ሁላችንም ሰው ሆነን የተወለድን ብንሆንም ሰውን ሰው የሚያደርገውን ሥራ ሠርተን እስከ ህልፈታችን ድረስ ሰው ሆነን የምንዘልቅ ብዙ ላንሆን እንችላለን። ምክንያቱም ሰው መሆን ረቂቅ በሆኑ እሴቶች ይለካል። ለህሊና ታማኝ፣ ለሞራል ሕጎች መገዛት፣ ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት፣ ለሰዎች መኖርን… ይጠይቃል። ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነልቡናዊ ሁኔታን አሟልቶ መያዝንም እንዲሁ። ይህ ግን በብዙዎች ላይ የሚሆን አይደለም። ለዚህ የተሰጡ ጥቂቶች ግን ሆነውታል።
ወይዘሮ ዘውዲቱ መሸሻ ግን ከራሴ ምቾት ችግረኛን መርዳት ይቅደም በማለት ጥሩ ኑሯቸውን ትተው ለሰው በመኖር አርአያነት ያለውን ተግባር ተወጥተዋል። በዚህም ሥራቸው ለዛሬው «የህይወት እንዲህ ናት» እንግዳችን አድርገናቸዋል። ለመሆኑ ይህ ለሰው መኖር እንዴት ተጀመረ፤ ዛሬስ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል የሚሉና የመሳሰሉትን በማንሳት ከእርሳቸው ጋር ቆይታን አድርገናል።
ከሸዋ በላይ
ወይዘሮ ዘውዲቱ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ማማ ምድር ወይም ሞላሌ ወረዳ ውስጥ አንባ ሲኖዳ በምትባል ቦታ ነው የተወለዱት። ያደጉትም በዚያው ሥፍራ ሲሆን፤ በብዙ ቤተሰብ መካከል ነው። ቤተሰቡ የችግረኛ ልጆችን ቤተሰቤ ብሎ የሚቀበልና የሚያሳድግ ነው። ስለዚህም የዛሬ ሰብሳቢነታቸውም ከዚያ የወረሱት መሆኑን ይናገራሉ።
ለቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ ሆነው እንደብርቅ እየታዩ አደጉ፤ ሁሉም ለእኔ የሚሏቸውም አይነት አጓጊ ልጅ ናቸው። በእርግጥ አንድ የተለየ ፀባይ እንዳለባቸው አይሸሽጉም። ይኸውም ሃይለኝነት ነው። በዚህም ብዙ ጊዜ እኩዮቻቸውንም ሆነ የሰፈር ሰዎችን እንዲደበድቡና በአስቸጋሪነት እንዲፈረጁ ሆነዋል። ከቤተሰብ ወጥተው እንዳያድጉና ትምህርትን በጊዜው እንዳይጀምሩም ያደረጋቸው ይህ ባህሪያቸው ነበር። ወላጆቻቸው እንዲማሩላቸው ይፈልጋሉ። ሆኖም ለመማር ከተማ መሄድ ግዴታ በመሆኑ ለብዙ ዓመታት ከእጃቸው ያላስወጡበት ምክንያትም ይኸው ነው።
ወይዘሮ ዘውዲቱ በሰው አይን የሚገቡ፤ መልከ መልካም እናት ናቸው። ዛሬን ያያቸው መለስ ብሎ ልጅነታቸውን ሲያስብ “አፋጀሽን” የሚያስብሉ አይነት ናቸው። ውብ እመቤት። በአካባቢያቸው ሲያጋጥማቸው በነበረው የጤና ችግር ምክንያት ከእናታቸው በግድ ተለይተው በአስር ዓመታቸው አዲስ አበባ መግባታቸውን ይናገራሉ። አራት ዓመት ሙሉም ምኒልክ ሆስፒታል እየተመላለሱ ይታመም የነበረውን አይናቸውን ታክመዋል። ይህም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ከበሽታቸው አልዳኑም። ይልቁንም አንድ አይናቸውን ከለላቸው። ዛሬ አይናቸው ከብለል ከብለል ሲል ለተመለከተ ይህንን ለመቀበል ያዳግተዋል። እውነታው ግን ይሄው ነው።
ወይዘሮ ዘውዲቱ በአይናቸው ሰበብ አዲስ አበባ በመግባታቸው የመማር ዕድል ገጥሟቸዋል። ሃይለኝነታቸው ግን ትምህርት ቤት ሳይቀር ወንዶችን ቀበቷቸውን እየፈቱ ይደበድቡ እንደነበር ያስታውሳሉ። ፖሊስም ቢሆን በድንጋይ ፈንክተው እንደሚያውቁ ያነሳሉ። ይሄ ሃይለኝነታቸው የሰለቻቸው አያታቸው ምንም ማድረግ ስላልቻሉ ከአንዱ ትምህርት ቤት ወደ አንዱ ያዟዟሯቸው እንደነበርም አይረሱትም።
በቁንጅና ከእናታቸው ጋር እንደሚመሳሰሉ የሚናገሩት ወይዘሮ ዘውዲቱ፤ እናታቸው ብዙዎች የሚመኟቸው አይነት ሴት በመሆናቸው የሁለት ወር ቅሪት እያሉ አባታቸው ቢሞትም ቶሎ ሌላ ወንድ ማግባት የቻሉ መሆናቸውንም አጫውተውናል። በዚህም አባቴ ብለው ያደጉት በህይወት የተለዩትን አባታቸውን ሳይሆን የእንጀራ አባታቸውን መሆኑን ይናገራሉ። እርሳቸውም በጣም ይወዳቸውና ይንከባከባቸው እንደነበርም ይገልፃሉ። በቤት ውስጥ ከመብላትና ከመጠጣት ውጭ ምንም አይነት ሥራ እንዳይሠሩ ያደርጓቸዋልም።
«የእንጀራ አባቴ ተንከባካቢዬ ብቻ ሳይሆን እናቴም ጭምር ነው። በጣም እወደዋለሁ። ይሁንና አንድ ወቅት ላይ በጠና ታምሜ እዚህ አትቀበርም ተብሎ ወደ አያቴ ቤት ተወሰድኩ። በአያቴም ፀሎት ዳንኩ። ከዚያ ግን አያቴ ልጄም ሆነች ልጇ እርሱ ጋር መሄድ የለባቸውም በማለታቸው በእዚያው ቀረን። ይህ ደግሞ ከምወደው አባቴ አለያየኝ» ሲሉ ይቆጫሉ። ከዛም አያታቸው ጋር እያሉ እናታቸው ሃይለኛ ባል አገቡ። ይህ ደግሞ ለእርሳቸው መርዶ እንደነበር ያነሳሉ። ምክንያቱም ተደባዳቢ ነው፤ እናታቸውንም ሆነ እርሳቸውን በየቀኑ ይደበድባቸዋል። በዚህም ከእርሱ ጋር ተስማምተው መኖር ስላቃታቸው ወደ አዲስ አበባ መጥተው ሚስማር ፋብሪካ በአባታቸው እናት ቤት እንዲያድጉ ተደረጉ።
ወይዘሮ ዘውዲቱ እንደ ልጅ ተጫውተው አላደጉም። ምክንያቱም ከቤተሰብ ውጭ የዕድሜ ጓደኛ የላቸውም። ቢኖራቸውም መግባባት ስለማይችሉና ስለሚመቷቸው የዕድሜ ጓደኞቻቸው ከእርሳቸው ጋር መጫወትን አይፈልጉም። ስለዚህ ብዙ ጊዜያቸውን ያሳለፉት በቤት ውስጥ ከቤተሰብ ጋር እየተጫወቱ ነው። ይሁንና ከዚህ የተለየ ከጎረቤት ጋር የሚያቀራርባቸው ነገር እንደነበር ያነሳሉ። ይኸውም የተቸገረ አይተው አለማለፋቸው ነው፤ ከቤት ውስጥ ሽሮ በርበሬ ሳይቀር ሰርቀው ችግረኞችን ይረዳሉ። ምንም ሃይለኛና ተደባዳቢ ቢሆኑም በነበራቸው የለጋስነት ባህሪያቸው ጎረቤት ይወዳቸው እንደነበር አውግተውናል።
በተለያዩ ጊዜያት ካላቸው ባህሪ አንፃር የተለያዩ ቅጽል ስሞች ይወጡላቸው እንደነበር የሚያነሱት ወይዘሮ ዘውዲቱ፤ ከሁሉም በላይ የሚገርማቸው “ከሸዋ በላይ” የሚለው መጠሪያቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ሸዋዎች መልከ መልካም ሃይለኛና ለጋስ በመሆናቸው ከሸዋ በላይ ማን አለ ለማለት ሲፈልጉ ይህንን ስም አወጡልኝ ይላሉ።
አመል ያወጣል ከመሐል
አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ የቄስ ትምህርት የጀመሩት ወይዘሮ ዘውዲቱ፤ ካቴደራል ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ገብተው እስከ ዳዊት ድረስ ደግመዋል። የወቅቱ የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ዘመድና የንስሐ አባት ስለነበሩ ደግሞ ምንም እንኳን አስቸጋሪ ባህሪ ቢኖራቸውም እንዳያቋረጡ ተደርገዋል። መፈሳዊነትና ግብረገብነትም መማር መጀመራቸው የባህሪ መሻሻል እንዲያመጡ ዕድሉን አመቻችቶላቸዋል። ይህ ሲጠናቀቅ ደግሞ ጉዞ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ሆነና በቀድሞ አስፋወሰን በአሁኑ ምስራቅ ጎህ ትምህርት ቤት ገቡ።
እስከ አምስተኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ከዩኒት ሊደሩ ጋር በመጋጨታቸው ምክንያት ትምህርት ቤት አልሄድም አሉ። አያት ግን ከትምህርታቸው እንዲቀሩ አይፈልጉምና ትምህርት ቤት ቀይረውላቸው እንዲማሩ አደረጓቸው። ምኒልክ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትም አስገቧቸው። በዚህም ቢሆን ብዙ አልቆዩም፤ ሃይለኝነታቸው ከብዙዎች ጋር ስላጋጫቸው ከስምንተኛ ክፍል በድጋሚ ትምህርታቸውን አቋረጡ። በዚያ ላይ የእናታቸው መሞት ታክሎ ትምህርቱን እንዳይቀጥሉ አድርጓቸዋል።
ከዓመታት ቆይታ በኋላ በነበራቸው ውጤት ተወዳድረው በቀድሞ ልዕልት ተናኘወርቅ ትምህርት ቤት በመግባት በባልትና ውጤቶች ዝግጅት በዲፕሎማ ተማሩ። ከዚያ በኋላ ግን ትምህርታቸውን አልቀጠሉም። በተመረቁበት ሙያ እየሠሩ ብዙዎችን ወደ መሰብሰቡና መርዳት ገቡ።
ለሰው መኖር
«በየመንገዱ የወደቀ ሰው ማየት ለእኔ የሁልጊዜ ህመም ነው። ሁሉን አንስቼ ደግሞ አልችልም። በተለይ አሁን በዕድሜም ሆነ በኢኮኖሚ ይህንን ማድረግ የምችልበት ላይ አይደለሁም። ስለዚህ ሁልጊዜ እነርሱን እያየሁ በህመማቸው ከመታመም ውጭ ምንም ምርጫ እንዳይኖረኝ ሆኛለሁ» ሲሉ የሚናገሩት ባለታሪኳ፤ ዛሬ ሎተሪ ቢደርሰኝ ብዬ የምመኝበት ቀን ብዙ ነው። ምክንያቱም ለለቅሶም ሆነ ለተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ከቤቴ ስወጣ በስቃይ ውስጥ ያሉትን የማያቸውን ሰዎች አድንበት ነበር። ግን ሎተሪውም ቢሆን ዕድለኛ ብቻ ስለሚያገኘው ሀሳቤ እውን አይሆንም። እናም ዘላለም ጭንቀታቸው እያሳመመኝ ይዘልቃል ይላሉ። እኔን መሰል በጎ አድራጊም ሳላይ ብሞት ይቆጨኛል ብለዋል።
እንደኛው ተፈጥረው እንደኛው ሰው ሆነው ከደጅ ሲያድሩ ማየት የማያመው ሰው ይኖራል ብለው እንደማያምኑ የሚናገሩት ወይዘሮ ዘውዲቱ፤ መንግሥት ጣልቃ ቢገባ ይላሉ። ምክንያቱም የባህሪ ልዩነት ለሁሉም ሰው ያስፈልጋል። ደጉ ሰው በጎ ነገር እንዲያደርግ ችግረኛው የሚያሳየው ባህሪ ወጣ ያለ ነው። በዚህም ትሁቱ፣ መለወጥ የሚችለው እንኳን እንዳይለወጥና በጎ እንዳይታሰብለት ያደርጋል። እናም መንግሥት የሚቀጣውን እየቀጣ መስመር ቢያሲዘውና በጎ አድራጊዎችን እያበረታታ ለችግረኞች ቢደረሱ አገራችን ምንም ለማኝ አይኖርባትም ይላሉ። በተለይ የራቁት ዳንስ ቤቶች በእጅጉ ሊታዩና ከችግራቸው የሚወጡ ወገኖች እንዲኖሩ ቢሠራ መልካም እንደሆነ ያነሳሉ።
ወይዘሮ ዘውዲቱ መጀመሪያ የበጎ አድራጎት ተግባራቸውን የጀመሩት ከአርሲ አካባቢ ተፈናቅለው መንገድ ዳር በወደቁ 26 አባወራዎችና የልጅ ልጆቻቸው አማካኝነት ነበር። ወቅቱ በ1984 ዓ.ም ሲሆን፤ የመንግሥት ለውጥ የተደረገበትና ብዙዎች በችግር ውስጥ የወደቁበት ነው። እናም እርሳቸው ችግር እስኪያልፍ ድረስ ኑ እኔ ቤት አብረን እንኑር ብለው አስገቧቸው። ወቅቱ ሲረጋጋ ግን አባወራዎቹ ጥገኛ እንዳይሆኑ ስለፈለጉ መቋቋሚያ ሰጥተው ወደ ቀያቸው መለሷቸውና እንዲሠሩ አደረጉ። ልጆቹንና የልጅ ልጆቹን ግን አለቀቋቸውም። ምክንያቱም ትምህርት አስጀምረዋቸው ነበር።
እነዚህን ልጆች እያስተማሩ እያለ ደግሞ ከአካባቢው የነበሩ ሰዎች የወደቁ ልጆችን ሲያገኙ ወደ እርሳቸው እንዲያመጡ የሚረዳው ልጅ ቁጥር እንዲበራከት ሆኖ 250 ደረሰ። ይህ ሁሉ ተረጂ የሚቦርቅበት ቤት አዲሱ ገበያ አካባቢ ከአንድ መነኩሴ የገዙት ቤት ነበር። ይሁንና በመንገድ ምክንያት በመፈረሱና ምትክ ባለመሰጠቱ የተነሳ መርዳትን ገንዘባቸው ያደረጉት ወይዘሮ ዘውዲቱ ልጆቼን አልበትንም ብለው ተከራይተው ማኖር ጀመሩ። ነገር ግን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በልጆቹ ብዛት ምክንያት ብዙ ወጪ ይጠየቅ ጀመር። ልቀቁ እስከመባልም ደረሱ። በዚህም ያላቸውን ሁለት መኪና እና ቤታቸውን ሸጠው እንኳን መደጎም አቃታቸው።
የልጆቹን መበተን ማየት አልፈልግም ብለውም ገዳም ገቡ። ይሁንና ሌላ የገዙት ቤት በመኖሩ እርሳቸው በሌሉበት ቆርቆሮ በቆርቆሮ ተሠርቶ ልጆቹ እንዲገቡ ተደረገ። እርሳቸውም ከሄዱበት ተሸምግለው ተመለሱ። አሁን እነዚያን ለወግ ማዕረግ አብቅተው ሌሎችን ተክተው እያሳደጉ ይገኛሉ። አንዳንዶቹም ባደጉበት እና ለወግ ማዕረግ በበቁበት ቤት በሙያቸው ተቀጥረው ያገለግላሉ።
በእርሳቸው ቤት የሚኖር ልጅ አለመማር አይችልም። በብሔር፣ በሃይማኖትና በመሳሰሉት ተጽዕኖ እንዲፈጠርበት አይደረግበትም። ስለዚህም በትምህርታቸውም ውጤታማ ሆነው ለሌሎች ወገኖቻቸው እንዲደርሱ ነው የሚያድጉት። አሁን በግቢያቸው ውስጥ 40 ልጆችን የሚንከባከቡ ሲሆን፤ ቤተሰብ ላይ ሆነው የሚረዷቸው 30 ልጆችም አሏቸው። በቀጣይም አቅሜና ዕድሜ ካለኝ በሰዎች አጋዥነት ከዚህ በላይ አደርጋለሁ የሚል ተስፋ እንዳላቸውም አጫውተውናል።
ፈተና
250 ልጆችን ሰብስበው በሚደግፉበት ወቅት የገጠማቸውን ችግር መቼም እንደማይረሱት ይናገራሉ። ሰዎችን ከመጠን በላይ በማመናቸው እስከ እስር መዳረጋቸውን ያስታውሳሉ። ምክንያቱ ደግሞ አንድ የሚረዳቸው ዶክተር ዕቃ ያመጣና አስቀምጡልኝ ይላቸዋል። ሰዎችን የሚወዱትና የሚያምኑት ወይዘሮ ዘውዲቱም በክብር ዕቃውን ተቀብለው ያስቀምጣሉ። ሆኖም በደቂቃዎች ውስጥ ፖሊስ መጥቶ ፍተሻ ይጀምራል። የተጠቀለለው ሲፈታም የጦር መሣሪያ ሆኖ ይገኛል። ወዲያው እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል በማለት ወደ ማረሚያቤት ወሰዷቸው።
ለፍርድ ሳያቀርቧቸውም ወራትን አሳለፉ። በመጨረሻ ግን ለፍርድ ሲቀርቡ ዳኛውን በማስፈቀድ ዶክተሩን ጠየቁት። እርሱም ምንም እንደማያውቁና እርሱ እንዳደረገው ተናገረ። በዚህም ምክንያት ከእስር ተፈቱ። ግን አሁንም ቢሆን መታመንን አላቆሙም። ምክንያቱም ለእኔ መታመን ጥንካሬ ነው ብለው እንደሚያምኑ አጫውተውናል።
በልጆቹ ህመም ምክንያት ብዙ ችግሮችን አሳልፈው እንደነበር ያነሳሉ። ግን አምላክ ችግርን ያውቃልና ሁሉም ወዲያው ይድኑልኝ ነበር። አስከሬን ከቤቴ ወጥቶ አያውቅም። ብዙ ንብረቶቼን በህመማቸው ምክንያት ባጣም ጎድሎብኝ አያውቅም። ይልቁንም በበጎ ልጆቼ እየካሰኝ ነው ይላሉ። በገንዘብ የማይተኩትን ሀብቶቼን አትርፎ ስለሰጠኝም አምላኬን አመሰግነዋለሁ ይላሉ።
ልጆቹ በባህሪም ሆነ በተለያየ መልኩ ቢፈትኗቸውም ይውጣ ብለው አያሰናብቱም። ራሱ ከሰለቸው መሄድ ይችላል። እኔ ግን ይህንን አድርጌ ዕድሉን ማበላሸት አልፈልግም። ከዚህ ቢወጣ አወዳደቁ ስለሚከፋ ለማንም የምመኘው ተግባር ስላልሆነ አላደርገውም። በዚህም በትግስቴ ብዙዎች እንዳይበላሹና የተሻለ ባህሪ ማምጣታቸውን ያስታውሳሉ።
ልጆቹን ሰብስበው ሲያሳድጉ የገቢ ምንጫቸው የባልትና ውጤት እንደነበር የሚያስረዱት ባለታሪኳ፤ ለትልልቅ ሆቴሎች በብዛት የባልትና ውጤታቸውን ይወስዱላቸው ነበር፤ በዚህም ብዙ ገቢ እንደነበራቸው ይገልፃሉ። ይሁንና ዛሬ ለሚያሳድጓቸው ልጆች ብዙ የሚጎላቸው ነገር እንዳለ ያነሳሉ። እግር የጣለው ሁሉ እየደጎመ፤ እንደእነ ካፕቴን እግዜሩና ባለቤቱ ዶቄት እያስፈጨ የሚያመጣ ሌላኛው ካፒቴን አይነት ባያግዟቸው ቤቱ ተዘግቶ ይህንን ማድረግ ይከብዳቸው እንደነበርም አጫውተውናል። ይህ ደግሞ ከህመምም በላይ ህመም ይሆንባቸው እንደነበር ነግረውናል።
ሌላው ፈተናዬ ነበር ያሉን ደግሞ ከወረዳው የሚደርስባቸው የዕለት ከዕለት ጭቅጭቅ ነው። “አቅምሽ በመድከሙ እነርሱን መንከባከብ አትችይም። ሠራተኛ ካልቀጠርሽ ደግሞ ልጆቹን በትኝ “ይባሉ እንደነበር ያስታውሳሉ። በቅጥር ግቢውም ቆርቆሮ ኳ ባለ ቁጥር ሮጠው መጥተው ያስቆሟቸው እንደነበርም ይናገራሉ። ይሁንና ሳይደግስ አይጣላ እንዲሉ ሆነና የእሳት አደጋ በመከሰቱ ምክንያት መገናኛ ብዙሃን ሲያገኟቸው እውቅናውም አብሮ መጣ። በወቅቱ ሦስት ወፍጮን ጨምሮ ልጆቹን የሚያስተዳድሩበት ብዙ ንብረት ተቃጥሎባቸዋል። መኖሪያ ቤቶቹም ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል። ነገር ግን መገናኛ ብዙሃን ስላስተዋወቃቸው ቀበሌው ክርክሩን ትቶ በራሱ ወጪ ቤቱንም ሆነ አጥሩን ቆርቆሮ በቆርቆሮ አጠረላቸው። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጎበኟቸው በኋላ ብዙ ችግሮች እየተፈቱላቸው መሆኑን ያነሳሉ። በቅርቡም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ፎቅ እንደሚሠራላቸው የተገባላቸው ቃል ተስፋቸውን አለምልሞታል። የተጋረጡባቸው ፈተናዎች ሁሉ እንደሚቃለሉላቸው ተስፋ ያደርጋሉ።
ቤተሰብ
ያገቡት በቤተሰብ ግፊት ነበር። ራሱ ቤተሰብ መረጠና ዳራቸው። ይህ ደግሞ ብዙ ፈተናዎችን እንዲያልፉ አስገደዳቸው። ብዙ ትምህርትም አስተማራቸው። እንዴውም የልጅነት ሃይለኝነቱም በመጠኑም ቢሆን የተገታው ከዚህ በኋላ መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ ውስጥ አልፈው አንድ ልጅ አግኝተዋል። ይህም አስደስቷቸዋል። ይሁን እንጂ ቆይታቸው በፈተና የታጀበና ለብዙ ጊዜ በህመም ውስጥ ያሳልፉ እንደነበር ያነሳሉ። ምክንያቱም ልጅ ለመወለድ ብዙ ሐኪም ተፈራርቆባቸዋል። በመጨረሻ በፈረንጆች አማካኝነት ቢገላገሉም ለበሽታ ዳርጓቸዋል። ዛሬ በባህላዊ መድሃኒት ቢድኑም።
ከዚያ በኋላ ልጅ ለመውለድ እንዳልቻሉ የሚናገሩት ወይዘሮ ዘውዲቱ፤ የልጅ ጥማታቸውን ለማርካት የችግረኛ ቤተሰብ ልጆችን እየሰበሰቡ ልጆቼ ማለትን ገንዘባቸው አደረጉ። የአብራካቸው ክፋይ ልጃቸውም “የልጅ ልጅ አሳይታኛለችና አመሰግናታለሁ፤ በችግሬም ቢሆን ከጎኔ አትለየኝም።” ሲሉ ያመሰግናሉ።
ምሥክርነት
ቀሲስ አበባየሁ ፈቃዱ ይባላሉ። በሳይንስና ቴክኖሎጂ የጨረራ ኒኩለር ዘርፍ ባለሙያ ናቸው። ወይዘሮ ዘውዲቱን ያገኟቸው ከሦስት ዓመት በፊት ቢሆንም፤ ደቡብ ክልል በቤተክርስቲያን አገልግሎት ድሆችን ሲደግፉ ነበር የተዋወቋቸው። በዚህም ስለ እርሳቸው ብዙ ነገር ይናገራሉ። 46 ልጆችን በዲግሪና በዲፕሎማ አስመርቀው ድረው ኩለዋል። ይህ ደግሞ ለሰዎች መብራት እንደሆኑ የሚያሳይ ነው ይላሉ። እርሳቸው መሬት ላይ ተኝተው ችግረኞች ከፍ እንዲሉ የሚፈልጉ፤ ብዙ ጊዜም ከሚያሳድጓቸው ልጆች ጋር በመተኛት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ እናት መሆናቸውን ይናገራሉ።
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ቦታ ተረክበው ቁስቋም አካባቢ ለአንድ ሥራ ተቋራጭ ሥራውን በ20 ሚሊዬን ብር የሚፈጅ ውል ተዋውለው ሥራውን የጀመሩላቸው ያለምክንያት እንዳልሆነ የሚያስረዱት ቀሲስ አበባየሁ፤ በአዩዋቸው በማግስቱ መጥተው እርሶ በዚህ ዕድሜዎ የሚያደርጉትን አይቼ መተኛት አልቻልኩም ነበር ያሏቸው። እናም እኝህ እናት የችግረኞች ብርሃን ናቸው።
ስለዚህ አጋዦች እየመጡ ሊደግፏቸውና በእርሳቸው መብራትነት ብዙዎች ብርሃን እንዲያገኙ ማድረግ ለነገ የሚባል አይደለም ይላሉ። የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ለእነዚህ አይነት በጎ አድራጊዎች እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ የሚጠቁሙት ቀሲስ አበባየሁ፤ በጎነት ስጦታቸው የሆኑ ሰዎችን በባለሀብት በመደገፍ ማበርታት ያስፈልጋል። በባህሪ ልበ ሩህሩህ የሆኑ ሰዎች ምንም ባያደርጉ እንኳን ስለነእርሱ አልቅሰው ያስተምራሉና እነርሱን መጠቀም ይገባል ።
ቀሲስ አበባየሁ እንደሚሉት፤ እርሳቸው ከቤታቸው መውጣት አይፈልጉም። ምክንያቱም የችግሮኞችን የውስጥ ጉዳት የሚያዩበት ዓይን ለየት ስለሚል ልክ እንደነእርሱ ህመማቸው ይበረታልና ነው። ገንዘብ ቢኖርም የሚፈስበት፤ የሚያሳይ ሰው አለመኖሩ ለእኔ ብቻን አስፍቶታል። የእርሳቸው አይነት ሰዎች ግን ይህንን እየቀየረ ነው የሚል እምነት አለኝና እነርሱን እያሳየን ሰዎችን ከችግራቸው እናላቅቅ ይላሉ።
አንዳንዱ ወገኑ በረሃብ አለንጋ እየተጠበሰ ለዕርዳታ የመጣውን ሸጦ ይበላል። አንዳንዱ ደግሞ የራሱን ምቾት ትቶ ለሰው ይኖራል። ምቾቱን ትቶ ለሰው የሚኖር ከሚባሉት ውስጥ ደግሞ ወይዘሮ ዘውዲቱ አንዷ ናቸው። እናም ሰዎች መውሰድ ያለባቸው ከእርሳቸው ለሰው መኖርን እንደሆነ ያስረዳሉ። ለሌሎች አርኣያ የሚሆኑበት ተሽከርካሪ ስለሌላቸው ይህንን የሚያደርግ አካል ቢኖር የተሻለ ለችግረኛ መድረስ ይችላሉና በጎ አድራጊዎች እንዲደርሱላቸው ጥሪያቸውንም ያቀርባሉ።
መልዕክተ ዘውዲቱ
የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ የሆኑት ወይዘሮ ዘውዲቱ፤ ከተለያዩ አካላት በጎነታቸውን ተመርኩዞ የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል። ይህ ደግሞ ይበልጥ በመረዳዳት ድህነትን ከአገር እናጥፋ የሚለውን ሀሳባቸውን አጠንክሮላቸዋል። ወይዘሮ ዘውዲቱ በመንገድ ላይ የወደቁትን ማንሳት የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው። ምክንያቱም አንድ ቀን የሚዛመድበትን መንገድ እንፈጥርበታለን። እስካሁን በእኔ ቤት አድገው ለወግ ማዕረግ የበቁት ሁሉ ለእኔ ሥራ ደጋፊ ናቸው፤ ለተቸገረም ይደርሳሉ። ምክንያቱም ችግርንና ድጋፍን በሚገባ አይተውታል፤ ተምረውበታልም።
በእርግጥ ይላሉ ባለታሪኳ በእርግጥ ማጥገብና እንደሀብታም ልጆች ተሞላቀው እንዲያድጉ አልተደረጉም። ነገር ግን መጠለያና ምግብ አላጡም። ትምህርታቸውንም በሚገባ ተምረዋል። እየተማሩም ናቸው። በአስተዳደጋቸውም በጎ ማድረግን ተምረዋል። እናም መቼም ከበጎ ሥራ አይርቁም። ስለዚህ ሰዎችም ይህንን ብቻ ቢያደርጉ ብዙዎችን ከችግር ማዳን ይችላሉ። በአገሪቱ ውስጥም ማንም ተመጽዋች አይኖርም። እንደውም በአቅም ማጣት ሳይሰራ የቀረው ሃይል ሁሉ ወደ ሥራ ይገባል ይላሉ።
«የእኔ ምክር ችግረኞች ሀብት ናቸውና ካላቸው ሀብት እንጠቀም። በአምሳላችን የተፈጠሩ ናቸውናም ልንከባከባቸው ግዴታ አለብን። በመንፈሳዊውም ሆነ በኢኮኖሚው ሀብታም ለመሆን ከፈለግንም ይህንን ማድረግ ይገባናል። ጠላቴ ነው፤ ብሔሬ አይደለም፤ በሃይማኖት አንመሳሰልም የሚሉ ጉዳዮች በጎ ከማድረግ ያርቃሉና እነርሱን አርቀን በጎነትን ብቻ ገንዘብ አድርገን ወደ ፊት እንገስግስ ነው» ሲሉ ይመክራሉ።
ሰው መሆንን ብቻ ማስቀደም ደስታን ይሰጣል የሚሉት ወይዘሮ ዘውዲቱ፤ ሰዎች ሰው በመሆናቸው መታገዝ እንዳለባቸው ማመን ይገባል። ይህንን ያስተማሩኝ ደግሞ ቤተሰቦቼ ናቸው። በተጨማሪም በጎ አድራጊዎች የውስጥ ደስታን ይሰጡኛል። በተለይ እንደ እነቢኒያም (የመቅዶንያ መስራች) አይነት ልጆች በአገር ውስጥ በርከት ብለው ባይና ብሞት ሞትኩ አልልምም ብለውናል። ሰው እንዳይጠፋ፤ እንዳይወድቅ መከታ መሆን ይቻላልና ይህንን እናድርግ የመጨረሻ መልዕክታቸው ነው። እኛም በጎነት ዕድሜን ያረዝማልና ከእርሳቸው ተምረን ለችግረኞች ደራሽ እንሆን በማለት ሀሳባችንን ቋጨን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው