
የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ በሰፊው እየተሠራ ነው። ይህን ተከትሎም ምርትና ምርታማነቱ በየዓመቱ እየጨመረ ይገኛል። አርሶ አደሩ ከዚህ ምርትና ምርታማነቱ በአግባቡ ተጠቃሚ መሆን ይኖርበታል።
ይሁንና አርሶ አደሩ ለምርቱ ተገቢውን ዋጋ እያገኘ ካለመሆኑ ጋር በተያያዘ ከእርሱ ይልቅ ደላሎች ተጠቃሚ ሲሆኑ ኖረዋል። በምርት ወቅት ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት ሲል አቆይቶ ቢሸጠው በጥሩ ዋጋ ሊሸጠው የሚችለውን ምርት በርካሽ ሲሸጥ ኖሯል።
ከቅርብ ጊዜ ይህን የአርሶ አደሩን ችግር የሚፈታ አሠራር ተዘርግቶ እየተሠራ ይገኛል። ይህ ‹‹ የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ብድር አገልግሎት›› በመባል የሚታወቅ አርሶ አደሩ ምርቱን አስይዞ የፋይናንስ ብድር አገልግሎት ማግኘት የሚችልበት አሠራር ሥራ ላይ ከዋለ ቆይቷል፤ ይህን ሥራ ማስፋት የሚያስችል ፕሮጀክት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያስጀመረው ይህ ፕሮጀክት የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ አገልግሎትን ለማጠናከርና ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑ ታምኖበታል። አርሶ አደሩ ምርቱን በማስያዣነት በማቅረብ ብድር የሚያገኝበት ሥርዓት ሲሆን፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚያስፈልገውን ገንዘብ ምርቱን ሳይሸጥ በማስያዣነት በመጠቀም ብቻ ብድር ማግኘት ያስችለዋል። የገበያ ዋጋው ሲስተካከል ምርቱን መሸጥ የሚችልበትን ሁኔታ ያመቻቸ ሥርዓት በመሆኑ የአርሶ አደሮችን ጫና ይቀንሳል።
መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 372/1996 ከወጣ 20 ዓመታት ተቆጥረዋል። የመጋዘን አገልግሎት የንግድ የሥራ ዘርፍ ሆኖ ወደ ትግበራ እንዲገባ የተደረገው ግን በ2014 ዓ.ም ነው።
አስፈላጊውን መዋቅራዊ አደረጃጀት በመፍጠር ምርት ሰብስቦ ለብድር ማስያዣነት መጠቀም የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ባለፉት አምስት ዓመታት በተደረገ ትግበራ ውጤት መታየቱን መረጃዎቹ ይጠቁማሉ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም ይህን የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ አገልግሎት ሥርዓትን ለማጠናከር እና አሠራሩን በሀገር አቀፍ ደረጃ የበለጠ ለማስፋፋት ያግዛል ያለውን ፕሮጀክት ነው ሰሞኑን ይፋ ያደረገው።
ይፋ የተደረገው መርሃ ግብሩ ለሁለት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፤ የወጪ ንግድን ለማሳለጥ፣ የምርቶችን ጥራት ለማስጠበቅ እንዲሁም የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓትን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ታምኖበታል።
መርሃ ግብሩን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ “ቅንጅት ለአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት” (አግራ) ፕሮጀክትና የኢንተርናሽናል ፋይናንሽያል ኮርፖሬሽን በጋራ ተግባራዊ የሚያደርጉት ነው።
በሁለት ዓመታት ትግበራው 150 ሺ አርሶ አደሮች በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ፣ 12 ሚሊዮን ዶላር ያህል ግብይት ወይም ብድር ይመቻቻል ተብሎ እንደሚታሰብ በይፋዊ መርሃ ግብሩ ላይ ተጠቁሟል።
ፕሮጀክቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ያስሚን ወሀብረቢ በዚህ ወቅት፤ በሀገር ውስጥ ገበያ ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም እንዲሁም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አርሶ አደሩ በብዙ ድካም ያመረተውን የሚያስቀምጥበት በቂ የመጋዘን አገልግሎት እና የፋይናንስ አቅርቦት የሚያገኝበት ሁኔታ ሳይኖረው መቆየቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም ምርቱን በተገኘው ዋጋ ለመሸጥ እየተገደደና በእሴት ሰንሰለቱ ውስጥ የመጨረሻ የምርቱ ተጠቃሚ ከሚከፍለው ዋጋ አርሶ አደሩ የሚያገኘው ድርሻ ዝቅተኛ በመሆኑ ለበለጠ ምርታማነት እንዳይነሳሳ አድርጎት ቆይቷል ብለዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ለወጪ ገበያ የሚቀርብ ጥራቱን የጠበቀ ጥሬ እቃ በጥራት፣ በብዛትና በአይነት ለማቅረብ እና በሀገር ውስጥ ገበያ ፍላጎትና አቅርቦትን ለማመጣጠን የግብይት እሴት ሰንሰለቱን ማዘመን እና የፋይናንስ አቅርቦት ማመቻቸት ላይ እየሠራ መቆየቱን ጠቁመዋል።
ባለፉት ዓመታት የግብርናው ዘርፍ የምግብ እህል ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር ከፍተኛ የገቢ ምንጭ በመሆን ለኤክስፖርት እና ለኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የሚደረገውን መዋቅራዊ ሽግግር በመደገፍና በማሳለጥ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይሁንና በዘርፉ የሚስተዋለው ረጅም የግብይት የዕሴት ሰንሰለት ለምርት ብክነትና ጥራት መጓደል በወጪ ንግድ አፈፃፀም አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድራል። ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ጥሬ እቃ በጥራትና በብዛት ለማግኘት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።
የግብይት ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ ማድረግ ከሚያስችሉ አሠራሮች አንዱ የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት መሆኑን በመረዳት ቀደም ሲል የወጣውን የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥ00ርዓት አዋጅ ቁጥር 372/1996 መነሻ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተፈፃሚ ለማድረግ ሲሠራ ቆይቷል። ለዚህም አስፈላጊ መዋቅራዊ አደረጃጀት በመፍጠር፣ ምርት ሰብል ለብድር ማስያዣነት መጠቀም የሚያስችል አሠራር ሥርዓት መዘርጋቱን አስታውቀዋል።
የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ አገልግሎት ራሱን የቻለ የንግድ የሥራ ዘርፍ ሆኖ እንዲወጣ በማድረግ የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ትግበራ ከገባ አንስቶ ውጤታማ ሥራዎች ተሰርተው ውጤት መመዝገቡንም አስታውቀዋል።
በዚህ መሰረት 141 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰብል ምርት በማስያዣነት ጥቅም ላይ ውሎ አርሶ አደሮች ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊየን ብር በላይ ብድር መውሰድ መቻላቸው ተጠቀሟል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ሥትራቴጂዎችን ቀርፆ በመረባረብ ወቅቱ የሚጠይቀውን የወጪ ንግድ ምጣኔን ማስተካከል፣ የኢንዱስትሪዎችን ጥሬ እቃ ለማሳደግ እንዲሁም የገበያ ፍላጎትና አቅርቦትን ለማመጣጠን እንዲቻል የግብርና ምርቶች አቅርቦትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳለጥ፣ የፋይናንስ አቅርቦት ማመቻቸት እና የግብይት ሥርዓት ማዘመን ያስፈልጋል።
ለሀገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እድገት መፋጠን አስፈላጊ ከሆኑት መንግሥታዊ ካልሆኑ የልማት ድጋፍ ሰጪ አካላት ጋር በትብብርና በቅንጅት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል። መንግሥታዊ ያልሆኑ የልማት አጋር ተቋማት በአዋጅ በተሠጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት መንግሥት ያልደረሰባቸውን ችግሮችን በመለየትና የመፍትሄው አካል በመሆን በሀገሪቱ የኢኮኖሚና ማሕበራዊ እንቅስቃሴ ተሳትፏቸው ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የጎላ ድርሻ እንዳላቸው አመልክተዋል። የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ አገልግሎት ሥራው ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሠራበት አስታውቀዋል።
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ፕሮሞሸን እና የግብይት ማሳለጥ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ በረከት መሠረት በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ፕሮጀክቱ የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ አገልግሎቱ የግብርና ምርቶች በአግባቡ ተቀምጠው በድህረ ምርት ወቅት የሚያጋጥምን ችግር መቀነስን በሚደግፍ መልኩ የተደራጀ ነው።
ፕሮጀክቱን ለጊዜው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ “ቅንጅት ለአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት” (አግራ) እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን በጋራ ሆነው ለሁለት ዓመታት ተግባራዊ ያደርጉታል። በዚህ የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ አግልግሎቱ ዘመናዊ የግብይት ዘዴ ይተገበራል።
በተለመደው መንገድ አርሶ አደሩ ብድር በቀጥታ ከባንክ የሚወስድበት እንዳለ ጠቅሰው፣ በቅድሚያ የአርሶ አደሩ ምርት ጥራት ታይቶ ተገምግሞ መጋዘን ውስጥ እንዲቀመጥ ይደረጋል ይላሉ። አርሶ አደሩ መጋዘን ውስጥ ባስቀመጠው የምርት ልክ ሰርተፊኬት እንደሚሰጠው፣ ደረሰኝም እንደሚቆረጥለት አብራርተዋል። አርሶ አደሩ ያንን ደረሰኝ እንደ ቋሚ ንብረት አስይዞ ብድር እንደሚፈቀድለት ጠቁመዋል።
ይህም መሰረት የሚያደርገው አርሶ አደሩ በእቃ ማከማቻ ደረሰኝ አገልግሎት ውስጥ ባስቀመጠው እህል መጠንና ጥራት ላይ ነው። መጋዘኑ ውስጥ ለማስቀመጥም የተወሰነ ክፍያ ይፈጸማል፤ ተመጣጣኝ የሆነ ወለድም ይኖረዋል።
ለጊዜው እንደማስጀመሪያነትም ስንዴ፣ አኩሪ አተርና በቆሎን ጨምሮ ስድስት የእህል አይነቶች መለየታቸውን ጠቁመዋል። በሂደት እየታየ ሌሎች የግብርና ምርቶች እየተለዩ በአዲሱ የዕቃ ማከማቻ ብድር አገልግሎቱ እንደሚካተቱ አመላክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ ለሁለት ዓመታት ይተገበራል፤ በዚህም እስከ 15 የሚደርሱ ባንኮች እንዲሳተፉ ይደረጋል፤ እስከ 45 ሺህ ቶን የሚደርሱ ምርቶችም በአገልግሎቱ ጥቅም ላይ ይውላሉ። ምርቶቹም በወቅቱ የገበያ ዋጋ መሰረት ብድር ማግኘት የሚችሉበት አሰራርም ይፈጠራል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መርጊያ ባይሳ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ አገልግሎት በአዋጅ ደረጃ በኢትዮጵያ የወጣው ከ20 ዓመት በፊት በ1996 ዓ.ም ነው። አዋጁ ከወጣ ረጅም ጊዜ ቢሆነውም በአገልግሎት ላይ የዋለው ግን በቅርቡ ነው። በተለይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ኃላፊነቱን ወስዶ ወደ ትግበራ ከገባ በኋላ የሙከራ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ ምርት ገበያም እንደ አንድ የመጋዘን ኦፕሬተር ሆኖ እየሠራ ቆይቷል።
በተለይ የፋይናንስ አካታችነት እድሉ የሌላቸው የአርሶ አደሮች የሕብረት ሥራ ማሕበራት፣ ዩኒየኖች እና በሀገር ውስጥ እሴት መጨመር ላይ የተሰማሩ አቀናባሪዎች የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሆነው የሚሠሩበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል።
ከዚህ አንፃር ምርት ገበያው ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት በግንዛቤ ፈጠራ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ሰርቷል። በተለያዩ መጋዘኖች በመገኘትም ተጠቃሚዎችን በማሰልጠን እና ግንዛቤ በመፍጠር ሌሎችም ወደ ተጠቃሚነት እንዲመጡ አስችሏል።
ይህም ካለው አቅም በሀገሪቷ በስፋት ከሚመረተው ምርት እና ከአርሶ አደሮቿ የፋይናንስ ተደራሽ አለመሆን አኳያ ገና ጅምር ሥራ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል። በዚህ ላይ እጅግ ገና ብዙ መሠራት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ከአግራ፣ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ትብብር እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋራ የተጀመረው ይህ ፕሮግራም ፕሮግራሙን በማስፋት ለአርሶአደሩ ግንዛቤ በመፍጠር አርሶ አደሩን የፋይናንስ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ነው። እንደ ተቋምም እንደ ኦፕሬተርም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በዚህ ላይ ተሳትፎ በማድረግ አገልግሎቱን ይበልጥ ለማስፋፋት ያስችለዋል የሚል እምነት እንዳላቸው አስገንዝበዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የፋይናንስ ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑ አካላትን ከመደገፍ አኳያ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ወደ ኢትዮጵያ የምርት ገበያ መጋዘኖች መምጣት አይጠበቅባቸውም። ምክንያቱም በሶስተኛ ወገን የመጋዘን ኦፕሬሽን አገልግሎት መሰረት በተለይ በሕብረት ሥራ ማሕበራት፣ አቀናባሪዎች እና ዩኒየኖች በራሳቸው መጋዘን ውስጥ ምርታቸውን ካከማቹ በኋላ ማኔጅመንቱን ብቻ በመረከብ ገንዘብ ለአጭር ጊዜ ተበድረው ሊጠቀሙ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በዚህ ላይ ግንዛቤው በሰፊው እንደሌለ ጠቅሰው፣ ይህን ግንዛቤ በስልጠና በመፍጠር በኩል ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ትብብር ጋር በመተባበር በርካታ መድረኮች መፈጠራቸውን አስታውቀዋል። ከዚህ አኳያም በባሌ፣ በወለጋ፣ በነቀምት፣ በባሕርዳር፣ በጅማ በርካታ ቦታዎች ላይ በመገኘት ግንዛቤ ለመፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል። ይሄንንም ወደፊት በሚገባ አጠናከሮ በመቀጠል በተለይ አርሶአደሩን እና ሕብረት ሥራ ማሕበራት የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች አመላክተዋል።
የግብይት ሥርዓቱን ማዘመን ከሚያስችሉ አሠራሮች አንዱ የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ ያስሚን፣ ይህም የግሉን ዘርፍ ጨምሮ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ሲተገበር መቆየቱንም ገልጸዋል::
በዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርአት ከ2014 ጀምሮ በተደረገው ትግበራ ውጤት እንደታየበት ጠቅሰው፣ በዚህም 553ሺ160 ኩንታል እህል በማሲያዢያነት በመጠቀም 141 አርሶ አደሮች ሁለት ነጥብ ሁለት (2.2) ቢሊዮን ብር ብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል::
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም