
አዲስ አበባ፡- ‹‹የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) በተለያዩ ዞኖች የሚነሳውን የክልልነት ጥያቄዎችን ለመመለስ ያስጠናው ጥናት ኢ-ሕገመንግስታዊ ነው›› ሲሉ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተቃወሙት። የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በምላሻቸው ‹‹ድርጅቱ ያስጠናው ጥናት ሕገ መንግሥቱን የሚደግፍ እንጂ የሚቃረን አይደለም›› ብለዋል።
የሲዳማ አርነት ንቅናቄ /ሲአን/ ሊቀመንበር አቶ ዱከሌ ላሚሶ እንደገለጹት የክልልነት ጥያቄው በሕገመንግሥቱ መሰረት መመለስ ሲገባው ባልተለመደ መንገድ በጥናት ይመለስ መባሉ ተገቢ አይደለም። የሲዳማ ህዝብ በዚህ ጥናት ላይ ተሳታፊ ሳይሆን ውጤቱ ይመለከተዋል መባሉም ስህተት ነው ብለዋል።
የጥናት ቡድኑ በተገኘው ውጤት ላይ ተመስርቶ ያቀረባቸው ሦስት ምክረ ሀሳቦችን ለመቀበልም ላለመቀበልም ምክንያታዊ መሆን እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ሊቀመንበሩ ከዚህ ይልቅ ምርጫ ቦርድ የሰጠው የአምስት ወር ጊዜ እንዴት መተግበር እንደሚገባ ከቦርዱ ጋር መነጋገር አማራጭ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።
በህገ መንግሥቱ ላይ ከተጠቀሱት ዘጠኝ ክልሎች ውጭ ያሉ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች በሂደት የራሳቸውን ክልል መመስረት እንደሚችሉ ሕገመንግሥቱ በግልጽ ያስቀመጠውን ድንጋጌ ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ጉዳዩ ይጠና መባሉ ኢ-ሕገመንግስታዊና ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው ብለዋል። ቀደም ሲል የተደራጁት ክልሎች በእንዲህ አይነት ጥናት ሳይደገፉ መብታቸውን እንዳስከበሩ የተናገሩት ሊቀመንበሩ ዛሬ ጥያቄውን መነሻ አድርጎ ጥናት መደረጉ ፍትሀዊነት የጎደለው ነው ብለዋል።
‹‹የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ የክልልነትን ጥያቄ ለማስተናገድ አይፈቅድም›› የሚለው አስተሳሰብም ተገቢ እንዳልሆነና ሀገሪቱን ለአደጋ የዳረጋትም ቀደም ሲል የሚነሱ ህገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጣቸው በመቅረታቸው እንደሆነ አቶ ዱከሌ አስታውሰዋል።
የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ ድርጅት ኃላፊ አቶ አንዷለም ታደሰ በበኩላቸው የክልል ጥያቄዎችን ለመመለስ ሲታሰብ መጀመሪያ ህገመንግስቱ ምን ይላል ተብሎ መጀመር ነበረበት በማለት የጥናት ቡድኑን፣ የጥናት ሂደቱንና ውጤቱን ሙሉ ለሙሉ እንደማይቀበሉ ተናግረዋል። የወላይታ ጉዳይ በወላይታ ህዝብና በሕገመንግሥቱ መሰረት የሚፈታ እንጂ እኔ ነኝ የማውቅልህ በሚል አካል ሊወሰን አይችልም ያሉት አቶ አንዷለም የጥናት ቡድኑ በመጀመሪያም ፖለቲካዊ አቋም የተያዘበትን ጉዳይ የጥናት ውጤት ለማስመሰል ያደረገው እንቅስቃሴ ሕገመንግሥታዊ አለመሆኑን አመልክተዋል።
‹‹የወላይታ ህዝብ እየጠየቀ ያለው ትናንት የተነጠቀውን የክልልነት መብት በሕገመንግሥቱ መሰረት እንዲረጋገጥለት ነው። የወላይታ ጥያቄ መልስ ቢያገኝ ለኢትዮጵያ አንድነትና ወደፊት መራመድ ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል እንጂ የሀገሪቱን ሰላም አያናጋም፤ አብሮነትን በማጠናከር የሀገሪቱ የወደፊት እጣፈንታ በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲቆም አስተዋጽኦ አለው›› ሲሉም አቶ አንዷለም ገልፀዋል።
የወላይታ ህዝብ ህገመንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ ክልል መሆኑን ማረጋገጡ አይቀርም በማለትም የሚመለከታቸው አካላት አላስፈላጊ ምክንያት በመደርደር ጥያቄውን ለማፈን የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ትተው በተባበረ ክንድ ሀገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋገር በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የሀዲያ ብሄር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት አባል የነበሩትና በአሁኑ ሰዓት የሀድያ አንድነት ንቅናቄ የፖለቲካ ድርጅት እያቋቋሙ ያሉት አቶ ኤርሱሎ ሊሬ በደቡብ የክልልነት ጥያቄን ለመመለስ የተጠናውን የጥናት ውጤት እንደማይስማሙበት ተናግረዋል።እርሳቸው እንደሚሉት በክልሉ የተደራጁት ብሄር ብሄረሰቦች ከመጀመሪያው ጀምሮ አንድ ላይ መደራጀታቸው ስህተት እንደነበር በመግለጽ አሁንም የቀረበው የጥናት ውጤት ይህንኑ የሚያስቀጥል ነው በማለት ተችተዋል።
በወቅቱ የነበሩ ፖለቲከኞች ያለህዝቡ ፍላጎት ብሄር ብሄረሰቦችን በአንድ ላይ በማደራጀት ክልል መመስረታቸው ጥያቄ ሲያስነሳ መቆየቱን የሚገልጹት አቶ ኤርሱሎ የጥናት ቡድኑ ክልሉ እንደነበረ ይቀጥል በሚል ያቀረበው የመጀመሪያው አማራጭ በተግባር የታየና ብዙ ችግር ያስከተለ በመሆኑ አማራጭ ሆኖ መቅረብ አልነበረበትም ብለዋል።ይህ አይነቱ አደረጃጀት ህዝቡን ማዕከል ያደረገና ፍትሐዊ የሆነ የልማት እንቅስቃሴ ላለመደረጉ ምክንያት እንደነበርም አስታውሰዋል።
በክልሉ የመልማት ዕድል ያገኙ የነበሩት በባለስልጣን የሚደገፉ ሦስትና አራት ከተሞች ብቻ እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ኤርሱሎ በጥናቱ ውጤት ክልሉ ህብረ ብሄራዊ በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ትሩፋቶችን አግኝቷል መባሉ የሀዲያ ዞንን እንደማይገልጽ ጠቅሰዋል። ወቅታዊ የሀገሪቱን ሁኔታ ለመሻገር ሲባል የክልልነት ጥያቄን ማዘግየት በሚል በሦስተኛ አማራጭነት የቀረበውም ሀሳብም ህገ መንግሥታዊ መብትን የሚጋፋ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በምላሻቸው እንዳመለከቱት ድርጅቱ ያስጠናው ጥናት ህገመንግሥቱን የሚደግፍ እንጂ የሚቃረን አይደለም።
ጥናቱ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ 11 ዞኖች ክልል ሆኖ የመደራጀት ጥያቄ ማቅረባቸውና የጥያቄዎቹን መንስኤዎችና መፍትሔዎች በመለየት የህዝቡን ፍላጎት ተረድቶ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አማራጮች አቅርቦ በህዝብ ውሳኔ እንዲሰጥ የሚያግዝ እንደሆነ ኃላፊው አስረድተዋል።
11 ምክር ቤቶች ክልል እንሁን ብለው ጥያቄ ማቅረባቸውን የተናገሩት አቶ ሞገስ ጥያቄ ያቀረቡበት መንገድም ህገ መንግስታዊ ነው ብለዋል። ነገር ግን ከወትሮው በተለየ እንዲህ አይነት ጥያቄዎች ሊበረክቱ የቻሉት ለምንድነው የሚለውን ማጥናት በምንም መስፈርት ኢ-ሕገ መንግስታዊ አይደለም።
ክልሉ ካለው ብዝሀነት አንጻር በአንድ ጊዜ እነዚህ ጥያቄዎች ይስተናገዱ ማለት ክልላዊ አንድምታውን ስለሚጎዳ ተጠንቅቆ ማየትና በዚያው ልክ ህዝብን ማወያያትም አስፈላጊ ነው ብለዋል። ጥናቱ ህገመንግሥቱን እንደማይጻረር የተናገሩት አቶ ሞገስ ወደ ህገመንግሥታዊ ድንጋጌ ከመሄድ በፊት የተሟላ መረጃ ይዞ ከህዝቡ ጋር መወያየት ጥቅሙ የጎላ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በእንዲህ አይነት ሁኔታ የመጣን ጥያቄ በመጣበት አግባብ ይስተናገድ ብሎ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ማስኬድ የታሪክ ተጠያቂ ስለሚያደርግም ጥያቄው የጥቂት አካላት ነው ወይስ የህዝቡ ነው ብሎ መለየትም እጅግ ጠቃሚ ነው ብለዋል። ስለዚህ የሕዝብን ስሜት ለማወቅና የጥናቱን ውጤት መልሶ ለህዝብ በማቅረብ ማወያየት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 1/2011
ኢያሱ መሰለ