
አዲስ አበባ፡- ከተቋማት ጋር የተደረገው ስምምነት በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምባሆ ቁጥጥር ሕጎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስፈጸም የሚያስችል መሆኑን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ገለጸ።
በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣንና በብሔራዊ ትምባሆ ቁጥጥር አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ተቋማት መካከልም የጋራ የመግባቢያ ስምምነት ትናንት ተፈርሟል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ እንደገለፁት፣ የትምባሆ ምርቶችን በተለያየ መንገድ መጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ የህብረተሰብ ጤናን ከሚጎዱ ነገሮች መካከል አንዱና ቀዳሚው ነው። እ.ኤ.አ. በ2024 በተደረገው ሀገር አቀፍ የትምባሆ ዳሰሳ ጥናት ግኝት መሠረት በአሁኑ ጊዜ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ እድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የትምባሆ ምርቶችን በተለያየ መንገድ ይጠቀማሉ።
ከ19 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ደግሞ በመንግሥት ተቋማት፣ በመኖሪያ ቤቶች በሬስቶራንትና መሰል የሕዝብ መሰብሰቢያ ስፍራዎች ላይ ለትምባሆ ጭስ መጋለጣቸውን ጥናቱ ያሳያል።
‹‹ትምባሆን በተለያየ መንገድ መጠቀም የሚያስከትለውን ዘርፈ-ብዙ የጤና፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ለመቆጣጠር መንግሥት በተለይ ጠንካራ የሕግ ማሕቀፎችን አፅድቆ በማስተግበር ትልቅ ርምጃ ወስዷል›› ያሉት ዋና ዳይሬተሯ፣ ለአብነትም የዓለም ጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ማሕቀፍን ማፅደቁንና ይህን ማሕቀፍ በሚያካትት መልኩ የምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ 1112/2011 በማፅደቅ ተግባራዊ ማድረጉንም ጠቁመዋል። ‹‹ይህ አዋጅ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአግባቡ በማስተግበር ሂደት የትምባሆ ቁጥጥር ላይ የተከናወኑ ተግባራት ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጣቸው ናቸው›› ብለዋል።
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱም በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምባሆ ቁጥጥር ሥራን በበላይነት እንዲያስተባብር ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው ቢሆንም፤ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ የመንግሥት፣ የግልና የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማትና ድርጅቶች ተሳትፎ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስገንዝበዋል።
ይህን ታሳቢ በማድረግም በትምባሆ ቁጥጥር መመሪያ ቁጥር 771/2021 መሠረት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ከ25 እስከ 30 የሚሆኑና ዘርፈ ብዙ ተግባርና ኃላፊነት ያላቸውን ተቋማት በመለየት የብሔራዊ ትምባሆ ቁጥጥር አስተባባሪ ኮሚቴ በማቋቋም የትምባሆ ቁጥጥር ተግባራትን መከናወናቸውን አብራርተዋል።
ይህ ኮሚቴ ከአዋጅ 1112/2011 ሕግ አወጣጥ ጀምሮ እስከ ማፀደቅ ሂደት እንዲሁም በሕጉ አፈፃፀምና አተገባበር ወቅት አሁናዊና መጪውን ትውልድ ከትምባሆና ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች ከሚያስከትሉት አስከፊ የጤና፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ለመታደግ የተጠናከረ ተሳትፎ ማድረጉን አስረድተዋል።
ይህን ውጤት ይበልጥ ለማስቀጠል አዳዲሶችን በማካተት ከ 20 በላይ ከሚሆኑ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን ጠቁመው፣ ይህም ጥምረት የትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነትን በተደራጀ መልኩ በጋራ ለመከላከል፣ ተቋማትን ከትምባሆ ጭስ ነፃ ለማድረግና ስለ ትምባሆ ጎጂነት የግንዛቤ ለማስጨበጥ፣ ከትምባሆ ኢንዱስትሪ ጋር የሚደረጉ የሽርክና/ስምምነት ለመከላከል፣ የተለያዩ የቁጥጥር ስልቶችን በመጠቀም/በመንደፍ የትምባሆ ምርትና ተጠቃሚነትን በጋራ ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።
‹‹ስምምነቱም የትምባሆ ቁጥጥር ሕጎችን በተቀናጀና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስፈጸም የሚያስችል ነውም›› ብለዋል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ የትምባሆ ምርቶችን በተለያየ መንገድ መጠቀም በየዓመቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለህልፈት ይዳረጋሉ። ከዚህ ውስጥ ከ7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በቀጥታ ትምባሆ ተጠቃሚ ሲሆኑ ከ 1̀ ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በተዘዋዋሪ መንገድ ለትምባሆ ጭስ በመጋለጥ የሚሞቱ መሆናቸው ታውቋል።
በታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም