
ጅግጅጋ፦ በሶማሌ ክልል ዓመታዊ የግመል ወተት ምርት ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ሊትር ወደ ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ማሳደግ መቻሉን የክልሉ አርብቶ አደር ልማት ቢሮ አስታወቀ። ክልሉ 16 ሺህ በላይ ከፊል አርብቶ አደሮችን በማሳተፍ በ27 ሺህ 700 ሄክታር መሬት ላይ የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎችን ማምረቱን ጠቁሟል።
በሶማሌ ክልል የአርብቶ አደር ልማት ቢሮ ኃላፊ አብዲቃዲር ኢማን (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ ተግባራዊ የተደረገውን የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር ውጤታማ ለማድረግ ቢሮው ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል።
በክልሉ በሌማት ትሩፋት የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የእንስሳት ርባታ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተገኘባቸው እንደሚገኝ አመልክተው፤ በተለይም በክልሉ በከተማ እና ገጠር አካባቢዎች ዘመናዊ የግመል ርባታ ሥራን ተግባራዊ በማድረግ፤ በግመል ወተት ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቧል ብለዋል።
በክልሉ ቀደም ሲል ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚታለቡ ግመሎች ቢኖርም፤ የሚገኘው የወተት ምርት አጥጋቢ አለመሆኑን በማስታወስ፤ የእንስሳቶችን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሠሩ ሥራዎች የክልሉ ዓመታዊ የግመል ወተት ምርት ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ወደ ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ሊትር ማደጉን ገልጸዋል።
በቀን እስከ 10 ሊትር ወተት የመስጠት አቅም ያላቸው ግመሎች በአያያዝ ችግር ከአራት ሊትር በላይ እንዳይሰጡ ማድረጉን አውስተው፤ ችግሩን ለመቅረፍ ዘመናዊ የግመል ርባታ ሥራ ተግባራዊ ሊደረግ ችሏል። በዋናነት የግመል ወተት ምርታማነት ለማሳደግ በመኖ አቅርቦት ላይ ሰፊ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት የወንዞች ተፋሰስ አካባቢ የሚገኙ 16 ሺህ በላይ ከፊል አርብቶ አደሮችን በማሳተፍ በ27 ሺህ 700 ሄክታር መሬት ላይ የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎችን ማምረት መቻሉን የሚናገሩት ኃላፊው፤ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች 256 ትላልቅ ሼዶች ተገንብተው በዘመናዊ መልክ እንስሳትን የማርባት ሥራን እንዲሠሩ መደረጉን አመላክተዋል። ይህም የግመል ወተት ምርትን ከማሳደግ በተጨማሪ የእንስሳት ምርታማነትን ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
በክልሉ ያለውን የቤት እንስሳቶችን ወደ ዘመናዊ ርባታ የመለወጥ ሥራ በከተሞችም ጭምር እየተስፋፋ መጥቷል ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ በቀጣይም ክልሉ የእንስሳት ሀብቱን በተገቢው መንገድ ወደ ውጭ ኤክስፖርት በማድረግ የአርብቶ አደሩን እና የሀገርን ገቢ የማሳደግ ሥራ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
በክልሉ የእንስሳት ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዙ ዕቅዶች የበለጠ ስኬታማ እንዲሆኑ መንግሥት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የምርምር ማዕከላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም