አዲስ አበባ፦ በትምህርት ቤቶች የሚገኙ ክበባት መልካም ሰብእና ያለው ትውልድ ከማፍራት ጀምሮ በመማር ማስተማሩ ሂደት የሚጫወቱት ሚና የጎላ በመሆኑ በአዲስ መልክ በማደራጀት ወደ ሥራ ማስገባቱን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በትምህርት ሚኒስቴር በአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ የሥርዓተ-ትምህርት ማበልጸጊያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ የቋንቋና ተጓዳኝ ትምህርቶች ሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዴስክ ኃላፊ አበበ ጋረደው (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ትምህርት ሚኒስቴር እንደ ሀገር ባሉ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ግለ-ሰብዕና እድገት ፤ለማህበራዊ ትስስር ፤ለአመራር ክህሎት እድገት፤ ለስሜታዊ መዳበር፤ ለትምህርት አቀባበል ችሎታ መጨመር እንዲሁም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እና ወደፊት መሠማራት በሚፈልጉበት ሙያ እንዲሠማሩ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ክበባት በአዲስ በማደራጀት ወደ ሥራ የማስገባት ተግባር አከናውኗል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያካሄደውን ሀገር አቀፍ ጥናት ግኝት የመፍትሔ ሃሳቦች መነሻ በማድረግ የትምህርት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት በትምህርት ሥርዓቱ መሠረታዊ ለውጦችን ለማምጣት የለውጥ መርሐ ግብሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን የዴስክ ኃላፊው አበበ (ዶ/ር ) ጠቁመዋል።
ከእነዚህ ለውጦች መካከል አንዱ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል ያለው የአጠቃላይ ትምህርት ፣ ሥርዓተ ትምህርት ሪፎርም መሆኑንም ገልጸዋል።ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።ይሄ ሥርዓተ ትምህርት በሚዘጋጅበት ወቅት ቀድሞ የነበረው የክበባት አደረጃጀት እና አተገባበር ሥርዓትም በክፍል ውስጥ የሚሰጠውን መደበኛ ሥርዓተ ትምህርት በሚያጠናክር መልኩ ተዘጋጅቶ ካለፈው 2016 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት ቤቶች ወደ ትግበራ እንዲገቡ መደረጉን አመልክተዋል።
ክበባትን በአዲስ የማደራጀት ተግባር ውስጥ መግባት ያስፈለገው ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በንድፈ ሃሳብ ከሚማሩት ትምህርት በተጨማሪ ከክፍል ውጪ እንደ ዝንባሌያቸውና ክህሎታቸው በተለያዩ ተግባሮች ላይ የሚሳተፉበትን እድል ለመፍጠር መሆኑንም አብራርተዋል።በአዲስ ተቋቁመው ወደ ሥራ የገቡት ክበባት ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጋር የሚናበቡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በ2015 ዓ.ም ጸድቆ ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀት እና አተገባበር ማንዋል በስምንት ጉድኝት ትምህርት ዘርፎች ስር 21 ክበባት ስለመኖራቸው ማመላከቱን ጠቁመው፤ ሆኖም ማንዋሉ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ሁሉንም የክበባት ዓይነቶች እንዲያቋቁሙ አለማስገደዱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ማንዋሉ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎ ቻቸውን ብዛት እና ተጨባጭ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚያቋቁሟቸውን ክበባት ብዛት እና ዓይነት መወሰን የሚችሉበት ዕድል እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር ክበባቱን ለማጠናከር አደረጃጀት እና አተገባበራቸው በክፍል ውስጥ በንድፈ ሃሳብ እንደሚሰጠው ሥርዓተ-ትምህርት እንዲሆን ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል እያደረገ መገኘቱንም አመልክተዋል።
ወጥ የሆነ ክበባት የሚጠቀሙባቸውን የተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀት ማንዋል አዘጋጅቷል፤ ክበባት የሚጠቀሙባቸውን ተጨማሪ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል ፤ሥልጠናዎች ሠጥቷል ፤የተጓዳኝ ትምህርት ከፍተኛ ባለሙያ መድቦ እንዲመራ አድርጓል ብለዋል።
የክልል እና ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎችም እንደየ ተዋረዳቸው ክበቦች ተጠናክረው ተማሪዎች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ በእዚሁ መልኩ ክበባትን ወደ ሥራ ማስገባታቸውን ጠቁመው፤ በቅርቡ በጸደቀው የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ 1368/2017 መሠረት የክበባት አደረጃጀት ተፈጻሚነት እንዲኖረው ለማድረግ የተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀት እና አተገባበር መመሪያ መዘጋጀቱን አስታውሰዋል።
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም