሴት ሆነሽ ጦር ሜዳ ውስጥ መገኘት በራሱ ፅናትን ይፈትናል። ከነገ ዛሬ በአውሮፕላን እደበደባለሁ የሚል ስጋት ስላለ ጥሩ እንቅልፍ መተኛት እንኳ አይታሰብም ነበር። ረሃብ ፣ድካም፣ ተራራ፣ ሸለቆ መውጣትም ሌላው የጦር ሜዳ አስከፊ ባህሪ ነው። ይህም ቢሆን ግን ዋና ትኩረታችን የነበረው ችግሩን ተቋቁመን ለውጥ ማምጣት የሚል ነበር። ለነገሩ ህይወትን ከማጣት በላይ ፈታኝ ነገር አለ ተብሎ የሚጠቀስ ነገር የለም። ግን አላማ ይዤ ስለምሞት ሌሎች ያንን አላማ ይዘው ይከተሉኛል። ስለዚህ ህይወቴንም እስከ መስጠት አስቤና ተዘጋጅቼ ስለወጣሁ ከዚያ በታች ያሉትን ችግሮች እንደችግርም አልወስዳቸውም ነበር።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ፈታኝ የትግል ህይወት በኋላ ኢህአዴግ የአገሪቱን የመንግስት መንበር ሲረከብ ከከፈሉት ዋጋ ልክ ቦታ ተሰጥቶኛል ብለው ያምናሉ?
ታጋይ አረጋሽ፡– ከትግል በኋላ የማዕከላዊ ኮሚቴው አባል ነበርኩ። ለነገሩ በትግሉ ወቅትም የማዕከላዊ ኮሚቴው አባል ነበርኩ። በሽግግሩ ወቅትም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር በመሆን አገልግያለሁ። ከዚያም ደግሞ የምክር ቤቱ ጸኃፊና ስራ አስፈፃሚ ነበርኩ። በ1992 ዓ.ም ምርጫ ተወዳድሬ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆኛለሁ። በኋላም በሚኒስትር ደረጃ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሆኜ ሰርቻለሁ። ሌሎች ሴት ታጋዮችም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ ቢኖሩም እንደ እኔ ለረጅም ጊዜ በምክር ቤቱ የቆየ ግን አልነበረም። በእርግጥ ይህንን ሁኔታ በደፈናው ስታይው ወንዶችን የማስቀደም አስተሳሰብ እንደነበር እሙን ነው። ሴቶችን የመፍራት ነገር ጥቂት በማይባሉ አመራሮች ዘንድ ይስተዋልም ነበር። በተለይም ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ጠንካራ ሴቶች ብንበዛ የሚመጡትን ጥያቄዎች የመፍራት እና በወንዶቹ በኩል እውነታውን ለመጋፈጥ ዝግጁ ያለመሆን ነገር ነበር።
ይህም ሁኔታ በአጠቃላይ የሚያሳየው በድርጅቱ ውስጥ የነበረው ፖለቲካ ጥርት ያለ እንዳልነበርና ትክክለኛ ዲሞክራሲ አለመኖሩን ነው። ይልቁንም የኢህአዴግ በተለይም የህወሓት አመራር የሚፈልገውን እንጂ የማይፈልገውን ሰው አያስገባም ነበር። በእነሱ አይን ጥሩ የሚሏቸውን ሰዎች ነበር እየመረጡ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሚያደርጉት። በወቅቱ ወጣ ያለ ሃሳብ የሚያመጣ ሰው አይፈለግም ነበር። የሚገርመው ሃሳብሽ ከአመራሩ ጋር የማይስማማና የማይደግፈው ከሆነ ሌላውም ተሳታፊ ችላ የሚልበት ሁኔታ ነበር። ስለዚህ የፀረ ዲሞክራሲው ልምምድ የነበረ ቢሆንም በጊዜ ሂደት እየባሰበት ነው የመጣው። በዚያ ሂደት ብዙ ሴቶች አቅም ቢኖራቸውም ስላልተፈለጉ ብቻ ሳይመረጡ የቀሩ አሉ።
አዲስ ዘመን፡– በ1993 ዓ.ም ለነበረው የድርጅቱ መከፋፈል የእርሶ ሚና ምን ነበር?
ታጋይ አረጋሽ፡– በ1993 ቱ የህወሓት መከፋፈል ዋነኛ ምክንያት በድርጅቱ የተደራጀ ቡድን ሳይሆን ልዩነት ያለው አስተሳሰብ መፈጠሩ ነው የሚል እምነት አለኝ። የተወሰነው ክፍል የተሟላ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ነበረው ለማለት ባልደፍርም በትግል ጊዜ የያዝናቸው እሴቶችና ተስፋዎች ነበሩ። እነዚያ እምነቶች ደግሞ ትግሉን ስንጀምር ዲሞክራሲ፣ ፍትህና ነፃነት የሰፈነባትን አገር የመፍጠር ዓላማን እውን ማድረግ ነው። ከአንድ ቤት አምስት ልጅ እየወጣ ትግሉን ያለምንም ማመንታት የተቀላቀለውና ያ ሁሉ ህዝብ የተሰዋውም ለዚሁ አላማ ብሎ ነው። ስልጣን ላይ ከመጣን በኋላ ግን ያንን መርሆ የመሸራረፍ ነገር እየሰፋና እያደገ መጣ። በሁለት ወገን በኩል የነበሩት የአስተሳሰብ ልዩነቶች እያደጉ መጡ።
በወቅቱ የነበረው አጀንዳ ቦና ፓርቲዝም የሚባል የፈረንሳይና የጀርመን ታሪክ መነሻ ተደርጎ ኢትዮጵያ ውስጥ «ቦና ፓርቲ» ስርዓት ለመመስረት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ተብሎ ነው ትንታኔ የመጣው። የቦና ፓርቲዝም ስርዓትን የሚያመለክተው ደግሞ እኛን ነው። የሚገርመው ይህ ስርዓት ኢ-ዲሞክራሲ የሆነ፥ ሙሰኛ፥ ሌሎቹን ጨፍልቆ ወደ ስልጣን የሚመጣ ሃይል ነው ተብሎ ተንትኖ እኔና ሌሎች የተወሰኑ ወገኖቼ ይህንን ስርዓት ለማምጣት እንደምንፈልግ ተደርጎ ነው የቀረበው። ይህ ስርዓት እንግዲህ የ19ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ የተከሰተ ታሪክ ነው።
በዚያን ጊዜ ታዲያ ይህንን ስርዓት ከአገራችን ሁኔታ ጋር የሚያስተሳስረውና ሊመጣ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ አልነበረም። በኛ ላይ የተፈጠረው የውሸት ታሪክ ነው። ይህንን እውነታ ግልፅ ለማድረግ ያህል ለምሳሌ የቦና ፓርቲዝም ስርዓት አለ ከተባለ የላብ አደሩና በቡርዣው ያለው ግጭት በጣም በከረረ ሁኔታ መታየት አለበት። ከታየ በኋላም እነዚህ ሁለት አካላት ተጋጭተው ተጋጭተው አንዱ ለአንዱ ማሸነፍ ሲያቅተው ቦና ፓርቲዝም አስተሳሰብ ያለው ሃይል እነሱን ለማስታረቅ ሞክሮ ስልጣን ለመያዝ ጥረት ሲያደርግ ነው ይህ ስርዓት አለ ለማለት የሚደፈረው።ይህ ሁኔታ ደግሞ በአገራችን አልተፈጠረም፤ አልነበረም።
በወቅቱ ያልተፈጠረ ነገር ትንታኔ አድርገው ሲያቀርቡ ከህወሓት አባላት ውስጥ የተወሰነው አካል አደናግሮ መመታት የሚፈልግ ሃይል መኖሩን ደመደምኩ። ደግሞም ጥያቄዎች በሚጠየቁበት ጊዜ ዛሬ የተመለሰው ነገር ነገ ደግሞ ሌላ ሆኖ ይቀርባል። በውይይቱ ወቅትም የውሸትና የማጭበርበር ነገር ይታይ ነበር። ከውይይቱ በኋላም በሃሳብ አሳምኖ ድምፅ ለማግኘት ጥረት ከማድረግ ይልቅ ድምፅ ለማግኘት ሲባል ሰዎች እየተጠሩ ቤተመንግስት የሚሄዱበት ሁኔታ ነበር። ይህንን ሳይ ህወሓት ጨርሶ አልቆለታል ብዬ ነበር የደመደምኩት።
በድለላ ድምፅ ለመግዛት እየሞከሩ መሆኑንም አመንኩ። ስለዚህ እንደዚህ ከሆነ በመጀመሪያ ስራዬን ትቼ ትግሉን የተቀላቀልኩበት ዓላማ መንገዱን መሳቱን ተገነዘብኩ። ስለዚህ ከድርጅቱ ጋር የምቀጥልበት ምንም ምክንያት የለኝም ብዬ አመንኩ። በዚህ እምነት ውስጥ እያለሁ እነሱ ራሳቸው ተቻኩለው እኔን ጨምሮ ለ13 አባላት የማገጃ ደብዳቤ ሰጡን። እኔ ለነገሩ እነሱ ባይሉኝም አዝማሚያው ስላላማረኝ የሚመስለኝን ነገር በአገኘሁት አጋጣሚ ስናገር ነበር። ከአሁን በኋላ ህወሓት አበቃለት የሚል ድምድሜ ላይም ደርሼ ነበር። ቢያግዱኝ ባያግዱኝም ደንታ አልነበረኝም።
አዲስ ዘመን፡– በወቅቱ በዚያ ሁኔታ ከድርጅቱ መሰናበትዎት ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ?
ታጋይ አረጋሽ፡- ተገቢማ አይደለም! ትክክልም ህጋዊም አይደለም። መደረግ የነበረበት በድርጅቱ ህገ ደንብ መሰረት ነበር። በህገ ደንቡ መሰረትም ማዕከላዊ ኮሚቴው ውስጥ ከነበርነው 30 አባላት ውስጥ 2/3ኛው ከተገኘ ነው ውሳኔ የሚወሰነው። በወቅቱ ግን ሁለቱ አስቀድመው ወጥተው ነበርና 28 ነበር የቀረነው። 15 በ13 ስንከፋፈል 2/3ኛ መሙላት አልቻልንም ነበር። ይህ በሆነበት ሁኔታ እኛን ማገድ የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ አልነበራቸውም። ስለዚህ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ነው የታገድነው የሚል እምነት አለኝ። ከማገድ ይልቅም ማዕከላዊ ኮሚቴው አብሮ መስራት ሲያቅተውና አብላጫ ድምፅ ሲያጣ አስቸኳይ ጉባኤ መጥራት እና የሁለቱም ቡድኖች ሃሳብ ተሰምቶ ውይይት መደረግ ነበረበት።
ከዚያም ያ አስቸኳይ ጉባኤ የወሰነው ውሳኔ ይፀናል። በወቅቱ ይህ እንዲሆን ጠይቀን ነበር፤ ነገር ግን እነሱ የማያዋጣቸው ሆኖ ስላዩት አገዱን። ስለዚህ በሁለቱም መንገድ የተፈፀመብን ነገር ህጋዊም ዲሞክራሲያዊም አልነበረም። በተለይ ለእኔ መታገድ ምክንያት ነው ብዬ የማስበው ሁልጊዜም ቢሆን የማምንበትን ነገር በግልፅና በድፍረት የምናገር መሆኔ ነው። በትግል ወቅትም ቢሆን አመራሩ ስላለው ብቻ የማላምንበትን ነገር አልቀበልም ነበር።
አዲስ ዘመን፡– ህወሓት በብሄር የተደራጀ ፓርቲ እንደመሆኑ ከአመራሩ ያፈነገጠ ሃሳብ መሰንዘር ብሄርን እንደመካድ ተደርጎ በሚቆጠርበት ሁኔታ ውስጥ የእርስዎ በድፍረት የተለየ ሃሳብ በማራመድዎ ከህዝብ መገለል አላጋጠሞትም? አሁንስ በእርሶ ልክ የማያምኑበትን በድፍረት የሚናገሩ አመራሮች አሉ ብለው ያምናሉ?
ታጋይ አረጋሽ፡- አሁን ያለው ሁኔታ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር የተሳሰረ ነው። ለውጡ ሲመጣ ፖለቲካው ራሱ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። መቶ በመቶ እንኳ ባልልም አብዛኞቹ መገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ ጥሩ ያልሆነ ፖለቲካ ይራመድ ነበር። ለምሳሌ ባነሳልሽ የትግራይ ህዝብንና ህወሓትን ለይቶ ያለማየት ነገር ነበር። ሌላው ህዝብ ግን ለ27 ዓመት ሲሰቃይ የትግራይ ህዝብ ልክ ተጠቃሚ እንደሆነ እና ከዚህ እህል እየተጫነ እንደሚሄድለት ይነገር ነበር። በጣም የበለፀገና ከድህነት የወጣ ተደርጎ የሚቀርብበት ሁኔታ ነበር። ከዚህ አልፎም የማስፈራራት ፖለቲካም ነበር። በተለይም የወልቃይት ነገር ሲነሳ ህገመንግስቱ በሚፈቅደው መንገድ ሳይሆን ህግ ተጥሶም ቢሆን መሬታችንን እናስመልሳለን የሚል አይነት ዛቻዎች ነበሩ።
እነዚህ ፖለቲካዎች ደግሞ ለህወሓት ጥሩ እድል ፈጥሮለታል። ለትግራይ ህዝብ ደግሞ ስጋት ነው የፈጠረበት። ይህ የጅምላ ፍረጃ ህዝቡ እኛና ህወሓትን ለምን ለይተው አያዩንም የሚል ጥያቄም እንዲያነሳ ምክንያት ሆነ። ልክ እንደሌላው ህዝብ ላለፉት 27 ዓመታት ሲጨቁኑንና አይተውን የማያውቁ፤ ኑሯቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ፤ አዲስ አበባንና ሌሎችን አካባቢዎች ሲያለሙ በትግራይ የተጀመረውን ልማት ለማፍረስ የሞከሩ አመራሮች ልክ እኛን እንደጠቀሙ አድርጎ ለምን ይነገራል የሚል ስሜት ፈጥሯል። በወቅቱ ትላልቅ በሚባሉ ባለስልጣናት ሳይቀሩ በህዝቡ ላይ ስጋት የሚፈጥሩ መልዕክቶች ይተላለፉ ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ ሌላ አማራጭ የሚሆን ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት በትግራይ አለመኖሩ ለህወሓት ፖለቲካ መጠቀሚያ እንዲሆን በሩን ከፍቶለታል ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ በዚህም በዚያም ያለው የኢትዮጵያ ምሁራን እኛን ለማጥቃት የዘመቱና ከህወሓት ለይተው የማያዩን እስከሆነ ድረስ ያለን አማራጭ ከህወሓት ጎን መቆም ነው የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል። ለጊዜውም ቢሆን ህወሓትን መግፋት የለብንም የሚል እምነት እንዲይዝም አድርጎታል። ስለዚህ ይህ ሁኔታ ስጋት የፈጠረው ነው የሚል እምነት አለኝ። ይሁን እንጂ የትግራይ ህዝብ የህወሓትን ማንነት አጥቶት አይደለም። ከማንም በላይ ያውቀዋል፤ የተቸገረበት የተሰቃየበት ድርጅት በመሆኑ ማለቴ ነው።
ባለስልጣናቱ ከዚህ ሸሽተው ሲሄዱ እኮ ህዝቡ ምን ሊያደርጉ ነው የመጡት ብሎ ነበር። መንግስት ተጠያቂ ሊያደርጋቸው ሲል ለምን ሸሽተው ወደ እኛ ይመጣሉ? የሚል ጥያቄም ያነሱ ነበር። ለምን መደበቂያ ያደርጉናል? የሌቦች መደበቂያ አንሆንም እስከማለትም ደርሶ ነበር። በነገራችን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መቀሌ በሄደበት ወቅት የነበረው መንፈስ እኮ በጣም የሚያስደስት ነበር። ህዝቡ በወቅቱ ተስፋ እና የመግባባት መንፈስም ነበረው። ከዚያ ከተመለሰ በኋላ ፖለቲካው እየተበላሸ ነው የሄደው። በእኔ እምነት ፖለቲካው የትግራይ ህዝብን አላቀፈም።
ያ የፖለቲካ ሁኔታም ባለስልጣናቱ መሸሸጊያ እንዲኖራቸው አደረገ። አሁንም ቢሆን የትግራይ ህዝብ ትዕግስተኛ ሆኖ እነሱን ተሸክሞ ቁጭ ይበል እንጂ የሚሉትን ፖለቲካ ይቀበለዋል ማለት አይደለም። የህወሓት አንዳንድ አባላት የሚያሰራጩትና ህዝብ ለህዝብ የሚያጣላውን ፕሮፖጋንዳ፥ የመነጠል ጥያቄ የህዝቡ ጥያቄ አይደለም። የተወሰኑ ምሁራን ነን ባዮች (ኤሊቶች) አሉ። ከመሪዎቹ ጋር ተሳስረው ያደጉና ሃብታም የሆኑ ሰዎች እንገንጠል የሚለውን ሃሳብ ሊያራምዱ ይችላሉ። በእኔ እምነት እንገነጠላለን የሚለው ሃሳብ እነሱ ለማስፈራሪያነት የሚጠቀሙበት መንገድ ነው። ይሁን እንጂ የትግራይ ህዝብ የመገንጠል ሃሳብ አስቦም አያውቅም ፍላጎትም የለውም። የሚጯጯሁት ግን እዛ ያሉት ባለስልጣናትና ምሁራን ናቸው።
ደግሞም ህወሓት በትግራይ ህዝብ ተደግፏል የሚባለው ነገር አልቀበለውም፤ አልተደገፈም። የህዝቡ አስተሳሰብና ፍላጎት የሚሰማው የሌለ ሆኖ እንጂ እውነታው ይህ ሆኖ አይደለም። ምክንያቱ ደግሞ መገናኛ ብዙሃኑን በሙሉ የተቆጣጠሩት እነዚህ አካላት ብቻ መሆናቸው ነው። በእርግጥ እነሱ የሚሉትን አጀንዳ የሚያራምድ ሃይል አለ። ይህ ሃይል ግን ተጠቃሚ ነኝ የሚለውና ስሜት የገዛው የወጣት ቡድን ነው። የተወሰነው ደግሞ ስራ ፈት የሆነና ገንዘብ ሰጥተን እናደራጃለን እያሉ የሚደልሉት ምስኪን የህብረተሰብ ክፍል ነው። ስለዚህ ህወሓት በትግራይ ህዝብ የተደገፈ ነው ብሎ መደምደም ስህተት ነው። ተደብቀው እየኖሩ ነው የሚለው ትክክል ነው።
የትግራይ ህዝብ ግን የህወሓትን አመራሮች የተሸከማቸው ግን ሌላ አማራጭ የለም የሚል ስጋት ስላለው ነው። ያ ስጋትም በኢትዮጵያ ከፍተኛ አመራሮች ደረጃ ትልቅ ሃይል እንደሚፈጥር፤ መተማመን እንዲፈጥር የተደረገበት ሁኔታም የለም። አሁን አሁን ይሻላል እንጂ እንዳውም እነዚህ አክቲቪስቶች የሚባሉት ሁሉ ፀረ ትግራይ አስተሳሰብ በስፋት ያራምዱ ነበር። እናም ይሄ ህዝብ ምን ያድርግ ታዲያ? አማራጭ የተደራጀ ሃይል የለውም፤ እንዳይኖረው ደግሞ ዲሞክራሲው ልክ እንደ መሃል አገር የተንሰራፋበት አይደለም። ህዝቡን በነፃነት እየኖረ አይደለም። ታፍኖ በስጋት ውስጥ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡– ከህወሓት ከተሰናበቱ በኋላ በቀጥታ ዓረናን ከሌሎች የትግል አጋሮች ጋር ለመመስረት ምን አነሳሳዎት?
ታጋይ አረጋሽ፡– ከህወሓት ከተገለልን በኋላ ዝም ብለን መቀመጥ እንደሌለብን አሰብን። አገሪቷ ውስጥ የነበረው ችግር የቆየና የደነደነ እንደሆነ ተማመንን። እኛ ከወጣንም በኋላ ድርጅቱ በአጠቃላይ የአንድ ሰው ነው የሆነው። ይህ የአንድ ሰው ድርጅት የመሆን አካሄድ ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን ተደምሮ የመጣ መሆኑን እንገምግም ብለን የተወሰነ ያለፍንበትን መንገድ ገምግመናል። በተለይም ከዲሞክራሲ አንፃር፥ በማህበራዊ ስራችን፥ የኢኮኖሚ ስራችን አኳያ የነበሩ ችግሮችን ለመገምገም ሞከርን። ከዚህ በፊትም ታግለናል፤ የታገልነው ግን ቀና ስርዓት ይመጣል ብለን ነው፤ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በሰላም ተመለስን እንጂ ህይወታችንንም ለመሰዋት ነበር የሄድነው። ስለዚህ ይሄ መንግስት ከሰማን ሃሳባችንን በተለየ መንገድ ማቅረብ አለብን ብለን ተነሳን። በዲሞክራሲ፥ በፍትህ፥ በመደራጀት ነፃነት በመናገር ነፃነት እና አስተዳደራዊ ችግሮችን በሚመለከቱ ያለንን ሃሳብ እንግለፅ ብለን እንቅስቃሴ ጀመርን።
በፓርቲ ደረጃ ከመደራጀታችን በፊት ግን «ህዝባዊ» የሚባል ጋዜጣ ማሳተም ጀምረን ነበር። በዚህ ጋዜጣ ታዲያ በ17 ዓመት የትግል ሂደታችን ብሎም መንግስት ከተመሰረተ አስር ዓመት በዚህ ሂደት የነበሩ የምንላቸውን ጉድለቶች እየፃፍን እናወጣ ነበር። ይህንን ያደረግነው አስቀድሜ እንዳልኩሽ አንድም ያለውን ጉድለት ህዝቡ እንዲያውቀው ለማድረግ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ህወሓት የሚማር ከሆነ ጉድለቶችን አይቶ እንዲያስተካክል ለማድረግ አልመን ነበር።
በተጨማሪም ጋዜጣው ህዝቡን ለማስተባበር ይረዳናል ብለን ነበር ያሰብነው። ይሁንና ጋዜጣው እስክ 1997 ዓ.ም ድረስ እየፃፈ ከቆየ በኋላ ታገደ። እናም ጋዜጣው ከታገደ በኋላ በቀጣይ ምን ማድረግ እንደሚገባን መከርን። መደራጀትና ያለንን ሃሳብ እንዳማራጭ ማቅረብ እንዳለብን እምነት ያዝን። ይህም ሃሳቡን ህዝቡ እንዲያውቀው ለማድረግ ያስችላል ብለን አሰብንም በ2002 ዓ.ም አረናን አቋቋምን። በምርጫ ወቅትም ለህዝቡ አንድ አማራጭ ሆነን ለመቅረብ አቅድን ስንሰራ ነበር።
አዲስ ዘመን፡– ዓረና ከተመሰረተበት አላማ አንፃር በትግራይ ክልል ምን ያህል ውጤታማ ነው ብለው ያምናሉ? ለህዝቡስ አማራጭ ሆኖታል ወይ ?
ታጋይ አረጋሽ፡- እንግዲህ ዓረና ከተመሰረተ ወዲህ በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል። በ2002 ዓ.ም ምርጫም ተሳትፏል። ግን እንደሚታወቀው ትግራይ ውስጥ መስራት በጣም አስቸጋሪ ነው። አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ለመስራት የማይቻል ነው። ምክንያቱም ህወሓት ከትጥቅ ትግል ጊዜ ጀምሮ የኖረና አደረጃጀቱን እና ሰንሰለቱን እስከ ጎጥና ቀበሌ ድረስ የዘረጋ ድርጅት ነው። በርካታ አባላትና ደጋፊዎች አሉት። ሚሊሻዎቹም የእነሱ ታጣቂዎች ናቸው። ህወሓት ደግሞ ከመጀመሪያ ጀምሮ ትግራይ ውስጥ ሌላ ድርጅት መሸከም አይችልም የሚል እምነት የነበረው ድርጅት ነው።
በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ በሚዲያ እየወጡ ሌላ ድርጅት መሸከም አይችልም የሚል ሃሳብ ሲዘረጉ የነበረበት ሁኔታ ነበር። አማራጭ ያለው ድርጅት ወደ ህዝብ መቅረብ የለበትም ብለው ወሰነውም ነበር። እኛንም የሰማዕታትን አጥንት ረግጠው ነው የወጡት፤ ከትምክህተኞች ጋር የተሰለፉ ናቸው እያሉ እንድንገለል ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር። ህዝቡ ግን እንደ አስተሳሰብ ከህወሓት ሌላ አማራጭ ድርጅት ቢኖር ምንም ጉዳት እንደሌለው ያምን ስለነበር የእነሱን ሃሳብ አልተቀበለም። እኛ ስንደራጅ አማራጭ ድርጅት እንዲኖር ህዝቡ ይፈልግ ስለነበርም ድጋፉን ወዲያው ነው የሰጠን።
እንቅስቃሴያችንን ስንጀምር ግን ህወሓቶች በጣም አጥቂ የሆነ አካሄድ ነበር የተከተሉት። በየገጠሩ ያሉ አባሎቻችን ማሰር፣ መደብደብ፣ ማሰቃየት፣ ከዚያም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲጣሉ ማድረግ፣ ከማህበረሰቡ እንዲገለሉ ማድረግ ጀመሩ። ስብሰባ በምናካሂድበት ወቅትም ድንጋይ ይወረውርብን ነበር። ፖሊሶች እየተመታን መሆኑን እያወቁ ህገወጦቹን ከመከልከል ይልቅ እናንተ ራሳችሁ ናችሁ ከተማውን የምትረብሹት የሚል ምላሽ ነበር የሚሰጡት። ለምሳሌ እንኳን ባነሳልሽ በ2002 ዓ.ም ምርጫ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በአድዋ በምወዳደርበት ጊዜ ሶስት ጊዜ ስብሰባ ለማድረግ ብንሞክርም የከተማ ዱሪዬዎችና ሱሰኞችን አደራጅተው ወደ ስብሰባው እንዲገቡ ያደርጉቸው ነበር።
ስብሰባው ልክ ሲጀመር ጠብቀው ይረብሻሉ፤ ይቃወማሉ፤ ይበጠብጣሉ። ከተሰብሳቢው ጋር መደማመጥ ሳንችል ስንቀርና ስብሰባው ሲታወክ ፖሊሶች ቆመው ነበር የሚያዩት። ስለዚህ እስካሁንም ድረስ ቢሆን ትግራይ ውስጥ የምንቀሳቀሰው እንደሚገድሉን አምነንን እንጂ ዲሞክራሲ ኖሮ እና ህዝቡን አግኝተን የምንፈልገውን ሃሳብ እናስተላልፋለን ብለን አይደለም። ስለዚህ ዓረና ከፍላጎቱ አንፃር የሚገባውን ያህል ሰርቷል ማለት አይቻልም። የሚያሰራው አካባቢዎ ሁኔታ የለም። ለእኛ አሁንም ትግል ውስጥ ነን፤ አራት ወጣቶች ተገድለውብናል። በርካቶች ቆስለውብናል። ስለዚህ አሁንም ገና ትግል ውስጥ እንዳለን ነው የሚሰማኝ።
አዲስ ዘመን፡– አሁን ከለውጡ በኋላስ ቀንሷል?
ታጋይ አረጋሽ፡- በፍፁም አልቀነሰም፤ በቅርቡም እንደርታ ላይ እንደምታስታውሱት ቤት ለፈረሰባቸው ሰዎች የእኛ አባላት ፍትህ እንዲሰጥ በመጠየቃቸው ምክንያት ታስረዋል። የተወሰኑት አባሎቻችን ላይም ድብደባ ደርሶባቸው ሆስፒታል ቢገቡም ከሆስፒታል በኋላም አስረዋቸዋል። ተምቤን ላይም ወጣቶቻችን የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እየተከታተሉ ያስሯቸዋል ያንገላቷቸዋል። በአጠቃላይ በመላው ትግራይ እኛ እንደልብ እንዳንቀሳቀሳቅ ተፅእኖ ያደርጉብናል። እንዳውም ብሶባቸዋል በሚባል ደረጃ ላይ ነው አሁን ያለው። የሚገርመው የዛሬ ዓመት ከተቃዋሚዎች ጋር ለመወያየትና አብሮ ለመስራት እንደሚፈልጉ ባለስልጣናቱ ሲናገሩ ነበር።
ከዚያ በኋላ ግን የወልቃይትና የራያ ጥያቄ ሲበዛ ህዝቡን «ይኸው መጡባችሁ»፤ እኛንም «ባንዳዎች ናቸው» እያሉ ይፈርጁን ጀመር። እናም ትግራይ ውስጥ ምንም አይነት ለውጥ የለም። እንዳውም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ተፅእኖው እየባሰ ነው የመጣው። ሰው በቀብር ላይ እንኳ እንዳይገኝ ማድረግ ኢ- ዲሞክራሲ ብቻ ሳይሆን ኢ-ሰብአዊ ተግባር ነው። ህወሓት በአሁኑ ወቅት በጭፍን እየሄደ ነው ያለው። ህዝቡም መተንፋሻ አጥቷል። ግን ደግሞ በየቦታው ተቃውሞ አለ። የመብት ጥያቄ አለ፤ የአስተዳደር ችግሮች ጥያቄዎች ቢኖሩም ህዝቡ ጆሮ የሚሰጠው የለም።
አዲስ ዘመን፡– ከለውጡ ጋር ተያይዞ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ እንደቀድሞ በጋራ የመስራት ነገር እየጠፋ መጥቷል፤ በተለይ ህወሓት ለውጡን የማይደግፍ በሚመስል ሁኔታ በተለያየ ጊዜ አቋሙን ሲገልፅ ይደመጣል፤ ይህ ሁኔታ በእርሶ እምነት ምንን ያሳያል? ምንስ ይዞ ይመጣል የሚል ስጋት አለዎት?
ታጋይ አረጋሽ፡– በእኔ እምነት ከመጀመሪያውም ለውጡ በትክክለኛ መንገድ የመጣ አይደለም። ይህም ማለት ህዝቡ መብት ተሰጥቶት፣ ነፃና ግልፅ ሁኔታ ተፈጥሮ ፣ መርጦ ያስቀመጠው ለውጥ አይደለም። በራሳችን ውስጥ የተፈጠረ ለውጥ ነው። ይህም ሆኖ ግን ለውጡ ሲመጣ መጀመሪያ ላይ ተስፋ ተፈጥሮ ነበር። መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማ ቀርበው ሲናገሩ የተናገሩት ንግግር ለብዙ ህዝብ ተስፋ የሚሰጥ አይነት ንግግር ነበር። እናም በህዝቡ ዘንድ ባሉት መሰረት ለውጡ እየተፈጠረ ቢያንስ ነፃና ግልፅ እኩል ምህዳር ተፈጥሮ ህዝቡ የሚፈልገውን ምርጫ በማካሄድ ወደ ስልጣን የሚያመጣበት ሁኔታ ይኖራል የሚል እምነት ነበር። ግን በሂደት ፖለቲካው እየተበላሸ መጣ።
አዲስ ዘመን፡– ግን እኮ ገና ምርጫ ተካሂዶ ውጤቱን አላየንም፤ እናም ይህን ለማለት አልቸኮሉም?
ታጋይ አረጋሽ፡- ምርጫው ባይካሄድም ከዚያ በፊት መደረግ የሚገባቸው ተግባራት እየተከናወኑ አይደለም። አሁን የመጣው ኃይል ቢያንስ ይህንን ሁኔታ እያመቻቸ መሄድ ይጠበቅበት ነበር። በተለይ ነፃና ገለልተኛ ስርዓት መፍጠር አጭር ጊዜ የሚጠይቅ ባለመሆኑ ያንን ለመፍጠር የሚደረገው እንቅስቃሴ ብዙም ተስፋ የሚሰጥ አይደለም። ህዝቡን ወሳኝ ማድረግ ካልተቻለ አሁንም ቢሆን ችግሩ አይፈታም። በዚያ ሂደት ያለመጓዙ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካው ተካረረ።
ሁሉም የየራሱ አጀንዳ መፍጠር ጀመረ። ለምሳሌ የትግራዩ ኃይል ትግራይን ከብቦ እንደ አንድ ግዛት የማድረግ ዝንባሌ ሲታይበት የአማራ ክልል ኃይልም የራሱን አስተሳሰብ የተካረረ ፖለቲካ የማራመድ አካሄድ ያዘ። በኦሮሚያ አካባቢም የማፈናቀል ችግሮች እየተፈጠሩ መጡ። ማዕከላዊ መንግሥቱና ኢህአዴግ እንደ ድሮው ጠንካራ ሆኖ መምራት ሲገባው የየራሱን ተራራ ይዞ የመጯጯሁ ነገር ነው የተፈጠረው። ይህ ሁኔታ ለእኔ በጣም አስጊ ሁኔታ ይፈጠራል። አገሪቱን ወዲህና ወዲያ የመጎተት ነገር ይታያል። ይህም አደጋ ነው።
በመሆኑም ኢህአዴግ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። በተለይም እርስ በርሱ ከመጋጨት ወጥተው ቢያንስ በአገር አንድነትና ሰላም ላይ ሊግባቡ ይገባል። ማዕከላዊ መንግሥቱም እነዚህን ኃይሎች መቆጣጠር ባይችልም እንኳ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሊያሳምናቸው ይችላል። ኑ እና አገር እናረጋጋ አገር ሰላም እናድርግ ብሎ ቢጠራቸው ይተባበራሉ የሚል እምነት አለኝ። አገሩን የሚወድ ሃይል ከሆነ ለሰላም ይተባበራል። ስለዚህ በዚህ መንገድ ለአገር መበታተን ስጋት የሚሆን ነገር መቀነስ ይገባዋል። የኢህአዴግ ማዕከላዊ አመራርም ወደዚህ እንዲመጡ መግፋት አለበት የሚል እምነት አለኝ። ሰላም ከተፈጠረ በኋላ ደግሞ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ ይጠበቃል። በነገራችን ላይ ሰላም የማስከበሩና የምርጫ ዝግጅት አብሮ ማስኬድ ይቻላል። ይህንን ካደረጉ በኋላ የምርጫውን ውጤት በሰላምና በፀጋ ለመቀበል ፍቃደኝነታቸውን ሊያሳዩ ይገባል። በተለይ ከማዕከላዊ መንግሥቱ በላይ የፖለቲካ ድርጅቱ ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ እንደ አማራጭ ያቀረቡት የምርጫ ውጤትን በፀጋ ተቀብሎ ስልጣንን የመልቀቅ መፍትሄ በተለይ ህወሓት ይቀበለዋል ብለው ያምናሉ?
ታጋይ አረጋሽ፡- እንግዲህ ኢህአዴግም ሆነ ህወሓት የህዝብን ውሳኔ ከመቀበል ውጭ ሌላ አማራጭ አላቸው ብዬ አላምንም። በነገራችን ላይ በህወሓት ዘንድ ብቻ ሳይሆን በአማራው በኩል ያለው መካረር ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው እየተከተሉት ያሉት። ማዕከላቸው አገር ማድረግ ሲገባቸው የየራሳቸውን ፍላጎትና ምኞት ለማሳካት እየሮጡ ነው የሚገኙት። ይህ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው። ይህንን ችግር መፍታት የሚቻለው የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ መጠናከር ሲችል ነው። ምክንያቱም ለማንም ሳይወግን ትክክለኛውን መልዕክት የማስተላለፍ አካሄድ መጠንከር አለበት። በተጨማሪም እንዲጋለጡ ማድረግ ይጠበቅበታል።
ህዝቡም ሁሉም ነገር ግልፅ ከተደረገለት የአገር አንድነትን የማይፈልጉትን ኃይሎች መግፋቱ አይቀርም። ስለዚህ ማዕከላዊ ሃይሉ ትክክለኛውን መልዕክት የማስተላለፍ ሃይልና አቅም ሊኖረው ይገባል። በሁለተኛ ደረጃ አሁን ያለው ኢህአዴግ ለብቻው ከሚንጠለጠል ሌሎች እህት ፓርቲዎችንም ማሳተፍ ይገባዋል። በተጨማሪም ያገባኛል የሚሉ ሃይሎች ሁሉ እንዲሳተፉ እድል መፍጠር ይገባዋል። ይህን ስልም ደጋፊ መሰብሰብ ሳይሆን የጋራ መግባባት ተፈጥሮ አገርን ለማዳን መረባረብ ይገባቸዋል። የጋራ ሲሆን ሃይል ይፈጥራል። ይህ ሲሆን ነው ህወሓትንም ሆነ ሌላውን ማሸነፍ ይቻላል። ግን ደግሞ ቅንነት ያለውና የሚታመን ጥሪ መሆን አለበት። ስለዚህ በዚህ መንገድ መስተካከል አለበት የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡– ህግን ከማስከበር አኳያ የትግራይ ክልላዊ መንግስት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን አሳልፎ ከመስጠት አኳያ ምን ሊሰራ ይገባል ይላሉ?
ታጋይ አረጋሽ፡– ከህግ ማስከበር ጋር አያይዘሽ ላነሳሽው ሃሳብ በመጀመሪያ መሆን አለበት ብዬ የማስበው ህግ ማስከበር ከመጀመሪያው መሰራት አለበት የሚል ነው። አንድ ወቅት ላይ እንዲያውም ህገመንግስቱ እንደሌለ ተደርጎ የሚገለፅበት ሁኔታ ነበር። በዚያ ወቅት ኢህአዴግም ምንም አላለም። ምንአልባት ወደ ስልጣን የመጡ ቡድኖች እንዳይቀየሙ ከመስጋት የመነጨ ሊሆን ይችላል። በነገራችን ላይ ህገመንግስቱ መቀየር የለበትም የሚል እምነት የለኝም። ግን እስኪቀየር ድረስ ህግ መኖር አለበት። የሚመራሽ ህግ መኖር አለበት። ዝም ብለሽ በባዶ ህገመንግስቱ ይጣል ማለት አትችይም። ያለውን እየተጠቅምን እንዲሻሻል የሚያደርግ ሁኔታ መፍጠር አለብን። እስከዚያ ድረስ ግን ያለው ህግ ነው ህጋችን፤ ያለ ህግ አገር ልትመራ አትችልም። ስለዚህ ህገመንግስቱ መከበር አለበት ብሎ መቆም አለመቻሉ ሌላ ጥያቄ ያስነሳል።
አዲስ ዘመን፡– ይቅርታ ላቋርጦትና ህገመንግስቱን ከፕሮፖጋንዳ በዘለለ በተግባር የተጣሰበት አጋጣሚ ስለመኖሩ ማሳያ ሊያቀርቡልኝ ይችላሉ?
ታጋይ አረጋሽ፡– ይሄ ለውጥ በመጣ ማግስት በጣም ብዙ መጯጯህ ነበር። ህገመንግስትንም ሆነ ባንዲራውንም ለመቀየር የሚደረጉ ትርምሶች ነበሩ። ይህ በሆነበት ጊዜ መንግስት ማስቆም ነበረበት ነው እኔ እያልኩ ያለሁት። ሁለተኛ ደግሞ የወልቃይትና የራያ ጥያቄ ሲመጣ ህገመንግስቱን አንቀበልም ብለው የሚከራከሩ ነበሩ፤ መከራከር ብቻ ሳይሆን በሃይል እንመልሰዋለን ብለው የሃይል እንቅስቃሴ የጀመሩ ነበሩ። ዲሞክራሲ ማለት ልቅ መልቀቅ ማለት አይደለም። የወልቃይትም ሆነ ሌላው ጥያቄ የሚመለሰው በሩጫና በሃይል ሊሆን እንደማይችል መንግስት ቁርጥ ያለ አቋሙን ማሳየት ነበረበት የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡– ግን እኮ ይህ አስተሳሰብ ላለፉት 27 ዓመታት ተበድያለው ከሚል አካል የመነጨ እንደመሆኑ በትዕግስት ማለፉ ተገቢ አይደለም እያሉ ነው? ደግሞስ ባለፉት 27 ዓመታት በህዝቡ ላይ ይደርስ ከነበረው በደል አንፃር በአንድ አመት ውስጥ ታየ የሚሉት ሁኔታ ጋር ሚዛን ውስጥ የሚቀመጥ ነው?
ታጋይ አረጋሽ፡- እንዳልሽው ባለፈው አንድ አመት የታየው ነገር ያለፉት 27 ዓመታት ይደርስ የነበረው ችግር ውጤት ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ህወሓት ከዳር ሆኖ ሃሳብ ሲሰጥ ራሱ የዚያ ጥፋት አካል እንደነበር የሚዘነጋው ይመስለኛል። ይህ ትክክል እንዳልሆነ አምናለሁ። ለዚህ ሁኔታ የዳረገን ህወሓት ይመራው የነበረው ኢህአዴግ ነው። ያ ጭቆና ስለነበር ደግሞ ሰው በግልፅ መናገር እንዲችል መንግስት እድል መስጠቱን አልቃወመውም። ግን ነፃነት ደግሞ ዝም ብለሽ ከለቀቅሽው ችግር ይፈጥራል። በደቡብና በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው የማፈናቀልና ትርምስ ሁኔታ እንደ ነፃነት ልንቆጥረው አንችልም። ምክንያቱም ህዝቡ ነው እየተንገላታ ያለው። ዜጋው ነው ከኖረበት ቀዬ እየተባረረና እየተገደለ ያለው። እኔ በነፃነት ምክንያት የመጣ ስለሆነ ምንም አይደለም አልልም። ነፃነት ገደብ አለው።
መሻገር የሌለበትን ደረጃ ተሻገረ። ስለዚህ በነፃነት ሰበብ የሰው ህይወት መጥፋቱን እኔ እኮንነዋለው።መፈናቀላቸውን እኮንነዋለው። የዲሞክራሲ ውጤት ነው አልለውም። በአጠቃላይ ግዴታውና ዲሞክራሲውን ካለማወቅ የመነጨ ነው ብዬ ነው የምወስደው። በሌሎች አካባቢዎች የመፈናቀል ሁኔታም አለ። ይሄ ራሱ በነፃነት የመጣ ነው ብዬ አልተነትነውም፤ ይልቁንም ስርዓት ማጣት የወለደው እንጂ። እናም ዲሞክራሲ መፍቀድና ስርዓቶች እንዲከበሩ ማድረግ አብሮ መሄድ አለበት ብዬ ነው የማምነው። አለበለዚያ ልቅ እየሆነ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ይመጣል። በዚህ ሁኔታ በመጨረሻ ተጎጂ የሚሆነው ህዝቡ ነው። ስለዚህ ያ ሚዛኑን መጠበቅ አለበት ነው የሚል እንጂ ችግሩ አሁን የተፈጠረ ነው የሚል እምነት የለኝም።
ወንጀል ሰርተው የተሸሸጉት ብቻ ሳይሆን ያልተሸሸጉትም መጠየቅ አለባቸው ብዬ አምናለሁ። መሰራት ካለበትም በከፊል አይደለም መሰራት ያለበት። በራስ መተማመን እንዲኖርሽ ከተፈለገ በህዝቡ አካባቢ ተዓማኒነት እንዲኖረው ትግራይ የተሸሸጉት ብቻ ሳይሆን እዚህ ሳይሸሸጉ ከመንግስት ጋር እየኖሩና እየሰሩት ያሉት በተመሳሳይ መጠን የሰረቁ በተመሳሳይ መንገድ ያጠፉ አሉ። ስለዚህ ይሄ ጥያቄ የጌታቸው እና ሌሎች እስር ቤት ያሉ አመራሮች ብቻ መሆን የለበትም። ይህም የትግራይ ህዝብ ጥርጣሬ እንዲያድርበት የሚያደርግ አንድ ምክንያት ነው። በሌላ በኩል አጠፉ የተባሉት እነጌታቸው ያንን ጥፋት ሲፈፅሙ ሌላው የመንግስት አካል ለምን ዝም ብሎ ተመለከተ? ተብሎ መጠየቅ አለበት። ጌታቸው ብቻውን መንግስት አይደለም። ኢህአዴግ የሰጠው አቅጣጫ ፍትሃዊና ትክክል ሆኖ ግለሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ቀይሮት ለራሱ ጥቅም አውሎት ከሆነ መጠየቅ ይገባዋል።
በነገራችን ላይ እሱ ይመራው የነበረው ተቋም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነበር። ስለዚህ ይህንን ተግባር በሚፈፅምበት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያውቅም ማለት አይቻልም። በመሆኑም በወቅቱ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መጠየቅ ይገባቸዋል። ይህን ስልም ደግሞ ያጠፉ አካላት ለምን ይጠየቃሉ ማለቴ አለመሆኑን እንድትገነዘቡልኝ እፈልጋለሁ። ግን የእውነት ለማጥራትና ለማስተካከል ከሆነ እዛጋ የነበረው አቅጣጫና ፖሊሲ ማን ነው ያወጣው? እሱ ያን ሲያደርግ እነሱ የት ነበሩ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። የግድ መታሰር አለባቸው ማለት ሳይሆን ቢያንስ ሁሉም ጥፋቱን በይፋ ተናግሮ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል ብዬ አምናለው። በነገራችን ላይ ይህ ሁኔታ ሲነገርበት ከነበረው ስጋት ተጨማሪ በደል ነው የሆነበት። ስለዚህ በህዝቡ አመኔታ እንዲኖር ከተፈለገ ሁሉም በሚዛኑና በደረጃው ተጠያቂ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በቀጣዩ ምርጫ ላይ ይሳተፋሉ ብለን እንጠብቆት? ለዚያስ እንደ ዓረና እየተደረገ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?
ታጋይ አረጋሽ፡– እኔ እስከመጨረሻው ድረስ ፍትሃዊ ስርዓት እስኪሰፍን ድረስ እታገላለሁ የሚል እምነት ነው ያለኝ። ህወሓቶች ችግር ሊፈጥሩብኝ እንደሚችሉ ከመጀመሪያውኑ አውቀዋለሁና ምንም አይነት ፍርሃት የለብኝም። እኔ አቅሜ እስከፈቀደ ድረስ እንቀሳቀሳለሁ። በምርጫው የመወዳደሩ ጉዳይ በእርግጥ እስካሁን አልተወሰነም። ያኔ የሚወሰን ነው የሚሆነው። ነገር ግን በፖለቲካው ግን በህይወት እስካለሁ ድረስ ለውጥ ስለምሻ ንቁ ሆኜ እንቀሳቀሳለሁ። ምክንያቱም በርካታ ወጣቶችን ቀስቅሼ ለለውጥ እንዲታገሉ ሳደርግ እንዲሰዉ ምክንያት ሆኛለሁ። እናም አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ተቀይሮ የሰላምና የመረጋጋት ሁኔታ እንዲመጣ ከዚያም ከትምህርት ቤት ጀምሮ የታገልንበት ነገር ሰፍኖ ለማየት እታገላለሁ። ባልደርስበት እንኳ ሌሎች ወጣቶች ይህንን አላማ ተረክበው እንዲያስቀጥሉት አደርጋለሁ። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ታላቅ ታሪክ ያላት አገር ሆና ሳለ በትርምስ ሳይሆን በልማትና በሰላም የሚመራት መንግስት እንዲኖራት እታገላለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ታጋይ አረጋሽ፡– እኔም ያለሁበት ስፍራ ድረስ መጥታችሁ ቃለምልልስ በማድረጋችሁ በጣም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ፣ ነሀሴ 4/2011
ማህሌት አብዱል