አዲስ አበባ፦ በኢትዮጵያ ያለውን የጤና አገልግሎት የጥራት፣ የፍትሐዊነት እና የዘላቂነት ችግሮች ላይ መፍትሔ ለማምጣት ተመራቂ የህክምና ዶክተሮች ከመንግስት ጋር በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 265 የህክምና ዶክተሮችን እና 23 የጥርስ ህክምና ዶክተሮችን ትናንት በዩኒቨርሲቲው ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት አዳራሽ አስመርቋል። በወቅቱ ፕሬዚዳንቷ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ያለውን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል የሚያስችሉ እቅዶች በመንግስት ደረጃ ተዘጋጅተዋል። ተመራቂ የህክምና ባለሙያዎች የዘርፉን የጥራትና የፍትሐዊነት ችግሮች ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ዋነኛ ተዋናይ ለመሆን ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ አንድ የህክምና ዶክተር አገልግሎት የሚሰጠው ለ15ሺ ሰዎች ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ ይህም ከዓለም አቀፍ ደረጃ ዝቅተኛው መስፈርት ጋር በእጅጉ የተራራቀ መሆኑን አስታውሰው፤ ተመራቂዎች የተማሩትን መሰረት በማድረግ ውድ የሰው ህይወትን የመንከባከብ እና የማዳን ስራ ላይ ሳይሰለቹ መስራት አለባቸው። የህክምና ሙያ በየጊዜው እየረቀቁ ከሚሄዱ ቴክኖሎጂዎች ጋር የተያያዘ እድገት ያለው ዘርፍ መሆኑንም አስረድተዋል።
ተመራቂ የህክምና ባለሙያዎች በየወቅቱ እራሳቸውን እያስተማሩ እና እያበቁ በህክምናው እንዲሁም በምርምር ዘርፉ አገራቸውን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል። ከህዝብ ቁጥር መጨመር እና ከተቀያያሪ የሰዎች ፍላጎት ጋር ተያይዞ አስፈላጊነታቸው እየጨመረ ስለሚሄድ ሳይታክቱ በስነምግባር የተደገፈ ሙያዊ አገልግሎት እንዲሰጡም አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና በበኩላቸው፤ የህክምና ሙያ ከሚሰጠው ጥቅም እና ክብር ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቱ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው፤ ኃላፊነቱ ምንጊዜም ተመራቂ ሐኪሞች በስራ ላይ ሆነው ልብ ሊሉት የሚገባ ጉዳይ ሆኖ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። «ኢትዮጵያም ከእናንተ ብዙ ትጠብቃለች» ሲሉ ለተመራቂዎች የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ቀጣዩ ዘመናቸው ሙያዊ ስኬት የሚያስመዘግቡበት እንዲሆንም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ምሩቃኑም በየትኛውም ጊዜና ቦታ ህብረተሰቡን፣ በታማኝነት፣ በቅንነትና በሚስጥር ጠባቂነት ለማገልገል ቃል ገብተዋል። ከተመራቂዎቹ መካከል 96 ዶክተሮች ሴቶች ሲሆኑ፤ 192ቱ ወንዶች ናቸው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2011
ጌትነት ተስፋማርያም