
አዲስ አበባ– የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ እና አፍሪካ ሕብረት በሱዳን ሰላማዊ ሽግግር እንዲደረግ ለተጫወቱት ሚና የምስጋና ሽልማት አበረከተ።
የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤት እና በነጻነት እና ለውጥ ኃይሎች መካከል ሲደረግ የነበረው ድርድር የሽግግር ሕገመንግሥት እና የፖለቲካ ስምምነት በመፈራረም መጠናቀቁን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ እና አፍሪካ ሕብረት ሁለቱን ወገኖች በማደራደር ላበረከቱት አስተዋጽኦ የምስጋና ሽልማት አበረከተ፡፡
በሱዳን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሱዳን ልዩ ልዑክ አምባሳደር መሃሙድ ድሪር፣ በሱዳን ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ እና ለአፍሪካ ሕብረት ልዩ ልዑክ መሃመድ ሃሳን ላባት የተበረከተ ነው፡፡
ሽልማቱንም የወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ተጠሪ ጄኔራል ሸምሰዲን አል ካባሺ በተገኙበት፤ የሱዳን ተጠባባቂ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ኦማር ዳሃብ አበርክተዋል።
የሱዳን ተጠባባቂ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ኦማር ዳሃብ በሽልማት ሥነሥርዓቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ኢትዮጵያና የአፍሪካ ሕብረት በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን እና የሽግግር መንግሥት ለመመስረት ሲካሄድ በቆየው የድርድር ሂደት በአደራዳሪነት ላደረጉት ከፍተኛ ጥረትና ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የምስጋና ሽልማቱ በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርና በቀጣይ በሁለቱ አገራት መካከል የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር በተለያዩ የትብብር መስኮች ለሚከናውኑ ተግባራት ጥረት መልካም መደላድል እንደሚፈጥር ይታመናል ሲል ኤምባሲው ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 1/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር