ልጅነትን ሰራቂው በደል

ልጅነት መቦረቅ ፣ ነጻነት እና ከሁሉም ጋር መተባበርን የሚወድ ነው። ልጆች በልጅነታቸው ሁሉም ሰው የሚወዳቸው ፣ ያያቸው ሁሉ ሊያቅፋቸው ሊስማቸው የሚያጓጉ ናቸው። ምህረት ለወላጆቿ የመጨረሻ ልጅ እንደመሆኗ በቤት ውስጥ ባሉ ሁለት ታላላቅ ወንድሞቿም ሆኑ በአክስትና አጎቶቿ እጅግ ተወዳጅ ናት። ምህረት ሁሉም ሰው የሚጠራት እሷም እንደ ልጅነቷ ለሁሉም ሰው የምትታዘዝ እና ከጓደኞቿ ጋር መጫወት አብዝታ የምትወድ ናት።

ምህረት እና ወንድሞቿ ናትናኤልና ታሪኩ በመሃከላቸው ምንም እንኳን የአራት ዓመት ያክል ልዩነት ያለ ቢሆንም ያላቸው የእርስ በእርስ ቅርበት እና ፍቅር ግን እኩያ ያስመስላቸዋል። የእነ ምህረት አባት አቶ ንጉሤ ምህረት የሁለት ዓመት ህጻን ልጅ እያለች ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት። በመሆኑም እናታቸው ወይዘሮ ወርቅነሽ አያሌው ልጆቿን ለማሳደግ እና በትምህርታቸው ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሰው የራሳቸውንም የእሷንም ሕይወት የተሻለ እንዲያደርጉ ትጥራለች። ናትናኤል ከአዲስ አበባ ውጪ በሥራ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሁለቱ ልጆቿ ታሪኩ እና የቤቱ የመጨረሻ ልጇ ምህረት ግን በትምህርት ላይ የሚገኙ ናቸው።

ወይዘሮ ወርቅነሽ ከምትሠራው ትንሽዬ የቡና ጠጡ ሥራ ባሻገር በምትኖርበት ወረዳ በመደራጀት በሴፍቲኔት ፕሮግራም ውስጥ በአካባቢዋ የጽዳት ሥራን ትሠራለች። ታዲያ አብዛኛውን ጊዜ ለሊት 11 ሰዓት ጀምሮ ከቤቷ ወጥታ ሥራዋን ጨርሳ የምትመለሰው አረፋፍዳ ነው። የወርቅነሽ ወንድም ሀብታሙ አያሌው እህቱ ባለቤቷን ካጣች በኋላ የራሱን ሥራ ለመፈለግ እና እሷን ለማገዝ በሚል የቤተሰቡ አባል በመሆን አብሮ መኖር ከጀመረ ከሁለት ዓመት በላይ ሆኖታል።

ድፍረት እና ክህደት

አቶ ሀብታሙ ከእህቱ ጋር መኖር ከጀመረ ጀምሮ ይህ ነው የሚባል የረባ ቋሚ ሥራ የለውም። በመሆኑም አልፎ ከሚሠራው ሥራ ውጪ አብዛኛውን ጊዜውን በወረዳው ባለው ወጣት ማዕከል ውስጥ እና በቤት ውስጥ ያሳልፋል። ታዲያ ሥራ የፈታ አዕምሮ የሰይጣን መጫወቻ ይሆናል እንደተባለው ይህ ሰው ላስጠጋቸው እህቱ ቤተሰባዊነትን በቤት ውስጥ ላሉ ሁለት እህትና ወንድም አጎትነቱን የሚያስተው በፍጹም የማይጠበቅ ባህሪን ከማሰብ አልፎ ማሳየት ጀምሯል።

አብዛኛውን ጊዜ በቤት ውስጥ የሚያሳልፈው ሀብታሙ ጊዜውን ከትንሹ ታሪኩ እና ከፍልቅልቋ ምህረት ጋር ያሳልፋል። ጎረምሳው ታሪኩ ከትምህርት ቤት የተረፈውን ጊዜውን ከጓደኞቹ ጋር በሰፈሩ ውስጥ በመጫወት ያሳልፋል። ምህረትም ብትሆን የራሷ ጓደኞች አሏት ነገር ግን ሰፊ ጊዜዋን በቤት ውስጥ ታሳልፋለች። በዚህ ምክንያት የሀብታሙ ሥራ የፈታ አዕምሮ ህጻኗን ምህረትን ገና 15 ዓመት ልጅ መሆኗን እሱም የእርሷ አጎት መሆኑን ረስቶ በፍትወት ልቡ ይመለከታት ጀመር። ከአንድ ሁለቴም ሊጎነትላት እና በሃይል ሊያስገድዳት ሲሞክር አምልጣ ከቤት ወጥታለች። ነገር ግን ልጅ ናትና ይህንን የትንኮሳ ድርጊት ደፍራ ለሰው መናገር አልቻለችም ።

እናት ወርቅነሽ የልጆቿን ሕይወት ለማቃናት እና የሚያስፈልጋቸውን ለማሟላት ከጠዋት አንስታ ጸሀይ እስከምትጠልቅበት ሰዓት ድረስ የምትለፋ ናትና ይህንን መገመት አልቻለችም። ይህ ደፋር ሰውም በእህቱ ፊት የአጎትነት እና የወንድምነት ባህሪውና ምህረትን ለብቻዋ ሲያገኛት የሚያሳየው የአውሬነት ባህሪ ፍጹም የማይተዋወቁ ናቸው ።

ማንነት ሲገለጥ

የክረምትን መግባት አስመልክቶ እለቱ የጀመረው መጣሁ መጣሁ በሚል የነጓድጓድ ድምጽና ጥቂት ካፍያ ነው። በመሆኑም ወርቅነሽ በጠዋት እየመጣ ያለው ዝናብ ሳይበግራት እለት ሥራዋን ለማከናወን ተነሳች። የሥራ ልብሷን ለብሳ አብረዋት የሚተኙ ልጆች ሲነሱ የሚመመገቡት አዘጋጅታ እና በተኙበት ብርድ እንይነካቸው ተጨማሪ ልብስ አልብሳ ፤ ወንድሟን ከወጣች በኋላ በሩን እንዲዘጋው በማሳሰብ ወደ ሥራዋ ሄደች።

ታዲያ በዚህ ጊዜ ሥራ በፈታ አዕምሮው የነገሰው ሥርዓት አልበኝነት እና ከሰው የወጣው ሥብዕናው ህሊናው ውስጥ መመላለስ ጀመረ። በዚያ ውድቅት እና ማንም ሰው በማይደርስበት ሰዓትም ትንሿን ምህረትን በማስፈራራት እና በማፈን ከተኛችበት ክፍል አንስቶ ድምጽ እንዳታወጣ በማስጠንቀቅ እርሱ በሚያድርበት ክፍል ውስጥ አስገድዶ ደፈራት።

ይህ ለትንሿ እና ፍልቅልቋ ምህረት እንዲህ ነው ብላ መግለጽ የማትችለው ዱብዕዳ ሆነባት። ህመሟን መሸከም ባትችልም ለሰው እንዳትናገረው እንኳን ይህ አውሬ ለአንድ ሰው እንኳ ትንፍሽ እንዳትል አስፈራርቷታል።

መሀሪ ያጣ ህመም

ምህረት ለመጀመሪያ ጊዜ በልጅነት አዕምሮዋ ልትቋቋመው የማትችለው በደል እና ሰውነት ቁስል ደርሶባታል። ይህ የአጎትነት ማዕረጉን በገዛ ፍቃዱ ያወለቀው የሰውነት ባህሪ የራቀው ግለሰብ ይህንን ድርጊቱን በተደጋጋሚ መፈጸሙን ቀጥሏል። ምህረትም ይህንን የምትነግረው ሰው አጥታለች ፤ በመሆኑም ይህ ስቃዩዋን በየእለቱ የምትጋፈጠው ሆኗል። አንድን የ16 ዓመት ህጻን ልጅ በዚህ ስቃይ ውስጥ ማሰብ እጅጉን ከባድ ሲሆን ይህ ነውር እና ድፍረት የተጠናወተው እና ህሊናውን ትቶ ራሱን ለስሜቱ ያስገዛ ሰው አስገድዶ መድፈር ከፈጸመባት በኋላ የእርግዝና መከላከያ መድሃኒት በግድ እንድትውጥ ያደርጋታል። ይህንን ድርጊቱን ለአንድ አመት ከሰባት ወራት ሲፈጽም ያለምንም ድፍረት የእህቱን ከቤት መውጣት የአካባቢውን ጭር ማለት እንደ ጥሩ አጋጣሚ ሲጠቀምበትም ቆይቷል።

በቃ የተባለ ሞት

ምህረት ገና የ15 ዓመት ልጅ ብቻም ሳትሆን በብዙዎች ዓይን ውስጥ የምትገባና ጨዋታ የምትወድ ናት። በሰፈር ውስጥም ሆነ በትምህርት ቤት ውስጥ ከጓደኞቿ ጋር ስትጫወት ራሷን አታውቅም። ይህ ፍልቅልቅነቷ እና ተጫዋጭነቷ ግን አሁን ላይ ደብዝዟል። ለብቻዋ መሆንን ትምህርት ቤት እረፍት በሚሆንበት ሰዓት ክፍል ውስጥ መቀመጥን አብዝታለች። ጊዜው በሄደ ቁጥርም ወደቤቷ መሄድን ጠልታለች። ለእናቷንም በምን መልኩ እንደምትነግራት ስታወጣ እና ስታወርድ በሃሳብ ስትዋልል ቆይታለች። ታዲያ አንድ ቀን ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ እናት ወርቅነሽ ሥራዋን አጠናቃ ወደ ቤቷ ስትመለስ በቤት ውስጥ ወንድሟና ልጇ ታሪኩን ብቻ አገኘቻቸው። ምህረት የት ነች የሚለውን ግን የሚያውቅም ሆነ የሚመልስ ግን አልነበረም ።

በጎረቤት ትኖር ይሆን የሚል ግምት ያስቀመጠችው እናት በቅርቧ ካሉ ጎረቤቶቿ ቤት ብትፈልጋትም አላገኘቻትም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆና ቤት ውስጥ መቀመጥ አልሆነላትም። ጭንቀቷ እየበረታ ሄደ ፤ በቅርቧ ያሉ ሰዎችም አንድ በአንድ ይሰበሰቡ ጀመር። በድንገት ግን አጎት ነኝ ያለው ሰው እንደደመደንገጥ ብሎ ከአካባቢው ተሰወረ።

እናትም ከሰዓታት ጭንቀት በኋላ ልጇን በጨለማ ውስጥ ብቻዋን ስትመጣ አገኘቻት። እናት ዓይኗን ባለማመን የት እንደቆየች ልጇን ለመቆጣት ብትፈጥንም ፤ በልጇ ፊት ላይ ግን ግልጽ የሆነ ፍርሃት ይነበብ ነበር። ትንሿ ምህረት ከቀናት በፊት እየተሰማት ያለውን እንግዳ ህመም እና ከአንድ ዓመት በላይ የተሸከመችውን ስቃይ መደበቅ አልቻለችም። እናት ይህች የምትሳሳላት እና በየቀኑ የምትደክምላት ልጇን የምታሳልፈውን ስቃይ ስትመለከት ራሷን መቆጣጠር አቅቷት ወደቀች። ሰዓቱ ወደ ምሽት 4፡00 ሰዓት እየተጠጋ በመምጣቱ ሁኔታውን ለመከታተል በቦታው የነበረው ፖሊስም እና ጎረቤቶቿ እንድትረጋጋ ካደረጉ በኋላ ጉዳዩን ለማጣራት አስቀድሞ ወደ አቅራቢያው የሚገኝ ሆስፒታል አመራ።

ሆስፒታሉም ህጻን ምህረት ነፍሰጡር ናት ሲል አረጋገጠ። ፖሊስ ቀጣይ ሥራው ያደረገው የህጻኗን ቃል መቀበል ሲሆን ፤ ቀጣዩ ሥራው ደግሞ ለቤተሰቡ ከለላ በመስጠት ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ማዋል ነበር።

ወንጀል ሲገለጥ

ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ኪንባ ሠፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ሲሆን በ1996 ዓ/ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 626/4/ሀ/ እና 628/ሀ/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰች ልጅ ላይ በፈጸመው የግብረ ስጋ ድፍረት ወንጀል ተከሶ ፍ/ቤት እንዲቀርብ ተደርጓል።

ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ እንዳስረዳው የግል ተበዳይ 15 ዓመት የምትሆን እና ከተከሳሽ ጋር በአንድ ቤት ውስጥ አብራ የምትኖር ስትሆን ተከሳሽ ቀኑ ባልታወቀ ሰኔ ወር 2014 ዓ/ም በመኖርያ ቤት ውስጥ በተደጋጋሚ የግብረስጋ ግንኙነት በመፈፀም ተበዳይዋን ለእርግዝና የዳረገ መሆኑ እና ቀኑ ባልታወቀ ግንቦት ወር 2014 ዓ/ም ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት እስከ 4፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ በመኖሪያ ውስጥ በተደጋጋሚ በማስፈራራት እና በማስገደድ የግብረ ስጋ ግንኙነት ፈጽሞባታል። ተከሳሽ በተበዳይ ላይ በፈጸመው የግብረ ስጋ ድፍረት በደል ወንጀል የፈፀመባት በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበታል።

ዐቃቤ ሕግ የተከሳሽን ጥፋተኝነት ያስረዳሉ ያላቸውን 2(ሁለት) የሰው ምስክሮችን እና 2 (ሁለት) የህክምና የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ የተከራከረ ሲሆን ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ቢሰጥም ተከሳሽ ያቀረበው የመከላከያ ምስክር ጥፋቱን ያላስተባበለ በመሆኑ ፍ/ቤቱ ተከሳሹን ጥፋተኛ ነው ብሎታል።

ውሳኔ

በመጨረሻም የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት ህዳር 12 ቀን 2016 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተከሳሹን በስምንት (8)ዓመት ፅኑ እስራት እና ከሕዝባዊ መብቱ ለ2 (ሁለት ዓመት) ተገድቦ እንዲቆይ በማለት ወስኖበታል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You