
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ በደን ልማት ዙሪያ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ የማህበራዊ ፖሊሲ ስርዓትና ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ ነጋሳ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ደን መልማት ከሚችሉ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ቢሆንም በዘርፉ የሚሳተፉ የግል ባለሃብቶች ቁጥር ዝቅተኛ ነው።
በደን ልማት የሚሰማሩ የግል ባለሃብቶች ደን ለማምረት ረጅም ጊዜ የሚወስድባቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አገልግሎት ስለማይመቻችላቸው ባለሃብቶቹ በዘርፉ እንዳይሳተፉ ትልቅ እንቅፋት እንደፈጠረባቸው ዶክተር አለማየሁ ጠቁመዋል።
የደን ምርቶች በህገወጥ መልኩ በተለያየ አቅጣጫዎች ወደ ገበያ ስለሚገቡ ደን በማምረት ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ግለሰቦች ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ እንቅፋት መፍጠሩን አመልክተዋል። በተጨማሪም ህገወጥ ምር ቶቹ የገበያ መዛባትንም ስለሚፈጥሩ ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ መቀዛቀዝ አይነተኛ ምክንያት መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
ከመሬት ይዞታ ጋር በተያያዘም ችግሮች መኖራቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም ባለሃብቱ የደን ምርቱ ደርሶ ምርታማ እስከሚሆን ድረስ መሬቱ የሱ ስለመሆኑ ዋስትና እንዳይኖረው ማድረጉን አብራርተዋል። በመንግሥትም በኩል መሬቱ የባለሃብቱ ስለመሆኑ በቂ ማረጋገጫ አለመኖር ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ተጨማሪ ማነቆ መሆኑን አንስተዋል።
የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግም ዘርፉን ያማከለ የፋይናንስ አቅርቦት ሊኖር እንደሚገባ ዶክተር አለማየሁ አመልክተው፤ በተለይም በልማት ባንክ አማካኝነት አነስተኛ ወለድ ያለው የረጅም ጊዜ ብድር አገልግሎት ለባለሃብቱ ማመቻቸት እንደሚገባ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። በመንግሥት በኩል በቂ የፋይናንስ አቅርቦት ከሌለም የልማት ባንክ ከዓለም ባንክ ጋር በመነጋገር የረጅም ጊዜ ብድር ማመቻቸት እንደሚኖርበት አሳስበዋል።
ከገበያ መዛባት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታትና በተለይ ህገወጥ የደን ገበያን ለማስቀረት ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓቶችን መዘርጋት እንደሚገባም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል። ከመሬት አሰራር ጋር በተያያዘም የግል ባለሃብቱ የአካባቢውን ህብረተሰብ ባሳተፈ መልኩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሰራር መፍጠርም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ፣ ነሀሴ 4/2011
አስናቀ ፀጋዬ