
‹‹ትምህርት ቤቱ የተዘጋው ከደረጃ በታች በመሆኑ ነው››
– ጽህፈት ቤቱ
አዲስ አበባ፡- በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከደረጃ በታች ናቸው ተብለው ከተዘጉት ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ብሌን መዋዕለ ህጻናትና ትምህርት ቤት፤ “ያለ አግባብ ተዘግቶብኛል” ሲሉ ባለቤቱ ገለጹ፡፡ የክፍለ ከተማው የአጠቃላይ ትምህርት ጥራና አግባብነት ሬጉላቶሪ ጽህፈት ቤት በበኩሉ፤ “ትምህርት ቤቱ የተዘጋው ከደረጃ በታች በመሆኑ ነው” ሲል አስታውቋል፡፡
በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ብሌን መዋዕለ ህጻናትና ትምህርት ቤት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ በኩረጽዮን ካሳሁን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ትምህርት ቤቱ ‹‹ከነርሰሪ እስከ አፐር ኬጂ›› ትምህርት በመስጠት ላይ የነበረ ነው።
በዚሁ አግባብ ለ2012 እና 2013 ዓ.ም ፍቃድ ለማሳደስ ማመልከቻ ቢያስገቡም የክፍለ ከተማው የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ጽህፈት ቤት ትምህርት ቤቱን ገምግሞ ውጤቱ ከ75ነጥብ በታች ሆኖ በመገኘቱ እንዲዘጋ አድርጓል፡፡
ትምህርት ቤቱን ከደረጃ በታች ሊያደርገው የሚችል ነገር እንዳልነበረ፤ ውጤት አሰጣጡም በዘፈቀደ በመሆኑ ያለ አግባብ መዘጋቱ ተገቢ አይደለም ሲሉም ነው ቅሬታ አቅራቢው የተናገሩት፡፡
እንደ አቶ በኩረጽዮን ገለጻ፤ የመመዘኛ መስፈርቱ ብዙ ቢሆንም፤ ትምህርት ቤቱ አሟልቶ ለተገኘው ነገር በትክክል ነጥብ አልተሰጠም፡፡ በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ የሚገኙት ማጫወቻዎች ለተማሪዎች በቂና ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ የጎደለውን ነገር ከመጠቆም ይልቅ በዘፈቀደ ነጥብ ዝቅ አድርገው ሰጥተዋል፡፡
ቀድሞ በነበረው አሰራር የመጀመሪያ ጊዜ ነጥብ ከተሰጠ በኋላ ትምህርት ቤቱ ማሻሻያ እንዲያደርግ በመንገር ለሁለተኛ ጊዜ ገምግመው ውጤት ይሰጡ ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ በአንድ ጊዜ 48 ነጥብ ሰጥተው እንደገና ሁለተኛውን ነጥብ ሳይሰጡ ትምህርት ቤቱ እንዲዘጋ ተደርጓል፡፡
አቶ በኩረጽዮን፤ ‹‹በጽህፈት ቤቱ በኩል የተቀመጡትን መስፈርት አሟልተናል፡፡ ትም ህርት ቤቱ መዘጋት የለበትም፤ ተማሪውና ሠራ ተኛውም መበተን የለበትም፤ ያልተሟላ ነገር ካለ ማስተካከያ እንዲደረግ መንገር አለባቸው፡፡ ጉዳዩን ለቅሬታ ሰሚ አካል አቅርበን መሟላት ያለበትን ነገር እንድናሟላ ነግረውን ለጽህፈት ቤቱ ሀሳቡን ብናቀርብም ጽህፈት ቤቱ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡›› ብለዋል።
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አጠቃላይ ትምህርት ጥራት አግባብነትና ሬጉላቶሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ራቢያ ያሲን በበኩላቸው፤ መስፈርቱ እውቅናና እድሳት ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ትምህርት ቤቱ በትምህርት ጥራት ለተማሪ ሥነ ምግባር ምቹነት የተቀመጠውን መስፈርት 75 ነጥብና ከዚያ በላይ ማምጣት ሲገባው ይህንን አሟልቶ ባለመገኘቱ መዘጋቱን ገልጸዋል፡፡
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፤ በመጀመሪያው ዙር 75 ነጥብ ማምጣት ባለመቻሉ ጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸው ግብዓቶችን እንዲያሟሉ እንደተ ነገራቸው፤ ባለሙያዎቹም በሁለተኛው ዙር ግምገማቸው ትምህርት ቤቱ የተሰጠውን ግብረ መልስ ማሻሻል ባለመቻሉና መስፈርቱን ባለማሟላቱ ውሳኔው ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ኃላፊዋ የትምህርት ቤት ደረጃ መዋዕለ ህጻናት ላይ ከምንም በላይ መሟላት አለበት በማለት፤ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚማሩት ህጻናት እንደመሆናቸው መጠን ከአንደኛ ደረጃነት በላይ እንክብካቤ ሲያስፈልጋቸው ትምህርት ቤቱ ግን በዚህ ቁመና ላይ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ ለመማር ማስተማር ሊያበቃው የሚችል ምቹ ሁኔታ ስለሌለው ተማሪዎች እንዳይጉላሉ ሲባል መዘጋቱን አስታውቀዋል፡፡
እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ፤ ትምህርት ቤቱ ከሌላው ትምህርት ቤት በላይ ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡ ነገር ግን የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ስልጠና ሲጠሯቸው አይገ ኙም። ራሳቸውን ለማሻሻልም ዝግጁ አይደሉም። መረጃ ሲጠየቁም አይሰጡም፡፡
‹‹በመስፈርቱ ላይ 108 ጠቋሚ ጉዳዮች ያሉ ሲሆን፤ አንድ ትምህር ቤት ህልውናውን ጠብቆ ለመቆየት እያንዳንዳቸው ተደምረው 75 እና ከዚያ በላይ ውጤት ማምጣት ይኖርበታል፡፡
እያንዳንዱ መስፈርት ለህጻናት ምቹ የመማሪያ ስፍራን ከመፍጠር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ትምህርት ቤቱ የሚጠበቅበትን መስፈርት አላሟላም፡፡ ግምገማውና ውጤ ቱም የተሰጠው በዘፈቀደ ሳይሆን በዘርፉ አገልግሎት በመስጠት ላይ ባሉት ባለሙያዎች አማካኝነት ነው›› ብለዋል ኃላፊዋ፡፡
በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ውስጥ ካሉት 349 ትምህርት ቤቶች 213 ትምህርት ቤቶች እድሳት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በራሳቸው ፍላጎት ከተዘጉት ሰባት ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ እስካሁን ከደረጃ በታች ናቸው ተብሎ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች ቁጥርም አራት መድረሱን ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2011
አዲሱ ገረመው