
-በአየር ትራንስፖርት 75 ነጥብ 2 ሚሊዮን መንገደኞች ተጓጉዘዋል
አዲስ አበባ፡- የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት የአስቻይነት ሚናውን እየተወጣ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ። በአየር ትራንስፖርት 75 ነጥብ 2 ሚሊዮን መንገደኞችን ማጓጓዝ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 40ኛ መደበኛ ስብሰባው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የ11 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል። ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፤ ከእቅድ ዝግጅት ጀምሮ እንደ ዘርፍ በተሰጠው ስትራቴጂካዊ አመራርና በተደረገው ጠንካራ ድጋፍና ክትትል የሴክተሩ የሬጉላቶሪ አቅም እየተሻሻለ መጥቷል።ይህም ዘርፉ እንደሀገር እየተገኘ ላለው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት የአስቻይነት ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በዘርፍ ከሚሠጡ አገልግሎቶች 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 13 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ ከእቅድ በላይ መፈጸም ተችሏል።በተመሳሳይ ከሲቪል አቪዬሽን አገልግሎት እና ከማሪታይም ዘርፍ ከመርከብ ምዝገባና ባህርተኞች አሠልጥኖ ወደ ውጭ ሀገር በመላክ 46 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷል፡፡
ይህም የተቋም ግንባታና የማዘመን ሥራዎች መጠናከር የአስቻይነት ሚናችንን ከመወጣት በተጨማሪ ሀብት የማመንጨትና ገቢን የማሰባሰብ አቅማችን እያደገ ሊሄድ የሚችል መሆኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ 913 ሚሊዮን ሕዝብ ለማጓጓዝ ታቅዶ እንደነበር ጠቁመው፤ ከእቅድ በላይ 960 ሚሊዮን ሕዝብ ማጓጓዝ መቻሉን አመልክተው፤ የአንድ ሀገር አቋራጭ አውቶቡስ አማካይ ዓመታዊ ኪሎ ሜትር ሽፋን በዓመቱ 107 ሺህ ኪሎ ሜትር ለማድረስ ቃቅዶ 105 ሺህ ኪሎ ሜትር በማድረስ ውጤታማ አፈጻጸም ተመዝግቧል ብለዋል።
በአየር ትራንስፖርት የዓለም አቀፍ መዳረሻ ቦታዎችን ከ138 ወደ 155 በማሳደግ 89ነጥብ 3 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ታቅዶ፣ የዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን 143 መድረሳቸውን ጠቁመው፤በእዚህም 75 ነጥብ 2 ሚሊዮን መንገደኞችን በማጓጓዝ የእቅዱን 89 ነጥብ3 በመቶ መፈጸም መቻሉን አብራርተዋል፡፡
የሎጂስቲክስ አገልግሎት ቀልጣፋ አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ የመልቲ ሞዳል አፈጻጸምን ከ60 ነጥብ 4 መቶ ወደ 80 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ 69 ነጥብ 85 በመቶ ማድረስ መቻሉን ገልጸው፤ ከ2016 ከተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ9 ነጥብ 19 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል።
የዘርፉን መሠረተ ልማት የተቀናጀ፣ ፍትሐዊና ተደራሽ ለማድረግ የተከናወኑ ቅንጅታዊ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን አንስተው፤ በቀጣይነትም የመንገድ ደህንነት ትራፊክ አደጋ፣ የትራንስፖርት ፍሰቱንና የንግድ ተወዳዳሪነትን የሚያውኩ የሕገ-ወጥ የመንገድ ላይ ኬላዎች ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት ጨምሮ ሌሎችም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ ይሠራል ብለዋል።
የምክር ቤት አባላት የትራፊክ አደጋ መጨመር፣ የሞጆ ደረቅ ወደብ ሥራ መጓተት፣ ሕገ ወጥ ኬላዎች መኖር፣ ለኤሌክትሪክ መኪኖች በቂ የቻርጅ ማድረጊያ ቦታ እና በተለያዩ ከተሞች የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ጨምሮ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፤ 68 በመቶ አደጋ የሚደርሰው አሽከርካሪዎች በሚፈጽሙት ስህተት ነው። ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት የአሽከርካሪዎችን አቅም ለማጎልብት እና ወደ ምዘና ሥርዓት ለማስገባት ሥራዎች ተጀምረዋል። የምዘና ሥርዓቱን ከሀሰተኛ ሰነድ እና ከሰዎች ንክኪ ነጻ ለማድረግ ከፋይዳ መታወቂያ ጋር የማስተሳሰር ሥራ እየተሠራ ነው። አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳም አደጋን ለመቀነስ እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።
የሞጆ ደረቅ ወደብ ሥራ የዘገየበት ምክንያት በሲሚንቶ እጥረት መሆኑን ጠቁመው፤ ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት በቀን ከሚያስፈልገው ሲሚንቶ ሲቀርብ የነበረው 22 በመቶ ብቻ ነው።አሁን ላይ ሥራውን በአምስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ታዳሽ ኢኮኖሚን ለማጠናከርን ለነዳጅ የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቁመው፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ለመጨመና የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ ቦታዎችን ለማስፋት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ እና ንግድ መሆኑን አንስተው፤ ተሳፋሪ መኖሩን፣ ከአየር ማረፊያ ያለውን ርቀትና የኢኮኖሚ አዋጭነት ጥናትን መሠረት አድርጎ ምላሽ የሚያገኝ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም