የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያን ህዳሴ እውን ለማድረግ የቆመ ግዙፍ ተቋም ነበር። ተቋሙን ዕውን ለማድረግም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ፈሷል።12 ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም በስሩ ከ96 በላይ ፋብሪካዎችን ይዟል በማለት የተቋሙ ኃላፊዎች ሲናገሩ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ የስኳር ፋብሪካዎችን፣ የያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክትንና ሌሎችንም ተግባራዊ ለማድረግ ኃላፊነት ወስዶ ሲሰራ ነበር።
ዛሬ በኮርፖሬሽኑ ላይ ተጥሎ የነበረው እምነትና ተስፋ የጠለቀ ይመስላል። የያዛቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች “መስራት አልችልም” በማለት አስረክቧል። በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብም ባለዕዳ ሆኗል። ኮርፖሬሽኑ ባለበት ዕዳ፣ እየተከናወኑ ባሉ የማሻሻያ ሥራዎችና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከዋና ዳይሬክተሩ ብርጋዴር ጀነራል አህመድ ሀምዛ፤ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ ወደ ተቋሙ መቼ መጡ? ከየትኛው ተቋም ነው ወደዚህ የተዛወሩት?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ የመጣሁት ሚያዚያ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ነው። በተቋሙም ምክትል ዋና ዳይሬክተር ነበርኩ።
አዲስ ዘመን፦ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ምን ሰሩ?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ ሥራ እንደጀመርኩ አምስት ቡድኖችን በማደራጀት በመልካም አስተዳደር፣ በፋይናንስ፣ በፕሮጀክት አስተዳደር፣ በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ፤ በግብይትና ሽያጭ ላይ የነበሩ ችግሮች ተጠንተው እንዲለዩ አድርጌያለሁ። ጥናቱን መነሻ በማድረግም የማሻሻያ እቅድ ተዘጋጅቶ ከባለፈው ታህሳስ ወር ጀምሮ እየተገበረ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በፋይናንስ ጥናታችሁ ምን አገኛችሁ?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ የፋይናንስ አሰራሩ የተቀናጀ አይደለም። የተሟሉ መረጃዎችም የሉም። ተቋሙ ዕዳውን፣ ተሰብሳቢውንና ሀብቱን አያውቅም። በየጊዜው ያሉ ሪፖርቶችም የተለያዩ ናቸው። በዚህ የተነሳ ተቋሙ ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ገብቷል። በድምሩ ኮርፖሬሽኑ የመንግሥት የፋይናንስ አሰራር አልነበረውም።
አዲስ ዘመን፦ የተጠናቀቀው የኦዲት ውጤት የሚያሳየው ምንድን ነው?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ የ6 ዓመታቱ ኦዲት የሚያሳዩት እንዴት እንደሰሩት አስተያየት ለመስጠት እንደሚያስቸግር ነው። በየጊዜው ኦዲት ሲደረግ የሚታዩ ችግሮች እየታረሙ ስላልመጡ ችግሩ ተደራራቢ ሆኗል።
አዲስ ዘመን፦ የፕሮጀክት አስተዳደርን በተመለከተ ጥናታችሁ ምን አሳየ?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ የፕሮጀክት አስተዳደራችን ስልት የለውም። ገንዘብ ይመጣል እንደተፈለገ ይወጣል። ያልታቀደና ያልተቀናጀ የፕሮጀክትና የሀብት አስተዳደር ስርዓት ነበረ። ከፕሮጀክት ባለቤቶችም ጋር መልካም ግንኙነት አልነበረንም። በመወጋገዝ፤ በመሰዳደብ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጥናቱ አረጋግጧል።
ፕሮጀክት ከሰጡን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ከኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽንና ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር መልካም ግንኙነት አልነበረንም። የእኛ ተቋም ተቋራጭ ሳይሆን ባለቤት ይመስል ነበር። የስኳር ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ወደ ፋብሪካው እንዳይገቡ ተከልክለው ነበር።
አዲስ ዘመን፦ በኮርፖሬሽኑ የነበረው የመልካም አስተዳደር ችግር ምን ነበር?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ ፦ የመጀመሪያው በሠራተኛው የሚነሳው የመልካም አስተዳደር ችግር በምን ህግ ነው የምንመራው የሚል ነው። በአሰሪና ሠራተኛ፣ በመከላከያ ወይስ በሲቪል ሰርቪስ ህግ ነው የምንተዳደርው የሚል ጥያቄ ነበራቸው። በጥናታችን የሰራተኛው ጥያቄ እውነት መሆኑን ከማየታችንም በላይ የህግ መደበላለቅ እንደነበር ተገንዝበናል።
ሌላው በሠራተኛው የተነሳው ቅጥር በቤተሰብ ነው የሚል ሲሆን፤ ይህም እውነት ሆኖ አግኝተነዋል። ለምሳሌ የታጋይ፣ የወታደር ልጅ በማለት የተቀጠሩ አሉ። የሰው ኃይል አስተዳደር ዳይሬክተሩ ልጁን ቀጥሮ አግኝተናል። ይህ በየትኛውም የመንግሥትም ሆነ የልማት ድርጅት አሰራር አይታወቅም። ይህን አሰራር ለመፍታት እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን ፦ በውሸት የትምህርት ማስረጃ ሰዎች እንደሚቀጠሩ ይነገራል። ይህ ምን ያህል እውነት ነው?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ ይህንን ለማጣራት በከፊል አማራ፣ ትግራይና ሱማሌ ክልል ካሉ ተቋማቶቻችን ውጭ ባሉት ላይ ባደረገነው ማጥራት 179 ሰዎች በሀሰት የትምህርት ማስረጃ ተቀጥረው ተገኝተዋል። ከነዚህ ውስጥ 12ቱ ወታደሮች ናቸው።
አዲስ ዘመን፦ ቴክኖሎጂን በማልማት ሂደት የተገኘው ችግር ምንድን ነው?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ ኮርፖሬሽኑ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ የነበሩ ብዙ ቴክኖሎጂዎች አሉት። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ፕላስቲክ ኢንዱስትሪ በንጉሱ ጊዜ የተቋቋመ ሲሆን ፣ጋፋት፣ ሆሚቾ፣ ደጀን አቪዬሽን፣ አቃቂ ቤዚክ ሜታል፣ ህብረት ማኒፋክቸሪንግ፣ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ በደርግ ዘመን የተቋቋሙ ናቸው። በጥሩ ደረጃ ላይ ያሉም ነበሩ። የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭን ብንመለከት ብዙ ነገሩ የተሰራው በደርግ ጊዜ ነው። አሁን ላይ ብዙም የተጨመረለት ነገር የለም።
ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመ በኋላ ፓወር ኢንጅነሪንግን ከፍቷል ከዚህ አንጻር በቴክኖሎጂ በኩል ኮርፖሬሽኑ ጥሩ ነገሮች ቢኖሩትም ወደ ሰው በመውሰድና በማገናኘት በኩል ግን ክፍተቶች ነበሩበት።
ሰዎች የሚሰለጥኑት ክፍተት ታይቶ ሳይሆን ጥቅምን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት መተግበሪያ አልነበራቸውም። ከዚህ አንጻር ቴክኖሎጂዎቹና ስልጠናው በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ አልዋሉም።
አዲስ ዘመን፦ ግብይትና ሽያጩ ምን ይመስላል?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ የገበያ ዳሰሳ ጥናት በማድረግ ክፍተቶችን ለይቶ ሽያጭ ማከናወን ዓላማው ቢሆንም ሲሰራ የቆየው ግን ያገኘውን ሁሉ በመሸጥና እቃ እያስመጣ በማከማቸት ላይ ነው።ይህ መሆኑ ደግሞ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የያዙ ንብረቶች በየቦታው ያለው ሲሆን፤ግን ደግሞ በካዝናው ውስጥ ምንም ገንዘብ የሌለው ተቋም ሆኗል። አሁን ላይ እንኳን እቃዎቹን ሸጦ ወደ ገንዘብ ለመቀየር ሂደቱ ከባድ ሆኗል።
አዲስ ዘመን፦ ኮርፖሬሽኑ ያለው ተሰብሳቢ ምን ያህል ነው?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ በእርግጠኝነት ተሰብሳቢያችን ምን ያህል እንደሆነ አይታወቅም። በመጀመሪያ ባደረግነው ጥናት 11 ቢሊዮን ብር ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በሰበሰብነው መረጃ 17 ቢሊዮን ደረሰ።
እንደገና ግብረ ኃይል በማቋቋምና በመዝገብ ላይ ተመስርተን ስንሰራው 12 ቢሊዮን ብር ሆነ። ይህንን መረጃ ይዘን “ያለብዎትን ዕዳ በመክፈል፤ የእርስዎ የሆነውን ኮርፖሬሽን ለውጥ ይደግፉ” በሚል ደብዳቤ ለባለእዳዎቹ የጻፍን ቢሆንም በአንድ ወር ዘመቻ ለመሰብሰብ ከተጻፈላቸው ባለዕዳዎች 40 ሚሊዮን ብሩን ለኮርፖሬሽኑ መክፈላቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ አቀረቡ። የተሰበሰበውን ገንዘብ መጠን ገና በትክክል አላወቅንም። መጥራት አለበት። ካለን ገንዘብ ሊሰበሰብ የማይችል ገንዘብ አለ።
አዲስ ዘመን፦ የማይሰበሰብበት ምክንያት ምንድን ነው?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ ከተሰብሳቢው ውስጥ ከ10 ዓመት በላይ የሆነው በይርጋ ስለሚታገድ ማስከፈል አንችልም። ባለዕዳዎች ይኑሩ አይኑረም አናውቅም።
ተሰብሳቢ ተብለው የተመዘገቡና መነሻ መረጃ ያጣንላቸው ከማን እንደሚጠየቁ፣ ለምን እንደሚሰጡና እስከአሁን የዘገዩበት ምክንያት ምን እንደሆነ የማይታወቁ በርካታ ናችው። ለምሳሌ እቃ ተሸጧል ተብሎ እኛ ያላቀረብናቸው። መሸጣቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ የሌላቸው አሉ። መረጃው ካልተሟላ ገንዘብን መሰብሰብ ካለመቻሉም በላይ የተሸጡት እቃዎች ባለመስራታቸው ክፍያ ያልፈጸሙም አሉ። በአጠቃላይ የተሰብሳቢ ገንዘብን ጉዳይ ገና አልጨረስነውም ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ ችግራችሁ የአሰራር ወይስ የመረጃ ማሸሽ ነው?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ መረጃ መሸሹን በእርግጠኛነት መናገር ባልችልም ከፍተኛ የአሰራር ችግር በመኖሩ ሰነዶች የጠፉ ይመስለኛል። በብሄራዊ ባንክ መወራረድ ያለበትና ከ 960 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ የያዘ ሰነድ በግለሰብ መሳቢያ የተገኘበት ተቋም ነው። አሰራሩ ዝርክርክ ስለነበር በማሸሽ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በእንዝላልነት የጠፉ ሰነዶች አሉ።
ስሙ የመንግሥት ይሁን እንጂ በየጊዜው ስለ ሥራው የሚያቀርበው ሪፖርት የለም። ኦዲት አይደረግም። የገንዘብ ወሰኑ አይታወቅም። የሆነ ሰው እንደፈለገ የሚያዝበትና የማፍያ አይነት አመራር የነበረው ነው። ለመንግሥትም የሚታዘዝ አልነበረም። መረጃ የመሸሹ ጉዳይ በህግ ስለተያዘ በዛው የሚረጋገጥ ቢሆንም ሥርዓተ አልበኛ መሆኑን ግን በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል።
አዲስ ዘመን ፦ በአንድ አገር ውስጥ አንድ ተቋም ብቻውን ስርዓተ አልበኛ ሊሆን ይችላልን?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ የሁሉም ተቋማት ድርሻ አለ። ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለኮርፖሬሽኑ የሚሰጠውና የከፈለው ገንዘብ ምን ላይ እንደዋለ ሳይጠይቅ ቢሊዮኖችን በድጋሚ የሚፈቅደው መንግሥት እንደመሆኑ ተጠያቂ መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፦ በማሳያ ሊያስረዱኝ ይችላሉ?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ ለምሳሌ የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለእኛ ተቋም የተሰጠውን 16 ቢሊዮን ብር እምን ላይ እንዳዋለው ገንዘብ ሚኒስቴር ሳይጠይቅ ዋስ ሆኖ ተጨማሪ 8 ቢሊዮን ብር አሰጥቷል።
ንግድ ባንክም ከተከፈለ ካፒታል በላይ በህግ ማበደርና ያበደረው ተቋምም ኪሳራ ቢገባ መጠየቅ እንደማይችል እያወቀ በ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ለተቋቋመው ኮርፖሬሽን 17 ቢሊዮን ብር አበድሯል።
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ኮርፖሬሽኑ የሚጠበቅበትን ቀረጥ በየሶስት ዓመቱ ማስከፈል ሲገባው ይህንን ባለማድረጉ አሁን የ11 ቢሊዮን ብር ዕዳ ውስጥ ገብቷል። የኮርፖሬሽኑ ችግሮች ገሀድ ስለወጡ ሁሉም የእኛን ተቋም፤ ይጠይቃሉ እንጂ በየደረጃው ምርመራ ቢደረግ ችግር የሌለበት ተቋም የለም።
ኮርፖሬሽኑ ምልክት እንጂ በአጠቃላይ ስርዓቱ ልቅ ነበር። ተቋሙ ሲሰራ የነበረው በዘፈቀደ ስለነበር ችግሩን በአንድ ዓመት እንኳን ማጥራት አልቻልንም።
አዲስ ዘመን ፦ ለተቋሙ መበላሸት የመጀመሪያው ተጠያቂ ማን ነው?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ ዋነኛ ተጠያቂው የኮርፖሬሽኑ ቦርድ ነው። ተቋሙ እቃዎችን መግዛትም ሆኖ መሸጥ ሲፈልግ ውሳኔ ማሳለፍ ያለበት ቢሆንም መርከብ ሲገዛና ሲሸጥ የሆቴሎችና ህንፃዎች ግዢ ሲፈጸም ቦርዱ አልወሰነም። በየዓመቱም የኦዲት ሪፖርት ጠይቆ አያውቅም።
የተቋሙ ኦዲት የተጠናቀቀው ባለፈው ዓመትና ዘንድሮ ነው። በአጠቃላይ ቦርዱ ስላልተከታተለው አመራሩ እንደፈለገ መፈንጨት ቻለ፤ በመሆኑም ከተቋሙ አመራር ቀጥሎ ተጠያቂ ቦርዱ ነው። ገንዘብ ሚኒስቴርም ያላግባብ ዋስትና በመስጠት፤ ኦዲት እንዲደረግ በማዘዝ መክሰሩንና ማትረፉን በማየት ስርዓት ማስያዝ ሲገባው ዝም ብሎ ገንዘብ ሲረጭ ነበር።
የቀድሞው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ኮርፖሬሽኑ በሚፈለገው ደረጃ ልማትን ሳይደግፍ፣ ቴክኖሎጂን ሳያስፋፋ ለመንግሥት ጠብ ያለ ነገር ሳይኖረው ገንዘብ ሲባክን ለምን ብሎ አልጠየቀም። ከዳር ሆኖ እየተመለከተ በእዳ ነው የጠመቀው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትም ተጠያቂ ነው። የያዩ ማዳበሪያ ፕሮጀክት፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በቀጥታ እያዘዘና ለኮርፖሬሽኑ ገንዘብ ሲሰጥ የነበረው፤ በዚህም የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር መንግሥት ወስኗል
እያሉ ጉዳዩን ሲያስፈጽሙ ነበር።
ብሄራዊ ባንክም ኮርፖሬሽኑ ከውጭ የሚገዛቸውን እቃዎች ሳያወዳድር መግዛት እንዲችል ውሳኔ አሳልፏል። የኮርፖሬሽኑን የግዥ ስርዓት የሚወስነው ቦርዱ ሆኖ ሳለ ጣልቃ መግባቱ ትክክል ካለመሆኑም በላይ ኮርፖሬሽኑ የወሰደውን የውጭ ምንዛሪ በወቅቱ ተከታትሎ አላወራረደም፡፡ ይህ ደግሞ እቃ ተገዝቶ ያልተወራረደ 12 ቢሊዮን ብር እንዲኖርና ተቋሙ አስፈላጊውን እቃ እንዳይገዛ አድርጎታል።
ይህን ለመፍታት ከድሮ ጀምሮ የተደረተ ሰነድ በመፈለግ ከ12 ቢሊዮን ብር ውስጥ የቀረው ዕዳ 2ነጥብ9 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው። ኮርፖሬሽኑን ገደል የከተቱት፣ የህዝብ ገንዘብ የግላቸው እንደሆነ እንዲሰማቸውና በማን አለብኝነት ያሻቸውን እንዲያደርጉ ያመቻቹት ከላይ የተዘረዘሩ ተቋማትና የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን ፦ ተቋሙ ከችግሩ እንዲወጣ መፍትሔው ምንድን ነው?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፤ ዕዳው ከባድ ነው። እዳው የመጣው በኮርፖሬሽኑ ችግር ብቻ ሳይሆን በባንክ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም በመንግሥት ቸልተኛነት በመሆኑ መንግሥት መሰረዝ ያለበትን መሰረዝ፣ ባንክም ብድሩንና ወለዱን ያንሳልን ብለን ባንጠይቅም ቀስ ብለን እንድንከፍል እድል ሊሰጠን ይገባል።
በተለይ ባንኩ ከዚህ በፊት የነበረውንም ሆነ አሁን ያለብንን ቅጣት ሙሉ ለሙሉ ማንሳት አለበት። ይህ የማይሆን ከሆነና ከተቀጣን ባንኩ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላለው ተቋም 17 ቢሊዮን ብር ብድር በመስጠቱ መጠየቅ አለበት።
አዲስ ዘመን፦ ዕዳው ሙሉ ለሙሉ የጠፋ ነው ማለት ነውን?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ ዕዳ ሲባል ሙሉ በሙሉ የጠፋ ነው ማለት አይደለም። ለምሳሌ ተገዝተው ለረጅም ጊዜ በመቀመጣቸው ለብልሽት የተጋለጡ በርካታ እቃዎች አሉን። የእዳውን ያህል ተሸጠው ገንዘብ ባያመጡም ቢሸጡ ግን እዳውን ያካክሳሉ ተቋሙም መቋቋም ይችላል። ነገር ግን በፕሮጀክቶች ላይ የት እንደገባ የማይታወቅም ገንዘብ አለ።
አዲስ ዘመን፦ ኮርፖሬሽኑ እዳውን በምን ያህል ዓመት ይከፍለዋል ይላሉ?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ እስካሁን በያዝነው እቅድ መንግሥት እንዲሰርዝልን የጠየቅነውን ትተን ዕዳውን ለመክፍል 15 ዓመት ይፈጃል። የጉምሩክ ዕዳችን ካልተሰረዘልን ደግሞ 30 ዓመት ይወስድብናል። መንግሥትና ጉምሩክ ከሰረዙልን ግን እሴቶች ስላሉን 15 ዓመት ላንፈጅ እንችላለን።
ለምሳሌ በትራክተሮቹ ካለብን 50 ሚሊዮን ዶላር በግማሽ ብንሸጣቸው እንኳን 25 ሚሊዮን ዶላሩን በአንድ ጊዜ እንከፍላለን።
አዲስ ዘመን፦ ለሽያጭ ተሰርተውና ተገዝተው ሳይሸጡ ለዓመታት የተከማቹ ንብረቶች በቁጥራቸውና በያዙት የገንዘብ መጠን ምን ያህል ይሆናሉ?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ በሁሉም ኢንዱስትሪ ያሉት ንብረቶች ቁጥራቸውን በዝርዝር ለመናገር አላስታውስም። በጣም የሚበዛ ክምችት ያለው በአዳማ ትራክተር ማምረቻ ፣ በደብረብርሃን ኢንፍራስትራክቸር ማምረቻ፣በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ፣ ህብረት ማኑፋክቸሪንግ ላይ ነው።
በሁሉም ኢንዱስትሪዎች በተገዙበት ዋጋ ተመርተው የተቀመጡ እቃዎች 14 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ ለምርት የመጡ እቃዎች 3 ቢሊዮን ብር ዋጋ አላቸው። በድምሩ 17 ቢሊዮን ብር የያዙ እቃዎች አሉን።
አዲስ ዘመን፦ 17 ቢሊዮን ብር የያዙት እቃዎች ምን ያህል ጊዜ ቆዩ ? አሁን ያሉበት ሁኔታስ ምን ይመስላል?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ ጸሐይና ዝናብ የተፈራረቀባቸው ስድስት ዓመታት ያህል ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ እቃዎቹ አይበሰብሱም ተብሎም አይጠበቅም። ካስት ተደርገው የተሰሩት እቃዎች ስትነካቸው የሚፈረካከሱም አሉ።
አዲስ ዘመን፦ ይህን ለማስተካከል ምን እየተሰራ ነው?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የገቡት እቃዎች ወደ አፈርነት ከመቀየራቸው በፊት ጥቅም ላይ ይዋሉ የሚል ጥያቄ ለመንግሥት አቅርበናል። ጥቅም ላይ ይዋሉ ስንል ማሽኖቹ አቅማቸውን ስለቀነሱ ዋጋቸውም ተቀንሶ እንዲሸጥ ማድረግ ማለት ነው።
መንግሥት ወስኖ ዋጋቸውን ቀንሰን ብንሸጥ ትንሽ ልንከስር እንችል ይሆናል፡፡ ዘንድሮ ካልተሸጡ ግን ለሚቀጥለው ዓመት ጨርሶ እንከስራለን። ይህን አጥንተን ለመንግሥት ልማት ድርጅቶችና ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እና ለገንዘብ ሚኒስቴር ለመላክ ዝግጅት አጠናቅቀናል።
ሪፖርቱን ከመላካችን በፊት ግን ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ባደረግነው ንግግር ያሉት ትራክተሮች ተፈትሸው የሚሰሩ ከሆነ በረሃማ አካባቢዎችን ለማልማት ለተያዘው ሥራ እነዚህ ትራክተሮች ሳይነሱ ሌላ የውጭ ምንዛሪ አንፈቅድም የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል።
ይህ ሲባል ግን የመንግሥት ልማት ድርጅት ስለሆንን በጥራት የሚሰሩትን ለይትን መስራታቸውን ማረጋገጥ ከስር ከስር ተከታትለን መለዋወጫ እያቀረብን መንግሥት የያዘውን ዓላማ በማሳካት ልማት እንዳይስተጓጎል እንሰራለን። ይህንን እንድናደርግም ገንዘብ ሚኒስቴር ከግብርና ሚኒስቴር ጋር አገናኝቶናል።
አዲስ ዘመን፦ ፋብሪካዎቻችሁ ከአቅማቸው በታች እየሰሩ ነው ፤ አንዳንዶቹም ሥራ አቁመዋል። ለምን?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ አንዳንዶቹ የማያመርቱት ድሮም ስለማያመርቱ ነው። ለምሳሌ የደብረብርሃን ኢንፍራስተራክቸር ፋብሪካ አስመጪ ነበር እንጂ ድሮም አምርቶ አያውቅም፤ አሁን አያመርትም። ማስመጣቱን ግን አቁሟል። በቀጣይም አስመጪ ሆኖ አይቀጥልም፤ ካስመጣ ደግሞ ቢያንስ መገጣጠም ይኖርበታል።
የሃይቴክ ኢንዱስትሪ ማምረቱን ያቆመው ሲቋቋም ጀምሮ በነበረበት ችግር ሲሆን፤ ፋብሪካው ‹‹ኤዲስ›› የሚባል ባለቤትነቱ የአቶ ሽመልስ በሆነ ድርጅት ላይ ተንጠልጥሎ መቋቋሙ ነው። ይህ ድርጅት ከ 2009 ዓም ጀምሮ ሥራውን በማቆሙ ሃይቴክም መቀጠል አልቻለም።
ሎኮሞቲቭም ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ አያመርትም። አሁን ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ፈርሷል። ግንባታው የተከናወነው በኮርፖሬሽኑ ቦታ ላይ ስላልነበረ ሀብት ባክኖ ነው ከቦታው ላይ የተነሳነው።
እንደ ቢሾፍቱ ያሉት ኢንዱስትሪዎች ግን ከበፊቱም ከ2ሺ10 በላይ አውቶብሶችን አምርተዋል። ገቢያቸውም ከባለፈው ዓመት የተሻለ ነው። በእነዚህ ላይም የአመራርና የኤሌክትሪክ ችግር ቢኖርም ምርቱ ከባለፈው ዓመት አልቀነሰም። ሌሎች ፋብሪካዎች ግን ከ50 በመቶ በታች ምርታቸው የወረደም አለ። ለምሳሌ አቃቂ ቤዚክ ሜታል በአመራር ችግር ምክንያት ከ50 በመቶ በታች ምርቱ ወርዷል። አሁን ይህን አስተካክለን በቀን 24 ሰዓት እያመረተ ነው። አንዳንዶቹ የገንዘብ እጥረት ስለነበረብን የሰራተኛ ደመወዝ ከመክፈል ውጪ ሥራ ብዙም ያልሰሩ አሉ።
በቀጣይ ችግሮቹን በመቅረፍና ከውጭ የሚገቡ ምርቶች እንዲገቡ በማድረግ ፋብሪካዎቹ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት በዝግጅት ላይ ነን። በዚህም ኢትዮ ፕላስተክ፣ ፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ይገባሉ። ለመንግሥት አስፈቅደን በረጅም ጊዜ ክፍያ ከምንከፍላቸው ድርጅቶች አብረን ለመስራትም ጨረታ አውጥተን ወደ ሥራ እንገባለን።
በ2012 ከህብረት ማኑፋክቸሪንግ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ውጭ አምራች ኢንዱስትሪዎቻችን ወደ ምርት የሚገቡ ሲሆን፤ የተለየ ችግር ያለባቸው ኢንፍራስትራክቸር፣ ሃይቴክና ሌሎች ፋብሪካዎች ወደ ምርት ላይገቡ ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፦ የተቋሙ አደረጃጀት በነበረበት ነው የሚቀጥለው?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ አደረጃጀታችንን በኢንዱስትሪያል ፕሮጀክት ሰርቪስ እያስጠናን ነው። ጥናቱን መሰረት አድርገን እንደ የደብረብርሃን ኢንፍራስትራክቸር ኢንዱስትሪ ያሉትን እናጥፋቸዋለን። መሬት ላይ የሌሉና የተፈለገውን ውጤት ያላመጡትን ፋብሪካዎች ይዘን አንቀጥልም።
አዲስ ዘመን፦ ጥናቱ በምን ደረጃ ላይ ነው?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ የኮርፖሬሽኑንና የኢንዱስትሪዎችን አወቃቀር አጥንተው አምጥተው ተችተን መልሰናል። በቀጣይ የአስተያየታቸውን ምላሽ ያመጣሉ።
አዲስ ዘመን፦ በደብረብርሃን ለማቋቋም የተገዛው የአክቺዌተር ፋብሪካስ?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ ፋብሪካውን ለማቋቋም የተገዛው ማሽን በጣሊያን አገር ከ50 ዓመት በላይ የሰራ ነው። ማንም ሊገጥመው አይችልም። በጣም ከማርጀቱ የተነሳ ሲመጣ ብትንትን ብሏል። ቢገጠምም 50 ዓመታት ለሰራ ማሽን መለዋወጫ አይገኝም የሚፈለገውን ምርትም አያመርትም። ግን ለግዢው 44 ሚሊዮን ብር ወጥቶበታል። 44 ሚሊዮን ብር ከጠፋም ይጥፋ እንጂ ተገጥሞም ላይሰራ ሌላ ገንዘብ አናባክንም። ሙያተኞችም ይህን ነው ያሉት።
አዲስ ዘመን፦በሌሎች ቦታዎች ለማቋቋም የተጀመሩ ፋብሪካዎችስ?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ በነቀምት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ ያደረግንበት የብረት ማቅለጫ ፋብሪካ አለ፤ ግን ለማቆም ተጨማሪ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል። አሁን ያሉንን ፋብሪካዎች ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ስለሆነ ይህን ያህል ገንዘብ ወጪ ማድረግ አንችልም። እንደ አማራጭ ግን ቀሪውን ገንዘብ የኦሮሚያ ክልል ጨምሮበት በሽርክና ፋብሪካውን ለማቋቋም ነው።
በአማራ ክልል ደብረ ማርቆስ ከተማ 230 ሚሊዮን ብር የወጣበት የክሬን ሊፍተር ማምረቻ በጅምር ላይ ያለ ፋብሪካ አለ። ይህንንም ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር በሽርክና ወደ ሥራ ለማስገባት አቅደናል። እነዚህ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ሲገቡ ለተቋሙ የሀብት ምንጭ ይሆናሉ።
አዲስ ዘመን፦ በአንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ሠራተኞች ያለሥራ ነው ደመወዝ የሚከፈላቸው። ወደ ሥራ ለማስገባት ምን እየሰራችሁ ነው?
ብርጋዴል ጀነራል አህመድ፦ ምርታቸው እያደገ ያለና ጭማሪ የሰው ኃይል የሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎች አሉን። ጥናቱ የሚመልሰው እንዳለ ሆኖ ሥራ የሌላቸውን ኢንዱስትሪዎች ሥራ ወዳላቸው እናዛውራለን።
በቀጣይም ከሠራተኞች ጋርም የህብረት ስምምነት በማድረግ በሥራቸው ልክ እንዲከፈላቸው ይደረጋል። በምንገባው የህብረት ስምምነት መሰረት የደመወዝ፣ የቦነስና ጥቅማ ጥቅም የሚወሰነው በውጤታማነት ላይ ተመስርቶ ነው ። ቁጭ ብዬ እከፈላለሁ የሚል አካሄድ ከዚህ በኋላ አይሰራም። መንግሥት የሰጠንን ትጥቅ ተጠቅመን እንሰራለን ካልሰራን እንሰናበታለን ። ይህ የሚቆየው ጥናቱ ተጠናቆ ወደ ሥራ እስከሚገባ ነው።
አዲስ ዘመን፤ በኮርፖሬሽኑ የነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከዚህ ለምን ለቀቁ?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፤ ኮርፖሬሽኑ የተቋቋመው በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 25/1984 መሰረት ነው። በዚህ አዋጅ የተቋቋመ ተቋም ሠራተኛ የሚመራው ደግሞ በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት ነው። የተቋሙ ሁሉም ሠራተኞችም በዚህ ህግ መተዳደር አለባቸው።
ከመከላከያ ሠራዊት አባላት 1ሺ541 የሚሆኑት መተዳደር ያለብን በመከላከያ ህግ ነው ስላሉ ወይ ኮርፖሬሽኑን ወይም መከላከያን መምረጥ ነበረባቸው በዚያ መሰረት 1ሺ541ዱ መከላከያን መረጡ። 345ቱ ኮርፖሬሽኑን መርጠው ቀሩ።
ሌላው ኮርፖሬሽኑ 15ሺ ሠራተኞች ያሉትና ከዚህ ውስጥ የመከላከያ ሠራዊት አባላቱ 2ሺ ሲሆኑ፤ ብዙሃኑ ሲቪል ሠራተኛ ህግ ይከበር ይላል። ህጉን ከማክበርና ጥቂት የሚጠቅሙ ሰዎችን ከማግኘት አንዱን መምረጥ ነው የሚመጣው። እኛ የሚሻለን ህግ ማክበር ነው። የመከላከያና የልማት ድርጅት አላማቸው የተለያየ ነው።ሁለቱን ቀላቅሎ መምራት አይቻልም።
መከላከያን ከመረጡት አንዳንዶቹ ኮርፖሬሽኑ መቼ ተነስቶ የተሻለ ደመወዝ ሊከፍለን ነው ያሉም ነበሩ። ተቋማቸውን ከወደቀበት ማንሳት ካልፈለጉ ተቋማቸው ገንዘብ ከፋይ ሊሆን አይችልም። መጀመሪያ ተቋሙ በእራሱ አልወደቀም። ተቋሙን የጣለው ሰው ነው። ምናልባትም ከጣዮች አንዱ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን አናስገድድም ሄደዋል።
ሌሎች ደግሞ ስንቀጠር ለወታደር ነው። ውትድርና ሙያችን ነው መከላከያ መሄድ አለብን ያሉም አሉ። እነዚህ መቶ በመቶ እውነታቸውን ከሆነ አደንቃቸዋለሁ። በመሆኑም የመከላከያ አባላት በመረጡት በፍላጎታቸው ነው የሄዱት። ሲወድቅ እንደነበሩ ሲነሳም ቢኖሩ ጥሩ ነበር። በፍላጎታቸው ነው የሄዱት። ከነሐሴ አንድ ጀምሮ ወደ መከላከያ ይሄዳሉ።
አዲስ ዘመን፦ በተቋማችሁ ፕሮጀክቶችን ከማስረከብ ጋር ተያይዞ ችግር እንዳለ ይነሳል። ይህ ምን ያህል እውነት ነው?
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ ከስኳር ኮርፖሬሽንና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በነበረው ርክክብ ኮርፖሬሽኑ በምን አይነት መንገድ ተቀየረ እስከማለት ደርሰዋል። ያለምንም ችግር ነው ያስረከብናቸው። በጣም ደስተኞች ናቸው።
አዲስ ዘመን ፦ ለሰጡኝ ቃለ ምልልስ አመሰግናለሁ።
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 1/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ