‹‹ፌስቱላ በኢትዮጵያ አስኪጠፋ መሥራት ይገባል›› – ዶክተር አምባዬ ወልደሚካኤል

የዛሬ እንግዳችን በእናቶችና ሴቶች ህክምና ላይ ጉልህ ዐሻራ ያሳረፉ ሰው ናቸው። በተለይ በሀገራችን በስፋት ትኩረት ተነፍጎት የቆየውን የፌስቱላ ህመም በቀዶ ሕክምና መፍትሄ በመስጠት ይታወቃሉ። የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት እና የዩሮ ጋይናኮሎጂስት ሰብ ስፔሻሊስት ናቸው። በአዲስ አበባ ፌስቱላ ህክምና ማእከል ከዶክተር ሀምሊን ካትሪን ጋር ሠርተዋል። በቆይታቸው ሜዲካል ዳይሬክተር መሆንን ጨምሮ በጥቅሉ ከ12 ዓመታት በላይ አገልግለዋል። እናቶችና ሴቶች በድህነት፣ በቅርበት ህክምና የሚሰጡ ተቋማት ባለማግኘት በፌስቱላ ከመሰቃየት እንዲድኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አምስት የሚደርሱ የፌስቱላ ማዕከላት እንዲቋቋሙ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ከኢትዮጵያ ተሻግረው የፌስቱላ ችግር በስፋት በሚታይባቸው የአፍሪካ ሀገራት በመዘዋወርም በቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስትነት አገልግለዋል። የፅንስና የማህፀን ህክምና ባለሙያዎችን በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ሀገራት እየተዘዋወሩ አሰልጥነዋል። በእናቶች ጤናና በፌስቱላ ህክምና ላይ ከሚሠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ረዘም ላሉ ዓመታት ሠርተዋል። እንግዳችን የህክምና ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ በእንግሊዝ ሀገር ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሊድስ ኢንተርናሽናል ስኩል ኦፍ ፐብሊክ ሄልዝ የተከታተሉ ሲሆን፤ በተለያዩ ሀገራት ልዩ ልዩ ስልጠናዎችም ወስደዋል።

እኚህ ሰው በፌስቱላ ህክምና እውቅና ያላቸው ዶክተር አምባዬ ወልደ ሚካኤል ናቸው። የዛሬው የሕይወት ገፅታ አምድ የእርሳቸውን ታሪክ ሰዎች መቃኘት ቢችሉ በብዙ ይማራሉ ብሎ በማሰቡ በ38 ዓመታት በህክምናው ሙያ ላይ የነበራቸውን አበርክቶ በሚከተለው መልክ ያቀርብላችኋል።

ትውልድ እና አድገት

አንጋፋዋ የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት እና የዩሮ ጋይናኮሎጂስት ሰብ ስፔሻሊስት ዶክተር አምባዬ ተወልደው ያደጉት በአዲሰ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ሾላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። በልጅነታቸው ቁጥብና ለትምህርት ልዩ ስፍራን የሚሰጡ እንደነበሩ ከአስተዳደጋቸው በቀላሉ መገመት ይቻላል። ለትምህርት ልዩ ስፍራን ከሚሰጡ ወላጆች ነው የተገኙት። እርሳቸውም በአንደበታቸው እንደሚሉት ‹‹የተማርኩት የካ ሴንተር የሚባል ትምህርት ቤት ነው። በትምህርት ላይ ጥሩ ዝንባሌ ነበረኝ›› በማለት ከቤት ወደ ትምህርት ቤት ከትምህርት ቤት ወደቤት ከማለት ውጪ በተለየ መልኩ ሌሎች ዝንባሌዎች እንዳልነበሯቸው ይናገራሉ።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በኡራኤል መለስተኛ ትምህርት፤ 11ኛ እና 12ኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በምስራቅ አጠቃላይ ጨርሰዋል። የቀለም ትምህርት መስመርን በልዩ ትኩረትና ዝንባሌ ይዘው የተጓዙት እንግዳችን፤ የመሰናዶ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማምራት ህክምናን ለማጥናት በቀጥታ ጥቁር አንበሳ ነበር የተመደቡት።

‹‹ልጆች ሆነን እኔ መምህር የመሆን ልዩ ፍላጎት ነበረኝ። ለአባቴ ሁሌም አስተማሪ እንደምሆን ነበር የምነግረው›› የሚሉት ዶክተር አምባዬ፤ በትምህርት ቤት ከጓደኞቻቸው ጋር ሲሆኑ እርስ በእርስ ማስተማርና መረዳዳት የሚለው እሳቤ ይማርካቸው እንደነበር ይገልፃሉ። ሁሌም በህሊናቸው የሚቀርፁት የመምህር ጋወን ለብሰው፣ ቾክ ይዘው በጥቁር ሰሌዳ ላይ ማስተማር ነበር። በዚህ ፍላጎትና እሳቤ ውስጥ ሆነው ነበር ለዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ጥሩ ውጤት ማምጣት የቻሉት።

ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

ጊዜው 1972 ዓ.ም ነበር። ዶክተር አምባዬ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ አመርቂ ነጥብ አስመዝግበው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመደቡ። በወቅቱ ተማሪዎች በእድል ነበር ምርጫቸውን የሚያገኙት። ተማሪዎቹ ፍላጎታቸውን ፎርም ላይ ቢያስቀምጡም ምደባው ግን በእነሱ ፍላጎት አልነበረም። እርሳቸው በጊዜው ‹‹የትኛው የትምህርት ክፍል ብገባ ስኬታማ እሆናለሁ›› የሚል ጥያቄ ቢያጭርባቸውም ውሳኔው ግን በእጃቸው አልነበረም። ሆኖም በወንድሞቻቸውና በቤተሰብ የቅርብ ሰው ምክር አንደኛ ምርጫቸውን ሜዲካል ለማድረግ ወሰኑ። ውጤታቸው ጥሩ መሆኑ ለቀጣይ የሕይወት መንገዳቸው የተሻለ እንደሚሆን ምክር አገኙ። በውሳኔያቸው ፀንተው ወደ ሜዲካል ትምህርት ክፍል በመግባት በዩኒቨርሲቲው ለአንድ ዓመት ከተማሩ በኋላ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተመድበው በዚያ ትምህርታቸውን ቀጠሉ።

‹‹መምህር የመሆን ፍላጎት ቢኖረኝም ሜዲካል ትምህርት ቤቱን ወደድኩት›› የሚሉት እንግዳችን ምክንያታቸው የነበረው በህብረት የማጥናቱ፣ መፅሀፍትን በትኩረት ለማንበብ ምቹ ሁኔታ ማግኘታቸው፣ በራሱ የህክምና ትምህርት ልዩ ዝንባሌ እንዲያዳብሩ አዲስ አቅጣጫ የሚያመላክት ትምህርቶች መማራቸው ነበር። በቆይታቸው ጠንካራ ሠራተኛ የመሆን የሕይወት ልምድ ከሜዲካል ትምህርት ክፍሉ ማግኘታቸውን ይናገራሉ።

ዶክተር አምባዬ በትዝታ መለስ ብለው የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን ሲቃኙ ለመምህራኖቻቸው ይሰጡት የነበረውን ክብርና ልዩ ቦታ ያስታውሳሉ። መምህራኖቻቸው የትምህርት፣ የህክምና፣ የጠንካራ ሠራተኝነት እና ሙያን የማክበር ሥነ ምግባርን እንዳስተማሯቸው ይናገራሉ። በጊዜው የህክምና ተማሪዎች ጥቂት ነበሩ፤ እርሳቸውን ጨምሮ ሴት ተማሪዎች ደግሞ ጥቂት በመሆናቸው የበለጠ መቀራረብና ፍቅር እንደነበር ያስታውሳሉ። የተግባር ልምምድን ልክ እንደ ከፍተኛ ዶክተር ልዩ ትኩረትና ጥንቃቄ ወስደው ሠርተዋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ አልፈው በ1978 ዓ.ም የህክምና ትምህርታቸውን አጠናቀቁ። በጠቅላላ ሀኪምነት ወደ ጋምቤላ ተመደቡ።

ጋምቤላ- የሙያ ፈር ቀዳጅ

የትምህርት ስንቃቸውን ቋጥረው እንደጨረሱ ያስተማራቸውን ማህበረሰብ በሙያቸው ለማገልገል ወስነው ነበር። በጊዜው እርሳቸው በጠቅላላ ሀኪምነት እንዲሠሩ የተመደቡት በጋምቤላ መቱ ሆስፒታል ሆነ። ከልጅነት እስከ እውቀት ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት የተማሩበት የትውልድ ቦታቸውን መልቀቅ ደግሞ የግድ ነበር።

‹‹ጋምቤላ በጣም ሞቃታማ መሆኑን አስታውሳለሁ፤ በመቱ ሆስፒታልም በርካታ ሀኪሞች አብረውኝ ይሠሩ ነበር›› የሚሉት እንግዳችን፤ ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ በቆዩበት ጊዜያት እጅግ ብዙ ታማሚዎችን ለማከም ጥረት ያደርጉ እንደነበር ያስታውሳሉ። በተለይ በወቅቱ በነበረው የሰፈራ ፕሮግራም የሚመጡ ዜጎች በወባ፣ በምግብ እጥረት እና በተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ይታመሙ ነበር። እነዚህን ዜጎች የማከም ኃላፊነት የእርሳቸውና የባልደረቦቻቸው ነበር። ሁኔታውን መለስ ብለው ሲያዩት ‹‹በጊዜው ማህበረሰቡ ከእግዚአብሄር በታች ሙሉ ሕይወቱን ለእኛ አምኖ ይሰጠን ነበር። እኛም ይህ ኃላፊነት ትልቅ የሞራልና የሥነ ምግባር መነሻ ሆኖናል›› ይላሉ።

በጋምቤላ አንድ ዓመት ከመንፈቅ በጠቅላላ ሀኪምነት ቆይተዋል። በጊዜው ልምድ ካላቸውም አብረው ከተመደቡትም ዶክተሮች ጋር በህብረት ተረዳድቶ ታካሚዎች አፎይታ እንዲያገኙ ያደርጋሉ። ከባልደረቦቻቸው ውስጥ ዶክተር መሰረት እሸቱ ይጠቀሳሉ። በሆስፒታሉ እርሳቸውና በስም የጠቀስናት ባልደረባቸው ብቻ ነበሩ ሴቶች። እነዚህ የሥራ ወራት ማህበረሰቡን ከመርዳት ባሻገር ልዩ ማህበራዊ መስተጋብር እና የሕይወት ልምድን ያገኙበት ሆነ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ነበር ለተጨማሪ ትምህርት ዳግም ወደ ትውልድ ቦታቸው አዲስ አበባ የመጡት።

ተጨማሪ ትምህርት

ዶክተር አምባዬ ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ የነበራቸው የጋምቤላ የሥራ ቆይታ በትምህርት ምክንያት ሊያበቃ የግድ ሆነ። በዚያ ያገኙት ልምድ ለዛሬው የሥራ ስኬታቸው ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ግን ያስታውሳሉ። በተለይ በቆይታቸው በእናቶች እና ሴቶች ጤና አንክብካቤ ላይ የነበረው ክፍተት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዚያ ዙሪያ ለማጥናት ግፊት አድርጎባቸዋል። በተለይ እርሳቸው በነበሩበት ወቅት ሴቶች በወሊድ ወቅት ያጋጥማቸው የነበረው ጫና ያሳስባቸው ነበር።

እናቶች ልጆቻቸውን ሲወልዱ ከሰዎች ተገልለው ብቻቸውን ሆነው ነበር። በጊዜው በነበረው ባህል ከማህበረሰቡ ሆነ ከህክምና ተቋማት ምንም ርዳታ አያገኙም። በጊዜው የተወሰነ መሻሻል የታይ የነበረ ቢሆንም የቀዬው ባህል ግን ሙሉ ለሙሉ ለወሊድና የጤና እንክብካቤ ትኩረት የሚያደርግ አልነበረም። ይሄ አጋጣሚ ታዲያ ዶክተር አምባዬ በፅንስና ማህፀን ህክምና ዘርፍ ስፔሻላይዜሽናቸውን እንዲሠሩ ገፋፋቸው።

እንግዳችን ለአራት ዓመታት በፅንስና ማህፀን ህከምና ስፔሻላይዝድ አድርገው አንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1993 ተመረቁ። በትምህርት ወቅት የነበራቸው ልምድና አጋጣሚ ደግሞ ረጅሙን የሕይወታቸውን እና የሙያ ጊዜያቸውን ካሳለፉበት የፌስቱላ ህክምና ጋር አስተዋወቃቸው።

ወደ ፌስቱላ ሆስፒታል

እንግዳችን በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በፅንስና ማህፀን ትምህርት ላይ በነበሩበት ወቅት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፌስቱላ ህክምና ማእከል ውስጥ ለሁለት ወር ሠርተው ነበር። በዚያ መሥራት የትምህርቱ አንድ የልምምድ አካል የነበረ ቢሆንም እርሳቸውን ግን ይበልጥ ከእናቶች ህክምና ጋር ይበልጥ ያቆራኛቸው አጋጣሚን ይዞ ነበር የመጣው።

ዶክተር አምባዬ ስፔሻላይዝድ ከማድረጋቸው በፊትም የፌስቱላ ህክምና እና የሚከሰትበትን አጋጣሚ ተማሪ እያሉ የማወቅ አጋጣሚው ነበራቸው። የሁለት ወራት የሆስፒታሉ ቆይታቸው ደግሞ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ልዩ ቦታ ካላቸው ከዶክተር ሬጅ እና ካትሪን ሃምሊን ጋር አስተዋወቃቸው። በዚያ የፌስቱላ ህክምና እና የእናቶችና ሴቶች በህመሙ የሚደርስባቸውን ስቃይ፣ መገለል ብሎም የህክምና ሁኔታ ለመረዳት ቻሉ። ሁለቱ የኢትዮጵያውያን ባለውለታ ከህክምና ባሻገር መምህራኖችም ስለነበሩ ስለ ህመሙና ስለመፍትሄው ለመማር እድሉን አግኝተዋል።

እንግዳችን በጊዜው በማህበረሰቡ ውስጥ አንድ የፌስቱላ ታማሚ የሆነች ሴት አሊያም እናት እርግማን እንደደረሰባት ተደርጎ ይቆጠር እንደነበር አወቁ። በህመሙ ምክንያት የሚደርስባቸው መገለል እና የህክምና አገልግሎት አለማግኘት አሳሰባቸው። በተለይ ከሩቅ ቦታዎች ህክምና ለማግኘት የሚደርስባቸው እንግልት በእርሳቸው ልብ ውስጥ ትልቅ መራራትን ፈጠረ። በጊዜው የካትሪን ሀምሊን ባለቤት ለተማሪዎች ገለፃ ሲሰጡ የፌስቱላ ታማሚዎችን ስቃይ እና መከራ ቁልጭ አድርገው ነበር የሚያሳዩት ይህ አጋጣሚ ዶክተር አምባዬ ትምህርቱን እያለቀሱ እና እያዘኑ እስከመከታተል አድርሷቸው ነበር።

በዚህ ምክንያት የሁለቱ የሀገር ባለውለታዎች ጥረት ለእርሳቸው ትልቅ መነሳሳትን ፈጠረ። የወጡበትን ማህበረሰብ በዚህ ሙያ ለማገልገል እንዲወስኑ መሠረት ሆናቸው። ለሁለት ወራት የህክምና ሂደቱን እና የዳኑትን የፌስቱላ ታማሚዎች ሂደት ሲከታተሉ ቆዩ። የእናቶችተስፋና ክብር ሲመለስ፣ ድነው ወደመጡበት ሲመለሱ ማየትና መማር ለዶክተር አምባዬ ትልቅ ሀሴት የፈጠረ አጋጣሚ ነበር። ‹‹በሕይወቴ ማሳካት የምፈልገው ምንድነው›› የሚለውን ጠጣር ጥያቄ ለራሳቸው ጠይቀው መልሱንም አግኝተው የፌስቱላ ታማሚዎች የማከም ጎዞን ተቀላቀሉ።

‹‹በሁለት ወራት ቆይታችን እነ ዶክተር ሀምሊን ይከታተሉን ነበር›› የሚሉት ዶክተር አምባዬ፤ በማእከሉ አብረዋቸው እንዲሠሩ ከሚፈልጓቸው ዶክተሮች ውስጥ እርሳቸውን ምርጫ አደረጉ። በጊዜው በዶክተር ሀምሊን ጥያቄ መሠረት ሆስፒታሉን ለመቀላቀል በቁ። እርሳቸውም ቀድሞውኑ የህሙማኑን ተስፋና ሕይወት ዳግም የሚመልስ የሞራል ልእልናን የሚያጎናፅፍ አገልግሎትን የመሰለ ነገር አለመኖሩ ገብቷቸው ነበር።

በአዲስ አበበ ፌስቱላ ሆስፒታል ሥራ ሲጀምሩ በአጋጣሚ የዶክተር ሃምሊን ካትሪን ባለቤት በመታመማቸው ምክንያት ሁለቱም ከኢትዮጵያ ውጪ ነበሩ። ዶክተር አምባዬም ሁለቱም ህክምናውን ጨርሰው እስኪመለሱ 50 የሚሆኑ በአብስትሪክት ፌስቱላ የተጠቁ ታማሚዎችን ቀዶ ህክምና በመሥራት ነበር የጠበቋቸው። ሁለቱም በእርሳቸው ጥረትና የሥራ ውጤት ተማርከው ነበር። በተለይ የዶክተር ካትሪን ባለቤት በሥራቸው ከጎናቸው በመሆን ማበረታቻዎችን ያደርጉላቸው ነበር። ይህ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ቀጥሎ ቀዶ ህክምና መሥራት ሲያቆሙ የራሳቸውን የሰርጀሪ መመርመሪያ ቁሳቁሶች በስጦታ መልክ ለሚያደንቋቸው ዶክተር አምባዬ ነበር በሽልማት መልክ የሰጡት። ይህ ስጦታ የበለጠ ሞራልና ፍላጎት እንዲያድርባቸው ሆነ።

እንግዳችን በአዲስ አበባ የአብስትሪክ ፌስቱላ ህክምና ሆስፒታል ውስጥ 12 ዓመታትን ሠርተዋል። ጥረታቸው እና ለታማሚዎች ፈውስ መገኘት የሚያደርጉት ትጋት በእጅጉ የሚያስደንቅ ነበር። ከእነ ዶክተር ካትሪን እና ከትምህርት ገበታቸው የቀሰሙትን ትምህርት መሬት በማውረድ እና በራሳቸው ከጊዜ ሂደት ያዳበሩትን ልዩ ክህሎት በማቀናጀት ውጤታማ ሥራ ሠርተዋል። በሆስፒታሉ ለአራት ዓመት በምክትል ሜዲካል ዳይሬክተርነት ለተጨማሪ አራት ዓመት ደግሞ በዋና ሜዲካል ዳይሬክተርነት በመሥራት ልዩ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ዶክተር አምባዬ የፌስቱላ ሆስፒታል የሕይወት መስመራቸውን እና መክሊታቸውን ያገኙበት እንደሆነ ያምናሉ። ከምንም በላይ እጅግ ዘግናኝ የሆኑ ጉዳቶችን የሚያስተናግዱ ሴቶችና እናቶችን ከስቃይ ማዳን የህሊና እርካታ አጎናጽፏቸዋል። ከአዲስ አበባ ውጪ ከርቀት ወደ ከተማው ብዙ ስቃይና እንግልት ውስጥ ገብተው የሚደርሱ ታካሚዎችም ነበሩ። ይህ እንግልት ለዶክተር አምባዬ በቀላሉ ሊታለፍ የሚችል አልነበረም። ሥራውን በጀመሩ ሰሞን ታዲያ ታማሚዎች ባሉበት አካባቢ ሆነው እንዲታከሙ ለማስቻል ፕሮጀክት በመንደፍ ተግባራዊ አድርገዋል። አምስት ቦታዎች ላይ የህክምና ማዕከላት እንዲቋቋሙ ምክንያት ሆነዋልም።

‹‹ሁሉም ታካሚዎች ለምን አዲስ አበባ ድረስ ይመጣሉ፤ የጽንስና ማህፀን ሀኪሞች ቀዶ ጥገናውን ባሉበት ለምን አይሠሩም›› የሚል ጥያቄ በማንሳትና ታማሚዎቹ ባሉበት አካባቢ በመሄድ ህክምናው መሰጠት አለበት ብለው በማመናቸው ለማዕከሎቹ መቋቋም እንደ ምክንያት ሆነዋልም። ብዛት ያላቸው ታማሚዎች ያሉበትን አካባቢ በመምረጥምና ወደዚያው በማቅናትም ቀዶ ሕክምናውንና ህክምናውን መስጠት ጀመሩ።

የመጀመሪያው ከአዲስ አበባ ውጪ የተቋቋመው የፌስቱላ ህክምና ማዕከል በባህርዳር ሲሆን፤ የህክምና መስጫ ማዕከሉን የቫልኔሮ ኮንስትራክሽን በድጋፍ ሠራላቸው። በባህርዳር እና በአካባቢው ያሉ ታማሚዎችም አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት ሳይጉላሉ ህክምና ለማድረግ ቻሉ። ሁለተኛው ደግሞ በኖርዊጂያን ድርጅት ድጋፍ በይርጋለም ተቋቋመ። በእነዚህ ከፍተኛ ስርጭት ባለባቸው አካባቢዎች ዶክተር አምባዬ ከዚህ ቀደም በራሳቸው ተነሳሽነት እየተዘዋወሩ ይሠሩ ነበር።

የማዕከላቱ መቋቋም ደግሞ ሥራውን ይበልጥ አቀለለው። ሶስተኛው ማዕከል የተከፈተው በመቀሌ ነው:: አራተኛው መቱ ሆስፒታል ላይ የተቋቋመው ሲሆን፤ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፌስቱላ ታካሚ በመኖሩ ምክንያት የተከፈተ ነው። አምስተኛው ማዕከል የነበረው በሐረር የተቋቋመው ነው።

ዶክተር አምባዬ ሶስቱ ማዕከላት ተቋቁመው አራተኛው በግንባታ ላይ እንዳለ ከሆስፒታሉ ለሌላ ኃላፊነት በግል ፍቃዳቸው ለቀቁ። በሆስፒታሉ በቁዩባቸው 12 ዓመታት ግን አያሌ አስተዋጽኦዎች ለሀገራቸው አበርክተዋል።

የዶክተር አምባዬ አስተዋጽኦ በኢትዮጵያ ብቻ የተገደበ አልነበረም። በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትም በመሄድ የአብስትሪክ ፌስቱላ ቀዶ ህክምና ይሰጡ ነበር:: የመጀመሪያው ከሀገር ውጪ የሄዱትና ህክምና የሰጡት ቦታ በታንዛኒያ ነው። በእዚያ 40 የሚሆኑ የፌስቱላ ታማሚዎችን ‹‹ሙሀንዛ›› በምትባል መንደር ውስጥ ሠርተዋል። ከዚያ በኋላ በኬንያ፣ ኡጋንዳ እንዲሁም በሌሎች በርካታ አፍሪካ ሀገራት በመዘዋወር ከሀገር የተሻገረ አበርክቶ አድርገዋል። በተለይ ስልጠናዎች እና ተሞክሮዎችን ማጋራት ላይ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው።

ዳግም እናቶችን ማገልገል

እንግዳችን የፌስቱላ ሆስፒታልን ይልቀቁ እንጂ ከእናቶችና ሴቶች የጤና ጉዳይ ግን መራቅ አልቻሉም። የመጀመሪያው ርምጃቸው የነበረው በአፍጋኒስታን ስለ ፌስቱላ ለማስተማር ጉዞ ማድረግ ነበር። ከዚያ እንደተመለሱ አዲስ የተቀላቀሉት ግብረ ሰናይ ድርጅት ‹‹ዋሃ›› (Women and Heath Alliance) የተባለ ድርጀት ውስጥ ነበር። እርሳቸው እና አንድ ሌላ ባልደረባቸው በመሆን በአዲስ አበባ በተመሳሳይ ፌስቱላ ላይ የሚሠሩ ማእከላትን አቋቋሙ።

ይሄኛው ፕሮግራም ከመጀመሪያው ሥራቸው የሚለየው ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑ ነበር። በልዩ ሁኔታ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ለማቀናጀት የፈለጉት የህክምና ተማሪዎች በቅርበት ስለ ችግሩ እንዲረዱ እና ሙያዊ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለማስቻል ነበር። በተለይ በፌስቱላ ላይ የሚሠሩ እንደ ዶክተር አምባዬ ያሉ ሀኪሞችን በብዛት ለማፍራት የታሰበበት ነበር። በመሆኑም በጅማ፣ በሃዋሳ እና በአሰላ ማእከላቱን በመክፈት ባልደረባቸው ዶክተር ሙሉ የድርጅቱ ካንትሪ ዳይሬክተር በመሆን ሥራውን ጀመሩ። ዋና ትኩረታቸውን ማስተማር ላይ በማድረግ እንደዚሁም ልዩ ልዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ ህክምናውን በመስጠት ለስምንት ዓመት ሲሠሩ ቆዩ።

የዋሀ ፕሮጀክት አንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 ሲያበቃ ዶክተር አምባዬ ግን የፌስቱላ ህክምና አገልግሎት መስጠትን አላቆሙም ነበር። በግላቸው በአሰላ ባህርዳር እና በልዩ ልዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ ታማሚዎችን ያክማሉ። በተጨማሪ ከፍተኛ የሠራተኛ ፍሰት ስለነበር ሀኪሞችን በማስተማር እና በማሰልጠን ላይ ትኩረታቸውን በማድረግ የፌስቱላ ህክምና ትኩረት እንዲያገኝ ታግለዋል። በመጨረሻም ይህንን ጥረታቸውን ተቋማዊ አድርጎ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ስላመኑበት የራሳቸውን ድርጅት ወደ መመስረት መጡ። በዚህ ጊዜ ነበር የፌስቱላ ታማሚዎችን በህክምና እና በኢኮኖሚ አቅማቸው ራሳቸውን እንዲችሉ የሚረዳውን የ‹‹ሆፕ አፍ ላይት›› ድርጅት ወደመመስረት የመጡት።

ሆፕ ኦፍ ላይት- አዲስ ተስፋ

እንግዳችን ለዓመታት በተለያዩ ተቋማት እና በግል ጥረትም ሲሠሩ የነበረውን ህክምና ለማስቀጠል በግላቸው ‹‹ሆፕ ኦፍ ላይት›› የሚል የግብረ ሰናይ ድርጅት መሠረቱ። ድርጅቱ ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማትን በማፈላለግ የፌስቱላ ታማሚዎች ህክምና እንዲያገኙ ከዚያም ሲሻገር የኢኮኖሚ ነፃነት እንዲኖራቸው አነስተኛ ንግድ እንዲመሠርቱ መሥራት ጀመሩ።

ይህ ደርጅት አሁን ከጅማ፣ አሰላ፣ ሀዋሳና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር ዳግም ግንኙነቱን በመቀጠል በፌስቱላ ዙሪያ ትምህርት እና ህክምናን ይሰጣል። ላለፉት አምስት ዓመታት በዚህ ሥራ ውስጥ ይገኛሉ። እንግዳችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው ግጭት ሥራቸው ላይ አክል እንደሆነ ቢናገሩም በተቻለ መጠን ግን የፌስቱላ ታማሚዎችን አግኝቶ ለመደገፍ ጥረት ላይ ናቸው። አዲስ ስምምነት በማድረግ ፕሮጀክቶችን ለመቀጠል እየሠሩም ይገኛሉ።

በአሁኑ ወቅት ‹‹ሆፕ ኦፍ ላይት›› ድርጅት በተለይም የእናቶች ጤና ላይ በተለይም በማህፀን ፌስቱላ እና በሌሎች መሰል እክሎች ጋር በተያያዘ የቀዶ ህክምናና ሌሎች የሕክምና አገልግሎቶችን ይሰጣል። በተጨማሪም የፌስቱላ ክብካቤና የቀዶ ሕክምና ጥራት ጋር በተያያዘ ብቁ ለሆኑ የጤና ባለሙያዎች እና የቅድመ ዝግጅት ስልጠና ይሰጣል።

ዶክተር አምባዬ ‹‹የፌስቱላ መሠረቱ ድህነት ነው›› ብለው ያምናሉ። በመሆኑም ዜጎች የተሻለ የጤና እንክብካቤና ክትትል እንዲያደርጉ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማሳደግ አለበት ብለውም በሆፕ ኦ ላይት ይህንን ግብ ለማሳካት እየሠሩ ይገኛሉ። የዓመታት ልምዳቸው እንደሚያሳያቸው ሁሉም ታማሚዎች እጅግ ዝቅተኛ ከሆነ የኑሮ ደረጃ የመጡ ናቸው። ይህንን እውነታ ለመቀየር ታካሚዎቹ ሲድኑ የተለያዩ (የንጽህና መጠበቂያ ሳሙና ማምረትን ጨምሮ) አነስተኛ ንግድ እንዲጀምሩ መቋቋሚያ ድጋፍ እያደረጉላቸው ነው።

የዶክተር አምባዬ- ነገ

ዶክተር አምባዬ ስለ ፌስቱላ ዛሬም ማስተማር በእጅጉ ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ። እርሳቸውም በአጭር ጊዜ ያስቀመጡት ግብ በድርጅቱም ይሁን በግላቸው የፌስቱላ በሽታ ቅድመ ግንዛቤ መስጠትና ማስተማር ይሻሉ። በተለይ ማህበረሰቡ ታማሚዎችን የሚገነዘብበትን መረዳት መቀየር እንደሚያስፈልግ ያምናሉ።

‹‹የፌስቱላ ህክምናውን እያገኙ ያሉ እድለኞች ናቸው ብዬ አምናለሁ›› የሚሉት እንግዳችን፤ ይህንን እድል ያላገኙ በየቤቱ በኢንፌክሽን እና በሽታው በሚያመጣው ተያያዥ ችግሮች ውስጥ ያሉ በርካታ ዜጎች በየሜዳው እንዳሉ ይገልፃሉ። ህክምናን ሳያገኙ በወሊድ እና በበሽታው ምክንያት ሕይወታቸው ያለፉ ዜጎቸ እንደሚያስቆጯቸውም ይናገራሉ። በመሆኑም ማህበረሰቡም ይሁን የህክምናው ባለሙያ ይህንን አስከፊ ችግር መረዳት እንዲችል ሥራዎችን እንደሚሠሩ ይናገራሉ።

‹‹ፌስቱላ በኢትዮጵያ እስኪጠፋ መሥራት ይገባል›› የሚሉት የዛሬው የሕይወት ገፅታ እንግዳችን፤ ይህንን ለማድረግ በቅድሚያ የማህበረሰብና የሀገር ልማት ላይ መሥራት ይገባል ይላሉ። የመጀመሪያው የፌስቱላ ታማሚ የተለየው በአሜሪካን ሀገር መሆኑን እንዲሁም ሆስፒታሉም የተሠራው በዚያው ሀገር እንደሆነ ጠቆም በማድረግ ‹‹ዛሬ ግን ህመሙ መኖሩ እስኪረሳ ድረስ ጠፍቷል›› ይላሉ። አሜሪካኖቹ ይህንን ማጥፋት የቻሉት በኢኮኖሚ እየበለፀጉ መምጣታቸው እና የህብረተሰብ ልማት ላይ በማተኮራቸው እንደሆነ ተናግረው፤ በተመሳሳይ በኢትዮጵያም ይህንን መንገድ መከተል ይገባል ይላሉ።

‹‹ማንም ሰው በኢኮኖሚ ሲበለፅግ ለጤናው ልዩ ትኩረት ይሰጣል፤ ክትትልም እንዲሁ በየጊዜው ያደርጋል›› የሚሉት እንግዳችን፤ ዜጎች ለጤናቸው የማያስቡ ሆኖ ሳይሆን የኢኮኖሚ አቅማቸው ስለሚገድባቸው ብቻ ፌስቱላን በመሰሉ ህመሞች አስከፊ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ይናገራሉ። ይህ እስኪሆን ድረስ ግን የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ ግንዛቤ መስጠት ይገባል ባይ ናቸው። ሁሉም ዜጎች እናቶችን መንከባከብ ወደ ህክምና ተቋም እንዲሄዱ መደገፍ ይገባል ይላሉ።

ቤተሰብ

ዶክተር አምባዬ ከባለቤታቸው ዶክተር መኩሪያ ላቀው ጋር 25 ዓመታትን የዘለቀ የትዳር ጥምረትን ፈጥረው እስካሁን ድረስ አብረው በፍቅር ይኖራሉ። ‹‹በዚህ ሁሉ የሙያ ጉዞዬ ላይ ባለቤቴ ከጎኔ በመሆን አግዞኛል›› በማለት ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀው የስኬታቸው ምክንያት የቤተሰብ፣ የጓደኛና የሥራ ባልደረባ ድጋፍ ጭምር ታክሎበት መሆኑን ሳይዘነጉ ይናገራሉ።

በህክምና ትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቁበት ጊዜ አንስተው ላለፉት 38 ዓመታት ማህበረሰባቸውን (በተለይ የፌስቱላ ታካሚዎችን) በማገልገል ዛሬ ላይ ደርሰዋል። የነገውም ህልማቸው ግዙፍ ነው። ፌስቱላን እስከነ አካቴው ማጥፋት ይሻሉ። ለዚህ ደግሞ አዲሱን ትውልድ ማስገንዘብ፣ በእውቀት ማስታጠቅና ኢኮኖሚ አቅሙን መገንባት ይገባል ይላሉ። የዝግጅት ክፍላችንም ዶክተር አምባዬን የመሰሉ ብሄራዊ ጀግኖች ብዙ ትምህርት አላቸውና እንጠቀምባቸው በማለት ራዕያቸውም እውን እንዲሆን በመመኘት መሰናዶውን እዚህ ላይ ቋጨን። ሰላም!!

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You