
በጎ ፈቃደኝነት የግለሰቦችን እና የህብረተሰብ ክፍሎችን ሕይወት ለማሻሻል በጣም ወሳኝ ከሆኑ መንገዶች አንዱ ነው። በጎ ፈቃደኝነት ምንም አይነት ክፍያን ሳይጠብቅ ሌሎችን ለመርዳት ጊዜን፣ ጉልበትን ወይም ችሎታን መስጠት ማለት ነው። በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በየዓመቱ በፈቃደኝነት ይሳተፋሉ። ጎዳናዎችን ያጸዳሉ፣ ልጆችን ያስተምራሉ፣ የታመሙትን ይረዳሉ፣ አካባቢን ይጠብቃሉ እንዲሁም አቅመ ደካማ አረጋውያንን ይደግፋሉ።
የበጎ ፈቃደኝነት ጥቅም ግን ርዳታና ድጋፉን ለሚያገኙ ብቻ አይደለም። አገልግሎቱን ለሚሰጡትም ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ መሣሪያ ነው። በሕይወት ውስጥ የበጎ ፈቃደኝነት በጣም አስፈላጊ ከሆኑት የመተሳሰብ እና የመደጋገፍ መንገድ ውስጥ አንዱ ነው።
በጎ ፈቃደኞች ለሰው ልጆች ርህራሄ ያላቸው ናቸው። ርህራሄ የሌሎችን ችግር የመረዳት እና የመስማት ችሎታ ነው። ከራሳችን አልፈን ዓለምን በሌላ ሰው ዓይን ማየት ነው፤ ማዳመጥ፣ መተሳሰብ እና ትስስር መፍጠር ማለት ነው። በዚህ በያዝነው በፍጥነት በሚቀያየር ዓለም ውስጥ ርህራሄ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ግጭት፣ መከፋፈል እና መገለል ይህን መሰል የሰው ልጆች መተሳሰብን የሚጠይቅ ነው። ብዙውን ጊዜ ሰዎች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በቋንቋ ወይም በሀብት ምክንያት ይከፋፈላሉ። ለዚህ ነው ርህራሄ እነዚህን ግድግዳዎች ሊሰብር ይችላል የሚባለው። ሰዎች በሰላም እንዲኖሩ፣ እንዲተባበሩ እና እርስ በርስ እንዲተሳሰቡ መሰል እሴቶች ያስፈልጋሉ።
የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በበጎ ፈቃደኝነት የሚሠማሩ ሰዎች በማህበረሰቡ መካከል የርህራሄ ስሜትን የመፍጠር እድላቸው ሰፊ ነው። የአሜሪካ የሥነ-ልቦና ማህበር መረጃ እንደሚጠቁመው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለነገሮች የሚኖረንን እውቀትና ሠብዓዊነትን ይጨምራል። በበጎ ፍቃደኝነት የሚሰማሩ ሰዎች የሌሎችን ፍላጎት የበለጠ መረዳት ይችላሉ። የሰዎችን ስሜት ለማዳመጥ እና በጥንቃቄ ምላሽ ለመስጠት የተሻሉ ናቸው።
በተባበሩት መንግሥታት በጎ ፈቃደኞች (UNV) ፕሮግራም የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው የበጎ ፈቃደኝነት ማህበራዊ ትስስርን ይፈጥራል። ይህ ማለት በበጎ ፈቃደኝነት የሚሠሩ ሰዎች በሌሎች ላይ እምነት መጣል እና ከተለያየ ባህልና አስተዳደግ ከወጡ ሰዎች ጋር ተግባብተው መሥራት የሚችሉ ናቸው። ሪፖርቱ እንደሚጠቁመው በጎ ፈቃደኝነት ማበረታታት መቻቻልን ለማምጣት፣ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ የሆነ ማህበረሰብ ለመፍጠር እድል ይሰጣል።
እ.ኤ.አ. በ 2021 «ጉርምስና» በሚል ርዕስ በሚታተም አንድ ጆርናል ላይ የወጣ አንድ ጥናት በስድስት ሀገሮች ውስጥ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ላይ በማተኮር ዝርዝር ውጤት ይፋ አድርጎ ነበር። በዚህም በበጎ ፈቃደኝነት አዘውትረው የሚሣተፉ ወጣቶች ለሠብዓዊነት ከፍ ያለ የርህራሄ ደረጃ እና ለሕብረተሰቡ የበለጠ ኃላፊነት እንደሚሰማቸው አረጋግጧል። በተለይ ወጣቶች በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲኖራቸው እና ከሰዎች ጋር በአክብሮት እንዲኖሩ እንደሚረዳቸውም ጥናቱ አመልክቷል።
በዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማህበራት (IFRC) የሚመራው ሌላ ዓለም አቀፍ የምርምር ፕሮጀክት ተመሳሳይ ውጤቶችን አሳይቷል። የማህበራቱ በጎ ፈቃደኞች የተሻለ የአእምሮ ጤንነት፣ ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር እና ስለሰው ልጅ ስቃይ ጥልቅ ግንዛቤ እንዳላቸው ተናግረዋል። እነዚህ ግኝቶች ርህራሄ የውስጥ ስሜት ብቻ እንዳልሆነ ይልቁኑ በተግባር የሚገለጥ ችሎታ መሆኑን አስመስክረዋል።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ጥናት ተመራማሪዎች በየሳምንቱ በበጎ ፈቃደኝነት የሚሠሩ ሰዎች 16 በመቶ የበለጠ የርህራሄና የሠብዓዊነት ስሜት ያላቸው መሆኑን አረጋግጧል። ጥናቱ ስለ መጪው ጊዜም በጎ ፍቃደኞች የበለጠ ተስፋ እንዳላቸው አመላክቷል። በጎ ፈቃደኝነት ለእነዚህ ሰዎች የመኖር ትርጉም፣ የዓላማና ቀና ስሜት እንዲኖራቸው ማድረጉን ይናገራል።
በርከት ያሉ በዓለማችን ላይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በተለይም በዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ እና አውሮፓ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በትምህርት ሥርዓታቸው ማካተት ጀምረዋል። በጎ ፈቃደኝነትን እንደ አንድ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎችን ማፍራት የሚቻልበት መንገድ አድርገው ይመለከቱታል። ለምሳሌ ፊንላንድ ውስጥ ተማሪዎች በማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሳተፉ ይበረታታሉ። በውጤቱም ተማሪዎችን በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የበለጠ ግንዛቤ እንዲኖራቸው አድርጓል።
በጃፓን በመንግሥት የሚደገፈው “በጎ ፈቃደኝነት ለነገ” የተሰኘ ፕሮግራም በሺዎች የሚቆጠሩ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በአገልግሎት እንዲሳተፉ ረድቷቸዋል። መንግሥት ፕሮግራሙን የሚቀላቀሉ ተማሪዎች ለደግነት፣ ለፍትሃዊነት እና ለቡድን ሥራ የበለጠ ዋጋ እንዲሰጡ እንደሚያግዛቸው ይገልፃል።
በጎ ፈቃደኝነት በአንዳንድ ሀገሮች እስር ቤቶችም ይተገበራል። በኖርዌይ ውስጥ እስረኞች መልሶ የማቋቋሚያ አካል በመሆን በማህበረሰብ ፕሮግራሞች ላይ በፈቃደኝነት እንዲሠሩ ይፈቀድላቸዋል። ይህ አሠራር በእስር ቤት ውስጥ ያሉ ጥቃቶችን ለመቀነስ እና በእስረኞች መካከል መግባባት እንዲጨምር አድርጓል።
በአፍሪካ በርካታ ሀገራት ውስጥ ወጣቶች ክህሎቶችን እንዲማሩ እና ሠብዓዊ ርህራሄን እንዲያዳብሩ ብሄራዊ የበጎ ፈቃድ ፕሮግራሞች ተግባራዊ ይደረጋሉ። ለምሳሌ በሩዋንዳ መንግሥት ወጣቶችን ወርሃዊ የብሄራዊ አገልግሎት ቀን ተደርጎ የሚቆጠረውን “ኡሙጋንዳ” እንዲቀላቀሉ ያበረታታል። በዚህ ቀን ወጣቶች ጎዳናዎችን ያፀዳሉ፣ የአካባቢ ማህበረሰብን ይደግፋሉ። ይህም በወጣቶቹ ሥነ ልቦና ውስጥ ሀገራዊ ኩራትን፣ አንድነትን እና መተሳሰብን እየገነባ ይገኛል።
በተመሳሳይ የአፍሪካ ህብረት ወጣቶች በጎ ፈቃደኞች ኮርፕስ (AU-YVC) ወጣት አፍሪካውያን በተለያዩ ሀገራት እንዲያገለግሉ ይፈቅዳል። ይህ ወጣቶች በሚኖሩበት ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ስለተለያዩ ባህሎች እና የአኗኗር ዘይቤዎች እንዲገነዘቡ እድል የሚሰጥ ነው። ሠብዓዊነት ከድንበር በላይ መሆኑን እንዲያዩና ከዚህ በፊት ለማያውቋቸው ሰዎች ሠሰብዓዊነት እንዲሰማቸው የማድረግ ትልቅ ሃይል አለው።
በጎ ፈቃደኝነት ከግጭት ወይም ከአደጋ በኋላ አዎንታዊ ሚና መጫወት የሚችል መሣሪያ ነው። እ.ኤ..አ በ2015 በኔፓል ከተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሺዎች የሚቆጠሩ በጎ ፈቃደኞች ተጎጂዎችን ለመርዳት ተሰብስበው ነበር። ብዙዎቹ መደበኛ የአደጋ ጊዜ ሥልጠና ያልወሰዱ ወጣቶች ነበሩ። ነገር ግን ቀና ጥረታቸው በሕይወት ለተረፉት ሰዎች ትልቅ መፅናናትን የፈጠረ ነበር።
በስደተኛ ካምፖች ውስጥ በጎ ፈቃደኞች ትምህርትን፣ ጤናን እና የተጎጂዎችን የአዕምሮ ጤንነት እንክብካቤን ለማድረግ የሚያስችል ትልቅ አቅም አላቸው። በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የስደተኞች ጥናት ማእከል የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በእነዚህ ፕሮግራሞች ውስጥ የሚሳተፉ በጎ ፈቃደኞች ብዙውን ጊዜ ስለ ዓለምአቀፍ ጉዳዮች ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ይኖራቸዋል።
በጎ ፈቃደኝነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋትና ማስተዋወቅ አንዱ ፈተና የሚሆነው ብዙ ሰዎች ለሰው ልጆች የሚሰጠውን ጥቅም አለመረዳታቸው ነው። አንዳንዶች የበጎ አድራጎት ሥራን ጊዜን እንደማባከን ብቻ ይቆጥሩታል። ሌሎች ደግሞ ሀብታሞች ብቻ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ያምናሉ። ዓለም አቀፍ ጥናቶች ግን ይህ ሃሳብ የተሳሳተ መሆኑን ያረጋግጣሉ። በሁሉም እድሜ ክልል፣ የኢኮኖሚ አቅምና ገቢ እንዲሁም የአስተዳደግ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች በበጎ ፈቃደኝነት መሥራት ይችላሉ።
መንግሥታት ወጣቶች ግንዛቤ እንዲኖራቸው የበጎ ፈቃድ እድሎች ላይ እንዲሳተፉ እድል መፍጠር አለባቸው። ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች የበጎ ፈቃድ ፕሮግራሞችን በካሪኩለማቸው በማካተት ትምህርት መስጠት ይኖርባቸዋል። ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች ወጣቶች በበጎ ፍቃድ ለሰዎች የሚያገለግሉበት አስተማማኝና ትርጉም ያለው መንገድ መፍጠር አለባቸው። መገናኛ ብዙሃን የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን ያላቸውን አወንታዊ ጥቅሞች በማስተዋወቅ ማስተማር።
እ.ኤ.አ በ 2022 የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም በጎ ፈቃደኝነት በወጣቶች መካከል መተሳሰብን ለመገንባት የአመራር ክህሎትን ለማዳበር ከሚቻልባቸው መንገዶች ውስጥ እንደ ዋና መንገድ ከተቀመጡ ዝርዝሮች ውስጥ አስፍሮታል።
አሁን የምንኖርበት ዓለም በጎ ፈቃደኝነትን በተሻለ መንገድ ለመፈፀም እድል የሚሰጥ ነው። በተለይ ቴክኖሎጂ በጎ ፈቃደኝነትን ቀላል አድርጎታል። እንደ ቮለንተርማች (VolunteerMatch) ዩኤን ቪ ኦላይን (UNV Online) እና አይዲያሊስት (Idealist) ያሉ የኦንላይን መድረኮች ሰዎች ከቤታቸው ሆነው እንዲሳተፉ አድል እየፈጠሩ ናቸው። በተለይ መጣጥፎችን መጻፍ፣ ፖስተሮችን መንደፍ፣ በኢንተርኔት በኩል የምክር አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ትልቅ እድል ፈጥሯል።
የሃርቫርድ የጤና ብሎግ በቅርቡ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በመደበኛነት በጎ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች 25 በመቶ የበለጠ “ደስተኛ” ናቸው።
ለዚህ ነው በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ጥናት ያወጡ ተመራማሪዎች በጎ ፈቃደኝነት በትርፍ ጊዜ እንሚሠራ ተጨማሪ ተግባር መታየት የለበትም የሚሉት። እንደ ተመራማሪዎቹ ሃሳብ በጎ ፈቃደኝነት የሕይወት አካል መሆን አለበት። ወደ ትምህርት ቤት ወይም ወደ ሥራ እንደምንሄደው ሁሉ በበጎ ፍቃደኝነት ለማገልገልም ጊዜ መመደብ ይኖርብናል ይላሉ። በጎ ፈቃደኛ የምንሆነውም ሌሎች የእኛ ርዳታ ስለሚያስፈልጋቸው ብቻ ሳይሆን በሞራል፣ በአስተሳሰብ እና በሠብዓዊነት ረገድ ሕይወታችን መሻሻል ስላለበት ነው። እንደ ሰው እርስ በእርስ መተሳሰብ በምንኖርባት ዓለም ላይ የተሻልን ሰዎች ያደርገናል። በጎ ፈቃደኝነት ይህንን ክህሎት አንድናዳብር የሚረዳን መሣሪያ ነው።
ለዚህ ነው በዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን ላይ በጎ ፈቃደኝነትን የሀገራችን መገለጫ እሴት፣ ባህል ለማድረግ መንግሥት፣ ትምህርት ቤቶች፣ መገናኛ ብዙሃን እና ሁሉም ማህበረሰብ በጋራ መሥራት አለባቸው ለማለት የወደድነው።
በጎ ፈቃደኝነት ተቆርቋሪነትንና፣ ሰላማዊ ማህበረሰብ ለመገንባት ይረዳል። ሰዎችን በፍቅር፣ በመተሳሰብና በርህራሄ ያገናኛል፤ እርስ በእርስ ፍቅር እና መከባበርን እንዲኖር ያስተምራል። ልብንና አእምሮን ከሠብዓዊነት ጋር አዋህዶ ይቀርፃል። ከላይ በዝርዝር ለማንሳት እንደሞከርነው ዓለም አቀፍ ጥናቶች ይህንን እውነታ ደጋግመው አረጋግጠዋል። በመሆኑም ይህንን እውነታ ሁላችንም (በተለይ ወጣቶች) መረዳት ይኖርብናል። በመሆኑም እያንዳንዱ ወጣት በበጎ ፍቃደኝነት የማገልገል እድል የሚያገኝበትን የወደፊቷን ኢትዮጵያ እንገንባ፤ ደግነት የጠነከረበት ስሜት እና ጥላቻ ሳይሆን መተሳሰብና ፍቅር አገርን ሚመራበት ወደፊት። ሰላም!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም