
በአዳማ መሀል ከተማ ከፖስታ ቤት አቅራቢያ በስተቀኝ ሲታጠፉ በኮብልስቶን የተነጠፈ መንገድ ያገኛሉ። በዚህ መንገድ ላይ ደግሞ የከተማዋ የትራንስፖርት አማራጭ የሆኑት ባጃጆች እየተውተረተሩ ይጓዛሉ።
ትላልቆቹና መካከለኞቹ የህዝብ ማመላለሻ መኪኖችም ከወዲያ ወዲህ ይመላለሳሉ። በዚያው ልክ ደግሞ ከላይ እታች የሚለው ሰው መንገዱ የአንድ መንገድ ማሳለጫ ሳይሆን ትልቅ አውራ ጎዳና እንዲመስል አድርጎታል።
ይህንን መንገድ ይዘው ወደ ውስጥ ሲዘልቁም አንድ ያልታጠረ ሰፊ ሜዳ ይታያል። መኪኖች በሁሉም አቅጣጫ ይገባሉ ይወጣሉ። ሰዎችም ከወዲያ ወዲህ እየተራወጡ ወደ መኪኖቹ ይገባሉ።
የትራንስፖርት መኪኖቹ ረዳቶች ጥሪ መናኸሪያ መሆኑን ይናገራል። አሸዋማ ባህሪ ያለው ሜዳ ለመኪኖቹና ለተሳፋሪዎች ጭቃ ባይሆንም ምቹ አይደለም። በችኮላ መሰራቱንም የሚያስታውቁ በአሸዋ የተገረፉ ቤቶችም በሜዳው አንድ ጥግ ይታያሉ። ይህ አዲሱ የአዳማ መናኸሪያ ነው።
በዚህ መናኸሪያ በአገልግሎት አሰጣጡ ተሳፋሪዎች፣ የተሽከርካሪ ባለቤቶችና ሹፌሮች እንዲሁም የኮሚሽን ሰራተኞች የተለያዩ ቅሬታዎችን ያነሳሉ። ወይዘሮ ኪያ ተስፋዬ በመናኸሪያው የኮሚሽን ሠራተኛ ሲሆኑ፤ እርሳቸው እንደሚሉት መናኸሪያው ከከተማው ወጣ ያለ በመሆኑ ተሳፋሪዎች በአገልግሎት አሰጣጡ እየተንገላቱ ናቸው። ታክሲም አይገኝም። በተለይም ሌሊት ለመሳፈር የሚመጡ ሰዎች ግቢው አጥር ያልነበረውና ጥበቃም ስለሌለው ዝርፊያ ይፈጸምባቸው ነበር ይላሉ።
የአዳማን መናኸሪያ በተደጋጋሚ እንደሚጠቀሙ የሚናገሩት አቶ ጊዮን አበበ በበኩላቸው፤ መናኸሪያው ስፋቱ መልካም ቢሆንም ግቢው አለመደልደሉ፣ አስፈላጊ አገልግሎት የሚሰጡ ቢሮዎች፣ መጸዳጃ ቤቶች፣ ካፍቴሪያ ለመኖሩና በአጥር አለመከለሉ ለተሳፋሪ አስቸጋሪ መሆኑን ያመላክታሉ።
ወይዘሮ ከበቡሽ ደቻሳም ‹‹ለመናኸሪያው መሰረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ነገሮች ሳይሟሉ ከድሮ ቦታው ወደዚህ መቀየሩ ተገቢ አይደለም። መሬቱ አልተስተካከልም፤ አጥር የለውም። በሌላ በኩልም ወደ መናኸሪያው የሚወስደው መንገድ ኮብልስቶን በመሆኑ ለተገልጋይ ምቹ አይደለም›› ይላሉ።
ከአዲስ አበባ አዳማ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት አቶ ሰለሞን በለጠ፤ ተሳፋሪዎች በመናኸሪያው መራቅና እንደ ልብ ታክሲ ባለማግኘታቸው ሲማረሩ እንደሚሰሙ ይናገራሉ።በሌላ በኩልም የመናኸሪያውን መግቢያ የሚያሳይ ምልክት አለመኖሩ ችግር እየፈጠረ እንደሚገኝ በመግለፅ፤ መናኸሪያው አጥር ግቢ ኖሮት ለአገልግሎት ሰጪውም ለተገልጋዩም ምቹ ይሆን ዘንድ የሚመለከተው አካል ሥራውን ሊያጠናቅቅ እንደሚገባ ያመለክታሉ።
‹‹መናኸሪያው ቢሮ፤ አጥርና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሳይሟሉ ነው ቦታውን እንዲቀይር የተደረገው›› ያሉት ደግሞ ሹፊር አማን አብዲ ናቸው:: የጸጥታውን ጉዳይ ለማስተካከል እየተሰራ ቢሆንም አሁንም አልፎ አልፎ ችግር እንደሚስተዋልና ነባሩ መናኸሪያ በቶሎ ተሰርቶ ወደ ቦታው መመለስ ጥሩ እንደሚሆን ይናገራሉ።
በመናኸሪያው ተቆጣጣሪ የሆኑት አቶ ሙስጠፋ ከድር እንደሚሉት ቦታው የተቀየረው በጊዜዊነት ነው፤ አሁን ላይ አጥሩን ለማሳጠር የከተማ አስተዳደሩ እቅድ ይዞ እየሰራ ነው። አልፎ አልፎ የሚታየውን የጸጥታ ችግርና ስርቆት ለመቆጣጠር የከተማው ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን በቅንጅት እየተሰራ ነው።
የአዳማ ከተማ ትራንስፖርት ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ጉተማ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ ከነባሩ መናኸሪያ ወደ ቁጥር አንድና ሁለት የተዛወረው ነባሩን መናኸሪያ ከተማዋን በሚመጥንና ዘመናዊነትን በተላበሰ ሁኔታ ለመገንባት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግንባታው የተጀመረ በመሆኑ ከአንድ ዓመት ከ6 ወር በኋላ እንደሚጠናቀቅ ገልፀዋል።
በከተማዋ በጊዜዊነት አገልግሎት እየሰጡ ካሉት መናኸሪያዎች ይህኛው ከበጀት ችግር ጋር ተያይዞ አጥርና ለተገልጋዮች የሚሆን መጠለያ አልተሰራለትም፤ችግሩን ለመፍታት ከክልሉ ትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር በመነጋገር በጀት እንደተለቀቀ እንደሚጠናቀቅ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
ሥራ አስኪያጁ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ችግር እንደሌለና ህዝቡ የሚያነሳው ጥያቄ ከስጋት የመነጨ መሆኑን በመናገር ጸጥታው በመናኸሪያው ፖሊስ፣ በከተማ አስተዳደሩ ፖሊስና በተደራጁ ደንብ አስከባሪዎች እየተጠበቀ እንዳለ ይጠቁማሉ።
ሥራ አስኪያጁ ለሠራተኞችና ለማህበራት ቢሮ በኮንቴይነር መገንባቱን ጠቅሰው፤ የቢሮ አገልግሎት ችግር እንደሌለና ወደመናኸሪያዎቹ የሚወስድ የትራንስፖርት እጥረት አለ ተብሎ የተነሳው ቅሬታም ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል።
ከኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በሻምቦ፣ ደምቢዶሎ፣ ያቤሎና አምቦ ላይ ዘጠኝ ደረጃቸውን የጠበቁ መናኸሪዎች በአንድ ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር እየተገነቡ ሲሆን፤ ግንባታቸው 96 በመቶ ደርሷል። የጅማ፣ አዳማ፣ ነቀምት፣ ሻሸመኔና ሮቢ መናኸሪያዎች ግንባታዎች በዘንድሮው ዓመት የተጀመሩ በመሆኑ እስከሚቀጥለው ዓመት ሰኔ ወር ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 1/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ