
አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያ ፈተናዎች ሳይበግሯት የዓባይ ግድብን በተባበረ ክንድና በዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ጫፍ ላይ ማድረሷ ሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የታሪክ ተመራማሪ እና መምህር አየለ በከሪ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ገለጹ።
አየለ በከሪ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ እንደ ግብጽ ያሉ ሀገራት ኢትዮጵያውያን ወንዙን ለማልማት የሚያስፈልጋቸውን ሀብት እንዳያገኙ የተለያዩ አሻጥር ሲሠሩ ቆይተዋል። ኢትዮጵያውያን ፈተናዎች ሳይበግሯቸው በተባበረ ክንድና በዲፕሎማሲያዊ ጥበብ በዓባይ ላይ ትልቁን ግድብ በመገንባት ለፍጻሜ ጫፍ ላይ አድርሰውታል ብለዋል።
ግድቡን በራስ አቅም ገንብቶ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ በጀት፣ ሰላም እና ውይይት ይፈልጋል ያሉት አየለ በከሪ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፤ ይህንንም ኢትዮጵያ በብቃት በመወጣት ለሌሎች ምሳሌ ትሆናለች። በዚህም በግብጾች አካባቢ መደናገጥ እንደተፈጠረ አመልክተዋል።
ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ አለመፍታት ፤ ከምክክር ይልቅ ለጦርነት ቅድሚያ መስጠት የታሪክ ስብራቶች መሆናቸውን ገልጸው፤ እነዚህ ችግሮች ለታሪካዊ ጠላቶች መግቢያ ቀዳዳ እንዳይሆኑ በፍጥነት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአሁኑ ጊዜ ከምን ጊዜውም በላይ ለሀገር ኢኮኖሚና እድገት እንዲሁም ሰላም ኢትዮጵያውያን በትብብር የሚሠሩበት ወቅት ነው ያሉት አየለ (ፕ/ሮ)፤ በተለይ በችግር ውስጥ ሆኖ የዓባይ ግድብን መገንባት የተቻለበትን ጥበብ በሌሎች ሀገራዊ ልማቶች ላይ ማንጸባረቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት ከሚረጋገጥባቸው መስፈርቶች ውስጥ አንዱ በሀገር ውስጥ ያለውን ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ሀብት በነፃነት መጠቀም መቻል መሆኑን አመልክተው፤ በዚህም ሀገራችን የዓባይ ግድብን በመገንባት ሉዓላዊ ሀገር መሆኗን በተጨባጭ አስመሰክራለች ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን የተፋሰሱን ሀገራት ታሳቢ ባደረገ እና ዓለም አቀፍ ሕግን ባከበረ መልኩ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን አየለ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ገልጸዋል።
ግብጾች ኢትዮጵያን ተጠቃሚ በማያደርግ መልኩ በዓባይ ወንዝ ላይ ታሪካዊ መብት አለን እንደሚሉ ያስታወሱት ፕሮፈሰሩ ፤ ኢትዮጵያ ለወንዙ በ85 በመቶ ውሃ እያበረከተች የተጠቃሚነት መብቷን የሚከለክላት ሕግ እንደማይኖር አስታውቀዋል።
እ.እ.አ በ1929 እና በ1959 የወጡት ሕጎች መጀመሪያ ግብጽን ቀጥሎ ሱዳንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው። ግብጽ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በነበረችበት ወቅት እንግሊዞች ዓባይ ወንዝን ከምንጩ ለመቆጣጠር ይፈልጉ ነበር፤ ሕጎቹም የዚሁ እውነታ ነጸብራቅ ናቸው ብለዋል
ግብጽ ሁል ጊዜ ኢትዮጵያውያን በእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ እንዲኖሩ ትፈልጋለች ። ይህም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ትኩረት እንዳታደርግ፣ ኢኮኖሚዋ እንዳያደርግ፤ የውጭ ርዳታና ብድር ፈላጊ ሀገር እንድትሆን ማድረጉን አመልክተዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም