ባሳለፍነው ሳምንት በአገራችን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ያተኮረ ዶክመንተሪ ፊልም ተዘጋጅቶ በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለስርጭት መብቃቱ ይታወሳል፡፡ ዶክመንተሪው ፊልም በተላለፈ ማግስትም የበርካታ ዜጎች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ በርግጥ በዶክመንተሪ ፊልሙ የታየው ልብን የሚነካና ዘግናኝ በመሆኑ ብዙዎች በዚህ መልኩ ቢነጋገሩበት አይገርምም፡፡ መነጋገሪያ ካደረጉት ጉዳዮችም ውስጥ ዋነኛው “የሰው ልጅ ይህንን ያህል ጭካኔ በሰው ልጅ ላይ ለምን ሊፈጽም ቻለ?” የሚለው ጥያቄ ልዩ ትኩረት ሊሰጠውና ያለንበትን ዘመንም እንድንመረምረው የሚያስገድደን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ እኔም ለዛሬ በዚህ ዙሪያ የራሴን ትዝብት ላቀርብ የተነሳሳሁት ልክ እንደ አብዛኛው የአገራችን ህዝብ በዶክመንተሪው ላይ የተመለከትኩት ግፍና መከራ ልቤን ስለነካው ነው፡፡
በምንገኝበት 21ኛው ክፍለዘመን የሰው ልጅ ከፍተኛ የስልጣኔ ማማ የረገጠበት እንደሆነ በርካታ ማሳያዎችን በማንሳት መግለፅ ይቻላል፡፡ በተለይ በስልጣኔያቸውና በእድገታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱት የአሜሪካ፣ አውሮፓና የኤሲያ አህጉራት ለሰው ልጅ የተሻለ ዓለም ለመፍጠር የሚያስችላቸውን የቴክኖሎጂ ፉክክር ተያይዘውታል፡፡ የበለፀጉት አገራት ከምንኖርባት ምድር ሌላ በርካታ ለሰው ልጅ መኖሪያነት ሊሆኑ የሚችሉ ፕላኔቶች መኖራቸውን ወደ ማረጋገጥና ይህንንም በተግባር ወደ መሞከር የተሸጋገሩበት ሁኔታ እንዳለም እንሰማለን፡፡
ከዚህ ዝቅ ስንል ደግሞ ዓለም እርስ በርሱ የሚያደርገው ጦርነትና ግጭት እንደተጠበቀ ሆኖ አንዱ ለሌላው የሚያደርገው ድጋፍም በበጎ ጎኑ የሚነሳ ተግባር ነው፡፡ የአንድ አገር ህዝቦች የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥማቸውም ሆነ በተለያዩ ሰው ሰራሽ ችግሮች ለከፋ ጉዳት ሲዳረጉ ቀድሞ የሚደርሰው መንግሥታቸው አልያም የሌሎች አገራት መንግሥታት ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት የመረዳዳት ባህሉ ምንም እንኳ ገና ብዙ ቢቀረውም ብዙ ድልድዮችን የተሻገረ ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ ተግባራት የሚከወኑት ደግሞ የሰው ልጅ ክቡር በመሆኑ እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ የሰው ልጅን ከእንስሳት ከሚለዩ መገለጫዎችም ውስጥ አንዱና ዋነኛው ሰው የሚያስብና በምክንያት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሰው ልጅ ተገቢውን ክብር እንድንሰጥ ያስገድደናል፡፡
በርግጥ በዓለም ላይ ይህ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህርይ ተለውጦ ሰዎች ልክ እንደ አውሬ በሰው ልጅ ላይ አረመኔያዊ ግፍ ሲፈጽሙ ተመልክተናል፡፡ በዓለም ላይ ሃያል ናት በምንላት አሜሪካ እንኳ በጓንታናሞ እስር ቤት ውስጥ በርካታ ግፎች ሲፈጽሙ ኖረዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካዋ የሮቢን ደሴት ለዘመናት ሲፈፀሙ የነበሩ ግፎችን ተመልክተናል፡፡ በአፍሪካ በበርካታ አገራት ሰው የሰው ልጅን ለቁም ስቃይ ሲዳርግ በቴሌቪዥን መስኮት አይተን እንባችንን አፍሰናል፡፡ በዓረብ አገራት በርስ በርስ ጦርነት ሰበብ ሰዎች ሰብዓዊ መብታቸው ሲገፈፍና በቁማቸው ለስቃይ ሲዳረጉ፣ ከዚያም አልፎ በጅምላ ሲጨፈጨፉም አይተን አንብተናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ድርጊቶች በሰው ልጅ የተፈፀሙ አረመኔያዊ ድርጊቶች ናቸው፡፡
ያም ሆኖ ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ለራሳችን ከምንሰጠው ክብርና ከፈጣሪ ጋር ካለን ቁርኝት አንጻር እንዲህ አይነት ኢሰብዓዊና ከሰውልጅ የማይጠበቅ ተግባር መስማታችን ፈፅሞ የማይጠበቅና እንግዳ ነገር ነው፤ ወዴትስ እያመራን ነው የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያን ለሌሎች የበለፀጉ የምንላቸው አገራት ጭምር በጨዋ ስነምግባራችን እና በጠንካራ ባህላችን የምንታወቅ ህዝቦች ነን፡፡ በዓለም ላይ የዴሞክራሲ ስርዓት ሳይታወቅ በገዳ ስርዓት ዴሞክራሲን ለሰው ልጅ ያስተዋወቅን ህዝቦች ነን፤ በዳጉ ባህላችን ዜጎች በሃቅ ላይ የተመሰረተ የመረጃ ልውውጥ እንዲያደርጉ ለሌሎች ያስተማርን ህዝቦች ነን፤ በአገር ሽማግሌዎች አማካይነት ትላልቅ የሚባሉ ችግሮችን በቀላሉ የመፍታት ጥበብና ባህል ያካበትን ህዝቦች ነን፤ ዜጎቻችንን ለባርነት አሳልፈን አንሰጥም ብለን ዘመናዊ መሳሪያ ከታጠቀ የውጭ ጠላት ጋር ተዋግተን ከራሳችንም አልፈን መላውን ጥቁር ህዝቦች ነፃ ያወጣን የነፃነት ተምሳሌቶች ነን፣ በውስጣችን የበቀሉ ፀረህዝብ መንግሥታትን በየጊዜው ታግለን የጣልንና ለነጻነት ትልቅ ዋጋ የከፈልን ነጻ ህዝቦች ነን፡፡ ታዲያ ዛሬ ላይ እንዲህ አይነት የጋራ ወርቅ ባህል ያለን ህዝቦች እንዴት እርስ በርሳችን በዚህ መልኩ ልንጨካከን ቻልን፣ እንዴትስ ከባህላችን የወጣ ተግባር ልናዳብር ቻልን? የሚለው ሳይንሳዊ መልስ ሊያገኝ ይገባል፡፡
በተለይ በህግ ስም ሰዎችን በግድ ይዞ ከአንድ ቤት ካስቀመጡ በኋላ ለህሊና በሚከብድ ደረጃ የጭካኔ ድርጊት እስከመፈፀም እንዴት ተደረሰ? ይህ ለመስማትም የሚዘገንንና እኩይ ተግባር በሰው ልጅ የተፈጸመ ነው ለማለትም እስከሚከብደኝ ድረስ አስፈሪ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ተግባራትን የሚፈጽሙ አካላት አንድም ፈጽሞ የሰው ልጅ ባህሪያቸውን አጥተዋል፤ አልያም ቀድሞውንም ለሰው ልጅ ጠብታ አዘኔታ ያልፈጠረባቸው አውሬዎች ናቸው፡፡
ከሁሉ በላይ በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉት አካላት የዚህችን አገር የነገ ሁኔታ ለመወሰን ስልጣን በእጃቸው የሚገኝ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት መሆናቸው ችግሩን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡ በአንዳንድ አገራት በተለያዩ ህገወጥ ንግዶች ላይ የተሰማሩና ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ የሆኑ የማፍያ ቡድን አባላት አረመኔያዊ ተግባራትን ሲፈጽሙ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ደግሞ አብዛኞቹ በአደንዛዥ እፆች እየታገዙ ነው፡፡ አንዳንዶቹም በጦርነት የፈረሱ አገራትን መሸጋገሪያ ያደረጉ የማፍያ ቡድን አባላት ናቸው፡፡ በባህርና በድንበሮች አካባቢ የሚፈፅሟቸው ግፎች እንዳሉም የሚታወቅ ነው፡፡
‹‹የፍትህ ሰቆቃ›› የሚለውን ዶክመንተሪ ፊልም ስንመለከት እውን እነዚህ ሰዎች ላይ የተፈፀመው ግፍ ምን ለማግኘት ነው የሚል ጥያቄን አጫረብኝ፡፡ በምርመራ ወቅት መረጃ ለማግኘት የሚደረግ ነው እንዳልልም አንድ ሰው በዚህ ደረጃ መረጃን በመደበቅ ራሱን ለዚህ አይነት ስቃይ አሳልፎ ይሰጣል የሚል ግምት የለኝም፡፡ የሰው ልጅን እግሩን በተደጋጋሚ በመቁረጥ ኢሰብዓዊ ድርጊት መፈፀም ምን ለማግኘት እንደሆነም አይገባኝም፡፡
እነዚህ አካላት በተደጋጋሚ የሰው ልጅ ላይ በሚፈፅሙት ግፍና ስቃይ ምክንያት ለስነልቦና ቀውስ የተዳረጉና ሰዎችን የማሰቃየት በሽታ የተጠናወታቸው የአዕምሮ ስንኩላን ናቸው፡፡ ምንም ቢሆን ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው በህግ ጥላ ስር የሚገኝን ሰው በዚህ ደረጃ ለማሰቃየት የሚያስችል ምንም አይነት አመክንዮ ይኖረዋል የሚል ግምት የለኝም፡፡
ኢትዮጵያዊያን እኮ ለሰው ልጅ የሚያዝኑ ህዝቦች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የድህነት ደረጃው የከፋ ቢሆንም ሳይበላ የሚያድር ሰው የሌለው ህዝባችን እርስ በርሱ የመረዳዳትና የመተዛዘን ባህሉ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አንድ ሰው ተቸግሮ እጁን ለማያውቀው ሌላ ኢትዮጵያዊ ቢዘረጋ ባዶ እጁን አይመለስም፡፡ ከኢትዮጵያም አልፎ ሰሞኑን ከሶርያና ከየመን ወደ አገራችን ለመጡ የውጭ ዜጎች እጁን የሚዘረጋው ኢትዮጵያዊ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ይህንን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ህዝብ ያፈራቸው እነዚያ ስልጣን ላይ የወጡ አካላት ታዲያ ይህንን ኢትዮጵያዊነትን እንዴት ይዘነጉታል፡፡
በአገራችን ለሰው ልጅ ትልቅ ክብር ያላቸውና ዘመናቸውን ሙሉ ሰዎችን ሲንከባከቡ የኖሩ፣ አሁንም ከራሳቸው በላይ ለተጎዳ ወገናቸው ቀንና ሌሊት የሚሰሩ በርካታ ዜጎች አሉ፡፡ እነ ወ/ሮ አበበች ጎበና እድሜያቸውን ሙሉ የሰው ልጅን ከወደቀበት ሲያነሱና ሲንከባከቡ የኖሩ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው፡፡ በሜቄዶንያ የምናየው ሰብዓዊነትም እንዲሁ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ሰዎች ከወደቁበት ቀና ብለው እንደሰው ልጅ እንዲኖሩ፣ በአእምሮ ችግር ምክንያት የተጎዱ ዜጎች አገግመው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ለማድረግ ራሳቸውን ለሰው ልጅ አሳልፈው የሰጡ ውድ የኢትዮጵያ ዜጎች ናቸው፡፡ ታዲያ እንዴት እነዚህን የመሳሰሉ ብዙ ሺህ ዜጎች ያፈራች አገር ሰውን የሚያሰቃዩ አረመኔዎችን ማፍራት ቻለች የሚለው አሁንም ጥያቄ ነው፤ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንደሚባለው ሆኖ ካልሆነ በስተቀር፡፡
ከ27 ዓመታት በፊት ኢህአዴግ ስልጣን ለመያዝ የቻለው እኮ መላው አገራችን ህዝብ በአረመኔያዊ ድርጊቱ ዜጎቹን ያማረረውን ደርግን በመቃወም ከታጋዮች ጎን በመሰለፉ ነው፡፡ ታዲያ ያ ተረስቶ ዛሬ በዚህ ህዝብ ላይ እንዴት እንዲህ አይነት ጭካኔስ ይፈፀማል?
የሰው ልጅ ይወለዳል፣ ያድጋል ይሞታል፡፡ ይህ ሂደት ደግሞ ማንም የማይሽረው የተፈጥሮ ፀጋ ነው፡፡ ይህንን ሂደት ለማለፍም ቢበዛ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ እድሜ አይኖረንም፡፡ በዚህ ዘመን ታዲያ ምድራችን በአግባቡ ከሰራንባት ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ከኛም አልፎ አጠገባችን ለሚሆኑ ሌሎች ዜጎችን በቂ የሆነ ፀጋ ተላብሳለች፡፡ ከኛ የሚጠበቀው ጠንክረን መስራትና ለመለወጥ ዝግጁ መሆን ብቻ ነው፡፡
በተለይ በተለያዩ የህይወት አጋጣሚዎች ከራሳችንና ከቤተሰባችን አልፎ ሌሎችን ለማስተዳደር ኃላፊነት ላይ የመቀመጥ እድሉን ያገኘን ዜጎች ይህንን የኃላፊነት ጊዜያችንን በጥንቃቄ ልንይዘው ይገባል፡፡ ምናልባት ከአጠቃላይ የህይወት ዘመናችን አንድ ሦስተኛውን እድሜ ወይም ከዚያ ትንሽ ከፍ ያለ ዘመን በስልጣን ላይ ብንቆይም በዚህ ጊዜ ለሌሎች የሚጠቅሙ ተግባራትን ለማከናወን ዝግጁ መሆን ይኖርብናል፡፡
የመንግሥት ኃላፊነት ለዘላለም ወይም እድሜ ልክ የሚኖርበት ርስት አይደለም፡፡ ዛሬ ስልጣን ላይ ያለ አካል ነገ ተራ ዜጋ ሊሆን ይችላል፡፡ በወጣትነት ዘመኑ ያገኘውን ስልጣን በጉልምስና ወይም በእርጅና ዘመኑ አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ታዲያ በዚህ የጉልበት ዘመኑ ያገኘውን ይህንን ወርቃማ እድል በአግባቡ ቢጠቀምበት ለሌሎች የሚተርፍ መልካም ስራን መስራት ይችላል፡፡ ከዚያም አልፎ በእርጅና ዘመኑ ለራሱም የሚከበርበትን ሞገስ ያገኝበታል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ከቆመ ደግሞ የኋለኛውን እድሜውን ለፀፀትና ለተጠያቂነት መዳረጉ አይቀሬ ይሆናል፡፡
አንድ ሰው በልጅነቱ የሚያስበው ስለራሱ ብቻ ነው፤ ከዚህም ባላይ አይጠበቅበትምና፡፡ ለዚህ ነው በዚህ የልጅነት እድሜ የቤተሰብ ጥገኛ የሚሆነው፡፡ ከዚያ ከፍ ሲል ቤተሰብ መመስረት ይጀምራል፡፡ በዚህ ጊዜ ሃላፊነትን መሸከም “ሀ” ብሎ ይጀምራል፡፡ ከዚያ በኋላ ከፍ ሲል ልጆች ማፍራት ሲጀምር ደግሞ ያለው ኃላፊነት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በመንግሥት ተቋምም ይሁን በግል ድርጅት በኃላፊነት ቦታ ላይ ሲቀመጥ ወይም የመንግሥት ስልጣን ሲይዝ ደግሞ ተጨማሪ የቤተሰብ አባላትን ማፍራቱን መገንዘብ አለበት፡፡ በዚህ ስሜት ውስጥ የሚኖር ሰው የሚመራውን ሰራተኛ ወይም የሚያስተዳድረውን ህዝብ እንደራሱ ቤተሰብ የማየት ሃላፊነትን ያዳብራል፡፡ ከዚህ ውጭ ጥፋት የሚፈጽም አካል ወይም የህብረተሰብ ክፍል ቢገኝ እንኳ ማረም በሚያስችል ደረጃ ቅጣት እንዲያገኝ ያደርጋል እንጂ ግፍና በደል አይፈጽምበትም፡፡ ለመሆኑ ልጁ ጥፋት አጠፋ ብሎ እጁን ለመቁረጥ ወይም አካሉን ለማጉደል የሚነሳ ዜጋ ይኖራል? ከቤቱ የሚያሳድጋቸውን እንስሳት እንኳን ጥፋት ቢያገኝባቸው በዚያ አይነት ሁኔታ ለከፍተኛ ስቃይና መከራ የሚዳርግ ሰው አይኖርም፤ የአእምሮ ህመምተኛ ካልሆነ በስተቀር፡፡
ያም ሆኖ ግን አሁን ያየናቸው ግፎች በአገራችን ተፈጽመዋል፡፡ በእንደዚያ አይነት ሁኔታ የሰው ልጅ ለስቃይና ለመከራ ተጋልጧል፡፡ ከዚህ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንዳሉት ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች እንዲከናወኑ የግድ ይላል፡፡ “ግፈኞች የግፋቸውን ዋጋ በህግ እንዲቀበሉ ማድረግ፣ “ፍርድ ለልጅ፣ ጥራጊ ለደጅ” ይተርፋል እንዲሉ ይህ ግፍ በልጅ ልጆቻችን ዳግም እንዳይፈፀም የሚያደርግ አስተማማኝ ሥርዓት መዘርጋት እና ከእነርሱ የተሻልን መሆናችንን በተግባር ማሳየት”፡፡
በተለይ ከዚህ በኋላ ላለው ጉዳይ ትኩረት መስጠቱ ጠቃሚ ነው፡፡ በአገራችን ከዚህ ቀደም በደርግ ስርዓት ሲፈጸሙ የነበሩ በርካታ ግፎች እንደነበሩ የሚታወስ ነው፡፡ ሰሞኑን ባየነው ማዕከላዊ በሚባል ስፍራ አካላቸውን ያጡ፣ ነፍሳቸውን የተነጠቁ ዜጎች ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡ እነዚህን የግፍ ተግባራት ቆጥረን ሳንጨርስ በዚሁ ስፍራ ሌላ በደል ማየታችን ካለፈው የማንማር መሆናችንን የሚያሳይ ነው፡፡ አበው “ስትሄድ የመታህ ድንጋይ ስትመለስ ከደገመህ ድንጋዩ እሱ ሳይሆን አንተ ነህ” ይላሉ፡፡ የተፈፀሙ ተግባራትን ስንኮንንና ስንረግም ኖርን፡፡ ከነሱም አብዛኞቹ በፈጸሙት ተግባር ለዓመታት በእስር ቤት ቆዩ፡፡ ነገር ግን ያ ክፉ ታሪክ ላይመለስ አልተቀበረምና ጊዜ ጠብቆ ዳግም አገረሸ፡፡ እናም ዴሞክራሲን ያጎናፅፈኛል፤ ወደ ብልፅግና ያመራኛል ያልነው ሁለተኛው ስርዓትም በዚህ መልኩ በግፈኞች ተጠልፎ ዳግም የሰብዓዊ መብት ጥሰትን አሳየን፡፡ ለመሆኑ መቆሚያው የት ይሆን? ነገስ እንዲህ አይነት ድርጊት እንዳይደገም ምን መሰራት አለበት? የሚለው ትልቅ የቤት ስራ ሊታሰብበትና ሊሰራበት ይገባል፡፡
ዛሬ ላይ ያሉ መሪዎቻችን ነገ ሰዎች ሲገረፉ ቆመው የሚያዩ ሳይሆን ይህ እንዳይፈፀም የሚከላከሉና አስተማማኝ ስርዓትን ፈጥረውልን የሚያልፉ እንዲሆኑም እንመኛለን፤ እንፈልጋለንም፡፡ ይህ እንደሚሆንም እናምናለን፡፡ ምክንያቱም አሁን ባለው ሁኔታ ቢያንስ ጥላቻና ቂም በቀልን የመፀየፍና፣ በእንዲህ አይነት ተግባር ውስጥ ገብተው ኢሰብዓዊ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላትን ለፍርድ የማቅረብ ጅማሮው በራሱ በስርዓቱ ውስጥ በመፈፀሙ የለውጡ ትልቁ ማሳያ ነው፡፡ ግን ደግሞ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ዝቅ ብሎ ማየትና አስተማማኝ ስርዓት መዘርጋትም ተገቢ ነው፡፡ትናንሽ መንግሥታትም ተፈጥረው ህዝቡን በየጓዳው ለስቃይ እንዳይዳረጉ ማድረግ ነገም ተመሳሳይ ታሪኮችን እንዳይደገሙ ዋስትና ይሰጣል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2011
ውቤ ከልደታ