
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ወደብ ያጣችበት መንገድ በጣም ያስቆጨኛል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ክፍል አራት የቃለ ምልልስ ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት ወደብ የላትም። ይሄ የሆነበት መንገድ በጣም በጣም ያስቆጨኛል።
ያስቆጨኛል ስል አንዳንዶች ዘመን ያመጣው አጀንዳ ይመስላቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆኔ በፊት የዛሬ አስርም 15 ዓመት በይፋ በቪዲዮና በጽሁፍ ያሉ አቋሞቼ ናቸው ብለዋል።
በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባት ምንም ጥያቄ እንደሌለው አመልክተው፤ ያጣችውን የባሕር በር ጉዳይ በንግግር ማግኘት አለባት። ያ ካልሆነ የተጎዳና የተሰበረ ሀገር በዘላቂነት የሰከነ ሰላም ያመጣል ብዬ አላስብም።መቼም ይሁን መቼ በንግግር ይህ ጉዳይ መስመር መያዝ እንዳለበትም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ወደብ ማጣቷ ግፍና ትልቅ በደል መፈጸሙን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመው በታሪክም ሆነ በፈለገው መስፈርት ይሄ ያስቆጨኛል፤ መፈታት አለበት ብዬ በጽኑ አምናለሁ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙስናን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያም ሌብነት ኢትዮጵያ ውስጥ ልክ እንደ ርዳታው አንዱ ስብራትና ጥፋት መንገድ የምንለው ካልተገራ በቀር ብልፅግናን ለማሳካት እንቅፋት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ሌብነትን ለመከላከል ብዙ አስረናል፤ ብዙ አባረናል፤ ብዙ ቀይረናል ሰዎች፤ ግን አንዱ ይቀየራል አንዱ ይመጣል፤ ባህሉ እስካልተቀየረ ድረስ የሚሸረሸር ሆኖ አላየነውም ነው ያሉት።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ሠርተን ጥረን ግረን ኢትዮጵያን ስንቀይር ነው ችግራችን የሚቀረፍ የሚለውን እምነት በከፍተኛ አመራር ደረጃ በስፋት በውይይት በሥልጠና የራዕይ መጋራት ሥራ ሠርተናል፤ መቶ በመቶ እያንዳንዱ ሰው ምንም እንከን የለበትም ብዬ ደፍሬ መናገር ባልችልም አብዛኛው ከፍተኛ አመራር በእርግጠኝነት ሌብነት ውስጥ የለበትም።
ሌብትን እንደ አንድ ትልቅ ስብራት ልክ እንደ ልመናው አይተን በምዕራፍ ከፍለን እየሠራንበት ያለ ጉዳይ ነው። ለዚህም ሕዝቡም በተለይ ሌቦችን በማጋለጥና ባለመተባበር ተባባሪ እንዲሆን አስገዝበዋል።
በትንሽ ያልታመነ በትልቅ አይታመንም። በትንሽ ላይ ስርቆት የጀመረ ከፍ ሲል አያቋርጥም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሌብነትን ጸያፍና የእድገት ነቀርሳ መሆኑን ሕዝቡ ተባብሮ ትርክቱን ገንብተን እድገት እየመጣ ሲሄድ ይሄ ሰው የሚያስመርረው አደገኛ የሆነው የሌብነት ልምምዳችን እየቀነሰ፤ በሲስተም በሚታገዝ የፈጠነ አገልግሎት እየሰጠን ሕዝባችን እፎይታ የሚያገኝበት ዘመን እየተፈጠረ እንደሚሄድ በእጅጉ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ ገልጸዋል።
ሳሙኤል ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም