
አዲስ አበባ፡- በ2016 በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተሰበሰበ ቀረጥና ታክስ መኖሩን ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ገለጸ። በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2016 በጀት ዓመት የሂሳብ የፋይናንሺያል የሕጋዊነት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት አቅርቧል።
ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፤ በገቢዎች እና በጉምሩክ ባለሥልጣን በተለያዩ አካላት በተደረገው ማጣራት የተገኘው ያልተሰበሰበ የመንግሥት ቀሪ ቀረጥና ታክስ እዳ በአዋጁና በመመሪያው መሠረት መሰብሰቡን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፤ በ2016 በጀት ዓመት 3 ቢሊዮን 617 ሚሊዮን 010ሺህ 962 ብር ያልተሰበሰበ ቀረጥና ታክስ መኖሩን ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።
በ11 የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ እዳ በጠቅላላው ብር 2 ቢሊዮን 390 ሚሊዮን 263 ሺህ 915 ብር፣ በተለያየ ሂደት ላይ የሚገኝ የግብር ዕዳ በ 10 የገቢዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች 1 ቢሊዮን 226 ሚሊዮን 747ሺህ 46 ብር በድምሩም ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ እንዳልተሰበሰበ መረጋገጡን ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል።
የግብር፣ የታክስና ቀረጥ ሂሳብ በወቅቱ ክትትል ተደርጎ ገቢ እንዲሆን ካልተደረገ የልማት ሥራዎች እንዳይፋጠኑ እንቅፋት ከመፍጠሩም በተጨማሪ በገቢ አሰባሰቡ ሂደት ላይ ያለውን የክትትል ክፍተት የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ዋና ኦዲተሯ ገለጻ፤ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹ እና በዋናው መሥሪያ ቤት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ግብር ከፋዮች ያለባቸውን ዕዳ እንዲከፍሉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ቀጣይ ርምጃ በመውሰድ ያልተሰበሰበውን ቀሪ የቀረጥና ታክስ እዳ መሰብሰብ እንዳለባቸው በተላከው ሪፖርት ማሳሰባቸውንም አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ መሥሪያ ቤቶች አገልግሎት የሰጡበትን ሂሳብ በተገባው የውል ሥምምነት መሠረት በወቅቱ የሚሰበስቡ መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በዱቤ ከሰጠው የማስታወቂያ አገልግሎት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ሳይሰበሰብ የቆየ ብር 168 ሚሊዮን 480ሺህ 898 በኦዲት መገኘቱን ጠቁመው፤ የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻሊይዝድ ሆስፒታል ለጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች የህክምና አገልግሎት የሰጠበት ብር 75ሺህ 601 ብር ጨምሮ በጠቅላላው ከ168 ሚሊዮን 566ሺህ 499 ብር በወቅቱ ያልተሰበሰበ መሆኑንም ገልጸዋል።
መሥሪያ ቤቶቹ ገቢው በወቅቱ ክትትል አድርገው ካልሰበሰቡ በእቅድ የያዙትን ሥራ እንዳያከናውኑ ጫና ከመፍጠሩም በተጨማሪ በገቢ አሰባሰቡ ሂደት ላይ ያለውን የክትትል ክፍተት የሚያመላክት ነው ብለዋል። በመጨረሻም ያልተሰበሰበው ውዝፍ የገቢ ሂሳብ እንዲሰበሰብ ተገቢው ጥረትና ክትትል እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም