
በካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኔይ የሚመራው ሊብራል ፓርቲ የሀገሪቱን አጠቃላይ ምርጫ ማሸነፉ ተገለፀ።ማርክ ካርኔይ እና ሊብራል ፓርቲ በካናዳ ምርጫ ድል እንደቀናቸው የተናገሩ ሲሆን፣ የዶናልድ ትራምፕ አቋም ለውጤቱ እንዳገዛቸው ተገልጿል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጥር ወር ጀምሮ የጎረቤት ሀገር የሆነችው ካናዳን 51ኛዋ የአሜሪካ ግዛት እንደምትሆን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ነበር።ይህም ሊብራል ፓርቲው በምርጫው እንዲያሸንፍ እንደረዳው ተገልጿል። ዶናልድ ትራምፕ ይህንን አቋማቸውን ይፋ ከማድረጋቸው በፊት የወግ አጥባቂው ተወዳዳሪ ፒር ፖሊየቭ ያሸንፋሉ ተብሎ ይገመት ነበር። ሀገሪቱ ላለፉት አስርት ዓመታት የመሩት የሊብራሉ ፓርቲ አባሉ ጀስቲን ትሩዶ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ምንም ለውጥ ባለማሳየታቸው በፓርቲው ደጋፊዎች ዘንድ ቅሬታ ተፈጥሮ ነበር ተብሏል።
የካናዳ ሊብራል ፓርቲ ሀገሪቱን ለረዥም ዓመት ያስተዳደሩትን ትሩዶን አስወግዶ የባንክ ባለሙያ የሆኑትን ማርክ ካርኔ መሪው አድርጎ ከመረጠ በኋላ “አስደናቂ” የተባለውን የምርጫ ውጤት አግኝቷል። ማርክ ካርኔይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ብቻ ሳይሆን በሉዓላዊነቷም ላይ አደጋ መደቀናቸውን በመግለጽ የመራጮችን ልብ ማሸነፍ ችለዋል።
“አፈር ልሶ” ነው የተነሳው የተባለው የካናዳ ሊብራል ፓርቲ ለአራተኛ ጊዜ አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መምራት የሚያስችልን ድምጽ ማግኘቱ ተገልጿል። ከዚህ በፊት የማዕከላዊ ባንክ ገዢ የነበሩት እና ለፖለቲካ አዲስ የሆኑት ማርክ ካርኔይ የአሜሪካውን ዶናልድ ትራምፕ መጋፈጥ ይጠበቅባቸዋል። የሀገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን የሆነው ሲቢሲ እንደዘገበው ሊብራል ፓርቲው መንግሥት መመሥረት የሚያስችለውን ከፍተኛ ድምጽ ማግኘቱን ሰኞ ምሽት ይፋ አድርጓል።
ይህንንም ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ ግዛቶች የሚገኙ የፓርቲው ደጋፊዎች ደስታቸውን እየገለፁ ነው። ፒየር ፖሊየቭ ለወግ አጥባቂ (ኮንሰርቫቲቭ) ፓርቲ ደጋፊዎች ከዋና ቢሯቸው ኦታዋ ኦንታሪዮ ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ካርኔይን “እንኳን ደስ አለዎት ማለት እፈልጋለሁ” ብለዋል። አክለውም የወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ የሆኑት ፒየር ፖሊየቭ ውጤቱ የሀገሪቱ ሊብራል ፓርቲዎች ጥምር መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችላቸው በቂ ድምጽ አላገኙም ሲሉ ተናግረዋል።
“የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ አባላት በዚህ ምሽት ልትደሰቱበት የምትችሉት በርካታ ነገሮች አሉ” ያሉት ፖሊየቭ “ከ20 መቀመጫዎች በላይ አግኝተናል። ይህም ፓርቲያችን እኤአ ከ1988 ወዲህ ካገኘው ከፍተኛው መቀመጫ ነው” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ካርኔይ ለደጋፊዎቻቸው የእንኳን ደስ ያለን መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን አሜሪካ “መሬታችንን፣ የተፈጥሮ ሀብታችንን እና ሀገራችንን” ትፈልጋለች ሲሉ ተናግረዋል።
“ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሊሰብረን እና ሊቆጣጠረን ይፈልጋል፤ ያ ደግሞ በጭራሽ ፈጽሞ አይሆንም” ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ካናዳ በታሪክ “እጥፋት” ላይ ትገኛለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ከአሜሪካ ጋር የነበረን የቆየ የትብብር ወዳጅነት አብቅቷል” ብለዋል። “አሜሪካ ካደረሰችብን የክህደት ድንጋጤ ወጥተናል። አሁን እርስ በእርሳችን ልንደጋገፍ ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ካርኔይ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በሚቀጥሉት ቀናት “የሁለቱ ሉዓላዊ እና ነጻ ሀገራት የወደፊት መጻዒ ዕድል ላይ እንወያያለን” ብለዋል። ሀገራቸው ከአውሮፓ እና ሌሎች አጋር ሀገራት ጋር ያላትን ወዳጅነት አጠናክራ እንደምትቀጥልም አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካናዳ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን የንግድ ጦርነት በድል እንደምትወጣው ቃል ገብተዋል።
ሀገራቸው ከባድ ጊዜ ከፊቷ እንደሚጠብቃት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለካናዳ የተሻለውን ለማስገኘት ባለን ነገር ሁሉ እንፋለማለን” በማለት “ለታላቋ ሀገራችን ነጻ የሆነ መጻዒ ጊዜ እንፈጥራለን” ማለታቸው ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም