ፍትህ አስከባሪዎቹ ዱቡሻና አፊኒ

ስሜት ኮርኳሪ ጥቅሶች ከሚነበብባቸው ቦታዎች መካከል የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ መኪኖች ዋነኞቹ ናቸው። መኪኖች ለአጭርም ሆነ ለረዥም ጉዞ ከተለያየ ቦታ ለሚንቀሳቀሱ ሠዎች ለተወሰነ ሰዓት የጋራ ቤታቸው ይሆናል። ታዲያ በዚህ ቆይታ ዘላቂ ግንኙነት ከመፍጠር አንስቶ የተካረረና ፖሊስ ድረስ የሚደርሱ ጸቦች ይስተናገዳሉ። ለዚህም ይመስላል በተለይ በአዲስ አበባ ታክሲዎች ነገር አትፈልጉን አይነት ጥቅሶችን መመልከት አዲስ ያልሆነው። ከነዚህ ጥቅሶች ውስጥ “ነገረኛ ተሳፋሪ አደባባይ ላይ ወራጅ ይላል” የሚለው ጥቅስ ይገኝበታል። እውነት ነው አንዳንዴ ሕግ ላክብር ያሉ አሽከርካሪና ረዳት ማውረድ የማይቻልበት አደባባይ ላይ ካለወረዳችሁኝ በሚል ትልቅ ጸብ ይነሳል።

እነዚህ ታክሲ ያገናኛቸው ሰዎች ነገ ደግሞ የመገናኘት እድላቸው አነስተኛ ቢሆንም ለያዥ ለገላጋይ የሚቸግር ጸብ ውስጥ ይገባሉ። ከመሃል አንዱ ማለፍን ቢያስቀድም ነገሩ ይበርድ ነበር። ትላንት ማህጸን የተጋሩ የአንድ እናት ልጆች መሃል የተነሱ ሀሳቦች ጸብ ሆነው፤ እናት “ባጠባኋችሁ ጡቶቼ” ብላ እስክትማጸን ሲካረሩ ተመልክተናል። ምርጥ የትዳር ምሳሌ የነበሩ ጥንዶች በቀናት ልዩነት ጸበኛ ሆነው ይገኛሉ። ግጭት በጎረቤት፣ በትዳር አጋሮች፣ በቤተሰብ፣ በጓደኛሞች እንዲሁም በሥራ አጋሮች መሃል ያጋጥማል።

ግጭት በመልካም የሚመኙት ነገር ባይሆንም መፈጠሩ ግን አይቀሬ ነው። ዋናው ቁምነገሩ ግጭቱን በጊዜ መፍታቱ ላይ ነው። በሀገራችን ታዲያ በየአካባቢው እንደየባህሉ “እነሱማ ብለው እንዴት እምቢ ይባላል” ተብለው የሚታወቁ የሀገር ሽማግሌዎችና የሽምግልና ስርዓቶች አሉ። የእርቅ ሥነ-ስርዓት ከሚያካሄዱባቸው ሥርዓቶች መካከል የ‘ዱቡሻ’ና የ‘አፊኒ’ ሥርዓቶች ተጠቃሽ ናቸው። አፊኒ በሲዳማ ብሔር አባላት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የፍትህ ስርዓትና የእርቅ ሂደት ሲሆን ዱቡሻ ደግሞ በጋሞ አባቶች የሚከናወን የዕርቅና የሰላም ማስከበሪያ ሥርዓት ነው፡፡

በእጃቸው የሚይዙት እርጥብ ሳር መለያቸው የሆነው የጋሞ አባቶች በጋራ የሚመክሩበትና ፍትህ የሚያሰፍኑበት የዱቡሻ ሥርዓት ነው። በዚህ ቦታ በደል ደርሶብኛል፣ ድንበሬ ተገፍቷል፣ ጥቃት ደርሶብኛል፣ሀብቴ ተዘርፏል የሚል አካል የዱቡሻውን መሰብሰቢያ ቀን ጠብቆ አቤት ይላል። ያኔ ተከሳሽ በአጋጣሚ ከዱቡሻው (ባህላዊ ችሎት) ከተገኘ እዛው ይቀርባል። ካልተገኘ ለሌላ ቀን እንዲቀርብ መልእክተኛ ይላክበታል። በቀጠሮው ዱቡሻውን አክብሮ የቀረበን ተከሳሽ መመረቅ የዳኞች የመጀመሪያ ሥርዓት ነው።

በፍርድ ሂደት የተሰየሙ የጋሞ አባቶች የሚይዙት በትርና እርጥብ ሳር መለያቸው ነው። በማኅበረሰቡ ዘንድ እርጥብ ሳር በቁጣ የጋለ ስሜትን በማቀዝቀዝ ወደ ሰላማዊ ስሜት ይቀይራል። በትሩ የእውነተኛውን ስሜት በማወቅ ለእርቅ ያዘጋጃል ተብሎ ይታመናል። በጋሞዎች ዘንድ አባቶች የሚይዙት የበትር ጦር መሬት ላይ ተሰክቶ ሲቆም ማንም ሰው ለእርቅ ይዘጋጃል ተብሎ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ እምነት አለ። በዚህ ሂደት በዳይ የሚክስበት ተበዳይም የሚካስበት ሂደት ይሆናል።

ሆኖም ዱቡሻው ከፍ ያለ አካል ነውና ግጭቶች ሁሉ ወደዱቡሻ አይሄዱም። በጋሞ ባሕል መጀመሪያ ከበዳይም ከተበዳይም ወገን ተወካዮች ባሉበት የዘመድ ጉባኤ ያጋጠሙ ችግሮች ይታያሉ። በዚህ ሂደትም በርካታ ጉዳዮች ይፈታሉ። ሆኖም በዘመድ ጉባኤ በተሰጠው ውሳኔ ካልተስማሙ በአካባቢው የሚገኙና “ጭማ” በመባል የሚታወቁ የሀገር ሽማግሌዎች ጉዳዩን ያዩታል። በዚህ ሂደት ሦስትና ከዛ በላይ በሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች ጉዳዩን ይመረምራሉ። ከሀገር ሽማግሌዎቹ እድሜ ከፍ ያለው መሃል ላይ ይቀመጣል። ነገሩን አመዛዝነው የሀገር ሽማግሌዎቹ በዳይን ያርማል ተበዳይንም ይክሳል ያሉትን ውሳኔ ይወስናሉ። ሁለቱም ወገኖች በዚህ ሂደት ከተስማሙ ጸቡ በእርቅ ይጠናቀቃል። ግን እንደዘመናዊው ፍርድ ቤት የይግባኝ መብታቸው የተጠበቀ ነውና በውሳኔው ያልተስማማ አካል ጉዳዩን ወደዱቡሻ የመውሰድ መብት አለው፡፡

በሀገር ሽማግሌዎች ታይቶ ያልተፈታ ችግር ወደዱቡሻ ሥርዓቱ በሚወሰድበት ወቅት የሀገር ሽማግሌዎቹ እስካሁን የመጡበትን ሂደትና የወሰኑትን ውሳኔ ያስረዳሉ። ከዛ በመቀጠል ዱቡሻው ነገሩን ከሥሩ በመመርመር የሀገር ሽማግሌዎቹ ውሳኔ ልክ ከሆነ ያጸኑታል። ውሳኔው ላይ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ካሉ በማሻሻል ውሳኔ ያሳልፋሉ። ጉዳዩ በሀገር ሽማግሌዎች ታይቶ በውሳኔው ካልተስማማ ግለሰብ በተጨማሪ ጉዳዩን ወደዱቡሻ በቀጥታ የሚወስዱ አቤቱታ አቅራቢዎችም አሉ።

ተበድያለሁ ሲል ወደዱቡሻው የቀረበው ሰው የመጣበትን ምክንያት እንዲያስረዳ እድል ይሰጠዋል። የሀገር ሽማግሌዎቹ “የሞቱ ሰዎችን፣ ያለን እኛንም እይ፣ ፈጣሪንም ከላይ እይ፣ ዋሽተህ የምትሄድ ከሆነ ቤት አትደርስም፡፡” በማለት እውነት እንዲናገር ያስምሉታል። በማኅበረሰቡ ዘንድ በውሸት ክዶ መሃላ ከፈጸመ በሕይወቱ፣ በንብረቱ፣ በቤተሰቡ ላይ ይደርሳል ተብሎ ስለሚታመን ውሸት በጥብቅ የተከለከለ ነው። የጋሞ አባቶች የተበዳይንም የበዳይንም ሀሳብ በደንብ ያዳምጣሉ። ነገሩን በደንብ አሰላስለውና በጋራ መክረው ሲያበቁ ይበጃል ያሉትን ውሳኔ ያሳልፋሉ፡፡

በአብዛኛው በዱቡሻው የተላለፈ ውሳኔ ሁለቱም ወገኖች የሚቀበሉበት እድል ያመዝናል። አንዳንዴ ከሳሽም የተወሰነልኝ ውሳኔ ያንሳል ሲል፤ እንዲሁም ጥፋተኛ የተባለ አካል ያለጥፋቴ ተፈረደብኝ ሲል ውሳኔውን የማይቀበሉበት ሁኔታ ያጋጥማል። በዚህ ውሳኔያቸው ከጸኑ ከአካባቢው አለፍ ያለውና በርካታ አካባቢዎችን የሚሸፍነው ዱቡሻ ላይ ይግባኝ በማለት የመጨረሻ ውሳኔ ማስወሰን ይችላሉ። በዚህ ሂደትም ውሳኔው ሊጸና ወይም ሊሻሻል ይችላል። ሆኖም አብዛኛው ጉዳዮች ይግባኝ ጋር አይደርሱም።

በመጀመሪያው ዱቡሻ የአካባቢው ሽማግሌዎች ተከሳሹን ከዱብሻው ገለል አድርገው በመውሰድ ጥፋቱን ክዶ ከሆነ ጦሱ ለሱ ብቻ ሳይሆን በንብረቱም እንዲሁም በቤተሰቡ ጭምር እንደሚደርስና እውነቱን ቢናገር እንደሚሻል ያግባቡታል። ያኔ የካደው መልሶ ጥፋቱን ያምናል። ይህ ሳይሆን ቢቀር ነገሩን እንዲያስበው የማሰቢያ ቀን ይሰጠዋል። ያኔ ቤተሰቡና የአካባቢው ሰዎች ጉዳዩን ዘርዝረው በማስረዳት “እንዴት አልታየህም በዚህ ምክንያት እኮ ጥፋተኛ በመሆንህ ውሳኔው ተገቢ ነው” ይሉታል። በማግስቱ ወደዱቡሻው በመመለስ ጥፋቱን ማመኑንና የተወሰነበትን ካሳ ለመክፈል መስማማቱን ያሳያል። በጋሞዎች ይቅርታ ትልቅ ቦታ አለው። የተፈጠረ ጸብ በእርቅ ከተደመደመ በኋላ የታረቁ ወገኖች እስከጋብቻ በሚደርስ ዝምድና ድረስ ግንኙነታቸው ወደ ቀድሞው ቦታው ይመለሳል። ጋሞዎች በሙሉ መተማመን ዱቡሻ ላይ ቀርቦ የማይፈታ ችግር የለም ይላሉ።

ከዱቡሻ ጋር የተወሰኑ የጋራ እሴቶችን የሚጋራውና የሲዳማዎች ችግርና ግጭት መፍቻ ባሕላዊ የፍትህ ስርዓት “አፊኒ” ይሰኛል። “አፊኒ” ሰማችሁ? አወቃችሁ? አያችሁ ወይ? ማለት ነው። ሲዳማዎች አላግባብ የዘመዳቸው ደም በከንቱ ቢፈስ እሬሳውን እቤት አስቀምጠው ሰማችሁ ወይ ሲሉ “አፊኒ” ይላሉ። ማኅበረሰቡ እነሱ ላይ የደረሰው መጥፎ ነገር ሰምቶ ከበዳያቸው ጋር ተባብሮ ፍትህን አይነፍጋቸውምና ፍትህ እንደሚያገኙ በመተማመን “አፊኒ” ሲሉ ጆሮ ይሻሉ። በሲዳማ ባሕል ተበዳይ “አፊኒ” ብሎ በአቅራቢያው ላገኛቸው ሰዎች ችግሩን ካስረዳ በኋላ ነገሩ በረድ ይላል። በባሕሉ ማንኛውም ተበዳይ ቀጣይ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት “አፊኒ” በማለት የደረሰበትን ችግር የማሳወቅ ግዴታ አለበት።

“አፊኒ” ሲባል ነገሩ ከመክረር ይልቅ ለውይይት ክፍት ይሆናል። ተናዶ የመጣ አካል “አፊኒ” ሲባል ከንዴቱ በተወሰነ ደረጃ ሰከን የማለት እድል ያገኛል። በአፊኒ የሚዳኘው የከረረ ግጭት ብቻ አይደለም። አባቴ ትክክል አይደለም በድሎኛል ያለ ልጅ ለአባቱ እኩያ አፊኒ ሲል ነገሩን ያስረዳል። በአባቴ ተበድያለሁ የሚልን ሕጻን ሀሳብ ሳይንቁ የሚሰሙት አባቶች ለመፍትሄ አባትን ያናግራሉ። በተመሳሳይ ልጄ አጥፍቷልና ቅጣት ያሻዋል ያለ አባት ልጁ ላይ እጁን ከመሰንዘሩ በፊት አፊኒን ያስቀድማል። በባሕሉ ሳያስበው ቡጢ የተሰነዘረበት ሰው ቢኖር እንኳን ቡጢውን መመለስ ቢፈልግ መጀመሪያ “አፊኒ” ማለት አለበት። ይህ ሳይሆን ቢቀርና የተሰነዘረበትን ቡጢ ልመልስ ብሎ ቢሰነዝር ጥፋቱ ከመጀመሪያው ተማቺ ይልቅ በሁለተኛው ላይ ያይላል። ስለዚህም አፊኒ አላልክም በሚል ተመቺው ከተቀጣ በኋላ የመጀመሪያው ተመቺ “ለምን መታሃው?” ተብሎ ይጠየቃል። ግጭትን ማስቀረት ባይቻልም አፊኒ የምትለዋ ቃል ሰዎች ከገቡበት ግጭት የምታቀዘቅዝና ነገሩን በብልሃት የሚያመዛዝኑበት አቅም ይሰጣቸዋል፡፡

በሲዳማ አፊኒ ከቤት እስከ አደባባይ ጥቅም ላይ ይውላል። የሚጣሉ ሁለት አካላትን ያየ አካል “እኔ ገለልተኛ (ሦስተኛ አካል) ነኝና እናንተን ላስማማ አካል ወደማጉደል ሕይወት ወደማጥፋት አትሂዱ፡፡” በማለት ጊዜ ወስዶ የእነሱን ጉዳይ ለማየት ግብዣ ያቀርባል። ከተቻለ በአቅራቢያ በሚገኙ ሰዎች ተዳኝተው ጉዳዩ ይበርዳል። አለፍ ካለ ክሶች የሚታዩበት ባሕላዊ ፍርድ ቤት አለ። እዚህ ፍርድ ቤት የሚታደሙት በሀገሬው ይሁንታን ያገኙ ሽማግሌዎች፣ ተበደልን ሲሉ አፊኒ ባዮች፣ አጥፍተዋል የተባሉ እንዲሁም የፍርድ ሂደቱን መከታተል የፈለገ ማንኛውም አካል መከታተል ይችላል። ፍትህ ፈልጎ “አፊኒ” ያለ በደሌን ሰማችሁ ወይ? ሲል ወደ ፍርድ ሸንጎ የመጣ አካል በደሉን የማስረዳት ቅድሚያ እድል ይሰጠዋል። በዚህም የደረሰበትን በደል አንድ በአንድ ዘርዝሮ ያቀርባል። በቃል የቀረበውን አቤቱታ ሰምተው ሲጨርሱ ክስ የቀረበበት በአካል ቀርቦ መልስ ይሰጥ ዘንድ መልእክተኛ ይልኩበታል፡፡

በአፊኒ ስርዓት ተጠሪ የተጠራበትን ቀንና ሰዓት አክብሮ መገኘት የግድ ነው። አፊኒን አክብሮ በሸንጎው ላይ ያልተገኘ ለአምላክ ይነገርበታል የሚል እሳቤ አለ። ስለዚህ ሁሉም ቅሬታ የሚቀርብበት አካል ይሄን ስለሚፈራ የተባለውን ቀጠሮ አክብሮ ይገኛል። ከሳሽም ተከሳሽም ጉዳዩን ያስረዳሉ። የሀገር ሽማግሌዎቹ የሰሙትን ሲያሰላስሉ ቆይተው እውነታው ላይ ደርሰናል ብለው ሲያስቡ እንደሀገሩ ደንብ ሀሳባቸውን ከማሳወቃቸው በፊት “አፊኒ” ይላሉ። ይህ አፊኒ ትርጉሙ ሰማችሁን ወይ? ማለት ሲሆን ሌላኛው እውነታው አንተም ይመለከትሀል ሀሳቡ ለመስጠት ተዘጋጅ ማለትም ነው። በአፊኒ እውነታው የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን ሁሉም የታየውን ሀሳብ እየሰነዘረ የጋራ እውነት ላይ ይደረሳል። በሸንጎው ላይ የተገኘ በሙሉ ፍትህ ለማስፈን የሚጠቅም ሀሳብ ያገኘ ሲመስለው አፊኒን እያስቀደመ ይናገራል፡፡

በአፊኒ ሂደት መካድም ሆነ መዋሸት ፍጹም አይታሰብም፡፤ በዘመናዊ የፍትህ ስርዓት ታይቶ በምስክር ወይም በማስረጃ እጦት የቀረ ሂደት ወደ አፊኒ መጥቶ የመታወቅ እድሉ ከፍ ያለ ነው። በሀገሬው ደንብ በአፊኒ የካደ በሕይወት አይቆይም የሚል እምነት አለ። ስለዚህ ሌላ ቦታ የካደ ሁሉ አፊኒ ላይ ያምናል። በየክፍሉ ሲከናወኑ የነበሩ የፍርድ ሂደቶች ከተጠናቀቁ በኋላ ሁሉም በጋራ ተሰብስበው የጎሳ መሪ (ጋና) ባሉበት ፍርዳቸውን ያቀርባሉ፡፡አልተስማማሁም የሚል ተቀጪ ወይም ተካሽ ካለ መሪው መርምረው ውሳኔው ልክ ነው ካሉ ያጸኑታል። ልክ አይደለም ካሉ ጉዳዩ በድጋሚ ይታያል። ጋናው ነገሩን መርምረው የሚሰጡት ውሳኔ የመጨረሻው ነው።

በአፊኒም ሆነ በዱቡሻ በዳዮች ይቅርታ የመጠየቅና የመካስ ግዴታ ተጥሎባቸዋል። በተመሳሳይ ተበዳይ ወገኖችን የይቅርታ ልብ እንዲኖራቸው ባህሉ ኮትኩቶ አሳድጓቸዋል። ሁለቱም ወገኖች የይግባኝ መብታቸውን በመጠቀም እስከመጨረሻው ደረጃ የመሄድ መብት አላቸው። ሆኖም በሕብረተሰቡ ስምምነት የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ አካልን ውሳኔ መቀበል አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው፡፡

በከተማ አካባቢ የሚፈጠሩ ግጭቶች የመልካሙ ተበጀ “አይረሳም ተበዳይ ለካ የበደልሽኝን እንዳልረሳ ሆኛለሁ …” የሚለውን ዘፈን በማቀንቀንና ለይቶለት ለቂም በቀል ባይነሳም የበዳይን ውድቀት ለማየት በመመኘት ነው። በዱቡሻና አፊኒ ግን በዳይ ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ መጠየቅና መካስ ተበዳይም ይቅርታን መቀበል ግዴታ ነው። ሆኖም ውሳኔውን አልቀበልም የሚል አካል ካለ ማኅበረሰቡ ያገለዋል። ሠርጉ አይደምቅ፣ ሐዘኑ የጋራ አይሆንም። ሁሉም ይሄን ስለሚያውቅና የወጣበት ማኅበረሰብ የማይቀየር ሕግ ነውና የእርቅ ውሳኔውን ያከብራሉ።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You