
አዲስ አበባ፡- ተቋማት ከለውጡ በኋላም ለብሔራዊ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር የሚፈለገውን ትኩረት እየሰጡ አለመሆኑን ፅህፈት ቤቱ ጠቁሟል፡፡
በኢፌዴሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የብሔራዊ ሰብአዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይበቃል ግዛው ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ ለውጡን ተከትሎ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብሩን ለመተግበር ተነሳሽነት ቢስተዋልም በሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ በሰብዓዊ መብቱ ላይ የፍትህ አካላትን ጨምሮ ለውጡ ያመጣቸው በርካታ ውጤቶች አሉ፡፡ ከዚህ ውጭ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ላይ አንፃራዊ መሻሻል ቢታይም አሁንም ብዙ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የፅህፈት ቤት ኃላፊው በመርሐ ግብሩ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች መኖራቸውን በመጥቀስ ለውጡን ተከትሎ በእነዚህ ላይ መንግሥት ከመርሐ ግብሩ በላይ አልፎ ማሳካቱን፤ የድርጊት መርሐ ግብሩ ካስቀመጣቸው ዓላማዎች በላይ መሄዱንና ባለፈው አንድ ዓመት የዜጎች የሲቪል መብቶችና የፖለቲካ መብቶች መጎልበታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊው እና በሌሎቹ ላይ ከተቋማት ጋር ተያይዞ ክፍተት አለ ብለዋል፡፡ በእነዚህ በኩል በሰነዱ ያለውን ያህል እየተካሄደ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡
እንደኃላፊው ገለፃ፤ ሰብአዊ መብት ሙሉ ተከብሯል ለማለት አሁንም ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን መርሐ ግብሩ ከትልልቅ እስከ አገራዊ ጉዳዮች የተካተቱበት በመሆኑ ለመቆጣጠር እና ለመከታተል በጣም ከባድ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ ትምህርት በመውሰድ በቀጣይ ሶስተኛው ብሔራዊ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ለቁጥጥር በሚያመች መልኩ ይዘጋጃል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2011
ምህረት ሞገስ