የባህል ንዝረት

በእንግሊዘኛ ‹‹Culture Shock›› የሚባለውን ነው በጥሬ ትርጉም ‹‹የባህል ንዝረት›› ያልኩት። የባህል መደንገጥ ልንለውም እንችላለን። ድንገተኛ የባህል መለወጥ ማለት ነው። የባህል መፋለስ ልንለውም እንችላለን። ይሄ ማለት፤ አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ሰው በድንገት አውሮፓ ቢሄድና መኖር ቢጀምር የሚያጋጥመው ስነ ልቦናዊ ለውጥ ማለት ነው፡፡

ሩቅ መሄዱን እንተወው! እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ የጎንደር ሰው ሐረር፣ የሐረር ሰው ጎንደር፣ የሰሜን ሰው ደቡብ፣ የደቡብ ሰው ሰሜን እና የምሥራቅ ሰው ምዕራብ፣ የምዕራብ ሰው ምሥራቅ… ቢሄዱ የባህል ልዩነት ያጋጥማቸዋል። ያም ሆኖ ግን የአገር ውስጡ ለመማር እና ለመተዋወቅ እንጂ ለማስደንገጥ የሚሆን አይሆንም። የማያስደነግጥበት ምክንያት የሀገር ውስጡን ሄደን ባናየውም በቅርበት ስለምንሰማው ነው። የበለጠ እንድንተዋወቅ ደግሞ ሊሰራበት ይገባል።

የውጭ ሲሆን ግን የባህል መደንገጥ ያጋጥማል። ይህ የባህል መደንገጥ ግለሰባዊ ችግር ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ችግርም ሊያስከትል ይችላል። ለዚህ ምሳሌ የሚደረገው በተለምዶ ‹‹የ60ዎቹ ትውልድ›› የሚባለው የ1960ዎቹ ዓ.ም የተማሪዎች እንቅስቃሴ ነው፡፡

የታሪክ ባለሙያው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ባለፈው ዓመት የአብዮቱን 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እንግዳ ሆነው ነበር። የአብዮቱ ምክንያቶች ብለው ከጠቀሷቸው አንዱ የስነ ልቦና ልዩነት መፈጠር ነበር። አብዛኞቹ የእንቅስቃሴው አስጀማሪዎችና መሪዎች በአውሮፓ ሀገራት የተማሩ እና ለትምህርት የተላኩ ነበሩ፡፡

ይሄ ነገር ብዙዎች ሲሉት የነበረ ጉዳይ ነው። ተማሪዎቹ ከኢትዮጵያ ሲሄዱ አውሮፓን አስደናቂ ሆና አገኟት። ሀገራቸውን ከአውሮፓ ሀገራት ጋር ሲያነፃፅሯት በጣም አነሰችባቸው። በመሆኑም ለውጥ ፈለጉ። ለውጡን ግን ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ እና ከህዝቡ ስነ ልቦና ጋር በሂደት ከማስኬድ ይልቅ በአንድ ጊዜ ግልብጥብጡን ካላወጣነው አሉ። በ1967 ዓ.ም የተሳካ ቢመስልም እንዳሰቡት ግን አልሆነም፤ እነሆ እስከ አሁን ድረስ ጣጣው አላለቀም።

ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ‹‹ሕይወቴ እና የኢትዮጵያ እርምጃ›› በሚለው መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ ስለለውጥ እና ሥልጣኔ ገልጸዋል። ‹‹ሕጻን ልጅ በአንድ ጊዜ ሙዳ ሥጋ አንሰጠውም›› በሚል ምሳሌ ነበር ያብራሩት። ይሄ ማለት ኢትዮጵያን እንደ አውሮፓ ለማድረግ በአንድ ጊዜ እነርሱ የተጠቀሙትን ነገር ሁሉ መጠቀም የለብንም እንደማለት ነው። ቀስ በቀስ እና በማለማመድ ነው ማለታቸው ነው። በ60ዎቹ የነበረው አብዮት ግን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ልብ ብሎ ያስተዋለ እና በነባራዊ ሁኔታው የሄደ አይመስልም።

ነገርን ነገር ሲያነሳው ወደ ታሪክና ፖለቲካ ወሰድኩት እንጂ ላወራ ያሰብኩትስ ስለግለሰቦች ነበር። በእርግጥ በሀገር ላይ ችግር የሚያመጣውም የግለሰቦች ጉዳይ ነው። ግለሰቦች በአግባቡ ሲሰለጥኑ ሀገርም ትሰለጥናለች፡፡

የትዝብቴ ዋና ጉዳይ የሰለጠኑ ናቸው በሚባሉት ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባህሪ ነው። እነዚህ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ወደ አገራቸው ሲመጡ የሚያሳዩትን ባህሪ እናያለን። በዚያው በሚኖሩበት ሀገር ሆነው በየሚዲያው የሚናገሩትንም እንሰማለን። አንዳንዴ ሲገርመኝ ‹‹ሰው እንዴት የሰለጠነ ሀገር እየኖረ እንዲህ ይሆናል?›› እላለሁ። ወደ ሀገር ውስጥ ሲመጡ ደግሞ ባህሪዎቻቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች እናያለን።

እንዲያውም አሁን አሁን ልብ ብላችሁ ከሆነ ፊልሞችና ቀልዶች ሲሰሩ፤ የዲያስፖራ ገጸ ባህሪ ካለበት ግብዝ ተደርጎ ነው የሚሳለው። የሰለጠኑ ሆነው ሲያስተምሩ፣ ስነ ምግባርና ጨዋነትን አርዓያ ሆነው ሲያሳዩ፣ አስተዋይ ሲሆኑ… ከማሳየት ይልቅ አጉል ወፈፌ እና ግብዝ ሲሆኑ ያሳያል። ይህ የሆነው ዝም ብሎ ፊልሙን ወይም ቀልዱን አስቂኝ ለማድረግ በሚል ብቻ አይደለም፤ ከነባራዊ ሁኔታው በመነሳት ነው። ይህ ማለት ግን ሁሉም ዲያስፖራ እንደዚያ ነው ማለት አይደለም። ጎላ ብለው የሚታዩት ወፈፌዎችና ግብዞች ስለሆኑ ነው።

ከአንዳንድ ዲያስፖራዎች ከምገረምባቸው ባህሪያት አንዱ የሀገራቸውን ነባራዊ ሁኔታ የሚዘነጉት ነገር ነው። ብዙ ዓመት የሰለጠነ ሀገር ቆይታው ሲመጡ ሀገራቸው በሚፈልጉት ልክ አለመሰልጠኗ ሊያሳዝናቸው ይችላል፤ ከተቆርቋሪ ሰው የሚጠበቅ ነው። ዳሩ ግን ለማስተማር መሞከር እንጂ በየገቡበት ካፌ መጣላት መሰልጠን ሳይሆን እንዲያውም የባሰ አለመሰልጠን ነው። በሰለጠነው ሀገር ያዩትን ትህትና ማሳየትና አርዓያ መሆን ሲገባቸው ‹‹ለምን እንዲህ ይደረጋል!›› በሚል በቁጣ ይደነፋሉ። አገልግሎት ማግኛ ቦታ ሲሄዱ መሠረተ ልማት ያልተሟላ መሆኑን እያወቁ አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞችን ‹‹እንዴት እንዲህ ይደረጋል?›› ይሏቸዋል። አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞችም እንደ እብድ እያዩ ይታዘቧቸዋል። ያለ ቦታው አጉል የሰለጠኑ መምሰል እብድ ያስመስላል።

እንኳን በባህሪ በአለባበስ ራሱ አካባቢውን መምሰል ያስፈልጋል። ለምሳሌ፤ በቁምጣ መሄድ እንደ መቀናጣት(መዘነጥ) ስለሚታይ ብቻ በክረምት ብርድ ቁምጣ ማድረግ በወጣቶች ቋንቋ ‹‹ያስፎግራል›› የሚባል ነው። አለባበብ ቢያንስ የግል ምርጫ ነውና ማንም ሰው በሚመቸው ልክ መልበስ ይችላል ብለን እንለፈው።

ዋናው ጥያቄ፤ ውጭ አገር ቆይታው የሚመጡ አንዳንድ ሰዎች ለምን እንዲህ ይሆናሉ? የሚለው ነው። የባህል መፋለስ ስለሚያጋጥማቸው ነው። እጅግ ወግ አጥባቂ በሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ የኖረ ሰው በአንድ ጊዜ እጅግ ልቅ የሆነ ነገር ሲያይ የባህል ንዝረት ያጋጥመዋል። ከሚያየው ብዙ አስደንጋጭ ነገር በመነሳት አዕምሯዊ ውጥረት ሊያጋጥመው ይችላል፤ በዚህም ምክንያት የስነ ልቦና ባለሙያ ጋ እስከመሄድ ይደርሳሉ። ችግሩ ብሶባቸው የአዕምሮ ህመምተኛ ሲሆኑም አይተናል። ‹‹ለማበድ እንኳን ሀገር ያስፈልጋል›› የሚለው የመጋቢት ሐዲስ እሸቱ ንግግር አንድ ሰሞን በስፋት ሲዘዋወር እንደነበር እናስታውሳለን።

የባህል መፋለስ እንዳያጋጥም የተለያዩ ሀገራትን ባህልና የአኗኗር ዘይቤዎች መከታተል የተሻለ ይሆናል። ለምሳሌ፤ በሀገረ ቻይና ኢትዮጵያ ውስጥ ለምግብነት የማይውሉ ነገሮች እንደሚበሉ እንሰማለን። ይህን የሚያውቅ አንድ ኢትዮጵያዊ ቻይና ቢሄድ አይደነግጥም ማለት ነው። ምንም ሳይሰማ ኖሮ ድንገት ቢሄድና ሲበሉ ቢያይ ግን ይደነግጣል።

በሰለጠነ ሀገር ሲኖሩ ሥልጣኔውን መቅሰም ያስፈልጋል። ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ተማሪዎችን ወደ ውጭ ሲልኩ ‹‹የአውሮፓን ሰማይ ጠቀስ ፎቆች እና የተንጣለለ አስፋልት እንድትነግሩን አይደለም…›› ይሏቸው እንደነበር ይናገራል። የሚፈለገው እንዴት እንደሰሩት ማወቅ ነው። የእኛ ሰው ግን ከሰለጠነ ሀገር ሲመጣ የኖረበትን ሀገር እየጠቀሰ ‹‹መንገዳቸው እንደዚህ ነው፣ መስተንግዷቸው እንደዚህ ነው፣ ግብይታቸው እንደዚህ ነው….›› እያለ ይተርካል። አዎ! እናውቃለን እንደዚያ ነው፤ የተፈለገው ግን እኛም እንደዚያች ሀገር የተዘረጋ ሥርዓት እንዲኖረን ነው።

ለመሰልጠን የሰለጠነ ሀገር መሄድ የግድ አይደለም። ከ20 በላይ አውሮፓ ሀገር ውስጥ ኖሮ ከመጣ አንድ ኢትዮጵያዊ ይልቅ፤ ከሀገሩ ወጥቶ የማያውቅ ኢትዮጵያዊ የተሻለ ሥልጡን ሊሆን ይችላል። በትህትና፣ ሰው በማክበር፣ ነገሮችን በሰለጠነ መንገድ በማስተዋል ውጭ ሀገር ቆይቶ የመጣውን ሊበልጠው ይችላል፤ ከሀገሩ ወጥቶ የማያውቀው ፈረንጆች ያደርጉታል ለሚባለው የሰለጠነ ባህሪ ቅርብ ሊሆን ይችላል። ለመሰልጠን ዋናው ነገር መማር እንጂ የሰለጠነ ሀገር መኖር አይደለም።

የሰለጠነ ሀገር መኖር ነገሮችን በተግባር ለማየት ቢያስችልም፤ ችግሩ ግን የባህል መፋለስ ያጋጥማል። የሚፈጠርበት የባህልና የስነ ልቦና መፋለስ ግብዝ እና ተመፃዳቂ እንዲሆን ያደርገዋል። ያም ሆኖ ግን ጎበዝ እና አስተዋይ ከሆኑ የባህል መፋለሱን መቋቋም ይቻላል። እንዲህ አይነት ሰዎች ብዙ አሉ፤ ሀገራቸውንም በብዙ መንገድ እየጠቀሙ ነው።

የባህል መፋለስ እንዳያጋጥም የተለያዩ የዓለም ሀገራትን ባህልና አኗኗር ማወቅ የተሻለ ይሆናል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You