አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብትን በመጠቀም ውድቅ አደረገች።
15 አባላት ያሉት ምክር ቤቱ 10 ቋሚ ያልሆኑ አባላት ባቀረቡት የውሳኔ ሃሳብ ለ13 ወራት የዘለቀው ግጭት በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ቋሚ የተኩስ ማቆም እንዲደረግ እና ታጋቾቹ እንዲፈቱ በተናጠል ጠይቋል።
በውሳኔው ላይ የተሰጠውን ድምፅ የሻረችው አሜሪካ ምክትል አምባሳደር ሮበርት ዉድ ዋሽንግተን ታጋቾች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የሚጠይቅ የውሳኔ ሀሳብ ብቻ እንደምትደግፍ በግልጽ አቋሟን አሳውቃለች ሲሉ ገልጸዋል።
አምባሳደሩ “የጦርነቱ ዘላቂ ፍጻሜ የታጋቾቹን መለቀቅ ማካተት አለበት፤ እነዚህ ሁለት አጣዳፊ ግቦች የማይነጣጠሉ ናቸው ይህ የውሳኔ ሃሳብ ያንን አስፈላጊነት አላካተተም በዚህ ምክንያት አሜሪካ ልትደግፈው አትችልም” ብለዋል።
ዋሽንግተን የተኩስ አቁም ስምምነትን ትፈልጋለች ያሉት አምባሳደሩ ነገር ግን የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ጽሑፍ ለፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ ወደ ድርድር ጠረጴዛ መመለስ አያስፈልግም የሚል አደገኛ መልዕክት ያስተላለፈ ነበር ነው ያሉት።
የውሳኔ ሀሳቡን ያቀረቡት የምክር ቤቱ ተለዋዋጭ 10 አባላት አልጄሪያ፣ ኢኳዶር፣ ጉያና፣ ጃፓን፣ ማልታ፣ ሞዛምቢክ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ስሎቬኒያ እና ስዊዘርላንድ የውሳኔ ሃሳቡ ውድቅ በመደረጉ በአሜሪካ ላይ ትችት ሰንዝረዋል።
የማልታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አምባሳደር ቫኔሳ ከድምፅ ሂደቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር “ይህ ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ በመሻር መብት ምክንያት በድጋሚ ዓለም አቀፍ ሠላምን እና ደኅንነትን የማስጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉ በጣም እናዝናለን” ብለዋል።
የቻይናው አምባሳደር ፉ ኮንግ በበኩላቸው “አሜሪካ እሥራኤልን ለመጠበቅ ድምጿን በሰጠች ቁጥር በጋዛ የሚገደሉት ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፤ ከማስመሰል እንቅልፍ ከመነሳታቸው በፊት ስንት ሰዎች መሞት አለባቸው?” ሲሉ ጠይቀዋል።
በጥር 20 ከሥልጣን የሚለቁት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለእሥራኤል ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ እና የጦር መሣሪያ ድጋፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል በእሥራኤል እና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም ሲል አል አይን ዚውስ ዘግቧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም