ሜዲካል ቱሪዝም በኢትዮጵያ እንዴት እውን ይሆናል?

የሜዲካል ቱሪዝም ልማት ሥራዎች በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟሉና ጥራታቸውን የጠበቁ አስተማማኝ የጤና አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ተነግሯል። ለዚህም በአስር ዓመታት ውስጥ ገቢራዊ የሚሆን የሜዲካል ቱሪዝም ልማት ስትራቴጂ ፖሊሲ በመንግሥት ተቀርፆ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅቶች ተጠናቀዋል።

የሜዲካል ቱሪዝም ልማት ስትራቴጂ ፖሊሲው ለሕክምና አገልግሎት ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱ ዜጎችን 80 ከመቶ መቀነስና በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለማስፋት እንደሚያስችል ተገልጿል። በሂደትም ባለሙያዎችን በማሠልጠንና አዳዲስ የሕክምና አገልግሎት መስጪያ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለሜዲካል ቱሪዝም ልማት ትኩረት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።

ለመሆኑ በኢትዮጵያ የሜዲካል ቱሪዝምን እንዴት እውን ማድረግ ይቻላል? ሜዲካል ቱሪዝምን እውን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? በዚህ ጉዳይ ላይ የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎች ሃሳባቸውን ያጋራሉ።

ዶክተር ካሣሁን ኪሮስ በሙያቸው የፅንስና ማህፀን ስፔሺያሊስት ናቸው። በማህፀን ካንሰር ደግሞ የሰብ ስፔሺያሊስት ሕክምና ሙያ አላቸው። አሁን ላይ በአንድ ከፍተኛ የግል ሆስፒታል ውስጥ ሜዲካል ዳይሬክተርና ባለድርሻ ሆነው ይሠራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት የተለያዩ ሕክምናዎች ፍለጋ በርካታ ኢትዮጵያውያን በየጊዜው ወደ ውጭ ሀገራት ይሄዳሉ። ይህም ሀገሪቱን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስወጣት እንዳለ ይናገራሉ። እርሳቸው የሚሠሩበት ሆስፒታልም በውጭ ሀገራት ያሉ ሕክምናዎችን በማስጀመር ሰዎች እዚሁ በሀገራቸው እንዲታከሙ የማስፋፊያ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ።

መንግሥት በአስራ አንድ ሆስፒታሎች ሜዲካል ቱሪዝምን ለማስፋፋት በ2013 ዓ.ም ቦታ መስጠቱንም አስታውሰው፤ የሜዲካል ቱሪዝም ማስፋፊያ ቦታ ከተሰጣቸው ሆስፒታሎች ውስጥ አንዱ እርሳቸው የሚሠሩበት ሆስፒታል መሆኑንና የቦታውን ሊዝ ከፍሎ ለመረከብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ይገልፃሉ። ይህም መንግሥት ሜዲካል ቱሪዝምን በሀገር ውስጥ ለማስፋፋት ምን ያህል ትኩረት እንደሰጠና ዜጎች ወደ ውጭ ሀገራት ተጉዘው የሚያወጡትን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት ያለውን ፍላጎት ያሳያል ይላሉ።

የሕፃናት ቀዶ ሕክምና ስፔሺያሊስትና በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በዚሁ ዘርፍ በመምህርነትና በማማከር ሥራ ላይ ያሉት ፕሮፌሰር ሚሊያርድ ደርበው በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በርካታ ሰዎች ሕክምና ፈልገው ወደ ውጭ ሀገራት እንደሚሄዱና ይህም የሆነው በዋናነት የሕክምና አገልግሎቱን በሀገር ውስጥ ባለማግኘታቸው መሆኑን ይናገራሉ። በሀገር ውስጥ በሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት ላይ ሙሉ በሙሉ እምነት ባለማሳደራቸው ወደ ውጭ ሀገር ሕክምና እንደሚያማትሩም ይገልፃሉ።

አሁን ላይ ሜዲካል ቱሪዝምን በኢትዮጵያ ለማስፋት በመንግሥት በኩል ጥሩ ማበረታቻዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በተለይ የግል ሆስፒታሎች በዝቅተኛ ዋጋ መሬት እንዲያገኙ መደረጉ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት መሰጠቱን ማሳያ ነው ይላሉ። በሌላ በኩል የሕክምና መሣሪያዎች ከቀረጥ ነፃ ሆነው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡና ለሕክምና መሣሪያዎች ግዢ የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ እንዲሰጥ መደረጉ ዘርፉን ለማበረታታት በመንግሥት በኩል ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ይገልፃሉ።

ከሀገር ውጭ የሚሰጡ ሕክምናዎችን በሀገር ውስጥ መስጠት የማይቻልበት ምንም ምክንያት እንደሌለ የሚገልፁት ዶክተር ካሣሁን፤ ዋናው ነገር በሙያው የሠለጠነ የሰው ኃይል በበቂ ሁኔታ ማፍራት፣ የሕክምና መሣሪያዎችን፣ ቴክኖሎጂዎችንና የሕክምና መሠረተ ልማቶችን በበቂ ሁኔታ ማሟላት መሆኑን ይጠቁማሉ።

በውጭ ሀገር የሚሰጡ ሕክምናዎች በሀገር ውስጥ እንዲሰጡና ሜዲካል ቱሪዝም በሀገር ውስጥ እንዲስፋፋ ከማድረግ በዘለለ ግን ኅብረተሰቡ በሕክምናዎቹ ላይ እምነት እንዲያሳድር ከፍተኛ የግንዛቤና የማሳመን ሥራዎች ከወዲሁ መሠራት እንዳለባቸው ዶክተር ካሣሁን ይናገራሉ።

ፕሮፌሰር ሚሊያድርድ ደግሞ ለሕክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱ ታካሚዎችን ለማስቀረት በሀገር ውስጥ የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎት ማስፋት፣ ማዘመንና ጥራቱን መጨመር እንደሚገባ ይጠቁማሉ። ከዚህ አንፃር በተለይ የግል ጤና ተቋማት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያመለክታሉ። በሜዲካል ቱሪዝም እሳቤ አገልግሎታቸውን ማስፋትና ማዘመን እንደሚጠበቅባቸው ይገልፃሉ። በዋናነትም ራሳቸውን በሰው ኃይል፣ በሕክምና መሣሪያዎችና በመሠረተ ልማት አቅም መገንባት እንዳለባቸው ያሳስባሉ።

በሌላ በኩል ፕሮፌሰር ሚሊያርድ የዶክተር ካሣሁንን ሃሳብ በመጋራት ሕክምና ፈልገው ወደ ውጭ ሀገራት የሚሄዱ ታካሚዎች በሀገር ውስጥ በሚሰጠው ሕክምና እምነት ሊያሳድሩ እንደሚገባ ይገልፃሉ። ይህን ለማድረግ ደግሞ በተለይ የግል ሕክምና ተቋማት በሰው ኃይልና በሕክምና መሣሪያዎች ብሎም በቴክኖሎጂ የተሟላ የሕክምና አገልግሎቶችን ለታካሚዎች ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ያመለክታሉ። ከዚህ ባለፈ በሀገር ውስጥ የሚሰጠው ሕክምና ውጭ ከሚሰጠው ጋር ልዩነት እንደሌለው ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ መስጠት እንደሚያስፈልግም ፕሮፌሰር ሚሊያርድ ይጠቁማሉ።

በውጭ ሀገራት የሚሰጡ ሕክምናዎች በሀገር ውስጥ የሚሰጡ ከሆነና ሜዲካል ቱሪዝም በኢትዮጵያ ይበልጥ እየተስፋፋ የሚሄድ ከሆነ ጥቅሙ ለሀገር ውስጥ ታካሚዎች ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት ሀገራት ለሚመጡ ታካሚዎችም ጭምር ነው የሚሉት ዶክተር ካሣሁን፤ አሁንም ከኤርትራ፣ ሶማሊያና ጂቡቲ ለሕክምና ወደሀገር ውስጥ የሚገቡ ታካሚዎች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። በሀገር ውስጥ የሚሰጠው ሕክምና የበለጠ በዘመነ ቁጥር ደግሞ ከጎረቤት ሀገራት ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ሀገራትም ጭምር ሰዎች ሕክምና ፈልገው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበት ዕድል የሰፋ መሆኑን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ሲመጡ ለሕክምና የሚያወጡት ወጪ ሌላ ሀገር ከሚያወጡት ጋር በንፅፅር ያነሰ ከሆነ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የሚታከሙበት ዕድል ይበልጥ ሊሰፋ እንደሚችል ዶክተር ካሣሁን ይገልፃሉ። እነዚህ ከውጭ ሀገር ለሕክምና የሚመጡ ሰዎች እዚህ ባገኙት ሕክምና ከረኩና እምነት ካደረባቸው ደግሞ ቤተሰባቸውንና ዘመዶቻቸውን ለማሳከም ተመልሰው መምጣታቸው የማይቀር መሆኑን ያስረዳሉ። ይህ እንዲሆን ደግሞ በተለያየ መንገድ ከሌሎች ሀገራት መወዳደር የግድ እንደሚል ይጠቁማሉ።

ከሜዲካል ቱሪዝም አንፃር ኢትዮጵያ አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የሚጠቁሙት ዶክተር ካሣሁን፤ በመንግሥትም በኩል ለዘርፉ ትኩረት እየተሰጠ መምጣቱንና ሆስፒታሎች ሜዲካል ቱሪዝምን እንዲያስፋፉ ቦታ መሰጠቱም የዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን ይናገራሉ። ይህ እንዳለ ሆኖ ሜዲካል ቱሪዝሙን ለማስፋፋት እንዲያስችል ሆስፒታሎች በባንኮች በኩል የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ ያመለክታሉ።

ፕሮፌሰር ሚሊያርድ ደርበው በበኩላቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ ለሜዲካል ቱሪዝም አመቺ መሆኗን ገልፀው፤ በተለይ የሀገሪቱ የአየር ሁኔታ ለታካሚዎች ምቹ ከመሆኑ አንፃር ሰዎች ለሕክምና ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡ ሳይቸገሩ የሚታከሙበት ሁኔታ እንዳለ ይናገራሉ። የአየር ሁኔታው መልካምነት እንዳለ ሆኖ ግን ሜዲካል ቱሪዝምን በኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የሕክምና አገልግሎቶችን ማዘመንና ጥራታቸውን መጨመር እንደሚገባ ይጠቁማሉ።

ለሜዲካል ቱሪዝሙ እውን መሆን የሕክምና አገልግሎትና ጥራትን ከመጨመር ባለፈ ታካሚዎች ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ ከሚያገኙት ሕክምና በተጨማሪ እግረ መንገዳቸውን ሀገሪቱን በመጎብኘት ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ እንዲያወጡ የሜዲካል ቱሪዝሙን ከሌሎች የቱሪዝም መስኮች ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ ያመለክታሉ።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You