አዲስ ዘመን ድሮ

ወይ ዘመን! አቤት ጊዜ! የሚያስብሉን አንዳንድ ነገሮች ይኖራሉ፤ ለምሳሌ በ25 ሳንቲም መዋጮ መንገድ ተሠራ ቢባል፡፡ ከነበርንበት የደረስንበትን በአዲስ ዘመን ድሮ ገጾች ብዙ እናያለን፡፡ በባቡር የተገጩት ሁለቱ ፈረንጆች፣ ሌባ አዳኙ ሌባ ሆኖ መገኘቱንና ሌላም ለዛሬው ትውስታችን፡፡

በ25 ሳንቲም መዋጮ የተሠራው መንገድ ተመረቀ

ከመረዳጃ በቀር ለልማት ተብሎ የተዋጣው የ25 ሳንቲም ክፍያ የተሠራው መንገድ ተመረቀ፡፡ መንገዱን ያሠራው በገፈርሳ ወረዳ ግዛት የሰፈረ ገነት የልማት ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ የተቋቋመው በሰፈረ ገነት ዕድር ውስጥ ሲሆን ለልማት ተብሎ በተዋጣው ገንዘብ ተሠርቶ የተመረቀው ገንዘብ በሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ ካለው መንገድ አንስቶ ወደ ሕዝቡ መኖሪያ የሚደርስ ነው፡፡

ይህ መንገድም ቀድሞ ለእግር ጉዞ እንኳን አስቸጋሪ እንደነበረና በክረምትም ወራት የማጡ ኃይል በሕዝብ ላይ ከባድ ጉዳት ያደርስ እንደነበር አቶ ግርማ ሸንቁጤ የሰፈረ ገነት የልማት ፀጥታ ድርጅት ሊቀመንበር አስታወቁ፡፡

በ25 ሳንቲም የልማት መዋጮ አዲስ የተሠራው መንገድ ከ9 መቶ ሜትር በላይ ርዝመት ሲኖረው ሊሠራ የቻለው፤ ከልማት መዋጮ ከሰፈሩ አካባቢና ከሌሎች በጎ አድራጊዎች በተገኘው የገንዘብ እርዳታ ነው፡፡

በጠቅላላ መንገዱ ከአራት ሺህ ብር በላይ ፈጅቷል፡፡ መንገዱ ተመርቆ የተከፈተው በቀኛዝማች ዘለቀ ይጥና የሰሜን ማዘጋጃ ቤት ረዳት ከንቲባው ነው፡፡ ይህም ኅብረት ሥራ ለቀሩት ወረዳዎች ሁሉ ታላቅ ምሳሌ መሆኑን ረዳት ከንቲባው በምረቃው ወቅት ገልጠዋል፡፡

የሰፈረ ገነት የልማትና ፀጥታ ጥበቃ ድርጅት አሁን ካሠራው ሌላ በተጨማሪ አራት አውራ መንገዶችን ከፍቶ ከዋና ዋና መንገዶች ጋር ለማገናኘት ዕቅድ እንደላውና የ25 ሳንቲም መዋጮ እንደቀጠለ መሆኑን አቶ ግርማ ገልጠው፤ አዲስ በተመረቀው መንገድ ሥራ ላይ ሴቶች ተካፋይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ወደፊት የሚከፈቱ መንገዶች በጠቅላላው 10 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ የሚፈጁ ናቸው ተብሎ ተገምቷል፡፡

(አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 1966 ዓ.ም)

በባቡር የሞቱት 2 ፈረንጆች

ባለፈው በታኅሳስ 12 ቀን አቃቂ በሰቃ ላይ በባቡር ተገጭተው የሞቱት ሦስቱ ጣሊያኖች ለቁልቢ ገብርኤል ስዕለት ከሮማ ድረስ የመጡ መሆናቸው ተገለጠ፡፡

በባቡር አደጋ የሞቱት ጣሊያኖች ሪንስቶ፣ ማሪኒ እና ቶኒኖ እንዲዩ የተባሉ ናቸው፡፡ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ከሮማ ድረስ መጥቶ የነበረው ቶበሊ ማፊያ የተባለው በባቡር አደጋ በጠና ቆስሎ ሆስፒታል በመታከም ላይ ነው፡፡ ሦስቱ የውጭ ዜጋዎች ከአዲስ አበባ በባቡር ተሳፍረው ወደ ቁልቢ ገብርኤል ለመሄድ በጉዞ ላይ እንዳሉ አቃቂ ባቡር ስለቆመ ሀገር ለማየት ከመሬት ስለወረዱ በድንገት ባቡር ስለተገጩ ሁለቱ ወዲያው ሲሞቱ አንደኛው በጠና ቆስሎ በፖሊስ እርዳታ ለሕክምና አዲስ አበባ ተመልሷል፡፡

ጣሊያኖቹ ለስለት የሚሆን ልዩ ልዩ ዕቃዎች ሳይዙ እንዳልቀሩ የሸዋ ፖሊስ የማስታወቂያ ክፍል የተሰማው ጭምጭምታ ይገልጣል፡፡

(አዲስ ዘመን ጥር 10 ቀን 1966 ዓ.ም)

ሌባ አዳኙ ሌባ ሆኖ ተገኘ

በደብረ ማርቆስ አውራጃ የጎጃም ወረዳ ግዛት ውስጥ ሌባ አዳኝ (ነጭ ለባሽ) ገላዬ ካሣ የተባለውን የተሰጠውን አደራ በመዘንጋ የሰላማዊ ሕዝብን ሀብት ንብረት በመዝረፍ ሕዝብን በድሏል ሲባል ሲወራበት ከቆየ በኋላ፤ ሐሰትና ቅጥፈት የኋላ ኋላ መገለጣቸው አይቀርምና የመጨረሻው ጊዜ አቶ በላይ ደጉን ግምቱ አራት መቶ የሆነ ሀብት በመስረቅ ግላዊ ወንጀል ሠርቷል ተብሎ ስለተከሰሰና የሠራውም የስርቆትና የዘረፋ ወንጀል እጅግ የበዛ በመሆኑ፣ በፖሊስ በመከታተል ሁኔታው ተጣርቶ ደብረ ማርቆስ አስቻለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ፣ የሠራውም የስርቆት ወንጀል ተመስክሮበት ስለወንጀሉ 5 ዓመት ተፈርዶበት እወህኒ ቤት ገብቷል፡፡ ስለዘረፈውና ስለሰረቀው ገንዘብ ግን በፍትሐ ብሔር ተከሶ እንዲከፍል ተደርጓል፡፡

ይህን ሌባ አዳኝ የሚባል ስም የተሰጠው የመንግሥቱ ሌቦችን ወስላቶች፣ ነፍሰ ገዳዮችን ጭምር እየተከታተለ በመያዝና ለበላይ ባለሥልጣናት አቅርቦ አስፈላጊውን ቅጣት በማስወሰን የሕዝቡን ችግር እንዲያቃልል የተሰጠውን ሥልጣን ክዶ፣ አይሰማብኝም አይገለጽብኝም በማለት በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ይህን የስርቆትና የዘረፋ ወንጀል ሠርቶ መገኘቱ፤ የወስላቶች መንፈስ የተቆራኘው የማስተዋል ችሎታ የሌለው መሆኑን ከመረዳቱም ይልቅ፤ እሱን የመሰለ የሱን ውስልትና ተግባር እየተከተለ እንደዚሁ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ወንጀል ሲፈጽም ስለተገኘ፣ ፍሬው ብርሃኔ ስለተባለውም ሌባ አዳኝ ተከሶ የሠራው ወንጀል የተጨበጠ በመሆኑ፣ ውሳኔ ባልተሰጠ ጊዜ እስር ቤት እንዲቆይና ወደፊት ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሚወሰንበትን ፍርድ እንዲጠብቅ ተወስኗል፡፡

ስለዚህ ወደፊትም ቢሆን ፖሊሶች በበለጠ መከታተልና ይህን የመሰለውን እምነት አጉዳይ ወንጀለኛ በመመርመር ማግኘት የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡

(አዲስ ዘመን የካቲት 20 ቀን 1951 ዓ.ም)

ሦስቱ ሴቶች ተቀጡ

ወንዶች ከሚለብሱት ቁምጣ ያጠረ ቀሚስ /Supermini/ ለብሰው ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ ሲዘዋወሩ የተገኙት ሦስት ሴቶች በ6ኛ ፖሊስ ጣቢያ አማካይነት ተከሰው እያንዳንዳቸው አሥር ብር ተቀጡ፡፡

ወይዘሪት ገነት፣ ወይዘሪት ወይንሸት፣ ወይዘሪት ምሥራቅ የተባሉት ሦስት ሴቶች ነሐሴ 28 ቀን 1962 ዓ.ም. ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ ቆራጣ ቀሚስ ለብሰው ምክንያት ሳይኖራቸው በግዮን ሆቴል ቅጥር ግቢ ከእንግዶች ማረፊያ ክፍሎች ሲዘዋወሩ በፖሊሶች ተይዘዋል፡፡ ተከሳሾቹ ከተያዙ በኋላ በሰጡት ቃል ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ካዛንቺስ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተነስተው ለመታየት ብቻ ወደዚሁ ስፍራ መሄዳቸውን አምነዋል፡፡ በሦስቱም ወይዘሪቶች ላይ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 61 መሠረት በአራተኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦባቸው ተከሳሾቹ ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ ስለጠየቁ እያንዳንዳቸው አሥር ብር ተቀጥተዋል፡፡

(አዲስ ዘመን ነሐሴ 1962 ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You