በርካቶች ለባሕር ማዶ ያላቸው አመለካከት በተሳሳተ መልኩ የተቀረፀ በመሆኑ በአገራቸው ሠርተው ከመለወጥ ይልቅ ውጭን ናፋቂ እንዲሁም የቆዳ ቀለማቸው ነጭ ለሆኑ የሠው ልጆች ከፍተኛ ክብርን እንዲሰጡ ሲያደርጋቸው ይታያል፡፡ የሕይወት ዕጣ ፈንታን አለማወቅና መድረሻን አለመወሰንም ብዙዎችን ከመንገድ ሲያስቀር ጥቂቶችን ደግሞ በችግር ውስጥም ቢሆን የተሻለ ቦታ ላይ ያስቀምጣቸዋል፡፡ ይህን ጉዳይ ያነሳሁላችሁ ያለምክንያት አይደለም፡፡ ከሁለት አሰርት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ በሚገኝ የኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት የመማር ዕድል በማግኘት ቤተሠቦቹን በደስታ ያስፈነጠዘው አጋጣሚ ባላሰበው ጎዳና ወስዶት በአሁኑ ወቅት በጽዳት ሥራ ላይ ተሠማርቶ የሚገኝ ወጣትን ቅሬታ በመስማቴ ነው፡፡ የወጣቱን ቅሬታ መነሻ በማድረግም ሌሎች ቅሬታ አቅራቢዎችን፣ ተቋሙንና የሚመለከተውን አካል በማነጋገር ያዘጋጀነውን ዘገባ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አዲሱ ገበያ አካባቢ ነዋሪ ወጣት አበበ አንሙት(ሥሙ የተቀየረ) በግሪክ ትምህርት ቤት እንደተማረ ይናገራል።አባቱ በትምህርት ቤቱ በቧንቧ ሥራ ተሠማርተው ይሠሩ ስለነበር አንድ ልጅ የማስተማር ዕድል ይሠጣቸውና ባገኙት ዕድል በመደሰት ቦርሳውን አንግቦ ያመራል፡፡ ነገን ያለማወቅ እርምጃ ነውና በወቅቱ ቤተሠቦቹን ያስፈነጠዘው ይህ ዕድል በዚህ ጎዳና ወስዶት ለዛሬ የጽዳት ሠራተኝነት ያበቃዋል ብሎ የገመተ ግን እንዳልነበር በሐዘን ይናገራል፡፡
ዕድሉ የተሰጠው በትምህርት ቤቱ ውስጥ በሚገኘው አዳሪ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ 12ኛ ክፍል እንዳጠናቀቀ የውጭ የትምህርት ዕድል(ስኮላርሺፕ) እንዳገኘና ሕይወቱን ቁልቁል የወሰደው ችግር ‹‹ሀ›› ብሎ እንደጀመረ ያስታውሳል፡፡ የውጭ የትምህርት ዕድሉን ለማግኘት የሚጠበቀው ውጤት 9 ነጥብ 5 ቢሆንም እርሱ ግን 10 ነጥብ 2 በማምጣት እ.አ.አ. በ2006/2007 ወደ ግሪክ አገር ሄዶ የረጅም ጊዜ ሕልሙ ዕውን እንዲሆን የሚያስችለውን ዕድል ያገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ባገኘው ዕድል ሳይጠቀም የትምህርት ዕድሉ ለሌላ ሠው መሰጠቱን ያስታውሳል፡፡
በወቅቱ ያገኘውን የትምህርት ዕድል ማጣቱን ያወቀው የስድስተኛ ክፍል ግሪካዊ መምህሩ በእርሱ በኩል ግሪክ አገር በአንድ ኮሌጅ ውስጥ የትምህርት ዕድል አፈላልጎ እንዳገኘለት ይናገራል፡፡ ሆኖም ግን ትምህርት ቤቱ በዚህም ዕድል ተጠቃሚ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ ቅሬታውን በየደረጃው እንዳቀረበ የሚናገረው አበበ፤ በከንቱ ያባከናቸው የትምህርት ዘመናት ወደኋላ ሳይጎትቱት በአገር ውስጥ ለመማር አልያም ሥራ ለመሥራት ቢሞክርም እንኳ የተማረው በኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ባለመሆኑና በግሪክ ቋንቋ በመሆኑ ከምንም ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ለዓመታት ከተማረበት ግቢ ውስጥ እንዳይገባም እንደተደረገና በተደጋጋሚ ባቀረበው ቅሬታ በአሁኑ ወቅት አስኮ መስመር በሚገኘው የግሪክ ኦርቶዶክስ ዘላቂ ማረፊያ አካባቢ በጽዳት ሥራ እንደተቀጠረ ይናገራል፡፡ በወር ሁለት ሺህ ብር የሚያገኝበትን ይህን ሥራ በትምህርት ቤቱ ውስጥ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ማንም ሊያደምጠው የፈቀደ ግን እንዳልነበር ይገልፃል፡፡
የሚያልመው ሁሉ ከንቱ ሆኖ ሕልሙ ሳይሳካ በመቅረቱ ሙሉ ሕይወቱን ዝብርቅርቅ እንዳደረገውና ተጽዕኖ እንደፈጠረበትም ፊቱን ቅጭም አድርጎ ይናገራል፡፡ ተምሮ እንዳልተማረ እንደሆነ በማንሳትም ‹‹መክኛለሁ›› ይላል፡፡ በውጭ አገር ስታንዳርድ (መመዘኛ መስፈርት) እንደተማረ የሚያውቁ ሁሉ ባገኙት ሰዓት ከንፈር መምጠጣቸው ሥነልቦናውን እንደጎዳውና አንገቱን ያስቀረቅረዋል፡፡
‹‹ለምንድን ነው የምኖረው? ከዚህ በኋላ ተስፋዬስ ምንድን ነው?›› የሚል ጥያቄ ዘወትር በዓይነ ሕሊናው እንደሚያቃጭልበትም ይናገራል፡፡ ለዓመታት የለፋበትና ነገን የተሻለ በማድረግ የቤተሠቡን ኑሮ እንደሚለውጥበት ተስፋ የሰነቀበት የሕይወት መስመሩ እንዲሁ መና መቅረቱ ከመኖር አለመኖርን ምርጫው እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ትምህርት ቤቱ እንግሊዝ እና ግሪክ ክፍል በሚል በሁለት የተከፈለ ሲሆን፤ በግሪክ ክፍሉ የሚማሩት ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ምንም እንኳ ከወላጆቻቸው የውጭ የትምህርት ዕድል ይሠጣቸዋል በሚል ቢመጡም በገሃዱ ዓለም ግን ዕድሉ ለውስኖች የሚሰጥ በመሆኑ በርካቶቹ ዜጎች በጽዳት፣ በመልዕክት ሰራተኝነት፣ በግሪካውያኑ የቤት ሠራተኝነት እንዲሁም የወሲብ ባሪያ ሆነው እንደሚቀሩ ይጠቁማል፡፡
ብዙዎቹም የወሲብ ጥቃት ደርሶባቸው አልያም ጥቃቱን አምልጠው ለመብታቸው በመሟገታቸው ከትምህርት ቤቱ ተባረው ለሴተኛ አዳሪነት ብሎም ለጎዳና ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ በድርጊቱ ተሣታፊ የሆኑት ደግሞ ግሪካውያን መምህራኖችና የግሪክ ቤተክርስትያን ቄሶች እንደሆኑ ይናገራል፡፡ እርስ በእርስ የተያያዙ በመሆናቸውም ቅሬታ ቢቀርብም መፍትሔ የሚሰጥ አካል ግን የለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ፓትርያርኩ ቢለወጡም ‹‹የቀድሞው የግሪክ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ግን ሊደፍሩኝ ሙከራ አድርገውብኝ›› ነበር ይላል፡፡ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ሲያስታውስ ከፓትርያርኩ ጋር የመሥራት ዕድል አግኝቶ የትርጉም ሥራ በሚሠራበት ወቅት ነበር፡፡
በትምህርት ቤቱ በሴቶችና በወንዶች ላይ ከሚደረገው የወሲብ ጥቃት ባሻገር የመምህራን ችግር እንዲሁም ትምህርቱም በአግባቡ እንደማይሰጥ ይናገራል፡፡ ትምህርቱ ሰዓቱን በጠበቀ መልኩ ባለመሰጠቱም ልጆቹ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ወደ መማሪያ ክፍላቸው ገብተው ስድስት ሰዓት ላይ ይወጡና ወደ መኖሪያቸው ይገባሉ፡፡ ከማሕበረሰቡ ጋር አይቀላቀሉም ለብቻ ታፍነው ከሚቆዩበትም የትምህርት ቤቱ ግቢ ክረምት ላይ ወደ ቤተሰቦቻቸው ይላካሉ፡፡ በዚህ ላይ ሌላኛው ትልቁ ችግር የልጆቹ አመጋገብ ሥርዓት እንደሆነም አበበ ይጠቁማል፡፡ የግሪክ አገር መንግስት የቀድሞ እርዳታውን ያቆመ ሲሆን፤ ይህም ለችግሩ መነሻ ሳይሆን እንዳልቀረ ግምቱን ይናገራል፡፡
በየወሩ ከተማሪዎች የሚሰበሰበው ወርሃዊ ክፍያ ከፍተኛ ቢሆንም ልጆቹ ግን በሥርዓቱ አይመገቡም፡፡ ከልጆቹ ይልቅ የግቢው ውሻ የሚቀለበው የዶሮና የበግ ሥጋ ነው ይላል፡፡ በዚህም የእርሱ ሕይወት ቢበላሽና ተስፋው እንደጨለመበት ቢሰማውም ሌሎች ዜጎችን ለመታደግና የእርሱ ጽዋ እንዳይደርስባቸው ግን አሁንም ጊዜው እንዳልረፈደ ነው የሚናገረው፡፡ በትምህርት ቤቱ ከዕውቀት ገበታ ለመቋደስ የሚገቡ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ሲልም እራሱ ይጠይቃል፡፡
በመሆኑም መንግስት ሌሎች ዜጎችም እንዳይመክኑ ሊከላከል ይገባል ሲል ይመክራል። ተመሳሳይ ችግር እንዳለ የሚያምኑ ለ50 ዓመታት በተቋሙ የሠሩ ግለሰብና የውጭ የትምህርት ዕድሏን እንደተቀማች የምትናገር ቅሬታ አቅራቢ ብናገኝም ለዚህ ዘገባ ግን ልናካትታቸው አልቻልንም፡፡
ነገር ግን በትምህርት ቤቱ በመምህርነት ይሠራ የነበረና ከተጠቀሱት ችግሮች ባሻገር ሌሎች በርካታ ጉድለቶች እንዳሉ በትምህርት ቤቱ በእንግሊዝ ክፍሉ በሒሳብ መምህርነት ለሰባት ዓመታት ያስተማረው መምህር ኃያሉ ፍቃዱ ይናገራል፡፡ ከሥራው እስከለቀቀበት ጊዜ ድረስም የሠራተኛ ማሕበር አመራር ወይንም ዋና ፀሐፊ ሆኖ ሠርቷል፡፡ በዚህም ትምህርት ቤቱ ውስጥ ይታዩ የነበሩ ከፍተኛ የአሠራር ችግሮችን ፊት ለፊት ትግል ያደርግ ነበር። ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን የሚያዙበት መንገድ ክብር ያልተሞላበት መሆኑ ያማል ሲልም ሁኔታውን ያብራራል፡፡
ለተመሳሳይ ሥራ ከፍተኛ ልዩነት ያለው ክፍያ እንደሚፈፀምም ይጠቁማል፡፡ ለአብነት ያክል የእርሱ የተጣራ ወርሃዊ ደመወዝ ከአምስት ሺህ ያልዘለለ ሆኖ በተመሳሳይ ሥራ ለውጭ አገር መምህራን በአምስት እጥፍና ከዚያ በላይ የሆነ ክፍያ ይሠጣል፡፡ የተቋሙ የበላይ አመራሮች ችግሩን እንዲፈጥሩ የሚያግዟቸው ደግሞ ኢትዮጵያውያን ናቸው ይላል። በጽዳት እና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ላይ የሚስተዋለው የሥራ ጫናም ከፍተኛ ነው፡፡ ምንም እንኳ አልፎ አልፎ ለሕክምና እንዲሁም አንዳንድ ክፍያዎች ቢደረግላቸውም በቂ ጥቅማ ጥቅም እና ለሥራ የሚያስፈልጋቸው አልባሳት እንኳ የተሟላ አይደለም፡፡
ባልተሟላ የሥራ ሁኔታ ውስጥ የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንኳ ሳይታሰብላቸው የሚሠሩ ሠራተኞች የዘር መድሎ እንደሚደረግባቸውም ያስረዳል፡፡ ይህንና በትምህርት ቤቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን አስመልክቶ ትግል ያደርግ እንደነበር የሚናገረው መምህሩ፤ ይህን ምክንያት በማድረግ ያለአግባብ ከሥራ እንደተባረረም ይናገራል፡፡ በአንድ ወቅት በመምህራን በተዘጋጀ የመስክ ጉዞ ላይ ስላልተመቸው ባለመሄዱ ደብዳቤ ይፃፍበታል፡፡ ይህ የተደረገውም በቀለም መድሎው እንደሆነ ምላሽ መስጠቱንም አያይዞ ያስታውሳል፡፡ ከሌሎች አገራት መጥተው በሚያስተምሩ መምህራን ላይ ጉዞ አልሄዳችሁም በሚል የሚጠይቃቸው አለመኖሩንም ይገልፃል፡፡
ማንም ሠው በፍቃዱ የሚያደርገውን ግለሰባዊ ፈቃድን የሚሻ ጉዞ ላይ ተሳታፊ ሆኖ ባለመሄዱ ደብዳቤ ሲፃፍበትም የችግር ምንጭ የሆነው የቀለም መድሎ ነው ቢልም ሥም ማጥፋት ነው በሚል ምላሽ እንደተሰጠው ያስታውሳል፡፡ ማብራሪያ እንዲሰጥም ተደርጓል፡፡ በጽሑፍም ሆነ በቃል በትምህርት ቤቱ ቀለምን መሠረት ያደረገ መድልዎ እንደሚደርስ፣ ካለው የደመወዝ ልዩነት ባሻገር መኖሪያ ቤትን መሠል ጥቅማ ጥቅሞች እንደማይከበሩ፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያና ሌሎች በተቋሙ የሚስተዋሉ ልዩነቶች መኖራቸውን ይናገራል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ ቆይታ በኋላም ሥም ማጥፋት የተባለው ትግል በማድረጉ በመሆኑ ሙሉ የቦርድ አባላት ተሰብስበው ጉዳዩን ማስረዳት እንደሚፈልግ የሚገልጽ ደብዳቤ ቢሰጥም በነጋታው ግን ዳግም ወደ ሥራ ገበታው እንዳይመለስ የሚያደርግ የማሰናበቻ ደብዳቤ ይደርሰዋል፡፡ የስንብት ደብዳቤውም የመስክ ጉዞ ያለመሄድና ስም ማጥፋት በሚል ከሦስት ዓመት በፊት ከሥራ ተሰናብቷል።
እንግሊዝ ክፍሉ ላይ በብዛት የሚስተዋለው የአስተዳደር ችግር ሲሆን፤ ግሪክ ክፍሉ ላይ ግን መቼ ነው ልጆቹ የሚማሩት የሚል ጥያቄን በሚያጭር መልኩ የትምህርት አሰጣጥ ችግር መኖሩንና ተማሪዎቹ ጊዜያቸውን ውጭ ካለትምህርት እንደሚያሳልፉ በሥራ ላይ በነበረበት ወቅት መታዘቡን ይናገራል፡፡ ሁኔታውም ያልተማከለ የትምህርት ስርዓት እንዳለም አመላካች ነው ባይ ነው፡፡
‹‹በጭምጭምታ መምህራኖቹ እንዲሁም ቄሶቹ ግብረሰዶማዊ (ጌይ) እንደሆኑና ተማሪዎቹ ላይ የወሲብ ጥቃት እንደሚፈፀም ይወራ ነበር›› ይላል፡፡ ይህን የሰማ ማንኛውም የሠው ልጅ እንዴት ሊሆን ይችላል? የሚል የግርምት ጥያቄን መፍጠሩ ባያጠራጥርም በቆይታ ግን ይህን አስደንጋጭና እኩይ ድርጊት ላለማመን ቢጥሩም ከዕለት ወደ ዕለት በተቋሙ ሲደረግ የሚታየው ድርጊት ዕውነታ እንደሆነና ወሬው ሚዛን እንዲደፋ ማድረጉን ይገልፃል፡፡
በሌላ በኩል ልጆቹ ዕለት ተዕለት ዳቦ በእጃቸው ይዘውና ክክ ወጥ ሲበሉ የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ ውሾች ግን ዶሮና በግ በየቀኑ በጋሪ እየተገፋ ይገባላቸዋል ሲል በንጽጽር ያስቀምጣል፡፡ ይህን የሚመለከቱና ጥያቄ የሚያነሱም ተባርረው በሥነምግባር ጉድለት ወጡ ይባላል። ትክክለኛ ምክንያቱ ግን ተደፍረው አልያም እንቢ ብለው መሆኑ ይሠማል።
‹‹በዚህ መሠል እኩይ ተግባር ደግሞ መምህራኖቹ ብሎም ቄሶቹ ተሳታፊዎች›› ናቸው በማለት ያብራራል፡፡ በተያያዘ የግሪክ ኢኮኖሚ ከተጎዳ በኋላም የውጭ የትምህርት ዕድል በመቅረቱ ልጆቹ በግሪክ ቋንቋ ተምረው፣ አማርኛን እንኳ በቅጡ አስተካክለው መጻፍ ሳይችሉ ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው ምንድን ነው? የሚለው ሲታሰብ ጉዳዩን ይበልጥ አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ በቀጣይ ሕይወታቸውን ሊለውጥ የሚችል ትምህርትስ ለምን አይሰጣቸውም? ሲል ይጠይቃል፡፡ በዚህ አገርም ሆነ በውጭ ተቀባይነት የሚያገኙበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበትም ይናገራል፡፡
ተማሪዎቹ ለምንስ ግሪክ ቤተክርስቲያን ብቻ ይሄዳሉ? የፈለጉትን ሃይማኖትስ መርጠው የመከተል መብት የላቸውምን? በማለት መምህሩ ይሞግታል፡፡ ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የሚመጡት ልጆች የጥንት አጥንትና ደም ተቆጥሮ በግድ ግሪክ እንዲሆኑ ተደረጉ እንጂ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ በግቢው ሙሉ በሙሉ የሚኖሩት የሚማሩትም ኢትዮጵያውን ሲሆኑ፤ ግሪካዊ ስም እንደሚሰጣቸውም ይናገራል፡፡
በተቋሙ ዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉትን ችግሮች አስመልክቶ በዋናነት ጉዳዩ የሚመለከተውና ተጠያቂው ትምህርት ሚኒስቴር እንደሆነም ኃያሉ ይናገራል፡፡ ትምህርት ቤቱ አራት የተለያዩ ማህተሞችን እንደሚጠቀምም ይጠቁማል፡፡ ግሪክ ኮሙዩኒቲ የሚባለው ትምህርት ቤትም ኢንግሊዝ ክፍሉ እንደማይታወቅና በቦርዲንግ (በግሪክ አዳሪ ትምህርት ቤቱ) ስር ሆኖ ልጆቹን መስዋዕት በማድረግ ግለሰቦች በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲሰበስቡና እንዲበለጽጉ እንዳደረጋቸው ይጠቁማል፡፡ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ልጆች ለጎዳና ሕይወት አውጥቶ እየጣለ፣ አዕምሮ እንዲመክን እያደረገና ሕልውናቸውን እያጠፋ እንደሆነ እየታወቀ ግለሰቦች በሚሰሩት እኩይ ተግባር የሁለት አገራት ግንኙነት ይበላሻል በሚል ተቋሙን ከተጠያቂነት መከላከል ተገቢነት የጎደለው ተግባር ነው ሲል የሚመለከታቸውን አካላት ዝምታ ይኮንነዋል፡፡
ትምህርት ቤቱን የሚያንቀሳቅሱት ሁለት ግለሰቦች አባትና ልጅ በመሆናቸው ጉዳዩን ከአገራት ግንኙነት ጋር ማገናኘት ተገቢ አይደለም የሚለው ኃያሉ፤ መንግስት በትምህርት ቤቱ የገቡና የወጡ ዜጎች በቁጥር ይዞ ያሉበትን መፈለግ እንዳለበትም ቀጣይ መፍትሔ አድርጎ ይጠቁማል። በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት ከተቋሙ የወጡ ዜጎች የት ደረሱ? የሚለው ሊፈተሽና ካሳ ካስፈለገም ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ተቋሙ ሕይወታቸውን በማበላሸቱ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ማዕከል ከፍቶም ቢሆን በዲፕሎማም ሆነ በዲግሪ መርሐ ግብሮች አልያም የሙያ ትምህርት እንዲያገኙ በማስቻል ልጆቹ ተስፋቸው ጨልሞ እንዳይቀር ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ክፍለ ከተማው
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ አበራ፤ ጽሕፈት ቤቱ በክፍለ ከተማው ከሚገኙ ቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውጪ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶን ቁጥጥር የማድረግ ሥልጣን እንደሌለው ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 50 በሚሆኑት የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ፍቃድና ዕውቅና ይሰጣል ክትትልም ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፍና ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤቶች ምን ይስሩ? ምን ይፈጽሙ? ክትትል ስለማይደረግ ፍቃድ ሰጪው አካልም ትምህርት ሚኒስቴር በመሆኑ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ምን እንደሆኑ አይታወቅም፡፡ ‹‹ከእኛ በላይ በመሆናቸው እኛን የሚመለከት አይደለም›› ይላሉ፡፡
በክፍለ ከተማው የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልማው ኃይሉ፤ በበኩላቸው ከአሠሪና ሠራተኛ ጋር በሚፈጠሩ አለመግባባቶች እንዲሁም ተቋማት ፍቃድ አውጥተው ከሚሠሩት ሥራ ውጭ ማህበራዊ ጠንቅ የሆኑ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ ከተገኙ ወደ ጽሕፈት ቤቱ የተለያዩ ቅሬታዎች ይቀርባሉ፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር በግብረ ኃይል የሚሠራው ሥራ ነውና ከዚህ ጋር ተያይዞ ጥቆማ ሲደርስ ይሠራል፡፡ የግሪክ ትምህርት ቤትን አስመልክቶ የቀረበ ቅሬታ አለመኖሩንም ይናገራሉ፡፡ በቀጣይ ግን ችግሮች ከተነሱ በትኩረት እንደሚሠራ ይናገራሉ፡፡
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የገቢዎች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የደንበኞችና መስተንግዶ ድጋፍ አገልግሎት የሥራ ሒደት መሪ ወይዘሮ ጽጌ ኮሬ፤ በትምህርት ቤቱ ሦስት ሥያሜዎች ምንም ዓይነት ማስረጃ እንዳልተገኘ ነገር ግን በዕድሩ ሥም መለያ ቁጥር /ቲን ነምበር / እንደተገኘና በዚህም የሠራተኞች የሥራ ግብርና የጡረታ ሂሳብ ብቻ እንደሚከፈል ይናገራሉ፡፡ ትምህርት ቤት ይሁን ሌላ ተቋም ግን እንደማይታወቅ ያስረዳሉ፡፡
ሰነዶች
ትምህርት ቤቱን አስመልክቶ ከተመለከትናቸው ሰነዶች መካከል አራት የተለያየ ሥያሜ ያላቸው ማሕተሞች ያረፈባቸው ደብዳቤዎችን አግኝተናል፡፡ በዚህም ሄለኒክ-ግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት፣ ግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት፣ ሄለኒክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት የሚልና የሄለኒክ-ግሪክ ማሕበረሰብ በኢትዮጵያ መረዳጃ እድር የሚሉ ናቸው፡፡ የመረዳጃ እድሩ መለያ(ቲን) ቁጥርም 0040663076 ሲሆን፤ ለትምህርት ቤቱ የሠራተኛ ቅጥርም ሆነ የሥራ ግብርና ጡረታ የሚከፈለው በዚሁ በእድሩ መለያ/ቲን/ እንደሆነ ሰነዶቹ ያመለክታሉ፡፡ እ.አ.አ. በ2017 የተደረገ የሥራ ቅጥር ውል ላይም ይኸው የእድሩ ማህተም ያረፈ ሲሆን፤ የመምህሩ ወርሃዊ ደመወዝም 2 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንደሆነ ያሳያል፡፡ የትምህርት ቤቱ ክፍያም በየዓመቱ የተለያየ ሲሆን፤ የ2018/2019 የትምህርት ዘመን በሩብ ዓመት /በተርም/ ወይንም ለሁለት ወር ከግማሽ ለቅድመ መደበኛ ከ 17 ሺህ 200 ብር ጀምሮ ለ12 ክፍል 33 ሺህ 650 ብር ነው፡፡
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽሕፈት ቤት ተቋሙ ተከስሶ ለፌዴራል
መጀመሪያ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ሁለተኛ የሥራ ክርክር ችሎት በቀን 22/11/2008 ዓ.ም. በመዝገብ ቁጥር ቂ/ክ/ን/ጽ/ቤት 343/08 በላከው ደብዳቤ በክፍለ ከተማው የመረጃ ቋት ውስጥ ያልተመዘገበ መሆኑን የላከበት ደብዳቤ ሌላው የተመለከትነው ሰነድ ነው፡፡ በተመሳሳይ በክፍለ ከተማው የወረዳ 01 ሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ለችሎቱ በመዝገብ ቁጥር ቂ/ክ/ከ/ወ01/ሰ/ማ/ጉ/ጽ/ቤት/299/08 በቀን 21/11/08 ዓ.ም በላከው ደብዳቤ እድሩ ሕጋዊ ፍቃድ ያለውና የተመዘገበ መሆኑን ማሳወቁ ይነበባል፡፡ ነገር ግን ትምህርት ቤቱ በወረዳው ቢገኝም በአስተዳደሩ የማይታወቅና ያልተመዘገበ መሆኑን ገልፆ መላኩ በደብዳቤው ሰፍሮ ይታያል፡፡
በተለያዩ ወቅቶች ሠራተኞች ምቹ የሥራ ሁኔታ እንደሌላቸው የላኩባቸው ሰነዶች ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ በቀን 26 ሕዳር 2009 ዓ.ም በቁጥር 66/2/3/1/12 ለትምህርት ቤቱ የላከው ደብዳቤ ከሰነዶቹ መካከል ይገኛል፡፡ በደብዳቤው የሥራ ውል፣ የሥራ ደንብ፣ የሠራተኛ ዝውውር፣ የሥራ ሰዓት እንዲሁም በምግብ ዝግጅት ሠራተኞች የሥራ ሁኔታን አስመልክቶ ቢሮው ያገኛቸውን ግኝቶች በዝርዝር አስፍሯል፡፡ በዚህም በአዋጅ 377/96 መሠረት መከበር ያለባቸውና የተጣሱ አሰራሮች መኖራቸውን ጠቅሶ እንዲስተካከሉም ለትምህርት ቤቱ ልኳል፡፡
ለውጭ አገር ሠራተኞች ውሉ በመልካም የሚታይ ቢሆንም ለኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ግን የሥራን ባህርይ መሠረት ያላደረገ የሥራ ውል መኖሩ፣ የሥራ ደምቡ ሁሉም ሠራተኞች ሊረዱት በሚችሉት ቋንቋ አለመደረጉ፣ የደመወዝና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን በሚያሳጣ መልኩ የሥራ ዝውውር መኖሩ፣ በሕጉ መሠረት ማንኛውም ሠራተኛ ሊሰራ የሚገባው በቀን ከስምንት በሣምንት ደግሞ ከ48 ሰዓታት አይበልጥም በሚል ቢደነገግም በተቋሙ ግን በወር 240 ሰዓታት የሚሠሩ እንዳሉና በሕዝብ በዓላት ቀናት ጭምር ሠርተው የትርፍ ሰዓት ክፍያ የማይፈፀምላቸው ሠራተኞች መኖራቸውን ማረጋገጡንና መታረም እንዳለበት ቢሮው ለትምህርት ቤቱ በላከው ደብዳቤ ማሳወቁን ሰነዱ ያሳያል፡፡
ትምህርት ቤቱ
በግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊ አቶ ወሰን ውበት፤ ትምህርት ቤቱ ሁለት ክፍሎች እንዳሉት በማንሳት የግሪክ ክፍሉ በግሪክ መንግስት ስር የሚተዳር ሲሆን፤ የእንግሊዝ ክፍሉ ግን የካምብሪጅ ስርዓተ ትምህርትን በመከተል እንደሚሠራ ያብራራሉ። ትምህርት ቤቱ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የመማር ማስተማር ሒደቱም በጥሩ ሁኔታ ይካሄዳል፡፡ በእርግጥ ድርጅቶች ውስጥ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም እርሳቸው ወደ ተቋሙ በመጡበት ሦስት ዓመታት ግን ጎልቶ የታየ ችግር አለመኖሩን ነው የሚገልጹት፡፡ የግሪክ ክፍሉ የሚመራው በሌላ ሰው በመሆኑ ብዙ ማለት እንደማይችሉ የሚገልጹት አቶ ወሰን፤ እንግሊዝ ክፍሉ ላይ ግን 1 ሺህ 100 ተማሪዎች እንደሚማሩ ይናገራሉ፡፡
የትምህርት ቤቱ ትክክለኛ መጠሪያ ግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት እንደሆነ የፍቃድ ምስክር ወረቀቱን በመመልከት ነግረውናል፡፡ ይህን በመመልከት ፍቃድ ከተሰጠበትና መንግስት ከሚያውቀው ሥያሜ በተጨማሪ ሌሎች ሥያሜዎቹ ታዲያ ከየት መጡ? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ የመረዳጃ እድሩን እንደሚያውቁት ነገር ግን ከትምህርት ቤቱ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ ‹‹ዝርዝሩን ግን በጥልቀት የማላውቀው ጉዳይ ስለሆነ ባልናገረው እመርጣለሁ›› ብለውናል፡፡ ፍቃዱ የተሰጠው ግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት በሚል ነው፡፡ ነገር ግን የሠራተኞች የሥራ ግብርና ጡረታ የሚከፈለው ደግሞ በዚሁ በመረዳጃ እድሩ በኩል ነውና ይህ ከአሠራር አንፃር ተገቢ ነውን? እርስዎ እንደገለጹልን እድሩ ከተቋሙ ጋር ግንኙነት ከሌለው የሠራተኛ ቅጥሮችንና የሥራ ግብርና ጡረታዎችን ስለምን በእድሩ ሥም መክፈል አስፈለገ? ስንል ዳግም ላቀረብንላቸው ጥያቄ ‹‹ይህንን አላውቅም›› የሚል ምላሽን ሰጥተውናል፡፡ እድሩ ለግሪክ ክለብ፣ ትምህርት ቤቱ ስር ላሉት እንግሊዝና ግሪክ ክፍሎች እንደ ጥላ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡
ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት ነው ከተባለ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ግሪካውያን ማሕበረሰብን ብቻ ነበር ማስተማር የነበረበት፡፡ ከዚህ አንፃር ትምህርት ቤቱ ለሌሎች ዜጎች ትምህርት እየሰጠ ይገኛልና ያስኬዳል
ወይ? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ አቶ ወሰን፤ ሁሉም የውጭ ዜጋ ገብቶ መማር እንደሚችል በምላሻቸው ያስረዳሉ፡፡ ዋናው ተልዕኮው የግሪክን ማሕበረሰብ በመሆኑም በደመወዝና በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች እየረዳ ይገኛል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር በሰጠው መመሪያ መሠረት ሁሉም ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤቶች የሚያስገቡት ገቢ ከራሳቸው ፍጆታ የዘለለ አይደለም፡፡ የግሪክ የዘር ሐረግ የሆኑ 80 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ጡረተኞች አሉ፡፡ ለእነርሱ የሚከፈለው ክፍያም ከፍተኛ ስለሚሆን የሚያገኘውና የሚያወጣው ሲሰላ ተመሳሳይ ነው፡፡ ለትርፍ የተቋቋመ አይደለም፡፡ በብዛት በግሪክ ክፍሉ የሚማሩት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውንም ያምናሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህን ዕድል አግኝተው መማራቸው ታዲያ ወንጀሉ ምን ላይ ነው? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹የኪስ ቦርሳውን እስካላጠበበበት ድረስ የሠፈሩንስ ሠው ሰብስቦ ማኖር ቢችል ምን ችግር አለው?›› ይላሉ፡፡ አያይዘውም እንደሌሎች የኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤቶች ሁሉ ተቋሙም ግብር አይከፍልም፡፡
የቀጣይ የተማሪዎች ዕጣ ፈንታን አስመልክቶ አቶ ወሰን በሰጡት ምላሽ፤ በቁጥር ተጨባጭ መረጃ ማውጣት ከባድ ቢሆንም ከጥርስ ሐኪም እስከ የኤሜሪካ ብሔራዊ የጠፈር ምርምር ኤጀንሲ (ናሳ) ድረስ የገቡ ዕውቅ የትምህር ቤቱ ተማሪዎች እንዳሉ መዘንጋት አይገባም፡፡ ‹‹ብዙዎች ግሪክ አገር ሄደው ተምረው ትልልቅ ቦታ ላይ የደረሱ እንዳሉ ሁሉ ተንጠባጥበውና ተንዘላዝለው የወደቁም አሉ›› ይላሉ፡፡ ለችግሩ ዋነኛው ምክንያት ግን የግሪክ መንግስት ይሰጥ የነበረው ስኮላርሺፕ በሙሉ መቅረቱ ነው፡፡ በዓለም ደረጃ የተፈጠረው ቀውስ መጀመሪያ የሰባበራት ግሪክን በመሆኑ በትምህርት ቤቱ ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለ ይገልፃሉ፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት የእንግሊዝ ክፍሉ እየደገፈው እንደሆነና ወደፊት ሊስተካከል እንደሚችል ያላቸውን ዕምነት ያመላክታሉ፡፡ በዚህም ችግር ብዙ ግሪክ ክፍል ላይ ያሉ ተማሪዎች ያለምንም ክፍያ ወደ እንግሊዝ ክፍሉ እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡
አቶ ወሰን፤ ቅሬታ አቅራቢው ወጣት አበበ አስኮ መስመር በሚገኘው የግሪክ ኦርቶዶክስ ዘላቂ ማረፊያ ስፍራ ላይ ሥራ እንዲቀጠር እንዳደረጉ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ሥራን እንደሚበድል ሁለት የቅርብ ኃላፊዎቹ በደብዳቤ እንዳሳወቋቸው ብሎም በእርሳቸው በኩል ማስጠንቀቂያ ሰጥተውትም እንደነበር በመናገር የቅጥር ውሉን አውጥተው ሲያሳዩን ቀጣሪ ድርጅት በሚለው ቦታ ላይ የመረዳጃ እድሩ ሥም ሰፍሮ ተመለከትን፡፡ እድሩ ከትምህርት ቤቱ ጋር ግንኙነት የለውም ብለውን ነበርና ታዲያ እዚህ ላይ ለምን ሰፈረ ስንል? ‹‹እሱን እንተወው፤ ሥያሜ ለውጥ አያመጣም›› በሚል መልሰውልናል፡፡
ተበደልኩ የሚል አካል ሥራውን በአግባቡ እየሠራ በደሉን ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይችላል፡፡ ‹‹የወሲብ ጥቃቱን አስመልክቶም ወደ ሕግ አካል ቀርቦ በማስረጃ መጠየቅ እየተቻለ ይኼን ያክል ኡኡታ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም›› ይላሉ፡፡ በመሆኑም ቅሬታው ከሥም ማጥፋት የዘለለ አይደለም በማለት ይኮንኑታል፡፡ ከትምህርት ዕድል መነጠቅ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን አስመልክቶ ወጣት አበበን ለአብነት በማንሳት ሥራ ከመቀጠሩ በፊት የትምህርት ቤቱ ዋና አመራር በየጊዜው እንደ አባት ድጋፍ ያደርጉለት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ግለሰቡም ሥብዕናቸው የተመሰገነ በመሆኑ የእርሱንም ሆነ የሌሎችን የትምህርት ዕድል የመንጠቅና ለሌላ አሳልፈው ይሰጣሉ ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ፡፡
ከሠራተኛ ቅጥር ጋር ተያይዞም ከውጭ ገበያ ላይም ሆነ በአገር ውስጥ የገቡ የውጭ ዜጎችን ቅጥር ለመፈፀም በአገር ውስጥ ዋጋ መቅጠር አይቻልም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሠዎች የተሻለ ጥቅም ለማግኘት ነው ከአገራቸው የሚወጡት፡፡ ስለዚህ ክፍያው ተገቢ ነው፡፡ ከደመወዙ ውጭ ግን የተቋሙን ሠራተኞች በእኩል መንገድ እንደሚስተናግዱ በመግለጽ የቀረበው ቅሬታ ትክክል እንዳልሆነ ያብራራሉ፡፡ በተቋሙም ለሥራ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረ በእረፍት ሰዓትም ሻይ፣ ቡናና ኬክ እንደሚሰጥ አክለው ያብራራሉ፡፡
ከሠራተኛ አያያዝ ውጪ ሌላው ቅሬታ የግሪክ ክፍሉ ላይ ተማሪዎች አመጋገብ ቢሆንም የተሻለ ምግብ እንደሚዘጋጅላቸው ነው ኃላፊው የሚናገሩት፡፡ ተማሪዎቹ በግሪክ ምግብ አዘጋጅ እንደሚዘጋጅላቸውና ሚኒስቶሮኒ፣ ዳቦ፣ ቺዝ፣ ወተት ስለሚሰጣቸው በምግብ ላይ ምንም ዓይነት ችግር የለም ይላሉ፡፡ ሲተችም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መሆን ይኖርበታል፡፡ ግለሰቦች በራሳቸው ድክመት በሚደርስባቸው ውድቀትም ሌሎችን ተጠያቂ ማድረግ ትክክል አይደለም፡፡ የወሲብ ትንኮሳና ጥቃቱን በተመለከተም የደረሰ ልጅ የደረሰችን ልጅ ሊከጅል ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን መምህር ተማሪውን በፆታዊ ግንኙነት ትንኮሳ ያደረሰበትና የቀረበ ቅሬታም ሆነ የተወሰደ እርምጃ የለም፡፡ በግሪክ ክፍሉም ላይ የወንድ መምህር እንደሌለና ከዳይሬክተሩ ውጪ ሴቶች እንደሆኑ ነው የሚገልጹት፡፡ ቄሶቹስ ቢሆኑ ወደ ትምህርት ቤቱ ምን ሊያደርጉ ይመጣሉ? በማለት ተማሪዎቹ ቄሶቹን የሚያገኟቸው በሣምንት አንድ ቀን ለአምልኮ ወደ ቤተክርስትያን ሲሄዱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ከኃላፊው ጋር የነበረንን ቆይታ እንደጨረስንም የግሪክ ተማሪዎቹን ማደሪያ እንዲሁም መመገቢያ ለመመልከት ችለናል፡፡ በጉብኝታችንም የመኝታ ክፍላቸው እንዲሁም መመገቢያቸው ጽዱና ማራኪ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ሆኖም ግን የወንዶቹ መኝታ ክፍል ከመምህራኑ መኝታ ክፍል ጋር አጠገብ ለአጠገብ መሆኑን ታዝበናል፡፡ በተያያዘ ኃላፊው በምላሻቸው ከነገሩን በተቃራኒው በትምህርት ቤቱ ከሚሠሩ ሠራተኞች ማረጋገጥ እንደቻልነው፤ አምስት ወንድ ግሪካውያን መምህራን እንደሚገኙና ቄሶቹም ዘወትር ወደ ትምህርት ቤቱ እንደሚሄዱ ነው፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር
በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ አስፋው መኮንን፤ የግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት ለረጅም ዓመታት በሥራ ላይ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤቱ ሲቋቋም በዋናነት አገልግሎቱን የሚሰጠው በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ ለግሪክ ዜጎች ነው፡፡ ትምህርቱንም በግሪክ አገር ስርዓተ ትምህርትና መመዘኛ ነው እንዲሰጥ የሚጠበቀው፡፡ ስለዚህ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት ሲባል የዛን አገር ማሕበረሰብ ለማስተማር ብቻ የሚቋቋም ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ተቋቁመው ተማሪዎች በማጣታቸው የተዘጉ ተቋማትም አሉ፡፡
ሚኒስቴሩ ድጋፉን የሚያደርገው መምህራኖችን ከውጭ አገር በቅጥር ለማምጣት ሲፈልጉ ወይንም እዚህ ሆነው በበጎ ፈቃድ የሚሠሩ ካሉ የመግቢያ ቪዛ እንዲሰጣቸው ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይጽፋል፡፡ ከገቡ በኋላ ደግሞ የመኖሪያ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ለሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያሳውቃል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግሪክ የሚኖር ኢትዮጵያዊ በንግድም ሆነ በዲፕሎማሲ ብዙ ዓመት እዚያ ኖረው በግሪክ አገር ሥርዓተ ትምህርት ልጆቻቸው ሲማሩ ከቆዩ በጀመሩበት ትምህርቱን እንዲጨርሱ ይደረጋል፡፡ ይሄ በተለየ ሁኔታ ሲሆን፤ ዋነኛ ተልዕኮው ግን በኢትዮጵያ የሚኖሩ ግሪክ ማሕበረሰብን አገልግሎት መስጠት ነው፡፡
የግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት አንዱ ክፍል የእንግሊዝ በመሆኑ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ሥርዓተ ትምህርት ልክ መሆኑን ከእንግሊዝ አገር በመምጣት በየጊዜው ይገመግማል፡፡ የእነርሱን ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ማሟላቱን በአደረጃጀቱና በአሠራሩ በመመዘን ዕውቅና ይሠጡታል። ተቋሙም ፍቃድ ለማደስ ወደ ሚኒስቴሩ ሲመጣ ይህ ይረጋገጣል። ሌላው ደግሞ ለግሪካውያን ለብቻ በግሪክኛ ቋንቋ የሚሰጥ ትምህርት አለ። ሚኒስቴሩ በሙያው የሰለጠነ መምህር መሆኑን፣ የብቃት ማረጋገጫ ምዘና መውሰዱንና ብቁ መሆኑን ክትትል ያደርጋል፡፡ እንዲሁም በአገሪቱ የመሥራት የእድሜ ጣሪያ 60 በመሆኑ ከዚህ በታች መሆኑ ተረጋግጦ የትብብር ደብዳቤውን ይጽፋል፡፡
የግሪክ ትምህርት ቤት እንግሊዝኛ ክፍሉ ግሪካውያንን ብቻ ሳይሆን ከ52 አገራት የመጡ ዜግነት ያላቸው ተማሪዎችን ያስተምራል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያውያንም እንደሚማሩ ያስረዳሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚገቡበት የተለያየ ምክንያት ያለ ሲሆን፤ ለአብነት በንግድና በተለያዩ ምክንያቶች በውጭ አገር ትምህርት ጀምረው የሚመጡ ተማሪዎች በተመሳሳይ ሥርዓተ ትምህርት መጨረስ አለባቸው በሚል ሚኒስቴሩ ሲጽፍ ይቀበላቸዋል፡፡ በተመሳሳይ አንድ ኢትዮጵያዊ አንድ ልጅ ውጭ አገር ወልዶ ልጁ በውጭ ሥርዓተ ትምህርት ጀምሮ ከመጣ ትምህርት ቤቱ እንዲቀበለው ይደረጋል፡፡ በኢትዮጵያ የተወለደ ወንድም ወይንም እህት ሲመጣ እነርሱም ይጻፍላቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በአንድ ቤት ውስጥ በሁለት የተለያየ ሥርዓተ ትምህርት መማር በልጆች ሥነልቦና ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ይኖራል በትምህርት አቀባበላቸው ላይም ክፍተት ይፈጥራል ተብሎ በመታመኑ ነው፡፡
ከትምህርት ቤቱ ተልዕኮ አንፃርና ግሪክ ሴክሽኑ ላይ ሙሉ በሙሉ የሚማሩት ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ቅሬታዎች ይቀርባሉና በዚህ ላይ ምን ይላሉ? ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ አቶ አስፋው ጉዳዩን አስመልክቶ ቅሬታ ወደ ሚኒስቴሩ መቅረቡን ያምናሉ፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግም የባለሙያዎች ቡድን ሄዶ አጣርቷል፡፡ ቅሬታው በግሪክ ቋንቋ ይማራሉ በኋላም ወደ ትምህርት ቤቱ ከሚገቡት ውስጥ ሁሉም ለውጭ ትምህርት አይላኩም፡፡ ይህም በግሪክ ቋንቋ ተምረው በአገር ውስጥ ትምህርታቸውን መቀጠልም ሆነ ሥራ መቀጠር እንደማይችሉና በዛው በትምህርት ቤት ውስጥ በተለያየ የጉልበት ሥራ ላይ እንደሚቀጠሩና እንደሚያገለግሉ ቅሬታ ቀርቧል፡፡ በትምህርት ቤቱ የቅሬታውን ትክክለኛነት ለማጥራት የሄደው የባለሙያዎች ቡድንም ይህንኑ ትክክለኛ መሆኑን አውቋል፤ ማረጋገጥም ችሏል፡፡
የቀረቡ ቅሬታዎችንና ባለሙያዎች ያረጋገጡትን ግኝት በመያዝም ሚኒስቴሩ የትምህርት ቤቱ አመራሮች፣ የቦርድ አባላትና ሚኒስትር ዴኤታው በተገኙበት ውይይት ተደርጓል፡፡ በመድረኩ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህራንና ሌሎች አመራሮች ለእረፍት ወደ ግሪክ አገር በመሄዳቸው ሊገኙ አልቻሉም፡፡ ሆኖም የቦርዱ ፀሐፊና በትምህርት ጉዳይ ላይ የሚሠሩት ተወካይ እንዲሁም አንድ የቦርድ አባል ተገኝተው አጠቃላይ ስለ ትምህር ቤቱ ሁኔታና ቡድኑ ይዞ ስለመጣቸው ግኝቶች ውይይት ተደርጓል፡፡ በወቅቱ ዋናዎቹ ሲመለሱ እንዲያሳውቋቸውና በጥልቀት ጉዳዩን ተመልክተው ሁለተኛ ዙር ውይይት እንደሚደረግ የቤት ሥራ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የሱፐርቪዥን ሪፖርት ላይ ያለው ዝርዝር ጉዳይ በጽሁፍ ግብረመልስ ተሰጥቷል፡፡
ቅሬታው ከመጣና ችግሩ እንዳለ ሚኒስቴሩ ካረጋገጠ ስለምን እርምጃ መውሰድ ተሳነው? ለአቶ አስፋው ያነሳንላቸው ጥያቄ ነበር፡፡ ዳይሬክተሩም በምላሻቸው፤ ‹‹እርምጃ ዝም ብሎ መውሰድ አስቸጋሪ ነው፡፡ ግሪክ ክፍሉ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሚኒስቴሩ ይቸገራል፡፡ የትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ከመጡ በኋላ ውይይት በማድረግ ከቆንስላውና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በጥልቀት የሚታይ ነው፡፡ በችኮላ የሚወሰዱ እርምጃዎች የሁለቱን አገራት ግንኙነት ሊያበላሹ ይችላሉና በመንግስት ከፍተኛ ደረጃ ውሳኔ የሚሰጠው ይሆናል ›› ብለዋል፡፡
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንደሚለውም ከውስጥ ወደ ውጪ በመሆኑ ቅድሚያ ለአገሩና የዜጎቹን ሁለንተናዊ ጥቅም ማስጠበቅ ላይ ያተኩራል፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ያሻክራል በሚል እሳቤ ዝምታን መምረጥ ተገቢ ነውን? ለዳይሬክተሩ ያቀረብንላቸው ሌላው ጥያቄ ነበር፡፡ እርምጃ ሲወሰድ የጋራ መሆን ይኖርበታል፡፡ ተቋሙም የመንግስትን ሐሳብ ማወቅ፤ መንግስትም ደግሞ እነርሱ የሚያነሱትን ሐሳብ ማድመጥ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ችግር በምን አግባብ ይስተካከላል? ካልሆነስ ምን መደረግ አለበት? የሚለው በጋራ ሊወሰንበትና ዕውቅና ሊወሰድበት ይገባል በሚል እንጂ ጉዳዩን ቸል ለማለት እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡
ትምህርት ቤቱ አራት የተለያየ ዓይነት ማህተም መጠቀሙን አስመልክቶ ተቋሙ አንድ በመሆኑ ሊጠቀም የሚገባ የነበረውም አንድ መለያ ሥም ነበር፡፡ ሚኒስቴሩም የሥራ ፍቃድ ሲሰጥ ግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት እንጂ ሌላ ሥሞቹን አያውቅም፡፡ እድር ግን አለው። እድር ደግሞ ሚኒስቴሩን አይመለከትም ይላሉ፡፡ ዋናዎቹ ባለቤቶች ሲመጡ ውይይት እንደሚደረግበትም ይናገራሉ፡፡ ተቋሙም የተለያዩ አገልግሎቶችን ከሚኒስቴሩ ፈልጎ ሲጠይቅ ግሪክ ኮሙዩኒቲ በሚል ሥም ነው፡፡ ዕድሩን በተመለከተም ዕድሩን በአመራርነት የሚያገለግል ከግሪክ አገር የሚመጣ ሰው እንዲገባ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ሚኒስቴሩ ክትትል ሲያደርግ፤ የትምህርት ቤቱ መምህራን የአስተዳደር ሠራተኞች ሙሉ ዝርዝራቸውን ኢትዮጵያውያን ምን ያክል እንደሆኑና ከውጭ አገር ዜግነት ያላቸውስ ምን ያክል ናቸው? የሚለውን የሚኒስቴሩ ባለሙያዎች ይመለከታሉ፡፡ ገንዘብ መቆረጡንና ለሚመለከተው አካል መግባቱንም ያረጋግጣል፡፡ የተቋሙ ሠራተኞችም የስራ ግብርም ሆነ ጡረታ በትምህርት ቤቱ ሥም ነው ሊቆረጥባቸው የሚገባው፡፡ ይህን መሠል ወጣገባነት ካለም ለምን ክፍተት እንደተፈጠረ ተቋሙ ይጠየቃል፡፡
በርካታ የግልና ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤቶች እየተዘጉ ይገኛሉ። በግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት የሚማሩትም አብዛኛውን የውጭ አገር ዜግነት ያላቸውና ኢትዮጵያውያን እንጂ ግሪካውያን አይደሉም፡፡ በእንግሊዝኛው ክፍል እየተማሩ ያሉትም በካምሪጅ ሥርዓተ ትምህርት እየተማሩ ያሉ በመሆኑ ይህንን ሥራ ወደ የውጭ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ሊወስዱት እንደሚገባ ሚኒስቴሩ ለተቋሙ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ሚኒስቴሩ ተቋሙን ሥርዓት ለማስያዝና ጉራማይሌ አሠራሩን በሕግ ወደ መስመር ማስገባት ይጠበቅበታል፡፡ለዚህ ግን የግል ትምህርት ቤቶች አዋጆች ሕጎችና መመሪያዎች መስተካከልና ወጥነት ያለው አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡ መመሪያውን የማሻሻል ሥራ መሥራትንም ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ቀደም ግልጽ መመሪያ አለመኖሩ ለዚህ መሠል ክፍተቶች ይዳርጋልም ይላሉ፡፡
የወሲብ ጥቃትን አስመልክቶ ከትምህርት ቤቱ ጋር በተደረገ ውይይት የተማሪዎች ሥነምግባር የሚል ጉዳይ ተነስቶ ነበር፡፡ በዚህም ተቋሙ በጉዳዩ ላይ ከወላጆች ጋር እንደሚነጋገርና በዚህ ጉዳይ ላይ ያሉ ነገሮችንም እየተከታተሉ እርምት እየወሰዱ እንደሆነ ከሚኒስቴሩ ጋር በነበራቸው የውይይት መድረክ መግለፃቸውን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ችግሩ በሚባለውና ቅሬታ በቀረበበት ደረጃ አለመሆኑን ተቋሙ መግለጹንም ይናገራሉ፡፡ በእንግሊዝ ክፍሉ ላይ ሁለት ተማሪዎች ክፍል ውስጥ ወሲብ ሲፈጽሙ መታየታቸውን ተከትሎ በትምህርት ቤቱ ችግር አለ ተብሎ ጉዳዩ ወደ አሉባልታ እንደተቀየረም ማስረዳታቸውን ይናገራሉ፡፡
በግሪክ ክፍሉ ላይ የሚነሳውን ተመሳሳይ የወሲብ ጥቃት ችግር አስመልክቶ ዳይሬክተሩ ምላሻቸውን ሲሰጡ፤ ይህን መሠሉ ችግር ውስብስብ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ የድርጊቱን ዕውነታነት የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ላይገኝም ይችላል፡፡ ቡድኑ ሲሄድም ቅሬታውን ሊያጣራ ሞክሮ ነበር፡፡ ሆኖም ግን የቡድኑ አባላት ቸግሯቸው ነው የተመለሱት፡፡ ትምህርት ቤቱ ሲጠየቅም በፍጹም ድርጊቱ እንደማይፈፀምና የትምህርት ቤቱን ሥም ለማጥፋት የሚደረግ ነው በሚል መልሷል፡፡
አንዳንድ የተማሪ ወላጆችም በጉዳዩ ላይ የሚያነሱት ሐሳብ አለ፡፡ ወላጆችም ለሚኒስቴሩ ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። በዚህም ከግሪክ ክፍሉ በተጨማሪ በእንግሊዝ ክፍሉም በትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ሥነምግባር ላይ ችግር አለ በሚልና የተማሪዎችን በደንብ አለመያዝ፣ የወሲብ ትንኮሳ መኖሩንም ወላጆች አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን የወሲብ ትንኮሳ ጥቃት የደረሰበት ሠው መረጃ በመስጠት ካላገዘ በስተቀር በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሚኒስቴሩ የተቋሙ የበላይ አመራሮች ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ጉዳዩን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያየዋል፡፡ ለዚህም ከወረዳው ጀምሮ እንዲያግዙ መደረግ አለበት፡፡ ከአደገኛ ዕፅ ዝውውር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችም በመኖራቸው በተጨባጭ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ ካልተሰጠ በስተቀር ሚኒስቴሩ በዓመትና በሁለት ዓመት በሚያደርገው ክትትል ብቻ ይህን መሠል ችግር መያዝ አይችልም፡፡ የተቀናጀ ሥራንም የሚጠይቅ ነው፡፡ ቅሬታው በተደጋጋሚ የተነሳ በመሆኑም ተቋሙ ራሱን ፈትሾ፣ አጣርቶና እርምጃ ወስዶ ሪፖርት እንዲያደርግ ሚኒስቴሩ አሳውቆታል፡፡
ቀጣይም የእርምት እርምጃ የሚወሰደው ግለሰብ ላይ እንጂ ተቋምን መዝጋት ጠቀሜታ የለውም፡፡ በመሆኑም ከመማር ማስተማር ውጪ በሆነ ተግባር ላይ የተሳተፈና ተግባሩ ሲፈፀም ዝም ብሎ የተመለከተ የድርጊት ተባባሪ የትምህርት ቤት አመራር ላይ የእርምት እርምጃ ይወሰዳል፡፡ የውጭ አገር ዜግነት ያለው በተግባሩ ተሳታፊ ከሆነና ችግር ካለበት ተቋሙ ግለሰቡን እንዲያሰናብት ሚኒስቴሩ ይመክራል፡፡ የከፋ ችግር ውስጥ ተሣታፊ ሆኖ ከተገኘም በኢትዮጵያ ሕግ ተጠያቂ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ ይህን ለማድረግ ግን ተጨባጭ መረጃና ማስረጃዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡
ሲጠቃለል
ትምህርት ቤቱ ኮሙዩኒቲ በመሆኑ ሊያስተምር የሚገባው በኢትዮጵያ የሚኖሩ የግሪክ ማሕበረሰብን እንደነበር የሚመለከታቸው አካላት ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት በተለይም በግሪክ ክፍሉ የሚማሩት ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ታምኗል፡፡ በዚህ መሐል ደግሞ ተቋሙ በኮሙዩኒቲ ሥም በመመዝገቡ ከእንግሊዝ ክፍሉ ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገባ ቢታወቅም ግብር ከፋይ ግን አይደለም፡፡ ተያይዞም የተለያዩ ሥያሜዎችን ይጠቀማል፤ ክፍያውንም የሚፈጽመው በመረዳጃ እድሩ ሥም ነው፡፡ በሌላ በኩል ከግሪክ ይሰጥ የነበረው የትምህርት ዕድል በመቆሙና በትምህርት ቤቱ የሚማሩበት ቋንቋ የግሪክ በመሆኑ ዜጎች በአገሪቱ ውስጥ ተምረውም ሆነ ሠርተው የመለወጥ ተስፋቸው የመነመነ መሆኑን የቀረበውን ቅሬታ ሚኒስቴሩም በማመኑ የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 1/2011
ፍዮሪ ተወልደ
Intel’s latest unveiling of standard high-speed connectivity promises to revolutionize the way we connect and interact with technology. By enhancing data transfer speeds and reducing latency, this innovation is set to improve everything from cloud computing to everyday internet usage. https://smartcityconsultant.com/2024/04/18/seco-com-express-type-6-module/
If you start using EluRyng after an abortion or miscarriage viagra priligy
Профессиональный сервисный центр по ремонту бытовой техники с выездом на дом.
Мы предлагаем: сервис центры бытовой техники москва
Наши мастера оперативно устранят неисправности вашего устройства в сервисе или с выездом на дом!
Профессиональный сервисный центр по ремонту компьютеров и ноутбуков в Москве.
Мы предлагаем: чистка macbook pro 16
Наши мастера оперативно устранят неисправности вашего устройства в сервисе или с выездом на дом!
Rugo H, Kabos P, Dickler M, John W, Smith I, Lu Y, et al [url=https://fastpriligy.top/]priligy over the counter usa[/url] It is also reassuring to see that one single algorithm cannot be used to treat every type of cardiovascular instability in the intensive care as it may lead to harm or benefit depending on the type of patient treated