
አዲስ አበባ፦ ሀገራችን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን አልፋ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ማሳካት የምንችለው ለትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ውጤት ማስመዝገብ ስንችል እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። በዓለም ላይ ከፍተኛ እድገት ያስመዘገቡ ሀገራት የልዕልናቸው ምንጭ የትምህርት ሥርዓታቸውን በአግባቡ ቀርጸው መተግበራቸው መሆኑን አመለከቱ።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች ትናንት ባስመረቀበት ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልእክት እንዳመለከቱት፤ ትምህርት በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የማይተካ ነው።
በዓለማችን ከፍተኛ እድገት ላይ የደረሱ ሀገራት የልዕልናቸው ምንጭ የትምህርት ሥርዓታቸውን በአግባቡ ቀርጸው በመተግበራቸው ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ሀገራችን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን በማለፍ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ማሳካት የምትችለው ለትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ውጤት ማስመዝገብ ስንችል ነው ብለዋል። ለእዚህም የትምህርት ተቋማት፣ ዜጎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ተመራቂዎች ዩኒቨርሲቲ በነበራቸው ቆይታ የሀገርንና የሕዝብን አደራ መወጣት የሚያስችላቸውን እውቀት እና ክህሎት እንደጨበጡ ያላቸውን እምነት ገልጸው፤ ትምህርት ትውልድን የሚቀርጽና የሚያንጽ መሣሪያ ነው። መማር ማለት የአስተሳሰብ እና የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ነው ብለዋል። የትምህርት ባለሙያነት ትውልድን በማነጽ ሀገርን የመገንባት ትልቅ ኃላፊነት መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት እንደሌለባቸውም አስገንዝበዋል።
“ምክንያታዊነት፣ ሰላም ወዳድነት፣ ትጋትና መተባበርን መለማመድ የስኬት ቁልፎች ናቸው። እንደ ሀገርም ሆነ በከተማ ደረጃ ያለእረፍት እየተሠራ ያለው ቀጣዩ ትውልድ እኛ ባለፍንባቸው አስቸጋሪ መንገዶች እንዳያልፍ ነው። ተመራቂዎችም ለተለወጠ ነገ የሚመጥን ብቃት ላይ መገኘት ይጠበቅባችኋል። ለተለወጠ ነገ ብቁ ሆኖ መገኘት ተጠቃሚነትን ለማሳደግም ያስችላል” ብለዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ለበርካታ ዓመታት የተለያዩ ስያሜዎችን በመያዝ በርካታ ምሩቃንን ለሀገር ሲያበረክት መቆየቱን አስታውሰዋል።
በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ከተቋቋመ ጀምሮም ተማሪዎችን ተቀብሎ በመምህርነት እና በትምህርት ባለሙያነት እያሠለጠነ እንደሚገኝ አመልክተው፤ አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያግዙ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ምሩቃን በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንዳለባቸው፤ሥራ ጠባቂ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ ሆነው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን መጥቀም እንዳለባቸው፤ በሥራ ወቅት የሚያጋጥማቸውን ውጣ ውረዶች በብልሃት በማለፍ ነገዎቻቸውን ብሩህ እንዲያደርጉ መክረዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን አንድ ሺህ 989 ተማሪዎችን በትናንትናው ዕለት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አዳራሽ አስመርቋል።
በፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም