የሕዳር እሸት

ከአባቷ ዲያቆን ተክለማርያም ከእናቷ ከወይዘሮ ገበያነሽ አሰፋ በ1974 ዓ.ም በወርሃ መጋቢት ለቤቱ የመጀመሪያ ልጅ የሆነችው ሴት ልጅ ተወለደች። ጥንዶቹ ጎጆ ከቀለሱ ስምንት ዓመት በኋላ ‹‹አይወልዱም መሃን ናቸው›› እየተባሉ በሚታሙበት ጊዜ ወደዚህች ዓለም የመጣችው መሰረት ቡቃያነቷ ጎምርቶ ዓላማና ግቧ ተሳክቶ ሥራ ከምግባር የሰመረላት ጀግና እንስት ሆነች። ይህን እውነታ ያወቁ ሁሉ ታዲያ፡-

“ምጣዲትም ጥቁር ታወጣለች ነጭ፣

የእኔማ መሰረት ከሴቶች በላጭ።

እያሉ ያወድሷታል። የበኩር ልጅ በመሆኗ “አይንፈስብሽ” ተብላ ለቤቱም ለውጪውም አጃቢዋ፣ ተንከባካቢዋም በዛ። እሷ ግን “ነገኮ የባለቤቴ እንጂ የእናንተ አይደለሁም” በማለት ከቤቱ ሥራ አልፋ ጉልጓሎውን፣ አረምና አጨዳውን ሳይቀር ጠንቅቃ በመልመድ ለቀዬው ሴት ልጆች ምሳሌ ሆነች። ይህን የተመለከተ ያገሬው ሰው በጋብቻ ለመተሳሰርና ዝምድና ለመፍጠር የወላጆቿን ደጅ መጥናቱ በረከቱ።

ውሎ አድሮ ውለታ እንዲሆን ያሰቡ ሁሉ በባሕሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን የሕዳር እሸት በማምጣት የወላጆቿን እንቢታ ለማለዘብ እሽቅድድሙ ቀጠለ። ተወልዳ ባደገችበት መንዝ ‹‹ላሎ ምድር›› ወገሬ ከተማ እንጨት ልትሰብር፣ ውሃ ልትቀዳ በወረደች ቁጥር ጥቂት የማይባሉ እንደ ጆፌ አሞራ እየዞሯት ውሃ አጣጫቸው ለማድረግ ኳተኑ። ከትምህርት ስትሄድም “ቀለም ወግተናል” ያለው ሳይቀር ሳይቀድሙት ለመቅደም ካለ ዕድሜዋ ሽማግሌ አሰልፎ “ልጃችሁን ለልጃችን” ማስባሉን ያዘ። ዳሩ ምን ይሆናል እናት አባቷን ዘመድ ብቻ ሳይሆን በየደብሩ፣ በየገበያውና በየጉዳዩ የሚያገኛቸው ሁሉ “እንኳን ለሰው ለግዜርም ይሰጣል” እያለ መውቀሱ ተለመደ።

አጋጣሚው ይሁን ምላሳቸው ደርሶ ባይታወቅም በዘጠኝ ዓመቷ እብድ ውሻ ነክሷት በጠና ስለታመመችባቸው ወላጆቿ ከጅሩ ለመጣ አንድ ዲያቆን ሊሰጧት ፈቀዱና ያመጣውን የሕዳር እሸት ተቀበሉ። የሕዳር እሸት ማለት መቅደሚያ ሲሆን የወንድ ወገን ከሚያጯት ወላጆች ዘንድ በግ፣ ቅቤና ማሩን እንዲሁም ሌላ ቤት ያፈራውን እሸት በመያዝ በየዓመቱ ሕዳር 12 እየመጡ ሰርግ ተደግሶ ቤቷ እስካልገባች ድረስ ቃል ያጸናሉ፣ ውል ያድሳሉ።

የወንድ ወገን በራሳቸው ምክንያት ካልተውት በቀር የሴት ወገን ቃሉን ቢያጥፍ ላባከነባቸው ጊዜና ሃብት በሽማግሌ ተይዞ እንደማሕበረሰቡ ደንብና ባሕል ካሳ እንዲከፍል ይደረጋል፤ መሰረትም የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ጨርሳ ከወገሬ ወደሞላሌ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ስትዛወር የወንድ ወገን “ልጃችን ዲያቆን ስለሆነ ድንገት ብትሳሳት ክህነቱ ይፈርሳልና ጉዳያችንን ተፈጣጥመን እኛ ጋር ሆና ትማር” ሲሉ ሃሳብ አቀረቡ።

እናቷ ገበያ ነሽ ግን “ሴት ልጅ የወንድ እጅ ከምትጠብቅ ይልቅ ተምራ ራሷን የምትችልና በራሷ የምትወስን መሆን አለባት” ብለው ስለሚያምኑ ማምለጫ ብልሃት ዘየዱ። አስቀድመው መሰረትን ሲጠይቋት ፍላጎቷ መማር እንደሆነ ስለተገነዘቡ የወንድ ወገን በሽማግሌ አጥብቀው ሲይዟቸው “እኔማ እሽታዬን ሰጥቻለሁ፤ ‹‹እምቢኝ›› ካለች ግን ለማስገደድ እንዴት እችላለሁ? ስታናግሯት አይሆንም ያለቻችሁ እንደሆነ ግን የበላሁትን እሸትና የተመላለሳችሁበትን ዋጋ እከፍላለሁ” አሉ። የቱንም ያህል ምንም ነገር ቢመጣ ሰርጉ እንደማይከናወን ልባቸው እያወቀ።

የወንድ ወገን ተስፋ ቆርጦ ፊቱን ሲያዞር መሰረት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በአንድ ልብ ሆና መከታተል ጀመረች። ዛሬ ላይ በተገናኘን ጊዜ የትምህርት ቤት ትዝታዋን በምልሰት ስትተርክልኝ ትካዜውም ፍንደቃውም ከገጿ ይነበብ ነበር። ከቤተሰቦቿ በአደራ መልክ የተቀበሏት አጎቷ አረጌ ሃይለሚካኤል ከንባብ እንዳትርቅ ከውጤት እንዳትጎድል ክትትል ቢያደርጉባትም “ለራሴ አንሳለሁ ማለት ነው? ወይስ ለመታመን አልበቃሁም?” የሚል ጥያቄ ጫረባትና ንዴቷ ኩርፊያ ወልዶ ከአጎቷ ጋር አቃቃራት።

ነገሩ እንዲህ ነው። “አብረን እናጥና” ይባባሉና ዘመዷ ቤት በሄደችበት አጋጣሚ አጎቷ አረጌ ያለችው እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ በማታ ይመጣሉ። መሰረት ግን “ምነው? የሴት ልጅ መሸሻ የወንድ ጉያ ብቻ መሰለህ? እኔ ብፈልግ ኖሮ ካንተ ቤት ማምጣት አቅቶኛል?” አለቻቸው አራስ ነብር እያደረጋት።

ወንድሞቿ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ስለደረሱ አባታቸው ሞላሌ ከተማ ላይ ቤት ገዙና የነሱንም የትምህርት ጉዞ ማቅናት በሷ ጫንቃ ወደቀ፤ ለነገሩ ይህን መሳይ ኃላፊነት ለመሰረት የሚከብድ አልነበረም፤ ምክንያቱም ገና በአስር ዓመቷ ለምዳዋለችና ነው። በደርግ ዘመነ መንግሥት እናቷ የቀበሌ ተሿሚ ስለነበሩ ኢሕአዴግ በገባበት ጊዜ ከቀያቸው ርቀው ሲሰደዱ “እህል እህል” የሚሉ እህትና ወንድሞቿን በመንከባከብ ባካባቢው ሰው ምልጃ እስኪመለሱ ድረስ ቤቱን ቀጥ አድርጋ አቆይታቸዋለች። ይህን ግዜ ነው መሰረትነቷን ያጸኑት።

“የልጆቼን አባት ያገኘሁት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቆይታዬ ነውና የነበረውን ሕይወት ሳወራው ጉንጬን ይሞላዋል” ትላለች መሰረት ፈገግታዋ እንደእንቡጥ ጽጌሬዳ ፈክቶ፤ እኔም የጨዋታዋ ሙቀት ተጋብቶብኝ እንደማለዳ ጸሃይ ወገግ ያለውን የወጓን ዥረት በብዕር የዕንባ ጠብታ የወረቀቴን ደረት እያቀለምኩ ነው። “በትምህርት ዓለም የልጅነት ትዝታ እልፍ ቢሆንም በዶርም ኪራይ የሚኖረው ገጠመኝ ግን ይለያል” ትላለች።

ሁሌም የገበያ ቀን ሲሆን እናቷ ይመጣሉና ባዶ ቤት እንዳይጠብቃቸው መሶብ ሙሉ እንጀራ ጋግራ ውሃ ልትቀዳ ወንዝ በወረደችበት አንድ ቀን የወንድሟ ጓደኞች ቁልፉን ካስቀመጠችበት አንስተውና ቤቱን ከፍተው ባዶ መሶብ አቆይዋት፤ በሌላኛው ቀን እሷም በተራዋ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና [ኢንትራንስ] ጨርሰው ለስንብት ያስደፉትን ሕብስት ወሰደችባቸው። “አንድ ጊዜ እንደዚሁ የማትሪክ ተፈታኝ ሳለሁ” አለች ሌላኛውን ገጠመኟን ልታወጋኝ እየዳዳት። “ምንም እንኳን ንግግሬ ጥናት ቢያስፈልገውም በኔ አረዳድ ለሴቶች ጾታዊ ትንኮሳ አያሌ ሰበቦች እንዳሉ አውቃለሁ፤ አንድ ቀን ልጅ እግር መምህር የፈተና ወረቀቴን ከሁሉም ተማሪ ነጥሎ አስቀረና ቤቴ መጥተሽ ውሰጂ አለኝ።

እኔ ግን ሞራሌ አልፈቀደምና ሴትነቴን በስንት አማላጅ ከችግር ታደኩት፤ ሁነኛ የቅርብ ሰው ስላለኝ አመለጥኩ። ሌሎች እህቶቼ ግን እንዴት ሆነው ይሆን? ይኸውልህ ከዚያን እለት ጀምሮ የትምህርት ፍላጎቴ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ቢቸልስበትም በድንግዝግዝ ተስፋ ቀጥዬ አሁን ካለሁበት ደረጃ ደርሻለሁ” አለች የሃዘን ደመና ፊቷን ሸብቦት።

ከሁሉም በላይ የዕድሜ ልክ ማሕደሯ ቢገለጥ እህል ውሃ ሰምሮ የዛሬ ባለቤቷ ዶክተር ሻረው ንጉሴ ጋር የተዋሃደችበት አጋጣሚ ቀዳሚ ምዕራፍ መያዙን ከሁኔታዋ መረዳት ይቻላል። ባዳመጥኩት ታሪክ መደነቄ በዝቶ ባስተውሎት ስመዝነው በሕልሜ አንጎራጉሬው ስነቃ እንደጠፋብኝ ዜማ ሥሥታም ያደርጋል።

መሰረት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቆይታዋን በጥሩ ውጤት ለመቋጨት መጽሃፍ ትራሷ ነበር። ዳሩ ምን ይሆናል! በወንድሞቿ ተመስሎ መውደድ መልህቁን ጣለና በመላመድ ሰበብ የሻረው ፍቅር ከልቧ ዘልቆ “ሲገባ በስውር፣ ሲወጣ በግርግር” የሚለውን ሃገርኛ አባባል አስተረተባት።

ከወንድሞቿ ጋር በጥናት ሰበብ ከዶርሟ መጥቶ ሲያድር በክፍል ደረጃ ሁለት እርከን፣ በዕድሜ ደግሞ አንድ ዓመት ስለምትበልጠው እንደታላቅ እህት አንጀቷ እንስፍስፍ ይልለታል። በትምህርቱ ያለው ጉብዝና ቀልቧን ገዛው። እስከወዲያኛው ሕላዌነቱን ሽታውም እጣ ፋንታዋ እንዲሆን ብታስብ ለእግዜር በተማጽኖ አዋየችው።

መሰረት ጸሎቷ ተሰምቶ በአንድ ነጠላ እስከማስቀደስ ደረሱና አሁን ላይ አምስት ልጆችን ለማፍራት በቁ። ኮከባቸው ስበቱ አይሎ ፍቅር ሙቀቱ ግሎ መተዛዘናቸው ገዝፎ አንድነታቸው ተጽፎ ውሃ አጣጭ ለመሆን በቁ። ‹‹የዛሬን አያድርገውና›› ቀድሞ ሌሎች ወንዶች ደብዳቤ ሲልኩላት እሱ ከወንድሞቿ ጋር እያነበበ “እገሌ ይሻልሻል” እያለ ያማርጣት ነበር።

እሷ የመጀመሪያ ዓመት የዩንቨርሲቲ ተማሪ፣ ዶክተር ሻረው ደግሞ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ያልታሰበ ልጅ መጣና ከትምህርት ሕይወታቸው አልፎ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የቀረቤታ መሻከር ገጠማቸው። ይሁን እንጂ ወንድሞቿ “እህታችን ወደቤት ካልተመለሰች እህል አንበላም” በማለታቸው በጸጸት በትር ሕሊናዋን ከመድማት ታድገውታል።

አባታቸውን በማሸነፍ የፍቅር አዝመራ እንዲያጭዱ አድርጓቸዋል። አባት በግዜው መቆጨታቸው አልቀረም። “ስንት የመንግሥት ሰራተኛ፣ ከበርቴ፣ በሃይማኖታዊ ስርዓት ውስጥ ስልጣን ያለው ሁሉ ሲለምነኝ እንዳልነበር እንዴት ተማሪ አግብታ ያገር መሳለቂያና መሳቂያ ታደርገኛለች? አሉ። ከእምቢታቸው ጋር ቀድሞ ይመላለስ የነበረውን አባባልም አልረሱም። ኋላ ሲቆጫችሁ “ለአንበሳ ያሳደግነው ውሻ ለዝንጀሮም ሳይሆን ቀረ” ብላችሁ እንዳትተርቱ›› መባሉን አስታውሰዋል ።

አባወራው መራራ ሃሞታቸው ምላጭ ሲያስውጣቸው ባለቤታቸው ግን የልጃቸውን ውሳኔ አጸኑ። “በደረጃ የማይመስላትን አግብታ ቢሆን ኖሮ በተጋጩ ቁጥር ‹‹አስተምሬሽ፣ እንዲህ አድርጌልሽ እያለ ባሪያው ያደርጋት ነበር። አሁን ግን ደግ አድርጋለች›› አሉ። እናት ሁለቱም እኩል ጠጠር ጥለው ለማደግ እንደማይፎካከሩ እያሰቡ ልጃቸውን ፊት ነስተው በጸጸት ከመቅጣት በፍቅር አስተምረው አሻጋሪ መፍትሄ መፍጠር እንደሚበጅ አመኑበት። በሰው ምላስ መገረፏ ለእሷም ለቤተሰቡም እንዳይጠቅም ቢገባቸው የበኩር ልጃቸውን እቅፍ ድግፍ አድርገው አረሷት።

“የመጀመሪያ ልጅነት መሰላል መሆን ነውና ልጄ የበታችነት ምስጥ አንቺነትሽን አላምጦ የውድቀት ንቅዘት እንዳያለብስሽ መቼም ቢሆን ሴትነትሽን ፈተናን መሻገሪያ ብልሃት አድርጊው አሏት። ‹‹ጥበብን ታጠቂ ራስን መቻል የዘወትር ሕልምሽ ይሁን” ሲሉ በመምከር ሞራሏን አበርትተው ዳግም ለትምህርቷ አበቋት።

መሰረት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአፕላይድ ባዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አገኘች። ዶክተር ሻረው ፈተና አላጣውም። ተማሪዎችና መምህራኑ “ከልጅነት ሳይወጣ የልጅ አባት ሆነ ” እያሉ ሞራሉን ሲያጎድፉት ሞከሩ። ወዳጁ ፍቅረ ተክለማርያም ግን ከጎኑ አልተለየውም። ጥንካሬውም ከእሱ ነበርና ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በፐብሊክ ሄልዝ ለመመረቅ ቻለ።

መሰረት በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ እንደሃይስኩሉ ሁሉ በሽርፍራፊ ውጤቶች ሰበብ የትምህርት ጉዞዋ በጋሬጣ እሾህ መሞላቱ አልቀረም። የእናቷ ምክር ጽናት ሆኗት ግን ከራሷ አልፋ ባደራጀችው የሴቶች ክበብ እልፍ እህቶቿን ከጥቃት ታድጋለች። ከባለቤቷ ጋር ርቀቱ የመለያየት ጥላ እንዳያጠላበት ስልክ ባይኖራቸውም በደብዳቤ እየተገናኙ ዛሬ ለተጎናጸፉት ስኬት በቅተዋል።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለች ቤተሰብን ላለማስቸገር ልጆችን ቤት ለቤት በማስጠናት ኪሷን ትደጉም ነበር። ከተመረቀች በኋላም ሥራ ባጣችበት አጋጣሚ ጥሪት ለመቋጠር መነሻ እርሾ ሆናትና በግልና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች በመምህርነት ቆየች። በቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ ዘጠኝ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ድጋፍ ሰጪ ብሎም የቅድመ መደበኛ ትምህርት ባለሞያነትም አገለገለች።

ይህ አጋጣሚ ወደ ቢዝነሱ ዓለም ለመቀላቀል አቅም ፈጥሮላታል። ሥራ የማትንቅ ነችና በተገኘው ዕድል ሁሉ ራስን ለመለወጥ የሞራል ከፍታዋን አሳድጋለች። “ምን ጊዜም ችግር ሲገጥመን ባሉበት ቆሞ መማረር ሳይሆን በማስተዋልና በማገናዘብ ከችግር ውስጥ መፍትሄን በመውለድ ለለውጥ መጣር ነው፤ ምክንያቱም እንቅፋት ሲመታ ወደፊት እንጂ ወደኋላ አይጥልምና” ትላለች እንግዳዬ መሰረት ።

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች የነበራት የስነጽሁፍ ተሰጥኦ አብሯት ባይዘልቅም ፍላጎቷን በደራሲ ወንድሟ ተወጥታዋለች።

ታናሽ ወንድሟንና ሴት ጓደኛዋን ይዛ በሃያ ሺህ ብር የጀመረችው የባልትና አቅርቦት አመርቂ ውጤት በማምጣቱ ከራሷ አልፋ ባለቤቷን እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ ለማስተማር በቅታለች። እሷም ብትሆን በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪ በፕሮጀክት ማኔጅመንት ደግሞ ማስተርሷን ለመማር ችላለች። መሰረት በባለቤቷ ስም “ሻረው የጤና ማማከር አገልግሎት” የሚል ፍቃድ አውጥታ ለሃምሳ ሶስት ሰዎች ቋሚና ግዚያዊ የሥራ እድል ፈጥራለች።

ዛሬ መሰረት የባልትና ውጤቶችን ኤክስፖርት ለማድረግ ባለሶስት ፎቅ ሕንጻ ገንብታ ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነች። ‹‹ከእጅ ወደአፍ›› የሆነ ኑሮዋን ቀይራ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሯ የሀገርና የወገንን አደራ የመወጣት ኃላፊነትን በመወጣት ላይ ናት። ይህች ብርቱ ሴት አርአያነቷ ለብዙሀን ነውና ‹‹እደጊ ተመንደጊ›› ልትባል ይገባል። ጥልፍልፍ አደናቃፊ እንቅፋቶችን አልፎም ለስኬት ይበቃል።

ሃብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You