መጽሐፉ የነገረን እና ያልነገረን
የመጽሐፉ ስም፡– አየርና ሰው
ደራሲ፡– መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ
የህትመት ዘመን፡– 1951 ዓ.ም
የገጽ ብዛት፡– 88
መጽሐፉ የመሸጫ ዋጋ አልተቀመጠለትም። ምናልባት ለመጀመሪያ ጊዜ በታተመበት ዘመን ለሚመለከታቸው አካላት ብቻ ለመስጠት ታስቦ ይሆናል። መጽሐፉ በ2003 ዓ.ም እና በ2010 ዓ.ም በድጋሜ ታትሟል፤ አሁንም ግን የመሸጫ ዋጋ አልተቀመጠለትም፤ በመጻሕፍት መደብር አይገኝም ማለት ነው። መጽሐፉ 88 ገጾች ብቻ ነው ያሉት። ከመቶ ገጽ በታች ያልተለመደ ስለሆነ «መጽሐፍ» ብሎ ለመጥራት እንቸገር ይሆናል፤ ይዘቱ ግን ውስብስብ ሳይንስ ያለበት ነው።
ወደ መጽሐፉ ይዘት ከመግባታችን በፊት ሁለት ነገሮችን ማየት አስፈላጊ ነው። የመጀመሪያው በተደጋጋሚ እንደምለው፤ ሰው ሥራውን ይመስላልና የመጽሐፉ ደራሲ መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ማን ናቸው? የሚለውን ነው።
መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ከ1994 እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ የኢፌዴሪ ርዕሰ ብሔር ሆነው ለ12 ዓመታት አገልግለዋል። በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በወታደርነት ውስጥ አልፈው መቶ አለቃ እስከመሆን ደርሰዋል። ከፕሬዚዳንትነታቸው ጊዜ ጀምሮ «መቶ አለቃ» የሚለው ማዕረጋቸው ብዙም ሲጠራ አይሰማም፤ ይልቁንም «አቶ» እየተባሉም ይገለጹ ነበር።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ድረ ገጽ በአንድ ወቅት ለሚዲያው የሰጡትን መረጃ ዋቢ አድርጎ እንዳስቀመጠው፤ በውትድርና አገልግሎት ዘመናቸው በቀድሞው የገነት ጦር አካዳሚ የመኮንንነት ኮርስ በመውሰድ፣ የበረራ አመራርን በመማር፣ ለመመረቅ የበቁ የመጀመሪያው የአየር ኃይል አባል ናቸው። በ1938 ዓ.ም በአየር ኃይል ትምህርት ቤት ውትድርናን አስተምረዋል። በዚህም የሬዲዮ ናቪጌሽን ሙያ በማስተማር አንጋፋ የሆኑ በርካታ የአየር ኃይል ሙያተኞች አፍርተዋል።
መቶ አለቃ ግርማ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በአቪዬሽን ቀዳሚ እንድትሆን የራሳቸውን ሚና የተወጡ ናቸው።
ወደ መጽሐፉ ይዘት ከመግባታችን በፊት ሌላው መታወቅ ያለበት ነገር የታተመበት ዘመን ነው። 1951 ዓ.ም ማለት እንኳን በኢትዮጵያ በአውሮፕላን ፈጣሪዎቹ አገርም አውሮፕላን ገና ብርቅ የሆነበት ነው። «ራይት ብራዘርስ» የተባሉት ወንድማማቾች በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1903 ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፕላንን ቢያበሩም የተዋጊ ጄት አውሮፕላኖች እስከ 1950ዎቹ ገና ነበሩ። ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ ነው የተስፋፉት። እንግዲህ መቶ አለቃ ግርማ ይህን መጽሐፍ ሲጽፉ የአውሮፕላን ታሪክ በዓለም እንኳን ገና ብርቅ ነበር ማለት ነው፤ በዚያን ዘመን ደግሞ እንዲህ እንደ አሁኑ መረጃ በቀላሉ የሚገኝበትም አልነበረም፤ በመስማት እና በማስተዋል ብቻ ነው የሚጻፈው።
ወደ መጽሐፉ ይዘት ስንገባ እንግዳ ቃላት ያሉበት ነው። እነዚህ እንግዳ ቃላት ሙያዊ ቃላት ናቸውና በሌላ መቀየር አይቻልም፤ እንግዳነታቸውም ከሙያው ውጪ ላለን ሰዎች ነው። እንዲህ ዓይነት በአንድ ሙያ ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርጉ መጽሐፎች በሙያው ቃላት ለመጠቀም ይገደዳሉ፤ እንዲያውም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በተቻለ መጠን በተለመዱ ቃላት ለማስረዳት ጥረት ተደርጓል፤ እንዲያውም ደራሲው በመጽሐፉ መግቢያ ላይ እንደሚነግሩን ለመጻፍ ያነሳሳቸው አንዱ ምክንያት በአገርኛ ቋንቋ ቴክኖሎጂውን ማስተዋወቅ ነበር። «በዚያን ዘመን እንግሊዝኛ የተማሩ ሰዎች ስላልነበሩ ፈረንሳይኛ መማር የግድ ነበር» ይሉናል። እርሳቸው በሚችሏቸው ቋንቋዎች ያነበቡትንና ያስተዋሉትን ለአገራቸው ለማስተዋወቅ ነው በአማርኛ ቋንቋ የጻፉት።
መጽሐፉ የአውሮፕላንን አፈጣጠር ታሪክ እና የፈጣሪዎቹን ስም ይነግረናል። መጀመሪያ የታሰበውም በሥዕልና በሃሳብ ብቻ ነበር። በሥዕል ደረጃ ታስቦ ከ190 ዓመት በኋላ ነው ወደ እውንነት የተቀየረው። እዚህ ላይ ዶክተር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት በ«ንባብ ለሕይወት»ፕሮግራም ላይ የተናገሩትን ልጥቀስ።
«ራይት ብራዘርስ» አውሮፕላንን ከማብረራቸው ከብዙ መቶ ዓመት በፊት አንድ የግሪክ ደራሲ በልቦለድ መልክ ጽፎት ነበር። በሃሳቡም፤ የሆነ በሰማይ ላይ እንደ አሞራ የሚበር ነገር እንደሚኖር አድርጎ ይናገራል። «የትኛውም ቴክኖሎጂ የሚጀመረው ከሃሳብ ፈጠራ ነው» ያሉት ዶክተር አብይ፤ ኪነ ጥበብ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ጀማሪ እንደሆነ ገልጸው ነበር።
የመቶ አለቃ ግርማ መጽሐፍም የሚነግረን ይሄንኑ ነው። አውሮፕላን ከመሰራቱ በፊት ሰዎች ከቀላል ቁሳቁስ በአሞራ ቅርጽ እየሰሩ ወደ ሰማይ ይወረወሩ ነበር፤ በንፋስ ኃይል በአየር ላይ በሚያደርገው ቆይታም ይመራመራሉ።
የመጠየቅ እና የመገረምን ጥበብ ይነግረናል። መገረም የጥበበኞች ተሰጥዖ ነው፤ መጠየቅና ማስተዋል የብልሆች ነው። አውሮፕላን አይቶ የማያውቅ ሰው ሲገረም ብናይ እንስቅበት ይሆናል (በእኛ ቤት አራዳ መሆናችን ነው) አይተነው በማናውቀው ነገር መገረም ብዙ ጊዜ «ፋራነት» እየመሰለን ልብ ብለን እንኳን አናየውም፤ ለጥበበኞች ግን ይሄ ቦታ የለውም።
በ«አየርና ሰው» መጽሐፍ ውስጥ አንድ እያሳዘነም ቢሆን የሚያስቀን ነገር አለ። በአየር ላይ በሚበሩ አሞራዎች የሚገረሙ ሰዎች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ሁልጊዜም ራሳቸውን ይጠይቃሉ፤ «እኛ መብረር አንችልም! እንዴት ነው ታዲያ እነዚህ አሞራዎች እንዲህ የሚበሩት?» እያሉ ይጠይቃሉ። ልብ ብለው ሲያዩም አሞራዎች ግራና ቀኝ የተዘረጋ ነገር (ክንፍ) አላቸው። «ይሄ ይሆን እንዴ እንዲበሩ የሚያደርጋቸው?» ብለው ጠየቁ። ይሄ ከሆነማ ነገሩ ቀላል ነው ብለው ከጎናቸው ክንፍ የመሰለ ነገር እየቀጠሉ ከከፍታ ቦታ ላይ መዝለል ጀመሩ። ነገሩ ግን እንዳሰቡት ሳይሆን እየወረዱ መፈጥፈጥ ሆነ።
እኛ ስናስበው «ምን ጅሎች ናቸው!» ብለን ይሆናል፤ ዳሩ ግን ይሄ ቴክኖሎጂ በእነዚህ ሰዎች መስዋዕትነት የተገኘ ነው። በእነዚህ ሰዎች መፈጥፈጥ የሰው ልጅ መብረር እንደማይችል ተረጋገጠ። የሰው ልጅ በራሱ መብረር ካልቻለ ታዲያ ምን ይሻለዋል? ብለው ጠየቁ። ከዚያም ልክ እንደ አሞራ የሚበር ቁስ አካል መሥራት እንዳለባቸው አመኑ፤ ተመኝተውም አልቀሩም አደረጉት!
የአውሮፕላን እንቅስቃሴ ከአየር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ነው። የመጽሐፉ ደራሲ እንደሚነግሩን ይህ ጥበብ የተገኘው ከአሞራና ከሌሎች በራሪ አዕዋፋት ልምድ በመውሰድ ነው። ያ አሞራዎችና ሌሎች በራሪ አዕዋፋት ያደርጉታል የተባለው ነገር ግን ሳይንሳዊ ጥናት ቢጠይቅም በማስተዋል ብቻ እርግጠኛ ለመሆን ይከብዳል። እርሳቸው እንደሚሉት የበራሪ አዕዋፋት ልምድ እንዲህ ነው።
ሁልጊዜም የሚበሩት በንፋስ ኃይል በመታገዝ ነው። የሚበሩትም የነፋሱን አቅጣጫ ተከትለው ነው። ለምሳሌ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ከነፈሰ በረራቸውም ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ይሆናል ማለት ነው። ሰውም ይሁን ሌላ የሚተናኮላቸው አካል ለመብረር በሚያመችባቸው አቅጣጫ ቢመጣ እንኳን ወደ አጠገቡ ይበራሉ እንጂ በሚመጣበት ተቃራኒ አቅጣጫ አይበሩም። የሚበሩትም ትንሽ በእግር በማኮብኮብ ነው። የሚተናኮላቸው አካል ቢመጣ እንኳን ወደአጠገቡ(በሚበሩበት ከመጣ) በእግር ካኮበኮቡ በኋላ ነው የሚበሩት።
ምናልባት ደራሲው በጥናት የደረሱበት ሊሆን ቢችልም ይሄን የአዕዋፋት እንቅስቃሴ ማመን ግን ይከብዳል። ምክንያቱም ሁልጊዜም የነፋስን አቅጣጫ ብቻ ተከትለው አይደለም የሚበሩት። በቀላሉ በመንገድ ላይ የምናገኛቸውን ወፎች ማስተዋል እንችላለን። ልክ ገና እንዳዩን በቀጥታ መብረር ይችላሉ፤ ምናልባት ግን የሚበሩት አጭር ርቀት ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል እኛ የምናገኛቸው ቀላል ያሉት ወፎች ስለሆኑ የአሞራዎችን ልብ ብሎ ማየት ይጠይቃልና ለጊዜው የደራሲውን ሃሳብ እንመን! አሞራዎች እንደዚያ የሚያደርጉ ከሆነ ከአውሮፕላን ማኮብኮብ ጋር ተመሳሳይ ነው ማለት ነው።
መጽሐፉ ከግማሽ በላይ በሚሆኑት ገጾቹ በፎቶ የሚያብራራ ነው። ከተለያዩ አገራት ተሞክሮዎችንና ገጠመኞችንም በጥቂቱ ያስቃኛል።
አስተያየት
መቶ አለቃ ግርማ ወታደር እንደመሆናቸውና አየር ኃይል እንደመስራታቸው መጽሐፉ ስለአየር ኃይሉ አይነገረንም፤ ምናልባት በዚያን ዘመን ከነበረው ሁኔታ ተነስተው ያን ያህል የተደራጀ መረጃ አይኖራቸውም ብለን እንለፈው። ዳሩ ግን መጽሐፉ ተሻሽሎ ለዘመኑ በሚሆን መንገድ መጻፍ ነበረበት። ስለወታደራዊ ተዋጊ አውሮፕላኖች የሚነግረን ነገር የለውም። መጽሐፉ ውስጥ ያለው መረጃ ማንኛውም አየር መንገድ የሚጠቀመው እንጂ በተለየ ሁኔታ ወታደራዊ የጦር አውሮፕላን ላይ የሚያተኩር አይደለም። «አየርና ሰው» እንደመባሉ እና ደራሲውም መቶ አለቃ እንደመሆናቸው ስለጦር አውሮፕላኖች የሚነግረን ነገር መኖር ነበረበት፤ ወይስ የጦር አውሮፕላኖች ከሌላው አውሮፕላን አይለዩም ይሆን?
እንዲህ ዓይነት በአንድ ሙያ ላይ የሚጻፉ መጽሐፎች ከፖለቲካዊና ልቦለድ መጽሐፎች በተለየ መንገድ የዚያን ሙያ ባህሪ ሊነግሩን ይገባል። በዚያ ሙያ ውስጥ ያሉ ሰዎች ወይም ወደዚያ ሙያ መግባት የሚፈልጉ ሰዎች ሊያነቡትና ባህሪውን ሊያውቁበት የሚገባ መሆን አለበት።
የሆነው ሆኖ ግን መጽሐፉ እንኳን በዚያን ዘመን አሁንም ብዙ የሚነግረን ነገር አለው። በአየር ኃይል ላይ የተለየ ትኩረት ባይኖረውም ከዚህ ተነስተው ዝርዝር ባህሪውን ለሚጽፉ መነሻ ይሆናል።
በመጽሐፉ ላይ የዓመተ ምህረት መምታታት ይስተዋላል፤ ይሄ ደግሞ ደራሲው በሕይወት ስለሌሉ አስተካክሎ ለማሳተም እንኳን ያስቸግራል። መጽሐፉ የሚጠቀመው በተለምዶ «የግዕዝ ቁጥር» የሚባለውን ኢትዮጵያዊ ቁጥር ነው። ይህ ቁጥር ደግሞ ብዙ ጊዜ ዓመተ ምህረት ላይ መሳሳትን ያስከትላል፤ ተጠቃሚው በትክክል አያውቀውም፤ በዚያ ላይ መጽሐፉ ላይ ራሱ በትክክል አልተጻፈም። ያ ቁጥር በባህሪው ሙሉውን በቁጥር ብቻ ካልሆነ ከፊደል ጋር እየቀላቀሉ ለመጻፍ አይመችም፤ ምክንያቱም ቁጥሮቹ ራሳቸውን ችለው የሚጻፉ ናቸው። ለምሳሌ አንድ ቦታ ላይ(ገጽ 26) 2500 ሜትር ለማለት ፰፭፡፻ ተብሎ ተጽፏል። ይሄ ቁጥር እንዴት ተብሎ እንደሚነበብ ግራ ያጋባል። ስምንት ቁጥር እና አምስት ቁጥር አንድ ላይ ተጽፈዋል። ከሁለት ነጥብ በኋላ ደግሞ መቶ ቁጥር ተቀምጧል። በቅንፍ ውስጥ 2500 ተቀምጧል።
ብዙ ቦታ እንዲህ በቅንፍ ውስጥ አማራጭ ቢሰጥ ጥሩ ነበር፤ ምናልባት ጊዜና ቦታ ስለሚወስድ አንዱን መጠቀም ተፈልጎ ከሆነ በትክክል መጻፍ ወይም የተለመደውን ዓለም አቀፍ ቁጥር መጠቀም ነው።
እንዲህ በአንድ ሙያ ላይ የሚያተኩሩ መጽሐፎችን ባለቤቶች ሊጽፉልን ይገባል። ይህም ስለዚያ ሙያ ሰዎች እውቀት እንዲኖራቸው ያደርጋል። በሌላ በኩል ደግሞ አንባቢዎች እንዲህ ዓይነት መጽሐፎችን ሊያነቡ ይገባል። ብዙ ጊዜ የተለመደው የፖለቲካ፣ የታሪክና የልቦለድ መጽሐፍ ብቻ ነው። በአንድ ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርገው የተጻፉ መጽሐፎች ሲነበቡም ሆነ ዳሰሳ ሲሰራባቸው አይተዋልምና እኛም ልናነባቸው ይገባል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2011
ዋለልኝ አየለ