አዲስ አበባ፡– ከእምቦጭ በተጨማሪ የውሃማ አካላትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሌሎች ሶስት መጤ የአረም ዝርያዎች በሶስት ሀይቆች ላይ መታየታቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ኢኮሃይድሮሎጂ እና የውሃ ጥራት ዴስክ ፕሮጀክት አስተባባሪ ወንደሰን አበጀ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በተደረገው ጥናት የውሃማ አካላትን ስጋት ላይ የሚጥሉ ከእምቦጭ አረም በተጨማሪ ሌሎች ሶስት መጤ ዝርያዎች በሎጎ፣ በጣና እና አርዲቦ ሀይቆች ላይ ተከስተዋል።
እነዚህ ልዩ መጤ ዝርያዎች በተለይ በውሃ ውስጥ ያሉ ሕይወት ያላቸው ዕፅዋት እና እንስሳት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ መሆናቸውን አመልክተው፤ እነዚህ መጤ አረሞች እንዳይራቡ እና ምርታቸው እንዲቀንስ ያደርጋሉ ብለዋል።
መጤ ዝርያዎቹ እንደእምቦጭ ሁሉ ሳይስፋፉ ከወዲሁ አፋጣኝ ርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበው፤ መጤ ዝርያዎች ወይም አረሞች እንደተከሰቱ ወይም እንደታዩ ሳይስፋፉ ወዲያውኑ ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።
እነዚህ መጤ ዝርያዎች በውሃ ውስጥ ያሉ እጽዋትና እንስሳት እንዳይስፋፉ በማድረግ ከውሃ ሀብታችን ልናገኝ የሚገባውን ጥቅም እንዳናገኝ በማድረግ በኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ እና የውሃ ሀብቱ የሚሰጠውን የሥነ-ምህዳር አገልግሎት እንደሚያዛቡ ገልጸዋል።ለምሳሌ እምቦጭ በክረምት ወቅት የቆቃ ግደብ ተርባይኖች ላይ በመጠምጠም ኃይል እንዳያመነጩ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ የመስኖ ሥራ እና የዓሳ ሀብቱ ላይም በተመሳሳይ ተፅዕኖ ያደርጋል ብለዋል።
በጣና ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተስተዋለው እምቦጭ በአሁኑ ወቅት ወደ አስር በሚሆኑ የውሃ አካላት ላይ ታይቷል ያሉት አቶ ወንደሰን፤ ችግሩን ለማስወገድ በፖሊሲ እና ስትራቴጂ ላይ ተመስርቶ በልዩ ትኩረት መሠራት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
እምቦጭን ለማስወገድ እና ለመከላከል በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም የእምቦጭ መስፋፋት እና የማስወገድ ሥራው ተመጣጣኝ ስላልሆነ እንደ ሀገር በውሃማ አካላት ላይ ትልቅ ስጋት እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል።
ዘላቂ መፍትሔው የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ከላይኛው ተፋሰስ ጀምሮ ማህበረሰቡ እና ባለድርሻ አካላት በቀንጅት መሥራት እንዳለባቸውና በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዋቀረው ኮሚቴ በስትራቴጂክ እቅድ ላይ ተመስርቶ በንቃት መንቀሳቀስ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
በመጤ አረሞቹ አደገኝነትና ጎጅነት ዙሪያም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እና ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ሥራ በመሥራት ከወዲሁ መከላከልና ማስወገድ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የውሃ ማማ ብትሆንም በዚያ ልክ እንዳልተሠራ ጠቅሰው፤ በተፋሰሶች ላይ መሠረት በማድረግ በክልሎች እና በአካባቢዎች ተመጣጣኝ የውሃ ስርጭት እንዲኖር መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
ጸጋዬ ጥላሁን
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም