በችግኙ መስታወት
ያ እንቶፈንቶ ነገሮችን ሁሉ ሲመዘግብ የነበረው የዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ (ጊነስ ቡክ) ግን ምን ካልሆንኩ ብሎ ነበር በሰዓቱ ያልተገኘው? አናውቀውም እንዴ የምግብ ጉርሻ ውድድር ሲመዘግብ? ታዲያ አሳሳቢ የሆነውን የዓለም የሙቀት መጠን መጨምርን የሚቆጣጠር ችግኝ ተከላ ለእሱ ጉዳይ አይደለም? ግደላችሁም እነዚህ ፈረንጆች በእኛ ላይ ያዳላሉ!
ባሳለፍነው ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ የተደረገው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም የዓለምን ሪከርድ ሰባብሯል። ለዚያውም በስንት እጥፍ ብልጫ እኮ ነው! እንደነ ቢቢሲ ያሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አስገራሚነቱን መስክረዋል። የአገር ስም እንዲህ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሲጠራ ኩራት ነው።
በአንድ ወቅት ከአንድ ጓደኛችን ተነስቶ የተከራከርንበት ሃሳብ ትዝ ይለኛል። ‹‹ኢትዮጵያ በአሸባሪነት ስም እንኳን ብትጠራ ስሟ በመነሳቱ ደስ ይለኛል›› ነበር ያለው። የተከራከርንበት ጉዳይ ይገባችኋል። በዚህ ከምትጠራስ ቢቀር ይሻላል ነበር የአንዳንዶቻችን ሃሳብ። የልጁን ሃሳብ ልብ ብላችሁት ከሆነ፤ በመጥፎ ነገር እንኳን ቢሆን የአገር ስም በዓለም ደረጃ ሲጠራ የሆነ ስሜት ይፈጥራል ማለቱ ነው። እንግዲህ ኢትዮጵያ በእንዲህ ዓይነት በጎ ነገር ስሟ ሲጠራ ደግሞ ደስታውን አስቡት!
ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ታሪካዊ ቀን ነው። የሚጸድቀው ችግኝ ስንትም ይሁን ስንት በአንድ ቀን ብቻ ከ353 ሚሊዮን በላይ መተከሉ ራሱን የቻለ ታሪክ ነው። ሌላው የዚህ ቀን ታሪካዊነት ምን ያህል አገር ወዳድ እንዳለ የታየበት ነው። ነገሮችን ሁሉ ከፖለቲካ ጋር የማያያዝ አባዜ ባለበት ሁኔታ ፖለቲካ አለመሆኑን ህዝቡ አሳይቷል። ማሳያ ይሆናሉ ያልኳቸውን ልጠቃቅስ!
በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉት የመንግሥት ተቋማትና ሠራተኞቻቸው ነበሩ። በመንግሥት የተጠራ ዘመቻ ላይ መገኘትም መንግሥትን እንደመደገፍ ይቆጠር ነበር (ለበጎ ከሆነ ቢደግፍ ምን ችግር አለው? የሚለው እንዳለ ሆኖ) በችግኝ ተከላው ቀን ግን ይህ አልነበረም። በይፋ መንግሥትን የሚቃወሙ አካላት ችግኝ ተክለዋል፤ የመንግሥትን ሕጸጽ ሲዘግቡ የነበሩ የግል መገናኛ ብዙኃን ሠራተኞች በዕለቱ በልዩ ዝግጅት ሲዘግቡና ችግኝም ሲተክሉ ነበር።
እስኪ እናስበው! ችግኝ መትከል ከፖለቲካ ጋር ምን ያገናኘዋል? ለምሳሌ አሁን ያለው ኢህአዴግ በምርጫ ተሸንፎም ይሁን ራሱ በቃኝ ብሎ ሌላ መንግሥት መጣ እንበል፤ ያ የሚመጣው መንግሥትም ያገለገለውን ያህል አገልግሎ ይሄዳል። በእነዚህ ሁሉ መሃል የአየር ንብረቱ የሚጠቅመው ለማን ነው? ራሱ ኢህአዴግም ቢሆን በምርጫ አሸንፎ በሥልጣን ላይ ቢቆይ ይሄ ችግኝ ለማን ነው የሚጠቅምው? እንግዲህ ህዝቡ ይሄ ሁሉ ገብቶታል ማለት ነው። የችግኝ ተከላው ቀን እንደ መስታወት ሆኖ አሳይቶናል።
ዳሩ ግን ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካ ነፃ ነበር ማለትም አይቻልም። ከዚህም ከዚያም ክርክሮች ነበሩ። ከለውጡ በፊት ተቃዋሚ የነበረ የአንድ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ በፌስቡክ ገጹ ‹‹ኢትዮጵያ በችግኝ ተከላ ክብረወሰን መስበሯ ምነው አናደዳችሁ?›› ብሎ ጽፎ ነበር። ከተሰጡት አስተያየቶች አንደኛው ‹‹አንተስ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስትቃወም የነበረው ለምን ነበር?›› የሚል ነው። ጸሐፊው ለዚህ አስተያየት ሰጪ የሰጠው ግብረመልስ፤ ችግኝ ተከላ ከህዳሴው ግድብ ጋር መነጻጸር እንደሌለበት ነው። ምክንያት ያደረገውም ችግኝ ተከላው ቀላል ፕሮጀክት ነው፣ ከፍተኛ ወጪ አይጠይቅም፤ ከጎረቤት አገራት ጋር ፖለቲካዊ ጣጣ የለውም የሚል ነው።
እርግጥ ነው የህዳሴው ግድብ ትልቅ ፕሮጀክት ነው፤ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል፤ ከጎረቤት አገራት ጋርም ፖለቲካዊ ጉዳይ አለበት። ግን ይሄ ከለውጡ በፊት ተቃዋሚ የነበረ ጋዜጠኛ የህዳሴውን ግድብ መቃወም ነበረበት? እንዲያ ከሆነማ እኮ አሁን ችግኝ ተከላውን ያላመሰገኑ ሰዎችም ምክንያት የሚሉት አላቸው። ከችግኝ በላይ አንገብጋቢ ጉዳይ አለ፤ ሰው እየተፈናቀለ ነው፤ ግጭቶች እየበረከቱ ነው፣ መጀመሪያ ሰላም ይስፈን ነው እያሉ ያሉት። የእነርሱ ምክንያት አሳማኝ እንዳልሆነ ሁሉ የእሱም አሳማኝ አይሆንም። ችግኝ መትከል መንግሥትንም ሆነ ህዝብን ሥራ የሚያስፈታ አይደለም (ሲጀመር በራሱ ትልቅ ሥራ ነው)፣ ችግኝ መትከል ክረምት በመጣ ቁጥር መደበኛ ሥራ ነው። የህዳሴው ግድብም ከመንግሥት በላይ የህዝብ ነው!
ሁለቱም የተከራከሩት ፖለቲካዊ ትርጉም ሰጥተውት እንጂ የህዳሴው ግድብም ሆነ ችግኙ የህዝብ ነው (እርግጥ ነው ግድቡ ፖለቲካዊ ይዘትም አለው)። እነዚህን ሰዎች እንደ ምሳሌ አነሳሁ እንጂ በዚህ መንገድ ሲነታረኩ የነበሩ ብዙ ናቸው። ከለውጡ በፊት ተቃዋሚ የነበረ ሰው ያ የሚጠላው አካል ስለሌለ ብቻ የግድ የሆነውን ሁሉ መደገፍ ሚዛናዊነት አይደለም። ከለውጡ በፊት የነበረውን አስተዳደር የሚደግፍም የግድ አሁን የሚደረገውን ሁሉ መቃወም ሚዛናዊነት አይደለም። ሁሉም በምክንያት ሲሆን ነው የሚያምር።
እንዲህ ዓይነት የጋራ ጉዳዮችና አሳታፊ ሥራዎች እንኳን ሲኖሩ ምናለ የራሳችንን ስሜት ባናራምድ? ለማንኛውም አገራችን በችግኝ ተከላ የዓለምን ክብረወሰን መስበሯ ለማንም ኩራት ነው!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2011
ዋለልኝ አየለ